«… እንደ ኮራ ሄደ፣ እንደ ተጀነነ» የሚል ዜማ እንዳለ እንሰማለን። በራሱ፣ ለሊጋባው በየነ በተዜመው ዜማ ሲነገር እንደሰማነው ማለት ነው። በሕይወት ዘመኑ ባደረገው አስተዋፅኦ እንደ ተወደደ፣ እንደ ተከበረ፣ እንደ ተፈቀረ … ነውና የሄደው የፍቅሩ ኬዳኔም ያው እንደ ሊጋባው በየነ ነው።
መቸም «በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የስፖርት ጋዜጠኝነት ለረጅም ዘመን ያገለገሉት አንጋፋው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛና ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።» በሚለው ዜና ያልተረበሸ የለም። በተለይም የዘመኑን መዘመን ተከትሎ መርዶው ዓለምን ለማዳረስ አፍታም አልፈጀበትምና ዜናው ከዳር እዳር ሲሰማ፤ ሁሉም፣ በተለይም ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ አድናቂና ባልረቦቻቸው ክው ብለዋል። ይህ «የሕይወት ሂደት» ነውና በዚሁ አልፈነው ወደ ፍቅሩ አጠቃላይ ሕይወትና ሥራዎች እንዝለቅ።
አቶ ፍቅሩ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም (ሌሊት) በ88 (87?) ዓመታቸው ሕይወታቸው ማለፉን ነበር ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጀምሮ በርካታ የመገናኛ ብዙሀን አውታሮች የተቀባበሉትና ወደ እኛ ጆሮ የደረሰው።
በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ታሪክ በዋናና ቀዳሚነት የሚነሱት ጋዜጠኛና ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ የተወለዱት በ1927 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ነው።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ደጋፊ የነበሩት አባታቸው የክለቡን ተጫዋቾች ከትምህርት ቤት ወደ ስታዲየም ያመላልሱ ነበርና ይህ ለፍቅሩ ኪዳኔ ወደ ስፖርቱ ዓለም ለመቀላቀል ምክንያት ሆነ።
በወቅቱ ከአባታቸው ጋር የመሆንና ከስፖርተኞቹ ጋር የመገናኘት ዕድል የነበራቸው አቶ ፍቅሩ፣ ይህ አጋጣሚ ወደ ስፖርቱ ዘርፍ ስቧቸው በኋላም የስፖርት መምህር ይሆኑ ዘንድ መንገዱን አመቻችቶላቸዋል። የመምህርነታቸው ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ ይበልጥ ወደ ሚታወቁበት ጋዜጠኝነቱ እንሂድ።
ፍቅሩ እንደ አንድ ፈር ቀዳጅ ጋዜጠኛ እና …
በኢትዮጵያ ሬዲዮና የተለያዩ የአገር ውስጥ የሕትመት ውጤቶች (የስፖርት ጋዜጠኝነትን የጀመሩት «1» ብለው በ «የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ» እና በl’Ethiopie d’aujourd’hui ላይ በመጻፍ ነው)፤ ስለ አገር ውስጥ ስፖርት መዘገብ የጀመሩት አቶ ፍቅሩ በ1943 ዓ.ም በሱዳን እና ኢትዮጵያ መካከል የተደረገውን ጨዋታ በቀጥታ በሬዲዮ ማስተላለፍ የቻሉ የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጠኛ ናቸው። የኢትዮጵያ ሬዲዮ ድርጅት ሲመሠረትም የመጀመሪያው የስፖርት የሬዲዮ ጋዜጠኛ ሆነው አገልግለዋል። (በኋላም የአሜሪካ ድምጽ ዘጋቢም፣ የጀርመን … ነበሩ።)
አቶ ፍቅሩ የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በ1961 ዓ.ም ሲመሰረት የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት የነበሩ ሲሆን በብስክሌት ፌዴሬሽን፣ ቴኒስ ፌዴሬሽን እና በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በዋና ፀሐፊነት፣ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት በመሆን አገራቸውን አገልግለዋል።
እንደ ኢዜአ የሕይወት ታሪካቸው ዘገባ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት የሜልቦርን ኦሎምፒክ ከቡድኑ ጋር በጋዜጠኝነት አብረው የተጓዙ፣ የቀድሞው የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ኹዋን አንቶኒዮ ሳማራንጅ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር፣ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር በኮንጎው ዘመቻ የተሳተፉ፣ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ፣ የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ፣ የሸዋ ጠቅላይ ግዛት እግር ኳስ ሊግ ዋና ጸሐፊ የነበሩ ታላቅ ሰው ነበሩ።
ከ1969 ወዲህ መኖሪያቸው አድርገው በቆዩበት በፈረንሳይ (ፓሪስ) ለሚገኘው ዕለታዊ የስፖርት ጋዜጣ ለኪፕ እና ሳምንታዊ የእግር ኳስ መጽሔት ፉትቦል ፍራንስ፣ ዶቼቬለ እና ሌሎች የዓለም አቀፍ ታዋቂ መገናኛ ብዙኃን በስፖርትና ተያያዥ ጉዮች ላይ ሠርተዋል።
ከአራት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ውስጥ የደመቀ ታሪክ ያላቸውን ባለውለታዎች ለማስታወስ ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ፍቅሩ ኪዳኔ «የሕይወት ዘመን ተሸላሚ» ሆነው መመረጣቸውም ይታወሳል። (ፍቅሩ ስፖርትና አጠቃላይ ፍልስፍናውን በተመለከተ ያላቸውን ግንዛቤ የበለጠ ለመረዳት ከሶከር ኢትዮጵያ ዶትኔት (ድረ-ገፅ) ጋር፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ ጋር በተያያዘ ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ይመለከቱ።)
ደራሲው ፍቅሩ ኪዳኔ
«ከጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ ጋር ለብዙ ዘመናት የሠራው፤ የመጀመሪያውን የስፖርት ዘገባ በሬዲዮ በቀጥታ ያስተላለፈው፣ በኢንተርናሽናል ስፖርት ፌዴሬሽኖች የፕሬስ ኮሚሲዮን እና በ1986 የሜክሲኮ የዓለም ዋንጫ የፊፋ የአንዱ ምድብ የፕሬስ ኃላፊ የመጀመሪያው ጥቁር፤ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበራት መሥራች» (ዳንኤል ክብረት፣ ኖቬምበር 21, 2010 ስለ «የፒያሳ ልጅ» በሰጠው አስተያየት ላይ ካሰፈረው መግቢያ የተወሰደ) የሆኑት ፍቅሩ ልክ እንደ ስፖርቱ ሁሉ፣ በድርሰቱ ዓለምም የተሳካላቸው ሲሆኑ፣ «የፒያሳ ልጅ» (ባለ 457 ገጽ) እና «የስፖርት ጨዋነት ምንጮች» የተሰኙ መጻሕፍት ደራሲ ናቸው። ሁለቱም ሥራዎቻቸው አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ሲሆን፣ በተለይ «የፒያሳ ልጅ» እጅጉን ተነባቢ ብቻ ሳይሆን ከብዙዎች መጻሕፍት መደርደሪያ ላይ እማይጠፋ፤ ያላገኙትም በፍለጋ ይንከራተቱለት ዘንድ ያስገደደ የደራሲው ቁንጮ ሥራ ነው።
እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን ጀግኖችን ሥራ እያዋዛ በማቅረብ ተወዳጅነትን ስላተረፈው «የፒያሳ ልጅ» መጽሐፍ ከላይ የጠቀስነው ምንጭ እንዳስነበበው ከሃምሳ ዓመት በፊት ፒያሳ አካባቢ የነበሩ ሲኒማ ቤቶች፣ ሻሂ ቤቶች፣ ጮርናቄ ቤቶች፣ የልብስ መደብሮች፣ ጠጅ ቤቶች እና ጠላ ቤቶች የማናውቀውን ሁሉ ያስኮመኩሙናል። በዚያ ዘመን ታዋቂ የነበሩትን ፊልሞች ያስቃኘናል። የዘመኑን አራዶች ፈሊጥ፣ የዘመኑ የእግር ኳስ ዳኞችን አሠራር፣ የተጫዋቾቹን አለባበስ እና አጨዋወት ከጎናችሁ ሆኖ የሚያወጋችሁ በሚመስል አቀራረብ ጽፎታል። (እዚህ ጋ የመሐመድ ሰልማንን «መሐሙድ ጋ ጠብቂኝ» ን ሳያነሱ ማለፍ ይከብዳል።)
ጋዜጠኛው ፍቅሩ በዚሁ ተወዳጅ መጽሐፋቸው የጥንቶቹ ልብስ ሰፊዎች፣ የመጀመሪያዎቹ የአዲስ አበባ ፀጉር ቆራጮች፣ የመጀመሪያዎቹ ታክሲዎች እና የታክሲ ሾፌሮች ምን እንደሚመስሉ በፎቶ ግራፍ ያሳዩናል። የመጀመሪያዎቹ ባለ ሱቆች፣ ባለ ሽቶ ቤቶች፣ ባለ መኪኖች፣ ባለ ቡና ቤቶች እነማን ነበሩ? ለሚለው መልስ ይሰጡናል።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከላይ በጠቀስነው ዓ.ም እና ጽሑፍ በታሪክ ብቻ የምናውቃቸውን የአገራችን ትልልቅ ሰዎች የልጅነት ትዝታ፣ ምን ይጫወቱ እንደነበር፣ ሲጫወቱ ስንት ብር እንደተበሉ ሳይቀር ይተርክልናል። የየአገሩን ሁኔታ በዘመኑ ከነበረው የኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር እየተነተነ ያስኮመኩመናል። ቁጭት እንዲያድርብን የዘነጋናቸውን ታላላቅ ሰዎች ያነሣል፣ የሠሩትን ሥራ ያዘክራል፣ ቅርሶቻችን የት የት እንዳሉ ያሳስበናል። የፒያሳ ልጅ። አዲስ አበባ እየተቀየረች ነው። ልደታ እና አራት ኪሎ በአዳዲስ ሠፈሮች እየተተኩ ነው። ነገም ፒያሳ በአዳዲስ ግንባታዎች እና ሠፋሪዎች ይቀየር ይሆናል። እንደ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ መጻሕፍት ያሉት መዛግብት ምናልባት ብቸኛ መረጃዎቻችን ሊሆኑ ይችላሉ። ከነ ሙሉ ትዝታቸው። [… ግዙና] አንብቡት። እርሱን ያላነበበ ሰው ከኢትዮጵያ ታሪክ አንድ ትልቅ ቁራጭ ይቀርበታል። አልታደልንም እንጂ አቶ ፍቅሩ ዛሬ በመላ ኢትዮጵያ ኮሌጆች እና ትምህርት ቤቶች እየዞሩ የማነቃቂያ ንግግር እንዲያደርጉ፣ ሥልጠና እንዲሰጡ፣ ምክር እንዲለግሱ፣ በሌሎች ጉዳዮችም እንዲጽፉ ማድረግ ነበረብን። ትልቅ ሰው ማውጣት እንጂ በትልቅ ሰው መጠቀም መቼም አልቻልንበትም።
(ፍቅሩ ኪዳኔን ከድርሰት ሥራዎቻቸውና ሥነጽሑፍ እሳቤ ጋር በተያያዘ ብዙ ማለት የሚቻል ሲሆን፤ ለዛሬው በዚሁ ቅምሻ አልፈን በሌላ ጊዜ ልናያቸው እንሞክራለን። ፈጣን ጸሐፊ ካለ ደግሞ ቢሄድበት እንደሚያዋጣው በቅንፍ ጠቁሞ ማለፍ ተገቢ ነው እንላለን።)
ሥራና ሕይወት በባህር ማዶ
እዚህም እዛም እንደ ጠቀስነው፣ አቶ ፍቅሩ የእግር ኳስ ጨዋታን በቀጥታ በራድዮ በማስተላለፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እንደነበሩ፤ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይም የስፖርት ዘገባዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች ሲያቀርቡ የነበሩ መሆኑን፤ በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥም ከአመራርነት ባለፈ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩት፣ የኢሳ ሃያቱ አማካሪ ጭምርም እንደነበሩ የሕይወት ታሪካቸውን ተከትለው ለአደባባይ የበቁ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ ኑሯቸውን በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ያደረጉት የኢትዮጵያ የስፖርት አምባሳደሩ አቶ ፍቅሩ በአገሪቷ ለሚገኘው ዕለታዊ የስፖርት ጋዜጣ ለኪፕ እና ሳምንታዊ የእግር ኳስ መጽሔት ፉትቦል ፍራንስ፣ ዶቼቬሌ (የጀርመን ድምፅ) እና ሌሎች የዓለም አቀፍ ታዋቂ መገናኛ ብዙኃን መሥራት የቻሉ ሰው ነበሩ።
ትዳርና ሕይወት
ዳንኤል ክብረት ከመሞታቸው ረዘም ያሉ አመታት በፊት «አቶ ፍቅሩ በ188 የዓለም አገሮች የዞረ ምናልባትም ብቸኛው ኢትዮጵያዊ» በማለት አስቀድሞ የተናገረላቸው ጋዜጠኛና ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ አንድ ልጅ ያላቸው ሲሆን ሁለት የልጅ ልጆችንም አይተዋል።
ፍቅሩ – በወዳጅ፣ አድናቂዎቻቸውና የስፖርት ቤተሰቦች አንደበት
ፍቅሩ ኪዳኔ በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት የመጀመሪያውና የሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች አርአያ የሆነ ነበር። ከእርሱ ጋር ለመመካከርና ልምዱንም ለመጋራት እመኝ ነበር። ፍቅሩ ኪዳኔ የኢትዮጵያ የስፖርት ታላቅ አምባሳደር ነበር (አምባሳደር መስፍን ቸርነት)። የስፖርት ጋዜጠኞች የእርሱን አርአያ ተከተሉ። እሱ በካፍ (የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን) ለእኔና ለአገሩ ትልቅ ሥራ የሠራ ጀግናና አገር ወዳድ የስፖርት መሪ ነበር። [ምን ያደርጋል] የቀብር ሥነሥርዓቱ በሚወዳት አገሩ ቢሆን ጥሩ ነበር (የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀል)።
ፍቅሩ ኪዳኔ ኢትዮጵያን ለዓለም በሚገባ ያስተዋወቀ ለኢትዮጵያ ስፖርት ጥብቅና የቆመ ሰው ነበር። እኔን ከታላላቅ የዓለም የስፖርት መሪዎች ጋር ያስተዋወቀኝ ጀግናና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ነበር (ሻለቃ አትሌት ኃይለ ገብረሥላሴ)።
ለስፖርቱ ተቆርቋሪ የነበረና የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር እንዲጠናከር የለፋ ታላቅ ሰው አጥተናል (የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ንዋይ ይመር)።
ፍቅሩ ሲታሰብ
የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ታላቁን የስፖርት ሰው ፍቅሩ ኪዳኔን የሚዘክር ፕሮግራም በካሶፒያ ሆቴል (ቦሌ) የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ ሻለቃ አትሌት ኃይለ ገብረሥላሴ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀልን፣ እና በርካታ ጋዜጠኞችና እንግዶች በተገኙበት የመታሰቢያና የሻማ ማብራት ሥርዓት ተከናውኗል። በመታሰቢያ ፕሮግራሙ ላይ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ በሕይወት ዘመናቸው የሠሯቸውንና የሰጧቸው ቃለ ምልልሶች ላይ ያተኮረ ዘጋቢ ፊልም የቀረበ ሲሆን፤ ይህንን እዚህ ጋ መጥቀስ ያስፈለገው ፕሮግራሙ በየአመቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ከሚል እምነት ነውና እንደሚሆንም እርግጠኞች ነን። (ለአንጋፋው ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ በአዲስ አበባ በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ አድናቂዎቻቸውና ሌሎች ጥሪ የተደረገለቸው እንግዶች በተገኙበት የአበባ ጉንጉን ማስቀመጥና የማስታወሻ መርሐግብር፣ የሽኝትና የጸሎት ሥነሥርዓት ተካሂዷል። ጥቅምት 10 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካኝነት ቀብራቸው በደማቅ ሥነ-ሥርዓት በፓሪስ ተካሂዷል።
ሲጠቃለል
የእግር ኳስ ጨዋታን በቀጥታ በሬዲዮ በማስተላለፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ፤ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በተለያዩ ቋንቋዎች የስፖርት ዘገባዎችን ሲያቀርቡ የነበሩ፤ የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር በ1961 ሲመሠረት የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት፤ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ በካፍ እና በኦሎምፒክ ኮሚቴ በአመራርነት ሲያገለግሉ የነበሩት፤ በካፍ እና ፊፋ ውስጥ ለረጅም አመታት ለአገራቸው ኢትዮጵያ ስፖርት ልዕልና ሲታገሉ የነበሩት፤ «የፒያሳ ልጅ» እና ሌሎች መጻሕትንም በማሳተም እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን ጀግኖችን ሥራ እያዋዙ በማቅረብ ተወዳጅነትን ያተረፉ ደራሲ፤ የአንድ ልጅ አባትና የሁለት የልጅ ልጆች አያት የነበሩት፤ በ1928 ዓ.ም የተወለዱት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ፣ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጥቅምት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን፤ ጥቅምት 10 ቀን 2015 ዓ.ም በደማቅ ሥነ-ሥርዓት በኢትዮጵያ ኤምባሲ በተደረገ ሽኝት፣ ወዳጅ ዘመድ፤ እንዲሁም፣ በርካታ አድናቂዎቻቸው በተገኙበት ሥርዓተ ቀብራቸው ይኖሩበት በነበረው ፓሪስ (ፈረንሳይ) ተፈጸሟል።
በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደርን ጨምሮ የበርካታ አንጋፋ ኢትዮጵያውያንና ዓለም አቀፍ የስፖርት ሰዎች በአካል እና በቪዲዮ የተደገፈ የኀዘን መግለጫዎችንም አስተላልፈዋል።
ከ«ነፍስ ይማር» በኋላ እኛም እንላለን፣ ስም ከመቃብር በላይ ይውላል!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16 / 2015