የመጀመሪያ ዲግሪውን በቢዝነስ ማኔጅመነት ያገኘ ቢሆንም አባቱ የግብርና ምርምር ስራዎችን ይሰሩ ስለነበር በልጅነቱ ሲያነባቸው የነበሩ አብዛኛዎቹ መፅሃፍቶች ከግብርና ጋር የተያያዙ ነበሩ። ካደገም በኋላ በከፍተኛ ትምህርት ቆይታው ለማሟያ ይሰራቸው የነበሩ ፅሁፎች ግብርናን የሚዳስሱ ነበሩ።
ስራ የጀመረው በአዳማ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሲሆን በመምህርነት በቆየባቸው ጊዚያት በተለይ በማህበረሰብ ፕሮጀክቶች ላይ አንዳንድ ፅሁፎችን እንዲያዘጋጅና ችግሮችን ቀረብ ብሎ እንዲያይ እድል ፈጥሮለታል። ዛሬ ላይ ለሚሰራው ስራም ትልቅ መሰረት ጥሎለታል።
በአርሲ ዩኒቨርስቲ የቢዝነስ ትምህርት ቤት ሲመሰረትም በመምህርነት አገልግሏል። በዚሁ ዩኒቨርስቲ ቆይታው በግብርናው አካባቢ ማህበረሰቡን ቀረብ ብሎ ያለበትን ችግርና የትኛው ችግር ወደ ቢዝነስ ሊቀየር እንደሚችል ለመረዳት ችሏል።
በኢትዮጵያ የግብርና ስራ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን እንደ እድል ተጠቅሞ ስራ መስራት ይቻላል የሚል እምነት በውስጡ በማደሩ ከዛሬ ስምንት አመት በፊት ‹‹ለእርሻ›› የተሰኘና በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ነው የተባለለትን ለአርሶ አደሮች የዲጂታል ግብርና አገልግሎት የሚሰጥ ምህዳር (ፕላትፎርም) በመፍጠር ወደ ስራ ገባ።
በዚህም በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግና በዚሁ ምህዳር (ፕላትፎርም) ስር ላሉ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር አስቻለው። የግሪን አግሮ ሶሊዩሽን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወጣት አብርሃም እንድሪያስ።
ወጣት አብርሃም የመጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘው ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ማኔጅመንት ሲሆን የሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ በዚሁ የትምህርት መስክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀብሏል። በተማረበት የትምህርት መስክም በአዳማና በአርሲ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህርነት አገልግሏል።
በመምህርነት አገልግሎት ቆይታው በማህበረሰብ ፕሮጀክቶች ላይ አንዳንድ ፅሁፎችን እንዲያዘጋጅ ረድቶታል። ችግሮችን ቀረብ ብሎ እንዲያይም እድል ፈጥሮለታል። ከዚህ ባለፈ በግብርናው አካባቢ ማህረሰቡ ያለበትን ችግር በቅርበት ለማየት አስችሎታል። ከዚህ ችግር በመነሳት ቢዝነስ መፍጠር እንደሚቻልም ተረድቷል።
ከመምህርነት አገልግሎቱ በኋላ በግብርናው ዘርፈ ላይ በስፋት ሲሰራ መቆየቱና ስራን የማስፋት ፍላጎት በውስጡ መኖሩ ይህን ፕላትፎርም ለመፍጠር ምክንያት ሆኖታል። በተለይ ቀደም ሲል የግብርና ማሽነሪዎችን ለአርሶ አደሮች በሚያከራይበት ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመሄድ እድሉ ነበረው። በዚህ ግዜም በጣም ሰፊ እድል እንዳለ ለማወቅ ችሏል። ነገር ግን ሁሉንም ፍላጎት አንድ ኩባንያ ብቻውን ሊያሟላ እንደማይችል ተረድቷል።
በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ግብርና ዝናብ ተኮርና ወቅትን ጠብቆ የሚከናወን በመሆኑ አንድ ስራ ብቻ በመስራት ውጤታማ የሆነ የግብርና አገልግሎት መስጠት እንደማይቻል ተገንዝቧል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ደግሞ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የመሬት ይዞት በጣም ትንሽ መሆኑን አውቋል። ከዚህ በመነሳትም እ.ኤ.አ በ2018 በዚህ ዘርፍ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ምን እንደሚመስል ኬኒያ፣ ናይጄሪያና ህንድ በመጓዝ የመጎብኘትና ተሞክሮውን የመቅሰም አጋጣሚው ነበረው።
በዚህም ሀገራቱ የግብርና አገልግሎታቸውን እንዴት ማሳደግ እንደቻሉና በጊዜው የዲጂታል ግብርና አገልግሎት በደምብ እየተለመደ የመጣበት መሆኑን በሚገባ ለመረዳት ችሏል። በኢትዮጵያ ግን በርካታ አርሶ አደሮች ጋር ለመድረስ በተለይ ያለው የግብርና ማሽነሪ አነስተኛ በመሆኑ ይህን ቢዝነስ በተለመደው መንገድ ለማሳደግ እጅግ አስቸጋሪ እንደነበርም አውቋል።
ይሁንና የግብርና አገልግሎቱን ዲጂታል ማድረግ ቢቻል የግብርና ማሽነሪዎች ያላቸውንና ሌሎች የግብርና ግብአቶችን የሚሸጡ ሰዎችን በማሳተፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ከድምዳሜ ላይ ደረሰ። በዚሁ መነሻነትም ‹‹ለእርሻ›› የተሰኘ የዲጂታል ግብርና አገልግሎት ፕላትፎርም ፈጠረ።
በግዜው ፕላትፎርሙ ስራ ላይ መዋል እንደጀመረ አንዱና ትልቁ ችግር በገጠር አካባቢ የበይነ መረብ (ኢንተርኔት) መሰረተ ልማት በበቂ ሁኔታ አለመኖር ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የአርሶ አደሮች የማንበብና የመፃፍ ክህሎት አናሳ መሆን ፕላትፎርሙ በሚፊለገው ልክ ስራ ላይ እንዳይውልና አርሶ አደሩን በቀጥታ ለማግኘት ችግር ፈጥሯል።
አርሶ አደሮች ያላቸው ስልክ ‹‹አንድሮይድ›› አለመሆንም ሌላኛው ችግር ነበር። ከዚህ ባለፈ ደግሞ አዲስ ቴክኖሎጂን ለመቀበል ያለው ፍላጎት ዝቅተኛ መሆንም ተጨማሪ ችግር ፈጥሯል። የግብርናው ዘርፍ እንደሌሎቹ ዘርፎች በግለሰብ ደረጃ በቀላሉ ተገብቶበት የሚሰራበት አለመሆኑና ከሌሎች መንግስታዊና የምርምር ተቋማት ጋር በመሆን የሚሰራበት መሆኑም ሌላኛው ችግር ነበር።
ከነዚህ ችግሮች በመነሳት በአራት ክልሎች ማለትም በኦሮሚያ ሳቡሬ፣ በሶማሌ ጅጅጋ፣ በአማራ ባህርዳርና በሲዳማ ሃዋሳ ላይ ቢሮ እንዲቋቋም ተደረገ። በነዚሁ ቢሮዎች አማካኝነትና አዲስ አበባ ላይ ባለው ቢሮ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች በቀጥታ አርሶ አደሩን አግኝተው ይነጋገራሉ ። ይህም ችግሩን ከምንጩ ለመረዳት አስችሏል።
በችግር ውስጥ ለመስራትም ጥረት ተደርጓል። በሌላ በኩል ደግሞ አርሶ አደሩ ማንበብ መፃፍ፣ የበይነ መረብ (ኢንተርኔት) እውቀት ችግር ስላሉበትና አገልግሎቱን በቀጥታ ሊጠቀም የማይችል በመሆኑ የሞባይል መተግበሪያና የጥሪ ማእከል ከመገንባት ባለፈ ‹‹ለእርሻ ኤጀንት›› የሚባሉ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ስራ የሌላቸው ወጣቶችን በማሰልጠን የሞባይል መተግበሪያውን በመጠቀም በአርሶ አደሩና በፕላትፎርሙ በኩል ድልድይ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። እስካሁንም 642 የሚሆኑ ወኪሎች (ኤጀንቶች) ሰልጥነው ስራውን እያከናወኑ ይገኛሉ።
አጋርነት መገንባት ግዜ የሚፈጅ ጉዳይ መሆኑን በማጤን በአጋርነት ከድርጅቱ አቅም በላይ የሆኑ ነገሮችን ለአብነትም አርሶ አደሮችን የማሰልጠን ስራዎችን እንዲያግዙ፣ ወጪዎችን እንዲያጋሩና እነርሱ ጋር ያለውን እውቀት እንዲያካፍሉ በማድረግ ችግሮችን ለመፍታት ተሞክሯል።
የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች አነስተኛ ማሳ ያላቸው በመሆኑ ግብርናቸውን ለማከናወን የተለያዩ አገልግሎቶችን ይፈልጋሉ። በተለይ ደግሞ ለወጣቱ ግብርና ከባድ ነው። መሬት ኖሯቸው የግብርና ማሽነሪዎችን ለማግኘትም ይቸገራሉ። መሬታቸውን ካረሱ በኋላም ምርጥ ዘር፣ ማደበሪያና ሌሎች ግብርና ግብዓቶችን በቀላሉ ማግኘት አይችሉም። ከግብርና ጋር የተያያዙ ምክሮችንም እንደልብ አያገኙም። ይህ ምህዳር (ፕላትፎርም) የተዘጋጀውም በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ የግብርና ስራውን ለማቅለል ነው።
ይህንን ለማድረግም የሞባይል መተግበሪያ፣ የጥሪ ማእከልና ለእርሻ ኤጀንት የሚባል ሞዴል ተገንብቷል። በዚህ ሞዴል አማካኝነት የእርሻ ኤጀንቶችን እንደ ድልድይ በመጠቀም ለአርሶ አደሩ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ አግሮ ኬሚካልና ሌሎች የግብርና ግብአቶች ይቀርባሉ።
ለእርሻ ኤጀንቶች አርሶ አደሩን ፍላጎት እየሰበሰቡ በአቅራቢያው ካሉ የግብርና ግብአት ሱቆች ጋር ያገናኛሉ። በአቅራቢው ካሉ የግብርና ማሽነሪ ባለቤቶች ጋርም ያገናኙታል። አርሶ አደሩ የተሻለ ውሳኔ እንዲወስን የአየር ንብረትና የማዳበሪያ መረጃዎችንና ሌሎች የተለያዩ ምክሮችን ያቀርባሉ።
ይህም አርሶ አደሩ ጉልበት ሳያወጣና ግዜ ሳያጠፋ እነዚህን የግብርና ግባአቶች በቀላሉና በፈለገው ግዜ እንዲያገኝ አስችሎታል። የግብርና ማሽነሪዎችንም ብዙ ሳይለፋ እንዲያገኝና የአየር ንብረት መረጃዎችንና ሌሎች የግብርና ምክሮችን ለማግኘት ረድቶታል።
በአሁኑ ግዜም በአራት ክልሎች ላይ በዚሁ ፕላትፎርም አማካኝነት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። በዚሁ ዲጂታል ፕላትፎርም አማካኝነትም 71 ሺ የሚሆኑ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል። ከ 642 በላይ ለእርሻ ኤጀንቶችም አሉ። ከ172 በላይ የትራክተርና ኮምባይነር ባለቤቶች በዚህ ፕላትፎርም ውስጥ ተካተው ለአርሶ አደሩ አገልግሎት ይሰጣሉ። 29 የሚሆኑ ደግሞ ግብአት የሚሸጡ የግብርና አገልግሎት ማእከላት በፕላትፎርሙ ውስጥ ተካተዋል። ከ3 ሺ 100 በላይ የመንግስት የግብርና ኤክስቴንሽን ኤጀንቶች ከዚህ ፕላትፎርም የምክር አገልግሎት ያገኛሉ።
በሂደት ደግሞ የአየር ንብረት ምክር አገልግሎት ለአርሶ አደሩ ሲሰጥ ምክሩን ተከትሎ አርሶ አደሩ በዝናብ መብዛት ወይም ማጠር ምክንያት ‹‹ሰብሌ ቢጎዳ ምንድን ነው የማደርገው?›› የሚል ጥያቄ ሲመጣ በዘንድሮው አመት ከኦሮሚያ ኢንሹራንስ ጋር በመሆን በአራት ወረዳዎች ላይ 129 የግብርና ኢንሹራንስ ፖሊሲ በሙከራ ደረጃ ተጀምሯል።
በአሁኑ ግዜ በግሪን አግሮ ሶሊዩሽን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለ51 ሰራተኞች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ሃያ አራቱ ለእርሻ ፕላትፎርም ላይ ይሰራሉ። በፕላትፎርሙና በአርሶ አደሮች መካከል ድልድይ ሆነው ለሚያሳልጡ 642 የለእርሻ ኤጀንቶች ወጣቶችም የስራ እድል ተፈጥሯል። የግብርና ግብአቶችን ከሱቆች ለአርሶ አደሩ ለሚያደርሱ ከ80 በላይ ለሚሆኑ የሞተር ሳይክል ባለቤቶችም ተመሳሳይ የስራ እድል ተፈጥሯል።
ግሪን አግሮ ሶሊዩሽን በለእርሻ ዲጂታል ፕላትፎርም በመጪዎቹ ሁለት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ለአርሶ አደሮች ተደራሽ የመሆን እቅድ አለው። ቴክኖሎጂውን በማጠናከር የሚያሰለጥናቸውን የኤጀንት ቁጥሮች በመጨመር አሁን ላይ ያለውን የአማርኛ ፣ ኦሮሚኛ ፣ ሲዳሚኛና ሶማሊኛ ቋንቋ በማሳደግ ለመላው ኢትዮጵያ አገልግሎቱ የሚዳረስበትን መንገድ ለማመቻቸትም ውጥን ይዟል።
በእንዲህ አይነት ዲጃታል ፕላትፎርሞች አፍሪካ ውስጥ ያሉ አርሶ አደሮች ያሉባቸው ችግርች ተቀራራቢ በመሆናቸው ኬኒያ፣ዛምቢያና ኮትዲቯር የገበያ እድሎችን ለማጥናት ሙከራ እየተደረገ ይገኛል። ተመሳሳይ ፍላጎት ካላቸው ድርጅቶችና መንግስታዊ ተቋማት ጋርም አጋርነት የማጠናከር ሃሳብም አለ።
‹‹የድርጅቱ ዋነኛ አላማ በ2025 እ.ኤ.አ 4 ሺ 500 ለእርሻ ኤጀንቶች መድረስ ነው›› የሚለው ወጣት አብርሃም፤ አንድ ኤጀንት በአመት እስከ 1 ሺ አርሶ አደር ይደርሳል ተብሎ እንደሚታሰብ ይናገራል። ይህም ለ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን አርሶ አደር አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያችልና በዚሁ አቅጣጫ መሰረት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ይጠቁሟል። የኤጀንቶቹ ቁጥር በመጨሩ በተለይ በገጠር አካባቢ ለወጣቶች የሚፈጠረው የስራ እድል የዚያኑ ያህል እንደሚጨምርም ያደርጋል።
አርሶ አደሩ የግብርና ግብአቶችን ለማግኘት ግዜውንና ጉልበቱን እንደሚያባክን ፤ ገንዘብም እንደሚያወጣ የሚናገረው ወጣት አብርሃም፤ በዚህ ፕላትፎርም አርሶ አደሮች ወደከተማ መምጣት ሳይጠበቅባቸው ግብአቶችን በለእርሻ ኤጀንቶች አማካኝነት በአቅራቢያቸው ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ይጠቁማል። ይህም የሚያወጡትን ግዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ እንደሚቆጥብላቸው ይገልፃል።
አርሶ አደሮቹ በነዚህ ኤጀንቶች አማካኝነት አገልግሎቱን ሲያገኙ 5 ከመቶ ኮሚሽን እንደሚከፍሉና ከዚህ በፊት ከሚያወጡት ወጪ ባነሰ አገልግሎቱን ለማግኘት እንደሚያስችላቸውም ነው ወጣት ቢኒያም የሚገልፀው። ከአርሶ አደሮቹ ላይ የሚሰበሰበው ኮሚሽን ለድርጅቱና ኤጀንቶቹ ገቢ እንደሚሆንም ያመለክታል። እስካሁን ፕላትፎርሙ ገቢ እያመጣ ቢሆንም ወጪውን ግን ሙሉ በሙሉ መሸፈን እንዳልቻለም ነው የሚናገረው።
ቴክኖሎጂ መሳሪያ እንጂ በራሱ አገልግሎት ሊሆን የማይችል በመሆኑ በተለይ ደግሞ ለአርሶ አደሩ ቴክኖሎጂ ለመሸጥ ቢሞከር ቴክኖሎጂውን ሳይሆን በቴክኖሎጂ በኩል የሚያገኘውን አገልግሎት እንደሚፈልግ ነው ወጣት አብርሃም የሚጠቁመው። ከዚህ አኳያ ይህን ለማድረግ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሰራሮችን የሚያውቁ በርካታ ወጣቶች በመኖራቸው ወደገጠር ወርደው አርሶ አደሩን በመቅረብ ውይይት ቢያደርጉ በግብርናው በኩል ያለውን ችግር በቴክኖሎጂ መፍታት እንደሚቻል ያመለክታል።
ከዚህ ባለፈ በግብርናው አካባቢ ተለማማጅ ሆነው ቢሰሩ፣ ወደ ግብርና ሚኒስቴር በመሄድ በቴክኖሎጂ ረገድ ምን አይነት እገዛ እንደሚያድርጉ ቢጠይቁና የአንድና የሁለት ወር የስራ ልምምድ ቢሰሩ፣ ግብርናን በተመለከተ መረጃ ቢያገኙ ብሎም መሬት ላይ ካለው አውድ ጋር ቢገናኙ ግብርና ላይ ብዙ ተአምር መስራት እንደሚቻልም ይጠቁማል።
ወደእነርሱ ድርጅት ወጣቶች ሲመጡ የመጡበትን ልምድና ያላቸውን እውቀት እንደሚያካፍሏቸውና ልምምድ ሲፈልጉም ትምህርት እንደሚሰጣቸው ነው ወጣት አብርሃም የሚያመለክተው። ወጣቶቹ ከሚፈልጉት ነገር ጋር አብሮ የሚሰራ ድርጅቱ የሚያውቀው አጋር ካለ ወደ እርሱ እንደሚላኩም ይናገራል።
በመሆኑም ራሳቸው አካባቢ ቁጭ ብለው እድል እንዲመጣ ከመጠበቅ በጥቂቱ ቴክኖሎጂ ላይ የሚሰሩት ነገር ካለ ወደፊት መጥተው ከድርጅቶች ጋር መነጋገር ቢችሉና በተለይ ገጠር አካባቢ ሄደው ገበሬውን ህይወቱን ቢያዩና የትኛው ነገር ዲጂታላይዝ መሆን ይችላል የሚለውን ቢረዱ በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚያስችላቸው ይመክራል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2015