ባለፈው ሳምንት ተቋማችን የአንድ ቀን ስልጠና አዘጋጅቶልን ነበር። ስልጠናውን የሰጡን ደግሞ ዶ/ር ወዳጄነህ መሐረነ ነበሩ። ዶክተሩ ስለምን እያስረዱ እንደሆነ አሁን በማላስታውሰው ምክንያት ስለ ፌስቡክ ኮመንት አነሱና የደረሳቸውን ስድብ ነገሩን። ከዚያ በኋላ ለተወሰኑ ሰዓታት አእምሮዬ ሲያብሰለስል የነበረው ስለ ስድቡ እና ስለ ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ነበር። እኔ በግሌ የሚሰድቡኝን ሰዎች ብሎክ እያደረግኩ አሰናብታለሁ። ነገር ግን አንዳንዴ ከስድብም በላይ የሚያስቀይሙ ነገሮችን የሚያደርጉ ሰዎችን በአካል የማውቃቸው ወዳጆቼ ስለሆኑ እንዲሁ እየተቃጠልኩም ቢሆን ችያቸው እቀመጣለሁ። ብሎክ አድርጌያቸው ብገላገል ደስ ይለኛል። አንድ ቀን ቆፍጠን እንደምል ተስፋ አለኝ።
የስነ ልቦና ባለሙያዎች ማኅበራዊ ሚዲያ በአዕምሮአችን ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳለው በየጊዜው ይገልጻሉ። ስለዚህም አንዳንዴ ብሎክ ማድረግ የአዕምሮ ጤና የመጠበቅ አካል ነውና ምንም ቅር ሊለን አይገባም። በዛሬው ትዝብቴ ፌስቡክ ላይ ያየኋቸውን የማይመቹ ባህሪዎች በመደብ በመደብ አስቀምጬ አንባቢዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ከሆኑ እነዚህን ሰዎች ከዙሪያቸው እንዲያርቁ እመክራለሁ፣ ጀመርኩ፣…
አንደኛ አንዳንድ ሰዎች ለሰላምህ እና ለጤናህ አደገኛ ናቸው። የሚጽፉት፤የሚፖስቱት የሚሰጡት ኮመንት ሁሉ የሚረብሽ ፤ ጭንቀት የሚፈጥር ይሆናል። ሁልጊዜ መጥፎ ዜናዎችን ይዘው የሚመጡ ፤ ጭንቀት የሚፈጥር ወሬን የሚለቃቅሙ ሰዎችን ምንም ያህል ብታውቋቸው እና ብትወዷቸው ብሎክ ልታደርጓቸው ይገባል። እነዚህ ሰዎች የሚጽፉት እና የሚለጥፉት በተለየ ሁኔታ ለእናንተ ተብሎ ባይሆንም እንኳ የሚለጥፉት ነገር እናንተ ግድግዳ ላይ መጥቶ ማየታችሁ እና መረበሻችሁ አይቀርም። ስለዚህም እነዚህ ሰዎች በዚያም አለ በዚህ ለአዕምሮአችሁ ጤና በጣም አደገኛ ናቸውና ብሎክ ብታደርጓቸው ጠቃሚ ነው።
ሁለተኛ በፖስታቸውም፤ በኮመንታቸውም ሆነ በሚጽፉላችሁ መልዕክት ሆን ብለው እናንተን የሚተነኩሱ ሰዎችን ማስወገድ ምንም ርህራሄ የማያስፈልገው ተግባር ነው። በኢንቦክስ ካላወራሽኝ ብሎ የሚነዘንዝ ፤ በለጠፋችሁት በማንኛውም ነገር ላይ ስድብ የሚያቀርብ፤ በኢንቦክስ ስድብ የሚልክ ፤ የብልግና ምስሎች እና ጽሑፎችን የሚልክን እና መሰል ሰዎችን ብሎክ ማድረግ ግዴታ ነው።
ሶስተኛ መጥፎ ትዝታ የሚቀሰቅሱባችሁን ሰዎች ብሎክ ማድረግ ለነገ የማይባል ሥራ ነው። በዚህ ውስጥ ብዙውን ጊዜ የሚካተቱት የቀድሞ የፍቅር አጋሮች ናቸው። በተለይም አንዳንድ የቀድሞ ቦይፍሬንዶች እና ገርል ፍሬንዶች ያንተን ወይም ያንቺን ወደፊት መራመድ የማይፈልጉ ይሆናሉ። ስለዚህም ባገኙት አጋጣሚ በሙሉ ወደኋላ ሊጎትቷችሁ መጣራቸው አይቀርምና እነሱን ማሰናበት ግዴታ ይሆናል።
አራተኛ አክራሪዎች ብሎክ መደረግ ካለባቸው ሰዎች መሐከል ቀዳሚዎች ናቸው። አክራሪዎች ሲባሉ በተለይም ከራሳቸው ሃይማኖት በበለጠ የሌላውን ሃይማኖት በመተቸት ላይ የተጠመዱ ሰዎችን ሰብስቦ ማስቀመጥ በጊዜ ሂደት ተጎትቶ የእነሱ ጨዋታ ውስጥ መግባትን ያመጣልና እነሱን ላለመምሰል እነሱን በብሎክ ማሰናበት ግዴታ ነው።
አምስተኛ በሀሳብ ላይ መከራከር የማይወዱ እና ፖስትህን እና አንተን ለይተው የማያዩ ሰዎች ብሎክ ባይገባቸው እንኳ ከፌስቡክ ጋደኝነት መፋቅ (አንፍሬንድ) መደረግ አለባቸው። እነዚህ ሰዎች ማንኛውንም የምትፖስተውን ነገር የሚያገናኙት ካንተ ብሔር፤ ሃይማኖት ወይም ሌላ መገለጫዎችህ ጋር ነው። ሀሳብህን ከመሞገት ይልቅ አንተን መስደብ ይቀናቸዋል። በክርክር ሲሸነፉ አንተ እንዲህ ያልከው እንዲህ ስለሆንክ ነው ብለው ነገር ይጠመዝዛሉ። ስለዚህም ማሰናበት አይጎዳህም።
ስድስተኛ ፌክ አካውንቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ብሎክ መደረግ አለባቸው። እነዚህ አካውንቶች የሚያቀርቡት መረጃም ሆነ የሚያወሩት ነገር የሚመች ቢሆን እንኳ ሐሰተኛ(ፌክ)መሆናቸው ከታወቀ ማስወገድ ሊያሳስብ አይገባም። ምክንያቱም ገና ከጀመሩ ሰዎቹ ፌክ አካውንት መክፈታቸው በራሱ አንዳች የተደበቀ ነገር እንዳላቸው አመላካች ስለሆነ ነው።
ሰባተኛ ስለ ሰው በፖስትም ይሁን በኢንቦክስ ወሬ የሚያቀባብሉ ሰዎች ብሎክ መደረግ አለባቸው። እርግጥ ሁላችንም ዝነኛ ስለሆኑ ሰዎች በየጊዜው እናወራለን እንከራከራለን እንቀልዳለን። ይህ ከዝና ጋር አብሮ የሚመጣ ስለሆነ የሚጠበቅ ነው። ነገር ግን በፌስቡክ ስላወቁት አንድ መደበኛ ሰው አጀንዳ አድርገው የሚያወሩ እና ሐሜት የሚያቀባብሉ አንዳንድ ሰዎች እንዳሉ ግልጽ ነው። እነዚህ የመንደር አመላቸውን ወደ አደባባይ ይዘው የወጡ ሰዎች የደህንነት ስጋት ናቸውና መሰናበት አለባቸው።
ስምንተኛ መልዕክት ኮፒ እያደረጉ የሚልኩልህ እና የማትፈልገው ግሩፕ ውስጥ እያስገቡ የሚያጨናንቁህ ሰዎች ከጓደኝነት ዝርዝር ውስጥ ወጪ መደረግ አለባቸው። እነዚህ ሰዎች ስላንተ ግላዊ መብት ምንም ግድ የሌላቸው ናቸው። እገሌ ድርጅት ለምናምን ሽልማት ሊሸልም ነው የሚል መልዕክት ከመቶ ሰው ደርሷችሁ አያውቅም? እንደዚህ አይነት ምንነቱ የማይታወቅ ነገር ኮፒ እያደረጉ የሚልኩ ሰዎች አንድ ቀን ቫይረስ ልከው አካውንትህን ሳያስበሉህ በፊት ቻው ልትላቸው ይገባል።
ዘጠነኛ ምንነቱ ያልተጣራ እና የሆነ ቦታ ያገኙትን ወሬ ገልብጠው የሚለጥፉ ሰዎችን አንድ ሁለቴ ካየሃቸው በኋላ ቻው ልትላቸው ይገባል። እነዚህ ተሳስቶ አሳሳቾች ናቸው። ያልሞተውን ሰው ሞተ ብለው ያስደነገጡህ የሉም? እነሱን ዓይነቶቹን ማለት ነው። እነዚህ ሰዎች ሌላ ቦታ ላይክ ያስገኘን ማንኛውም ነገር ገልብጠው መለጠፍ ብቸኛ ሙያቸው ነው። አንዳንዶቹማ ጭራሽ የሰው ጽሑፍ ሲዘርፉ ምንጭ እንኳን አይጠቅሱም። የሰው ውሸት ከመስረቃቸው በላይ የውሸት ምንጫቸውን አለመጥቀሳቸው ያስቦልካቸዋል።
አስረኛ የማይናገሩ የማይጋገሩ ፤ ፖስት የማያደርጉ ፤ ኮመንት የማይሰጡ ፤ በኢንቦክስም ድምጻቸው የማይሰማ ሰዎች ሰላማዊ ሰዎች ቢሆኑም በሀሳብ ገበያ ላይ ሀሳብ መሸጥ እና መለወጥን የማይቀበሉ ስለሆኑ ለሌላ ሀሳብ ላለው ሰው ቦታ ሊለቁ ግድ ይላቸዋል። እነዚህ ሰዎች ብሎክ ባይደረጉ እንኳ አንፍሬንድ ተደርገው ቦታ መልቀቃቸው አስፈላጊ ነው።
እኔ ይህን ካልኩ ዘንድ እናንተ ደግሞ የራሳችሁን ጨምሩበት። ዋናው ልብ ልትሉ የሚገባው ጉዳይ ግን ማንም ሰው ቢሆን በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል እየመጣ እንዲያውካችሁ እና አዕምሮአችሁን እንዲበጠብጥ ልተፈቅዱለት እንደማይገባ ነው። ቸር እንሰንብት!
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2015