የንግድን ጣዕም ያወቁት ገና ተማሪ እያሉ ነው። ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምረው ነብሳቸው ለንግድ አድልታለች። እሳቸውም ይህን ለመረዳት ጊዜ አላባከኑም፤ ከትምህርት የተረፈ ጊዜያቸውን ሁሉ ትናንሽ በሚባሉ የንግድ ሥራዎች አሟጠው ተጠቅመዋል።
ይህ ብቻ አይደለም፤ የሚያገኟትን ጥቂት ገንዘብ ሁሉ ወደ ሥራ በመቀየር ውጤታማ ለመሆን ወጥተዋል ወርደዋል። ሩጫና ትጋታቸው ፍሬያማ መሆን እስኪጀምር አላረፈም። ዛሬም ቢሆን ታዲያ ከሥራ የሚቀድም ጉዳይ እርሳቸው ጋ ቦታ የለውም፤ ለሥራቸው የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት ከላይ ታች ይላሉ።
ለንግድ ያላቸው ከፍተኛ ፍላጎት እንዲሁም ግንዛቤያቸው ተደምረው ተማሪ እያሉ አንስቶ ገንዘብ የመያዝ ዕድል አጋጥሟቸዋል። ገና በለጋ ዕድሜያቸው ገንዘብ መቁጠር የጀመሩት የዛሬው የስኬት እንግዳችን የቶፕ ውሃ ፋብሪካ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ድንቁ ናቸው።
አቶ አበበ ተማሪ እያሉ ጀምሮ የተለያዩ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ቤተሰባቸውን አላስቸገሩም። ይልቁኑም ለአርሶ አደር ቤተሰባቸው ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ያደርጉ እንደነበር ያስታውሳሉ። ያም ቢሆን ታዲያ ወላጆቻቸው ለትምህርት ቅድሚያ ይሰጡ ነበርና ከንግዱ ይልቅ ትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጎትጉተዋቸዋል። በተለይም ወላጅ እናታቸው ልጆቻቸው ተምረው ሲመረቁ ማየት ትልቁ ምኞታቸው ነበር። በወቅቱ ለንግድ ሥራቸው ቅድሚያ የሰጡት አበበ፤ ትምህርታቸውንም ከንግድ ሥራቸው ጎን ለጎን በማስኬድ ከዲፕሎማ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ በመማር የወላጅ እናታቸውን ምኞት አሳክተዋል።
በጅማ ዞን ጋቲራ ወረዳ ተወልደው ያደጉት አቶ አበበ፤ ለሥራ ቅድሚያ በመስጠት ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚቻል እንደሆነ ያምናሉ። እምነታቸውን መኖር በመቻላቸውም በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ ዛሬ ከቶፕ ውሃ ፋብሪካ በተጨማሪ በርካታ እህት ኩባንያዎችን እያሰፉ ይገኛሉ።
ተወልደው ባደጉበት ጅማ አካባቢ አጋሮ ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው በኋላም ወደ ጅማ በማቅናት የከፍተኛ ትምህርታቸውን በሴልስማንሺፕ ተከታትለው በዲፕሎማ ተመርቀዋል። የንግድ ሥራ እጅግ እያጓጓቸው በመምጣቱ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ገታ በማድረግ ሙሉ ጊዜያቸውን ለንግድ ሥራው ሰጥተው ቆይተዋል።
የሥራ ምርጫ ያልነበራቸው አቶ አበበ፤ በእህል ንግድ ተሰማርተው ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ያስታውሳሉ። በተለይም ከጅማ ወደ መቱ፣ በደሌና አዲስ አበባ በመጓጓዝ በእህል ንግድና በቡና ንግድ ለብዙ ጊዜ ሰርተዋል።
በንግድ ዓለም የሚያውቋት አዲስ አበባ ደግሞ በሌሎች ንግዶች መሳተፍ የሚችሉባቸውን የተለያዩ በሮች ለአቶ አበበ ከፈተችላቸው። አጋጣሚዎችን ሁሉ ወደ ዕድል በመቀየር ለሥራ የሚተጉ በመሆናቸውም ከጅማ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት በተለያዩ የጨረታ ሥራዎች ተሳትፈው ውጤታማ መሆን ችለዋል።የጨረታ ሥራውን አስከትለው ያቋቋሙት የጫማ ፋብሪካም ውጤታማ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በብዙ ጥረትና ትጋት መስመር እየያዘ የመጣውን የንግድ ሥራ እያስፋፉ የመጡት አቶ አበበ፤ ትምህርት የሁሉም ነገር መሰረት እንደሆነ ያምናሉ። ለዚህም ይመስላል ለሥራው ቅድሚያ በመስጠት ገታ አድረገውት የነበረውን ትምህርት ካላቸው ጊዜ ተሻምተው በተለያዩ የትምህርት መስኮች ወደ ለመማር ወደ ኮሌጆች ያቀኑት። በዚህም በቢዝነስ ማኔጅመንትና በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ማግኘት ችለዋል። በአሁኑ ወቅትም ከአገረ አሜሪካ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኦላይን እየተከታተሉ ይገኛሉ።
በአገሪቱ ተወዳዳሪ የሆነው ቶፕ ውሃ ፋብሪካን ከማቋቋም ባለፈ በአሁኑ ወቅት በሪልስቴት፣ በሆቴልና ለኮንስትራክሽን ግብዓት መሆን የሚችሉ ምርቶችን በማምረት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ አበበ፤ በተለይም የውሃ ፋብሪካው በሚገኝበት ቡራዩ ታጠቅ ኢንዱስትሪ መንደር በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ድርጅቱ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ በሥሩ ካሉት ሠራተኞች ጋር ያለው ግንኙነት ቤተሰባዊና ሳቢ ስለመሆኑም ፋብሪካውን በጎበኘንበት ወቅት መረዳት ችለናል።
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም የድርሻውን እየተወጣ የሚገኘው ይህው ድርጅት፣ በርካታ ሰው ተኮር አበርክቶዎችን እያደረገ ስለመሆኑም ተረድተናል። በቡራዩ ከተማ ታጠቅ ኢንዱስትሪ መንደር የግንባታ ሥራውን አጠናቅቆ በ2010 ዓ.ም ውሃ አምርቶ ለገበያ ማቅረብ የጀመረው ቶፕ ውሃ ፋብሪካ፣ ራሱን እያሳደገ በመምጣት እህት ኩባንያዎችን መውለድ ችሏል።
የዛሬ አምስት ዓመት አንድ ብሎ የጀመረው ቶፕ የውሃ ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት ስድስት ሳይቶችን በመገንባት የማምረት አቅሙን በማሳደግ የተደራሽነት አድማሱንም እያሰፋ ይገኛል። በአጭር ጊዜ ውስጥ አቅሙን እያሳደገ የመጣው ፋብሪካው፣ በሰዓት 18 ሺ ሌትር ውሃን ያመርት ከነበረበት ሁኔታ በአሁኑ ወቅት በሰዓት 138 ሺ ሌትር ውሃ እያመረተ ስለመሆኑ ተረድተናል።
በውሃ ምርት ሂደት ውስጥ ከ ሀ እስከ ፐ ያለው ሥራ የሚከናወነው በፋብሪካው ውስጥ እንደሆነ ያጫወቱን አቶ አበበ፤ ፕላስቲክ ኮዳዎቹን ማምረት የሚያስችል ጥሬ ዕቃ ከውጭ በማምጣት ክዳኑን ጨምሮ ፕላስቲክ ኮዳዎቹን በተለያየ መጠን እንዲሁም መግለጫውን የሚይዝ ላስቲክ (ሌብል) በፋብሪካ ውስጥ እንደሚመረት ይናገራሉ።
ይህ ብቻ አይደለም፤ ፕላስቲክ ኮዳዎቹ መልሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተሰብስበው ይፈጫሉ። የተፈጩትን ፕላስቲክ ኮዳዎችም ወደ ውጭ ሀገር በመላክ አገሪቷ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ፋብሪካው ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ከሚገኘው የውጭ ምንዛሬ በበለጠ ታዲያ ፕላስቲክ ኮዳዎቹ አካባቢን በመበከል የሚያደርሱትን ተጽዕኖ መቀነስ ቀዳሚ ሥራቸው እንደሆነም አስረድተዋል። ተፈጭተው ለውጭ ገበያ የሚላኩት ፕላስቲክ ኮዳዎች ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ሲሆን፣ በተለይም ለጅንስ፣ ለፖሊስተር ጨርቆችና ለክር ምርት ግብአትነት ይውላሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ መሆን የቻለው ቶፕ ውሃ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ በሚገኙ የክልል ከተሞችም በሙሉ ተደራሽነቱን ማረጋገጥ ችሏል። በገበያ ሰንሰለት ውስጥም ከ300 የሚልቁ ወኪሎች ተሳታፊ በመሆን ቶፕ ውሃን ከፋብሪካው በመረከብ በክልል ከተሞች ሁሉ ተደራሽ ያደርጋሉ። በገበያ ሰንሰለቱ ብቻ ለ300 ሰዎች የስራ እድል መፍጠር ችሏል፤ በምርት ሂደት ውስጥ ከ1500 ለሚልቁ ዜጎች በቋሚነትና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
‹‹በመስጠት መጉደል የለም›› የሚሉት አቶ አበበ፣ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ሲሳተፉ የንግድ ሥራው ከሚያገኘው ትርፋ ለሰዎች መትረፍና ብዙዎችን መጥቀም የሚችል ሥራ መሥራት ያስደስታቸዋል። አቶ አበበ ፋብሪካ መገንባት ሲያስቡም ፋብሪካ ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል መሆኑ አንደኛው ምክንያታቸው መሆኑን ያስታውሳሉ።
ከምርቶች ሁሉ ውሃን መምረጣቸው ደግሞ ውሃ ሕይወት በመሆኑና ሕይወት ላላቸው ነገሮች በሙሉ ጠቃሚ እንጂ ጎጂ አለመሆኑን በመረዳት ነው። ‹‹በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ለሰዎች ጥሩ ማድረግ ያስደስተኛል፤ ለሰዎች በማድረጌ ምክንያት የሚጎድለው የኪሴ ጎዶሎም በእጥፍ ይሞላል›› የሚል ዕምነት ያላቸው አቶ አበበ፤ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም የጎላ አበርክቶ ማድረጋቸውን ከሰጡን መረጃ ተረድተናል። ቶፕ ውሃ ፋብሪካ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከሚወጣባቸው መንገዶች አንዱ ፋብሪካው አምርቶ ለገበያ ከሚያቀርባቸው የውሃ ጠርሙሶች ሁለት ሳንቲም በመቀነስ ውሃ ላልደረሰባቸው አካባቢዎች ውሃ ማዳረስ ነው። በተለይም ውሃ አጠር በሆኑና ለድርቅ በተጋለጡ አካባቢዎች ክልል፣ ዘርና ሐይማኖት ሳይገድባቸው በማንኛውም የውሃ ችግር ባለበት አካባቢ መፍትሔ ለመሆን ይተጋሉ። ይህን መሰረት በማድረግም የመጀመሪያ ሥራቸውን ቦረና ላይ ጀምረዋል።
በአገሪቷ ድርቅ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ በሆነው ቦረና ያቤሎ አካባቢ ከብቶች በከፍተኛ ደረጃ በተጎዱበት ጊዜ ቶፕ ውሃ ቀድሞ በመድረስ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጉድጓድ በማስቆፈር የመጠጥ ውሃ ማውጣት ችሏል። የወጣው ውሃም 30 ቀበሌዎችን ተደራሽ ማድረግ የሚችል ሲሆን፣ በዚህም የአካባቢውን ማህበረሰብና እንስሳቱን መታደግ ተችሏል። በቀጣይም ይህንኑ በጎና የድርጅቱ ዓላማ የሆነውን ሥራ አጠናክረው በማስቀጠል ውሃ ለተጠሙ የማህበረሰብ ክፍሎች እርካታን ይዘው መድረስ የሁልጊዜ ዕቅዳቸው ነው።
በተለያዩ የልማት ሥራዎች የሚሳተፉት አቶ አበበ፤ በተለይም ቶፕ ውሃ በሚመረትበት በቡራዩ ከተማ ለትምህርት ቤት ግንባታ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሲያደርጉ በተመሳሳይ በገላን ከተማም እንዲሁ ሶስት ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለትምህርት ቤቶቹ መጠናቀቅ ምክንያት ሆነዋል። ከዚህ በተጨማሪም በትውልድ አካባቢያቸው ጅማ ዞን ጋቲራ ወረዳ ሰባ ሚሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቅ ባለ ስድስት ወለል ዘመናዊ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስገንብተው እያጠናቀቁ ይገኛሉ።
ሰው ተኮር በሆኑ የልማት ሥራዎች ሰፊ ተሳትፎ ያላቸው አቶ አበበ፣ አገር በምታደርገው ማንኛውም ጥሪ ምላሽ ለመስጠት በሚያደርጉት ጥረትም የጎላ አበርክቶ አላቸው። ገበታ ለአገርን ጨምሮ የተለያዩ አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ የበኩላቸውን ተወጥተዋል። በኮቪድ ወቅትም የተለያዩ እገዛዎችን ለማህበረሰቡ ሲያደርጉ እንደነበር ተረድተናል።
ከሁሉም ቀዳሚና የዜግነት ግዴታ በሆነው ግብር መክፈልም እንዲሁ ቀዳሚ ቀዳሚ የሆኑት አቶ አበበ፤ በ2014 ዓ.ም በአጠቃላይ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ግብር ከፋዮች መካከል አንደኛ በመውጣት ተሸላሚ እንደነበሩ አስታውሰው፣ በተያዘው በጀት ዓመት ካለፈው ዓመት በተሻለ በመክፈል ቀዳሚ ለመሆን እንደሚሰሩ ይናገራሉ።
በ2023 አፍሪካን ለመድረስ አቅዶ እየሠራ ያለው ቶፕ ውሃ፣ ድንበር ተሻጋሪ በመሆን ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ኩራት ለመሆን እየተጋ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም ቶፕ ውሃን ለሳውዳረቢያ ኤክስፖርት ለማድረግ ዝግጅን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በቀጣይም ለኬንያ፣ ለጅቡቲና ለሌሎች አገራትም ኤክስፖርት በማድረግ በምስራቅ አፍሪካ ገበያ የመግባት ዕቅድ አላቸው። ይህም አገር በእጅጉ እየተፈተነች ያለችበትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለል የበኩሉን አይነተኛ ድርሻ ይኖረዋል።
ቶፕ ውሃ እንደስሙ ከፍ በማለት ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ቀዳሚ ውሃ አምራች ለመሆን አቅዶ እየሠራ ስለመሆኑ ያነሱት አቶ አበበ፣ ከውሃ በተጨማሪም በሪልስቴትና በሆቴልም አሻራቸውን እያኖሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ለኮንስትራክሽን ግብአት መሆን የሚችሉ የተለያዩ ምርቶችን ለማምረትም የማሽን ተከላውን አጠናቅቀው ወደ ምርት ለመግባት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ወደፊት አንድትራመድ፣ እንድትበለጽግና በተለያዩ በረከቶቿ በዓለም እንድትታወቅ ለማድርግ እያንዳንዱ ዜጋ ድርሻ እንዳለው ያነሱት አቶ አበበ፤ በቀጣይም ፋብሪካቸው በምርት አቅርቦቱም ሆነ በጥራቱ ኢትዮጵያን ማስጠራት እንዲችል፤ ከአገር አልፎ በአፍሪካ፤ ብሎም በዓለም ኢትዮጵያዊው ቶፕ ውሃ እንዲታወቅና የአገር ኩራት እንዲሆን መሥራት ዕቅዳቸው እንደሆነ አጫውተውናል። ይህም ብቻ አይደለም በሪልስቴት፣ በሆቴልና በሌሎች የሥራ ዘርፎችም ለአገር የሚተርፍ ሥራ በመሥራት ኃላፊነትን መወጣት የግድ ነውና መሥራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2015