ዓለም በፈጣን የቴክኖሎጂ ለውጥ ላይ ትገኛለች። አገራት የኢኮኖሚ አቅማቸውን የሚያሳድጉትና ጡንቻቸውን የሚያፈረጥሙት ባላቸው የቴክኖሎጂ እድገትና የመፍጠር አቅም በመጠቀም እየሆነ መጥቷል። በቴክኖሎጂ አሰራርንና አኗኗን ማዘመን፣ ጊዜን ጉልበትን እንዲሁም አላስፈላጊ ወጪን መቀነስና ማስቀረትም እየተቻለ ነው። በተለያዩ ዘርፎች እየታዩ ለሚገኙ ለውጦች ቴክኖሎጂ ትልቁን ድርሻ እያበረከ ይገኛል። የግለሰቦች የመፍጠር አቅምን ጨምሮ በመንግስታት ቁርጠኝነትና በፖሊሲ በሚደገፉ ምርምሮች ምክንያት ምድራችን በርካታ እመርታዎችን በቴክኖሎጂ ማሳየት ችላለች።
ቴክኖሎጂን እንደ እድገት ማስፈንጠሪያ ከሚጠቀሙ ዘርፎች መካከል ፈጣን ለውጥ እያመጣ የሚገኘው ቱሪዝም አንዱ ነው። የዓለም ታሪክ፣ ቅርስ፣ ተፈጥሮና መሰል የመስህብ ስፍራዎችን ለማስተዋወቅ፣ ለማስጎብኘት፣ ለማልማትና ለመጠበቅ ቴክኖሎጂ ትክክለኛ አማራጭ ሆኗል። በተለይ በጉብኝት እና መሰል የቱሪዝም ጉዳዮች ላይ እንደ ቁልፍ ግብአትነት እየተወሰደ ይገኛል።
ከላይ ላነሳነው ጉዳይ ሁነኛ ምሳሌ ሊሆነን የሚችለው ዘመኑ ያመጣቸውን ረቂቅ ቴክኖሎጂዎች ተጠቅመን የቱሪዝም መስህብ የሆኑ ስፍራዎችን በአካል ሳንገኝ የምንጎበኝበት ሁኔታ መፈጠር መቻሉ ነው። ይህ አማራጭ “ቨርቹዋል ቱሪዝም” ይሰኛል። ይህም የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በመጠቀም ቱሪስቱ የሚወዳቸውን መስህቦች ምንም ሳይጎልበት ስፍራው እንደተገኘ እየተሰማው የሚመለከትበት አማራጭ ነው።
የቨርቹዋል ቱሪዝም ጽንሰ ሀሳብ የኮቪድ ወረርሽኝ በተስፋፋበት ወቅት በስፋት ይተዋወቅ እንጂ በስራ ላይ መዋል ከጀመረ ግን ረጅም ጊዜያትን አስቆጥሯል። በዋናነትም ቴክኖሎጂውን አገራት የመስህብ ሃብቶቻቸውን ለዓለም ለማስተዋወቅ በስፋት ተጠቀሙውበታል። የበይነ መረብና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ጎብኚዎች ተወዳጅ ስፍራዎችን መጎብኘት እንዲችሉ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንዲዘምንና ፈጣን ለውጥ እንዲያመጣ ምክንያት እየሆነ ነው። ይህ ፅንሰ ሃሳብ ከስማርት ቱሪዝም “smart tourism” ጋርም ይመሳሰላል።
የቱሪዝም ምሁርና ዓለም አቀፍ ተመራማሪው ዶክተር ሃይለይ ስቴንተን “Virtual tourism explained: What, why and where” ቨርቹዋል ቱሪዝም፤- ምንነቱ ፣ለምንነቱና የትነቱ በምን መልኩ እንደሚተገበር ባብራሩበት ሰፊ ዳሰሳዊ ጥናታቸው ላይ፤ ቨርቱዋል ቱሪዝም ካሉበት ስፍራ ራቅ ወዳለ የቱሪዝም መዳረሻ መጓዝ ሳያስፈልግ ‘የቨርቹዋል ሪያሊቲ’ ቴክኖሎጂን ከቱሪዝም ጋር በማዋሃድ የሚደረግ ጉብኝት ነው” በማለት አብራርተውታል።
እንደ ተመራማሪዋ ገለፃ፤ ይህ ቴክኖሎጂ ቀለል ካለ “የምስል እና ድምፅ” ስርጭትን በጆሮ ማዳመጫና ምልከታ ከመጎብኘት ጀምሮ ጎብኚዎች ውስብስብ በሆነ ረቂቅ ቴክኖሎጂ ስፍራው ላይ እንዳሉ ሆነው የስሜት ህዋስ በመቆጣጠር የቱሪዝም መዳረሻው ላይ እንዳሉ አርጎ እንዲሰማቸው እስከማስቻል ይደርሳል። በዚህ መልኩ በየትኛውም ስፍራ ላይ የሚገኙ ቅርሶች፣ የስልጣኔ መገለጫዎች፣ ታሪካዊ ከተሞች፣ የተፈጥሮ ስፍራዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የቱሪዝም መስህቦችን መጎብኘት ይቻላል።
ዶክተር ሃይለይ “ቨርቹዋል ቱሪዝም ቀስ እያለም ቢሆን ለውጥ እያመጣና እድገት እያሳየ ነው” በማለት አሁን አሁን ጎብኚዎች ስጋት ያለባቸው ስፍራዎች፣ በጊዜና በገንዘብ ምክንያት መድረስ የማይችሉባቸው የመስህብ ቦታዎችን በዚህ ቴክኖሎጂ በመጠቀም እየጎበኙ እንደሚገኙ የጥናት ውጤታቸውን ተመርኩዘው ይናገራሉ።
በቨርችዋል ቱሪዝም ከሚጎበኙ ታላላቅ ታሪካዊ ስፍራዎች መካከል የእንግሊዙ ቤተመንግስት አንዱ “Buckingham Palace” ሲሆን፣ ቤተመንግስቱን በስፍራው ተገኝቶ ለመጎብኘት አጋጣሚውን ማግኘት ያልቻሉ እና ለጉብኝት ወጪ መሸፈን ላቃታቸው ረቂቅ ቴክኖሎጂው ልዩ አማራጭ ፈጥሮላቸዋል። በቨርቹዋል ጉብኝት /This virtual tour/ አማካኝነት በውስጡ የሚገኙ እያንዳንዳቸውን ክፍሎች እና ቅርሶች መመልከት ይቻላል።
ሌላው የዚህ ቴክኖሎጂ ምሳሌ የሚሆነው ደግሞ ጥንታዊው የቻይና ግንብ /the Great Wall of China/ ነው። ይህንንም ቅርስ በተመሳሳይ በቦታው ተገኝተው መጎብኘት ለማይችሉ ጎብኚዎች መጎብኘት የሚችሉበት ሌላ የቴክኖሎጂ አመራጭ ተገኝቶላቸዋል። ሌላው የዋሽንግተን ዲሲውን የነጻነት ሀውልት / the Statue of Liberty/፣ የእስራኤል “ቅዱስ ስፍራዎች” እና በዓለማችን የሚገኙ ተወዳጅ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት መጎብኘት ይቻላል።
ኢትዮጵያና የቨርቹዋል ቱሪዝም ፅንሰ ሃሳብ ጅማሮ
ኢትዮጵያ ለቱሪስት መስህብነት ሊውሉ የሚችሉ በርካታ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ስፍራዎች አሏት። የሰው ዘር መገኛ ምድር እንደመሆኗ የበርካታ አስደናቂ የቱሪስት መስህቦች ባለቤት መሆኗ ያን ያህል አስገራሚ አይሆንም። ይሁን እንጂ ዓለማችን ላይ በጎብኚዎች መዳረሻነት ከሚታወቁት አገራት ተርታ ግን ለመሰለፍ አልቻለችም። በባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ እሴቶቿ በብዙ እጥፍ የምታስከነዳቸው አገራት ሃብቶቻቸውን የመጠበቅ፣ የማስተዋወቅና ምቹ መሰረተ ልማት በመገንባት የመንከባከብና የማስጎብኘት ተግባር በመስራታቸው ብቻ ቱሪዝም የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽና የጀርባ አጥንት እንዲሆን አስችለውታል።
“በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል” ይሉት አባባል አገሪቱ የቱሪዝም ዘርፉን በሚገባ ሳትጠቀምበት ቆይታለች። ሀገሪቱ ይህን ሀብት በሚገባ አስተዋውቃ የዚያኑ ያህል ቱሪስቶችን መሳብ ባትችልም፣ ከተለያዩ ዓለም ክፍሎች በመምጣት የአገሪቱን ድንቅ የቱሪዝም ሃብቶችን ከመጎብኘት ባለፈ ስለቱሪዝም መስህቦቹ ያላቸውን አድናቆት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በማሰማት ምስክርነታቸውን መስጠታቸውን ተክትሎ የመስህቦቹ የመጎብኘት እድል እየሰፋ መጥቷል። ሀገሪቱ ካላት የህዝብ ብዛት አኳያ ሲታይ ትርጉም ያለው የአገር ውስጥ ጎብኚ ባይኖርም፣ በአገራቸው ሃብት ኮርተው ዙሪያ ገባውን በመቃኘት ዓለም ትኩረት እንዲሰጠው የሚሞግቱም አሉ። በዚህ ዘመን ደግሞ ዘመኑ ባፈራው ዲጂታል ፕሮሞሽንና በቨርቹዋል ቱሪዝም በመጠቀም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሃብቶች ማስተዋወቅ ላይ መበርታት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ወዳጆች ምክረ ሃሳባቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።
ከጥቂት አመታት ወዲህ መንግስት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለቱሪዝም ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። በአስር አመት መሪ እቅዱ የኢኮኖሚው ምሰሶ በሚል ከያዛቸው አምስት ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ሆኗል። ለእዚህም ዘርፉን የሚመራ ራሱን የቻለ አደረጃጀት የተፈጠረ ሲሆን፣ በዚህም የቱሪዝም መስህቦችን ከማልማት፣ መሰረተ ልማቶችን ከመዘርጋት፣ መስህቦቹን ከማስተዋወቅና ለገበያ ከማዋል አኳያ እየተሰራ ነው።
በተለይ ቱሪዝምን በቴክኖሎጂ መደገፍ ለፈጣን እድገትና ለውጥ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን በመገንዘብ በዚያ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ነው። በቱሪዝም ዘርፍ በቴክኖሎጂ እየተሰሩ ካሉ በርካታ ስራዎች መካከልም የቨርቹዋል ቱሪዝም እና ስማርት ቱሪዝም አንዱ ነው። ለእዚህም በአዲስ አበባ ከተማ እንጦጦ ፓርክ ከሳምንታት በፊት በይፋ በተከፈተው አውደ ርእይ ላይ ያየነው ጉዳይም እንደ ማሳያ መውሰድ ይቻላል።
ይህ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በአዲስ አማራጭ ለማስጎብኘት እያስቻለ ያለ አውደ ርእይ በቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በፈረንሳይ መንግስት፣ በፈረንሳይ ልማት ደርጅት፣ በቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስትያናት፣ በቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ትብብር የተዘጋጀ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብፁዓን አባቶች ፀሎትና ቡራኬ፣ መንፈሳዊ ዝማሬ እንዲሁም ሚኒስትሮችና አምባሳደሮች ባስተላለፉት መልእክት የተከፈተው አውደ ርእይ፣ በቨርቹዋል ቱሪዝም እንዲሁም ቴክኖሎጂን መሰረት ባደረገ መልኩ የተዘጋጀና በአይነቱ ልዩ ነው።
በአውደ ርእዩ ላይ የላሊበላን ውቅር አብያተክ ርስቲያናት አጠቃላይ ገፅታ የሚያሳዩ የፎቶግራፍ ምስሎች፣ ቅርጾች፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ አኗኗር የሚያንፀባርቁ ምስሎች ከገለጻ ጋር ቀርበዋል። የመስህብ ስፍራው ለአካባቢው ማህበረሰብ ምን ማለት እንደሆነ የሚገልጹ አጫጭር የተንቀሳቃሽ ምስል መልእክቶችም ለእይታ ቀርበውበታል ።
ባሳለፍነው ሳምንትም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የቱሪዝም ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የሚደረገውን ጥረት የሚደግፈውን ይህን አውደ ርዕይ ጎብኝተዋል። በወቅቱም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በስፍራው ተገኝቶ የአገሩን ቅርስና ታሪክ በመጎብኘት እንዲያውቅ ጥሪ አድርገዋል።
አውደ ርእዩን መርቀው የከፈቱት የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እንዳሉት፤ ዲጅታል ኤግዚቢሽኑ ከሶስት ዓመት በፊት የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለማደስና ለመጠበቅ በገቡት ቃል መሠረት ከታቀዱት ስራዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ዋና አላማውም ቅርሱን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች በስፋት ማስተዋወቅ ነው።
“ይህ በአይነቱ ልዩ የሆነ የ3D ቨርቹዋል ሪያሊቲ ዲጅታል አውደ ርእይ እንደ ሀገር የዲጅታል 2025 እቅድ አንዱ አካል ሲሆን፣ ዘርፉን አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምድ ነው›› ሲሉም ሚኒስትሯ ገልጸዋል። በላሊበላ የተጀመረው ይህ የቪዥዋል ቱሪዝም ስራ በሌሎች የቱሪዝም መስህቦች ላይም በስፋት እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። በቀጣይ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን የሚመሩ መሰረታዊ ለውጦች እንደሚካሄዱ መልእክት ያስተላለፈ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ራሚ ማርሾ በበኩላቸው ይህ ዲጅታል አውደርዕይ 125ኛውን አመት የኢትዮጵያና የፈረንሳይ መንግስታት የሁለትዮሽ ግንኘነት አስመልክቶ መከፈቱን ገልጸው፣ በቀጣይም በኢትዮጵያ መንግሥትና በዩኔስኮ ጥያቄ መሠረት ከፍተኛ ጥናት ሲካሄድባቸው የቆዩ ቅርሶቹን የማደስ ስራዎች እንደሚሰሩ አስታውቀዋል። አጠቃላይ ስራውን አስመልክቶ የፈረንሳይ መንግስት በፈረንሳይ ልማት ድርጅት በኩል 500 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ማድረጉን አምባሳደሩ ገልፀዋል።
የፈረንሳይ መንግስት የኢትዮጵያን የቱሪዝም መስህቦች በመጠበቅ ስራው ከዚህ ቀደም በብሄራዊ ሙዚየም ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው፣ ቀጣዩ እቅድ በአዲስ አበባ ከተማና ሌሎች ክልሎች ያሉ የቱሪዝም መስህቦችን የማልማት እንዲሁም የሰው ሀይል የማሰልጠን ስራዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል።
የቨርቹዋል ሪያሊቲ ቱሪዝም አውደ ርእይ በተከፈተበት ስፍራ ጉብኝት ሲያደረግ ያገኘነው አቶ አስናቀ ብርሃኑ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጠው አስተያየት እንደተናገረው፤ ወደ ላሊበላ ለመሄድና ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን እንዲሁም በስፍራው የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን ለመጎብኘት ፅኑ ፍላጎት ነበረው። ይሁን እንጂ በጊዜ ጥበት ምክንያት እስካሁን ምኞቱን ለማሳካት አልቻለም። በእንጦጦ ፓርክ ውስጥ ቨርቹዋል ቱር እንደሚካሄድ ሲሰማ ግን እድሉ እንዳያመልጠው ፈጥኖ ወደ እዚህ ስፍራ መጥቷል።
በቴክኖሎጂ ተደግፎ የቀረበውን ይህን ታሪካዊ መስህብ በማየቱ መደነቁን ገለጾ፣ በቦታው በአካል የመገኘት ያህል ልዩ ስሜት እንደፈጠረበትም ተናግሯል። አገራቸውን ለማወቅ፣ ለመጎብኘት ፈልገው እሱን የገጠመው መሰል ችግር ለገጠማቸው ሰዎች “ቨርቹዋል ቱር” መልካም አማራጭ መሆኑን ይጠቁማል፤ አውደ ርእዩ ይህ አማራጭ እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ይናገራል። አገርም ተጨማሪ ገቢን መፍጠር እንደምትችል እምነቱ ነው።
እንደ መውጫ
በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው “የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ሰነድ” እንደሚያስረዳው፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ የዲጂታል ዕድሎችን በመጠቀም ፈጠራ የታከለበትና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያስችል በኢትዮጵያ መንግስት የሚመራ ተነሳሽነት ነው። ስትራቴጂው ከአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የአስር ዓመት የልማት ዕቅድን ከመሳሰሉ ቁልፍ አገራዊ ስትራቴጂዎች ጋር እንዲሁም እንደ አፍሪካ ህብረት አህጉራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ካሉ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂዎች ጋር የተናበበም ነው። በዚህ ሰነድ ውስጥ የቱሪዝም ዘርፉ እንደ አንድ ቁልፍ ጉዳይ ተካቷል። በተለይ ቴክኖሎጂን በማዘመንና ወደ ተሻለ ደረጃ በማሳደግ ኢትዮጵያ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚሰራ ሰነዱ ያመለክታል።
ቱሪዝምን ተወዳዳሪ ለማድረግ የዲጂታል አሰራር መዝርጋት እንደሚያስፈልግ ሰነዱ ግልፅ አድርጎ አስቀምጧል። ይህንን ለማድረግ ሶስት መልካም አጋጣሚዎች ተለይተዋል። የመጀመሪያው የቱሪዝም ዲጂታላይዜሽን ግብረ ኃይል በማቋቋም የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ዲጂታላይዝ ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የዲጂታል የገበያ ስርዓትን በማበጀት የቱሪስት ፍሰትን እና የቆይታ እና ተሳትፎ መጠኑን ማሻሻል ነው። ሶስተኛው ደግሞ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን የዲጂታል አገልግሎት እንዲሰጡ አቅም መገንባት ነው። ከሰሞኑ ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረው የቨርቹዋል ቱሪዝም የዚህ ጥረት አንዱ አካል ነው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20 ቀን 2015 ዓ.ም