በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተካሄዱ የሪፎርም ሥራዎች አበረታች ለውጥ እየታየ ይገኛል:: በአንጻሩ በተጠበቀው ልክ ውጤት ያልታየባቸው ዘርፎች ስለመኖራቸውም ይታመናል:: ከዚህ አኳያም የጥቁር ገበያና የዋጋ ንረት ይጠቀሳሉ:: የዋጋ ግሽበትና የጥቁር ገበያን በተመለከተ ችግሩ እየተባባሰ የመጣ በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ መፍትሔ ለማምጣት መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን መውሰዱን ቀጥሏል::
እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች መካከልም በቅርቡ ብሔራዊ ባንክ የወሰደው እርምጃ ይጠቀሳል:: እርምጃው በተለይም በጥቁር ገበያው ላይ ያለውን ጤናማ ያልሆነ አካሄድ ለማስተካከልና ገበያውን ለማረጋጋት ያለመ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ አስረድተዋል::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በተለይም የጥቁር ገበያንና የዋጋ ግሽበትን በተመለከተ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፤ በሥራ ላይ ያለውን የንግድ ስርዓት ማዘመን፤ በፊሲካልና ሞኒተሪ ፖሊሲዎች ላይ ለውጦችን ማድረግ ዘላቂ የሆኑ መፍትሔዎች እንደሆኑ ሁሉ፤ ችግሩን በዘላቂነት ማስቀረት እስኪቻል ድረስ ግን ህገወጥ ሥራ በሚሰሩ አካላት ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ የግድ ሆኖ ተገኝቷል::
የውጭ ገንዘቦችን በመጠቀም የሀዋላ ሥራ የሚሰሩ ህጋዊ ሰዎች ስለመኖራቸው የጠቀሱት ዶክተር ይናገር፤ እነዚህ ሰዎች ህጋዊ እንደመሆናቸው መሥራት ያለባቸው መሆኑን በማመን ህጋዊ ሆነው በሚሠሩ ሰዎች አማካኝነት አገሪቷ ከሀዋላ ብቻ በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ እንደምታገኝ አስታውቀዋል፤ እነዚህ አካላት ሊበረታቱ እንደሚገባ ገልጸዋል::
ይሁንና በህጋዊነት ስም አንዳንድ ህገወጥ ሥራ የሚሠሩ መኖራቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህን አካላት መቆጣጠር አስፈላጊ መሆኑን ነው ዶክተር ይናገር ያስታወቁት:: በተለይም ከባንኮችና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር መሥራት ሲጠበቅባቸው የማይሠሩና ከባንኮች ውጭ በግላቸው የሀዋላ ሥራን የሚሰሩ ህገወጦች ስለመኖራቸው ተናግረዋል:: በዚሁ ምክንያትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድ ዶላር በጥቁር ገበያ ዋጋው ሲመነዘር የሚጨምርበት መጠን በፍጥነት እያደገ መምጣቱ አዲስ የዕለት ዜና እየሆነ መምጣቱንም ጠቅሰዋል::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የዚህ ችግር መሰረታዊ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ቢሆንም፤ መሰረታዊ መፍትሔው በውጭ ምንዛሬ አቅርቦትና በውጭ ምንዛሬ አስተዳደር በኩል መሰራት ያለባቸውን የተለያዩ ሥራዎች መሥራት ነው:: ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ እስከዚያው ድረስ ግን በመሀሉ ችግሩን እያባባሱ ያሉትን ህገወጦች በመቆጣጠር መፍትሔ ማምጣት ተገቢ ነው :: ይህን መሰረት በማድረግም ማን ምን እንደሚሰራ በዝርዝር በማጥናት በህገወጥ የሀዋላ ሥራ ላይ የተሰማሩ 391 የሚሆኑ ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው ገንዘባቸውን ጨምሮ እንዲዘጋ ተደርጓል:: ከዚህ በተጨማሪም የስም ዝርዝራቸውን ለፍትህ ሚኒስቴር በመላክም አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድባቸው ይሆናል::
ህገወጥ የሀዋላ ሥራ የሚሠሩ ሰዎች የባንክ ባለሙያዎች ድጋፍ ያላቸውና ትብብር የሚያደርጉ እንደሆነም የጠቀሱት ዶክተር ይናገር፤ ይህን ህገወጥ እንቅስቃሴ ለማስቆም ጥረት ያላደረጉና እያወቁ ቸል ያሉ የባንክ ኃላፊዎችና ሠራተኞችን በማጣራት በየደረጃው እርምጃ የሚወሰድባቸው ይሆናል ብለዋል:: በቀጣይም በየጊዜው የሚኖረውን የሂሳብ እንቅስቃሴ ሞኒተር በማድረግ በህገወጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን በቀላሉ መለየት የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ተዘርግቶ እየተሰራ እንደሆነም አስገንዝበዋል::
የባንኩ ገዥ እንዳሉት ህገወጥነትን ለመከላከል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፤ በህገወጥ መንገድ የሀዋላ ሥራ የሚሰሩ፣ በኮንትሮባንድ የወርቅ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩና የሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን የሚያትሙ፣ የሚያሰራጩና የሚያዘዋውሩ ሰዎች ከህብረተሰቡ የተሰወሩ አይደሉምና ከህበረተሰቡ ጋር በጋራ በመሆን መከላከል እንዲቻል ባንኩ የተለያዩ አሰራሮችን ዘርግቷል:: በህገወጥ ሥራ የተሰማሩ አካላትን ለሚጠቁሙ ሰዎች ባንኩ ማበረታቻ በመስጠት ወሮታውን ይከፍላል፤ የቁጥጥር ሥራውንም አጠናክሮ ይቀጥላል::
በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ ላለው የጥቁር ገበያ መስፋፋት ምክንያቶቹ ዘርፈ ብዙ እንደሆኑ የጠቀሱት ዶክተር ይናገር፣ አንድ ሁለት ብለን ከምንጠቅሳቸው ምክንያቶች በተጨማሪ በተለያየ ምክንያት መባባሱን ተናግረዋል:: ለአብነትም የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ በማድረግ መንግሥት የተለያዩ የምግብ ሸቀጦችን እንደ ስኳር፣ የምግብ ዘይት፣ የህጻናት ወተትና የመሳሰሉት በፍራንኮ ቫሉታ አማካኝነት እንዲገቡ መፈቀዱን አስታውሰው፤ ይህ አሰራርም በራሱ ችግር ያለበትና የጥቁር ገበያውን በማባባስ በኩል ጉልህ ድርሻ እንዳለው ነው ያስረዱት::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ መንግሥት ፍራንኮቫሉታን ሲፈቅድ የነበረው እሳቤ ዶላር ከውጭ አገር ማግኘት የሚችል ማንም ሰው ዶላሩን ተጠቅሞ የምግብ ሸቀጦቹን ወደ አገር ውስጥ በማምጣት ለገበያ ማቅረብ ቢችል የዋጋ ግሽበቱን ሊያረጋጋው ይችላል ከሚል ግምት የነበረ ቢሆንም፤ እንዲህ አይነት ውሳኔዎች ከችግር የጸዱ ባለመሆናቸው የጥቁር ገበያውን በማባባስ ድርሻ አላቸው:: ይሁንና በፍራንኮቫሉታ አማካኝነት እየተፈጠረ ያለውን ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ለመከላከል ነጋዴው የሚጠቀመው ዶላር በውጭ አገር ያለና የራሱ ስለመሆኑ የሚያሳይ የባንክ ስቴትመንት እንዲያቀርብ የማድረግ አሰራርን በመከተል ፍራንኮቫሉታን ያለአግባብ እንዳይጠቀሙና ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የማድረግ ሥራ ይሰራል::
ከፍተኛ መጠን ያላቸው ምርቶች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ይናገር፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገቡ ገቢ ምርቶች ቁጥር ስፍር የሌላቸውና በዓመት ከ18 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ዕቃዎች የሚገቡ እንደሆነም ተናግረዋል:: ይህን ከፍተኛ መጠን ያለውን የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ ምርቶችን ገበያው እስከፈለገ ድረስ መግባታቸው ክፋት የሌለው መሆኑን ገልጸው፤ አገሪቷ አሁን ካለባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲሁም የአገር ውስጥ ምርቶችን ለማበረታታት ሲባል በአንዳንድ ምርቶች ላይ ማስተካከያ የሚደረግ እንደሆነም አስረድተዋል::
ከጥቁር ገበያና ከዋጋ ግሽበት ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ መሰረታዊና ዘለቄታዊው መፍትሔ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መሆኑንም ገልጸው፤ ለዚህም የተጀማመሩ በርካታ አበረታች ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ እንደሆነ ነው ያስረዱት:: በተለይም ምርትና ምርታመነትን ማሳደግ ለዋጋ ግሽበት ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን ጠቅሰው፣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን የሚያሳድጉ ሥራዎችን አጠናክሮ ከመሥራት ባለፈ የተገኘውንም የውጭ ምንዛሬ በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ ነው ብለዋል::
የውጭ ምንዛሪን በአግባቡ ለመጠቀም መንግሥት እየወሰዳቸው ካሉ የተለያዩ እርምጃዎች መካከል የቅንጦት የሆኑ ቁሳቁሶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ክልከላ ማድረግ አንዱ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት በቅርቡ 38 የሚደርሱ ቁሳቁሶች ወደ አገር ውስጥ ገበያ እንዳይገቡ ሆኗል:: መንግሥት መሰል እርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚገባ ቀደም ሲል ጀምረው ሲሞግቱ የነበሩ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችም በአሁን ወቅት ብሔራዊ ባንክ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ተገቢነት ያላቸውና ወቅታዊ እንደሆኑ ያነሳሉ::
አገሪቷ አሁን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ብሔራዊ ባንክ የወሰዳቸው እና እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎች ተገቢነት ያላቸው መሆናቸውን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዛፉ እየሱስ ወርቅ ዛፉም ይገልጻሉ:: በብሔራዊ ባንክ በኩል እየተወሰዱ የሚገኙት እርምጃዎች በበጎ የሚታዩ ያሉት አቶ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ በመንግሥት በኩል በሕገ ወጥ የገንዘብ ክምችት እና ምንዛሬ ላይ እንዲሁም በፍራንኮቫሉታ ላይ የተወሰዱት እርምጃዎች በበጎ የሚወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል::
በመንግሥት በኩል የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት፤ ያለምንም የውጭ ምንዛሬ ፍቃድ (ፍራንኮ ቫሉታ) በጉምሩክ በኩል በቀጥታ እንዲገቡ የተፈቀደውን ውሳኔ ያለአግባብ ጥቅም ላይ የሚያውሉ አካላት ተግባራቸው ተገቢ አለመሆኑንም ነው የተናገሩት:: ከዚህ አኳያ ሌሎች ቀዳዳዎች ሊኖሩ ስለሚችሉም መንግሥት በዚህ ረገድ ክትትል እንዲያደርግ ይመክራሉ። እየተባባሰ የመጣውን የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን ሲጠቀም የተዘረጋውን አማራጭ ምክንያት በማድረግ የሚፈጠሩ ችግሮች መኖራቸውን በመጥቀስ ቁጥጥርና ክትትል አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝበዋል::
መንግሥት እየተባባሰ ለመጣው የኑሮ ውድነት መፍትሔ ለማፈላለግ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ለሰሜኑ ጦርነት መቋጫ ሊበጅለት እንደሚገባና ለሰላም መስፈን ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል::
ኢትዮጵያ የገጠማትን የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተናዎች በመረዳት ችግሩን ለማቃለል መንግሥት እየሰራ ያለው ሥራ የሚበረታታ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ለመፍትሄው የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። በአገሪቱ ለሚስተዋለው የኢኮኖሚ ችግር ኃላፊነቱ የመንግሥት ብቻ አድርጎ መመልከት ትልቅ ስህተት መሆኑንም ነው ያሉት አቶ ዛፉ፤ ድርጅቶች በአንጻራዊ ሰላም ሁኔታ ሥራቸውን እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚገባም አስታውቀዋል። የኑሮ ውድነቱ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን በከፍተኛ ደረጃ ቢያጠቃም፣ የመንግሥትና የግል ዘርፉ ሰራተኞችንም ስለሚጎዳ ጉዳዩ ለመንግ”ሥት ብቻ ሊተው አይገባም ብለዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ኦርጂ መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች አስፈላጊና ተገቢነት ያላቸው ናቸው ይላሉ:: የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ በተለይም የቅንጦት ዕቃዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መደረጉ የውጭ ምንዛሬው ወደ ውጭ እንዳይወጣ ያደርጋል፤ እርምጃው ተገቢነት አለው ሲሉ ይገልጻሉ:: ለዚህም ቅድሚያ መሰረታዊ ፍላጎቶች መሟላት እንዳለባቸውም ይገልጻሉ::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ከ80 በመቶ በላይ ያለው የማህበረሰብ ክፍል የቅንጦት ዕቃ የሚፈልግ አይደለም:: ስለዚህ እጅግ በጣም እጥረት ያለባቸውና ለህዝቡ እጅጉን አስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎች አሉ:: ለአብነትም መድሃኒቶች፣ የህክምና መሳሪያዎች፣ በኢንዱስትሪ ውስጥ የሚገኙ ማሽነሪዎችና መሰል ቁሳቁስ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚያስፈልጋቸው ናቸው:: ስለዚህ ለእነዚህ ቅድሚያ በመስጠት መገዛት አለባቸው::
መንግሥት አሁን ከወሰዳቸው እርምጃዎች በተጨማሪም መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች እንዳሉም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ይጠቁማሉ:: ለዶላር እጥረት ምክንያት ከሆኑት መካከል አንደኛው ሙስናና ብልሹ አሠራር መሆኑን ገልጸው፤ ለአብነትም አገሪቷ ወደ ውጭ ገበያ በምትልካቸው ምርቶች የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ በሙስናና በማጭበርበር እዛው በውጭ አገር ባንኮች እንዲቀመጡ በማድረግ አገሪቷ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንዳታገኝ ይደረጋል ሲሉም ነው የጠቆሙት::
ይህም ስልጣንን መከታ በማድረግ የሚፈጠር ችግር መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ሲተገበር እንደነበና ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ እዛው መቅረቱን አስታውሰዋል:: መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ መንግሥት አሁን እየወሰደ ካለው እርምጃ በተጨማሪ ኤክስፖርት የሚያደርጉ ነጋዴዎች ዶላሩን ወደ አገር ውስጥ ይዘው መመለሳቸውንም መቆጣጠር እንዳለበት አስገነዝበዋል:: ከዚሁ ጎን ለጎን ወደ ውጭ ገበያ የሚላኩ ምርቶችን በማሳደግ እንዲሁም ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን በዘላቂነት መፍታት ይቻላል ብለዋል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16 / 2015