አዲስ አበባ፡– ለሀገር ዕድገት መሰረቱ አንድ ነት፣ይቅር ባይነትና እርቅ መሆኑን ከትናንት በስትያ በተካሄደው የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ 25ኛ ዓመት የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ የተገኙት የሩዋንዳና የኢትዮጵያ መሪዎች አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ ከትናንት በስትያ በሩዋንዳ ርዕሰ ከተማ ኪጋሊ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ ሌሎችን እንደ ራሳችን በማየት ያለፈ ብሶታችንን መርሳትና በአንድነት መንፈስ መሰባሰብ አለብን ብለዋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ በዚህ ዓይነቱ ቀውስ ውስጥ ማለፍ ተገቢ የነበረ ባይሆንም የሩዋንዳ ሕዝብና መንግሥት አንድነት፣ ይቅር ባይነትንና ዕርቅን የዕድገታቸው መሠረት አድርገው መነሳታቸውን አድንቀዋል፡፡
የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሚ በበኩላ ቸው ‹‹እ.ኤ.አ በ1994 በሩዋንዳ አንድም ተስፋ አልነበረም›› ያሉ ሲሆን፣ ይሁንና አሁን በሩዋንዳ አዲስ ብርሃን ዳግም ፈንጥቋል፤ ይህም የሆነው ሩዋንዳውያን በአንድነትና በይቅር ባይነት በጋራ እጅ ለእጅ ስለተያያዙ ነው›› ብለዋል፡ ፡ ሩዋንዳውያን እንደገና ቤተሰባዊ በመሆናቸው እጆቻቸው ተያይዘው የሀገሪቱን ምሶሶ ሠርተዋል፤ አሁን በጋራ እጅ ለእጅ በመያያዛችን እስከአሁን በጋራ ቆይተናል›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡
‹‹ሩዋንዳውያን ዳግም አንዳቸው ባንዳቸው ላይ አይነሱም›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በእያንዳንዱ ሩዋንዳውያን አዕምሮ ውስጥ መጥፎ ጠባሳ
ተቀርፆ የቀረ ቢሆንም አንዳችንም ብቻችንን አይደለንም፤ እኛ ሩዋንዳውያን ለአዲስ ጅምር ራሳችንን ሰጥተናል›› ብለዋል፡፡
የዘር ጭፍጨፋው 25ኛ ዓመት መታሰቢያ ዝግጅት ለዓለም ሕዝብ ተግባብቶና በልዩነት መሐል ተቻችሎ የመኖርን አስፈላጊነት ለማሳሰብ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በዝግጅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ የቻድ፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ የጅቡቲ፣ የኒጀር፣ የቤልጂየምና የካናዳ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት መሪዎች ተገኝተዋል፡፡
በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በ100 ቀናት ብቻ 800 ሺ ቱትሲዎች የተገደሉ መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ሩዋንዳ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት መሳብ የቻለች ሀገር ብትሆንም ጭፍጨፋው በሀገሪቱ ታሪክ ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2011
በአስናቀ ፀጋዬ