.የመከላከያ ሠራዊት ተሰማርቷል
አዲስ አበባ፡– የብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት በአማራ ክልል የኦሮሞ ልዩ ዞንና በሰሜን ሸዋ የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ለማረጋጋትና የዜጎች ሰላም ለማረጋገጥ አስፈላጊው፣ ህጋዊና ተመጣጣኝ ዕርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ማስተላለፉን አስታወቀ። የክልሉ መንግሥት ባቀረበው ጥሪ መሰረት የሀገር መከላከያ ሠራዊት መሰማራቱ ተገለጸ፡፡
ምክር ቤቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የዜጎች በሰላም የመኖር ዋስትና እና የሕግ የበላይነት ጉዳይ
ለድርድር የማይቀርብ የመንግሥት ዋነኛ ኃላፊነት ነው። በመሆኑም የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ለማረጋጋትና የዜጎች ሰላም ዋስትና እንዲያገኝ የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አስከባሪ ተቋማት አስፈላጊውን ህጋዊና ተመጣጣኝ ዕርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ ተላልፏል።
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና በሰሜን ሸዋ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ያለውን የሰላም መደፍረስ እንዲሁም በኬሚሴ እና በአጎራባች አካባቢዎች የተከሰተው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት በምንም አግባብ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ያለው መግለጫው፣ብጥብጡን ያቀናበሩት፣ ያነሳሱትና የፈጸሙትን አካላት ለህግ የማቅረቡ ጉዳይ በከፍተኛ ትኩረት ይሠራበታል። ለዚህም ጥናት የሚያደርግ ቡድን ከክልሉ እና ከፌዴራል ተቋማት ተሰማርቷል። በጥናቱ ውጤት መሠረትም በብጥብጡ ላይ እጁ ያለበት ማንኛውም አካል በህግ ተጠያቂ ይሆናል ብሏል፡፡
ችግሮች የሚከሰቱት በውስን የራሳቸው አጀንዳ ባላቸው የጥፋት ኃይሎች ሆኖ ሳለ በመደበኛውም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያ የህዝብ ለህዝብ ግጭት የተፈጠረ በማስመሰል የማራገብ ሥራ የሚሠሩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ጉዳዩን በሰከነ፣ ሙያዊ ስነ-ምግባርና የሀገርን አንድነት በሚጠብቅ መልኩ እንዲይዙት ምክር ቤቱ አሳስቧል።
በተጨማሪም መንግሥት ህግን ለማስከበርና የዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኑንና ሕገወጥ ተግባራት ላይ የሚሳተፉ አካላት ከድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ ሕግን ከማስከበር ወደ ኋላ እንደማይልም በመግለጫው ተቀምጧል፡፡
በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የምክትል ኢታማዦር ሹም ፅህፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ተስፋዬ አያሌው ትናንት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፣በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥት ባቀረበው ጥሪ መሰረት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢዎቹ ገብቶ የማረጋጋት ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል። አካባቢዎቹ እየተረጋጉ ቢሆንም በአንዳንድ ገጠራማ አካባቢዎች የተኩስ ልውውጡ የሚሰማ መሆኑን ጠቁመዋል።
አካባቢዎቹ በሁለቱም በኩል ታጥቆ ያለ ህዝብ የሚኖርባቸውና ሰፊ በመሆናቸው በብቃት ለመቆጣጠር ተጨማሪ ኃይል ወደ ስፍራዎቹ እየገባ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በሁሉም ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች እየገባ የማረጋጋት እና የመቆጣጠር ሽራ ያከናውናል ብለዋል። ተዘግተው ያሉ የደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ደብረ ሲና እና ደብረ ብርሃን መንገዶችንም የማስከፈት ሥራ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል። ግጭቶቹ
ባሉባቸው አካባቢዎች በሁለቱም ወገን ያሉ አመራሮች ከጉዳዩ እጃቸውን እንዲያስወጡም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን በበኩላቸው የተከሰተውን ችግር እስመልክተው ለአማራ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ በሰጡት መግለጫ፣ችግሩ ሲጀምር በአካባቢው ያሉ የፀጥታ ኃይሎች ለማብረድ ሙከራ አድርገው እንደነበር በመግለጽ እየጨመረ ሲመጣም ከፌዴራል የፀጥታ አካላት ከመከላከያና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በጋራ በመሆን ችግሩን ለማርገብና ጉዳቱን ለመቀነስ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ችግሩ እንዳይባባስ ሲሠራ የነበረ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ኃይሎች በፍጥነት መድረስ ባለመቻላቸው የሰው ህይወት ሊያልፍ ችሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በቀጣይም ችግሩን በማስቆም አካባቢው ወደ ነበረበት ሰላም እንዲመለስና ህዝቡም ወደሰላማዊ እንቅስቃሴው እንዲገባ ጠንካራ የሰላም ማስከበርና የፀጥታ ሥራዎች በፌዴራልና በክልል የፀጥታ አካላት የጋራ ጥረት የሚሠራ ይሆናል ብለዋል።
ችግሩን ለመፍታትም ከክልልና ከዞን አመራሮች እንዲሁም ከፌዴራል ሰዎችን በመመልመል ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን እየሠሩ እንደሆንም ተናግረዋል። ችግሩ እንዳይስፋፋና እንዲቆም ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው፣ የአካባቢው ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ ነገሮችን ተከትለው በሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ለተጨማሪ ችግር መንስኤ እንዳይሆኑ እና ለተጀመረው የሰላም ማስከበር ሥራ ህብረተሰቡ እንዲተባበር ጠይቀዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ