ዓለም በሳይንስና ቴክኖሎጂ የምርምር ውጤቶችና ግኝቶች እየተመራች ነው። ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በዚሁ ዘርፍ መመራት ከጀመሩ ክፍለ ዘመን ሊቆጠር ምንም ያህል አልቀረውም። አገራት ኃያልነታቸውን በቴክኖሎጂና የሳይንስ ምርምር ውጤቶች ላይ ተመርኩዘው እየገነቡ ናቸው፤ ወታደራዊ ጡንቻዎቻቸውን የሚለኩት በዚሁ ዘርፍ ባስመዘገቡት ስኬት ልክ ሆኗል።
በሰው ልጅ ጉልበት አይሳኩም የተባሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ብሩህ የመፍጠር አቅም ባላቸው ጥቂቶች በተፈለሰፉ ቴክኖሎጂዎች እውን ሲሆኑ አይተናል። አሁን ሁሉም ነገር በቴክኖሎጂና ረቂቅ ሳይንሳዊ ጉዳዮች ይመራል። ለዚህም ይመስላል አዲሱ ትውልድ ከዚሁ ጋር በተያያዙ እውቀቶች እንዲበለፅግ የሚፈለገው።
ምድራችን በሉላዊነት (globalization) መርህ እየተመራች ነው። ለዚህ ደግሞ ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በይነ መረብ እና መሰል የግንኙነት መድረኮች የአንበሳውን ድርሻ ይዘዋል። ገበያው እንዲሁ ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚል መስመር የያዘ ነው። ደህንነትና ጦርነቱ በሳይበር ምህዳር ውስጥ የሚጠቃለል ነው። በግርድፉ ቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ ውጤቶች የዘመናችን የኃያልነት ቁልፉን በመዳፋቸው ስር ማስገባት ችለዋል። በዚህ የፉክክር መድረክ ላይ ከፊት ለመሰለፍ ደግሞ ከጨዋታው መርህ ጋር መግባባትን ያሻል። በቅድሚያ ለቴክኖሎጂና መሰል ሳይንሳዊ ጉዳዮች በርን ክፍት ማድረግ ይጠይቃል።
ታላላቅ አገራት ይህን መስመር በሚገባ እየተከተሉት ነው። የኢንዱስትሪውን አብዮት ከጨረሱ ክፍለ ዘመን አስቆጠሩ። እድገታቸውን አልጋ ባልጋ ካደረጉ ታላላቅ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶች ጋር ወደፊት ብለው ግስጋሴያቸውን ቀጥለዋል። አሁን ወደ አራተኛው ትውልድ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተሸጋግረዋል። አዲሱን ትውልዳቸውን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ለማነጽ የተለያዩ ስልቶችን ይነድፋሉ።
በዚህ ረገድ ኢትዮ ቴሌኮም ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ለምታሳየው እመርታ ጉልህ ድርሻን እየወሰደ ይገኛል። የመንግሥት የልማት ድርጅት ሆኖ እየሠራ ያለው «ኢትዮ ቴሌኮም» ከዚህ አኳያ ሰፋፊ ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል። ኩባንያው ባለፉት አስርት ዓመታት ፈጣን እድገት ማስመዝገብ ከቻሉ ታላላቅ የመንግሥት የልማት ተቋማት መካከል እንደሚመደብ መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይ ተደራሽነትና ጥራትን ግብ በማድረግ ሰፊው የማኅበረሰብ ክፍል የቴሌኮም አገልግሎቶችን እንዲያገኝ እየሠራ ነው።
በኢትዮጵያ 2ኛው የቴሌኮም አቅራቢ ድርጅት ሳፋሪኮም በቅርቡ ድርሻ ገዝቶ ሥራውን እስከ ጀመረበት ጊዜ ድረስም ሙሉ ለሙሉ የአገሪቱን ዜጎች የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት እየሠራ ቆይቷል። አሁንም ቢሆን ኩባንያው ትልቁን ድርሻ ይዞ የተለያዩ የቴሌኮም ዘርፍ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ምርምሮችና ማስፋፊያዎችን በማድረግ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ማስተዋወቁንና ወደ ሥራ ማስገባቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ይህም የተጠቃሚውን ፍላጎት በተለያየ መንገድ ከመመለስ ባሻገር አቅሙን ለማጎልበትና ተወዳዳሪነቱን ከፍ ለማድረግ እንደሚረዳው ታምኖበታል።
ኢኮኖሚውንም ሆነ የእድገት ጉዞው በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተመራ እንዲሆን በማገዝ እንዲሁም አዳዲስ መንገዶችን በማስተዋወቁ በኩል ተቋሙ ልዩ ልዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት «ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025» ስትራቴጂን ለማሳካት ያግዛሉ ባላቸው ሰፋፊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና ፕሮጀክቶች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ አዲሱ ትውልድ ከቴክኖሎጂና ፈጠራ ሥራዎች ጋር ያለውን ዝምድናና ቁርኝት እንዲያሳድግ ለማድረግ የልህቀት ማእከል በመሆን የእውቀት ሽግግርና ልማት ለማድረግም እየሠራ ነው።
ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ስልጠናዎችን እየሰጠ ያለው ኩባንያው፣ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተመረቀው የሳይንስ ሙዚየምም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችንና አገልግሎቶችን ይዞ በመቅረብ ለጎብኚዎች እያሳየ ይገኛል። በተለይ ሕፃናት እና ወጣት ጎብኚዎች በሳይንስ ሙዚየሙ ኢትዮቴሌኮም ባቀረበው ዓውደ-ርዕይ የዘመናችንን ድንቅ የቴክኖሎጂና የዲጂታል ግኝቶች በአይናቸው አይተው እና ሞክረው ለፈጠራ እና ምርምር መነሳሳት የፈጠረ ራዕይ እንዲሰንቁ እየሠራ ያለው ተግባር በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል።
ዘመናዊ ክላውድ ላይ የተመሠረተ ሁሉን አቀፍ የግንኙነት ማእከል (Omni-channel Contact Center) ተግባራዊ ካደረገ ጥቂት ቀናት ነው የተቆጠሩት። በአገልግሎቱ ከዚህ ቀደም ደንበኞችን በድምፅና በተወሰኑ የሶሻል ሚዲያ አማራጮች የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በተናጠል ያስተናግዱ የነበሩ የጥሪ ማዕከሎችን አሠራር ያዘመነና በልዩ ልዩ አማራጮች ማለትም በድምጽ፣ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት፣ በኢሜል፣ በድረ-ገጽ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች፣ እንዲሁም ቻትቦትን (Chatbot) በመጠቀም የሚቀርቡ የደንበኞች ጥያቄያዎችን በአንድ ላይ አቀናጅቶ ለደንበኞች አገልግሎት ባለሙያዎች በማቅረብ ቀልጣፋና ተደራሽ የደንበኞች አገልግሎት ማቅረብ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ኩባንያው ይፋ አድርጎ ነበር።
ቴክኖሎጂው በአገር ውስጥ መጀመሩ ድርጅቶች እና ተቋማትም ይህን ተጠቅመው የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማሳለጥ ብሎም የደንበኞቻቸውን ተሞክሮ እና እርካታ በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ የሚችሉበት ትልቅ ዕድል መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ገልጸው ነበር።
የዝግጅት ክፍላችን በቅርቡ ተመርቆ ለሕዝብ አገልግሎት ይፋ የሆነው የሳይንስ ሙዚየም ተገኝቶ ምልከታ ባደረገበት ወቅትም ኢትዮ ቴሌኮም የተገበራቸውን የቴክኖሎጂ አማራጮች ለእይታ ቀርበው ጎብኝቷል፤ ከዚህ ባሻገር ደግሞ ሕፃናትና ወጣቶች የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በአካል በማየትም ሆነ ልምምዶችን በማድረግ ከህልማቸው ጋር እንዲቀርቡና ቀጥተኛ ትምህርት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ተግባራትን ሲያከናውኑ ለመመልከት ችሏል።
እየሩሳሌም ባዬ ትባላለች። እሷ የምትሠራበት ኢትዮ ቴሌኮም በሙዚየሙ ውስጥ ለታዳጊዎች የሚሰጠውን የሮቦት ደረጃ አንድ ስልጠና እየሰጠች እያለች አገኘናት። እርሷ እንደምትለው፤ ኩባንያው ተፈታተው አገር ውስጥ የገቡ ሮቦቶችን ታዳጊዎች መገጣጠምና አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ማድረግ እንዲችሉ በሙዚየሙ ውስጥ ስልጠና ይሰጣል። ይህም ታዳጊዎቹ ከቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ጋር የበለጠ ቁርኝት እንዲኖራቸውና ለወደፊት የመፍጠር አቅማቸው እንዲጎለብት እንደሚረዳቸው ትናገራለች።
እየሩሳሌም እንዳለችው፤ የዚህ ሁሉ አላማ ሕፃናትና ታዳጊዎችን በቴክኖሎጂ የበለፀገች አገር ተረካቢና መሪ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፤ ኢትዮ ቴሌኮም በሙዚየሙ ውስጥ የዱሮዎቹን፣ የአሁኖቹንና ወደፊት እንደሚመጡ የሚጠበቁትን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይዞ በመቅረብ እያስተዋወቀ ይገኛል። በዚህም ለማህበረሰቡም ሆነ ለኢትዮጵያ መንግሥት ታዳጊዎች ላይ ከስር መሠረቱ ጀምሮ የቴክኖሎጂ ፅንሰ ሃሳብ እንዲጎለብት መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
እየሩሳሌም ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ የሂሳብ (ማቲማቲክስ) ትምህርት ላይ ትኩረት አድርገን መሥራት ለአገር እድገት ወሳኝ ነው ትላለች። በሌላ በኩል ኢትዮ ቴሌኮም ሮቦቶች የ5ጂ ኔትወርክን ተጠቅመው የሰው ልጆች በሚሠሩበት ፍጥነት ፕሮግራም የተደረጉበትን ተግባራት እንዲያከናውኑ ለማስቻል ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ጠቅሳ፣ በዚህ ዘርፍ ላይ ወጣቶችም ሆኑ ታዳጊዎች ተሳትፈው እውቀት ቢጨብጡ በቀጣይ ጊዜያት አገሪቱ ውጤታማ ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባሮች ቁልፍ ድርሻ እንደሚኖራቸው ትጠቁማለች። ለዚህ መሰል ውጤታማ ሥራ ደግሞ ኩባንያው ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ነው ያስታወቀችው።
«በቀጣይም አገራችን ይህን መሰል የሳይንስ ሙዚየሞች አገራችን ያስፈልጋታል። ይህ እውን በመሆኑም ደስተኛ ነን» የምትለው እየሩሳሌም፤ ኢትዮጵያ እውን ልታደርገው ለቀረፀችው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ኢትዮ ቴሌኮም ቁልፍ አጋርና የፊት መስመር ተሰላፊ ነው ትላለች። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነውም በሙዚየሙ ውስጥና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጉልህ ድርሻና ኃላፊነትን ወስዶ እያከናወነ ያለው ተግባር መሆኑን ጠቅሳለች። እየሩሳሌም ኢትዮጵያን ዲጂታላይዝ የማድረጉ ግብም እንደሚሳካ እምነቷ ነው።
ታዳጊ ስምኦን ዮሐንስን ኢትዮ ቴሌኮም በሳይንስ ሙዚየም ውስጥ እየሰጠ በነበረው የደረጃ አንድ ሮቦት ፕሮግራሚንግ ስልጠና ላይ ያገኘነው። እርሱ እንደሚለው፤ በራሱ ፍላጎት የቀረቡለትን ሮቦቶች በፍጥነት በማስተካከል፣ ቀለማቸውን በመምረጥ እንዲሁም የራሱን መረጃዎች በሚፈልገው መንገድ ፕሮግራም በማድረግ የተለያዩ ልምምዶችን ማድረግ ችሏል። በዚህ ሙዚየም ውስጥ በመገኘቱ እጅግ ደስተኛ እንደሆነ የሚገልፀው ስምኦን ወደፊት በተለያዩ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና በሮቦት ፕሮግራሚንግ ላይ አዳዲስ ነገሮችን መሥራት እንደሚሻ ይገልፃል። በስልጠናው እውቀት ከማግኘቱም በላይ ወደ ትምህርት ቤቱ ሲመለስ ጓደኞቹም ይህን ስልጠና እንዲወስዱ እንደሚያበረታታቸው ነግሮናል።
ሌላኛው ታዳጊ ደግሞ ስሞን ታለ ነው። እርሱም በኢትዮ ቴሌኮም የሮቦት ስልጠና ላይ ነበር ያገኘነው። በተለይ ተፈታትቶ የተሰጠውን ሮቦት በምን መልኩ መልሶ መገጣጠምና እርሱ በሚፈልገው መልኩ መጠቀም እንደሚችል ከተማረ በኋላ በተግባር ሊሠራው ችሏል።
«በዚህ የሳይንስ ሙዚየም በመገኘቴ ተደስቻለሁ። ከዚህ ቀደም እንደዚህ ዓይነት ዘመናዊ ቴክኖሎጂና ስልጠናዎችን አይቼም ሆነ ሰልጥኜ አላውቅም ነበር» የሚለው ታዳጊ ስሞን ታለ፣ አሁን ግን ህልሙን የሚያሳካና እንዲበረታታ የሚያደርገው ዕድል እንዳጋጠመው ይናገራል። ወደፊት ታዋቂ እግር ኳስ ተጨዋች ለመሆን እንደሚፈልግ ጠቅሶ፣ በቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ ምርምሮች ላይ ውጤታማ ሥራዎች የመስራት ህልምም እንዳለውም ገልጧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሙዚየሙን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት፤ የሳይንስ ሙዚየሙ በሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል። በአገራችን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ቢኖርም ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ የተመቻቸ ቦታ ባለመኖሩ የወጣቶችን እምቅ የፈጠራ አቅም መጠቀም ሳይቻል ቆይቷል።
እንዲህ ያለ የሳይንስ ሙዚየም መኖሩ ወጣቶች ተሰጧቸውን አውጥተው ለመጠቀም ዕድል የሚፈጥርላቸው መሆኑንም ጠቅሰው፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተነቃቃ አዲስ ትውልድ ለመቅረጽም ዓይነኛ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።
ሳይንስና ጥበብን በሁለት አተያይ ያጣመረው ሙዚየሙ፣ በአገር ውስጥ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለእይታ የሚቀርቡበትና የሚተዋወቁበት፣ ምርምር የሚደረግበት፣ የምርምር ሥራዎች የሚቀርቡበት እና ወጣቶች ንድፍ ሃሳባቸውን ወደ ተግባር የሚቀይሩበት እንደሆነም አመልክተዋል። ወጣቶች እንዲጎበኙትም ጥሪ አቅርበው ነበር።
ሙዚየሙ ከተመረቀ አንስቶም በተለይ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት እጅግ በርካታ ወጣቶች ታዳጊዎች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች እየጎበኙት ይገኛሉ። የትናንት የኤፒድ ዘገባ እንዳመለከተው ፤ የሳይንስ ሙዚየም የጉብኝት ጊዜ ለአንድ ወር መራዘሙን ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል። የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት፤ የሳይንስ ሙዚየሙን ለመጎብኘት ባለው ሰፊ ፍላጎት ምክንያት የመጎብኛ ጊዜውን መጨመር አስፈልጓል።
እንደ ወይዘሪት ፍሬህይወት ገለፃ፤ የሳይንስ ሙዚየሙ በ19 ቀናት ውስጥ 357ሺህ ጎብኚዎች የጎበኙት ሲሆን፣ ባሳለፍነው ቅዳሜና እሁድ ብቻ ከ109ሺህ በላይ ሰዎች ጎብኝተውታል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ መዚየሙን ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ዜጎች እንዲጎበኙት ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል። ሙዚየሙ ትናንት (ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም) ብቻ ከ75 ሺህ በላይ ጎብኚዎችን አስተናግዷል ብለዋል።
የፈጠራ ሥራዎቻቸውን፣ አገልግሎቶቻቸውን ይዘው የቀረቡት ኩባንያዎች እና ድርጅቶችም በርካታ ናቸው። በቦታው የተገኘንም የሚጠይቁት እየጠየቁ፣ የሚያስረዱት እያስረዱ፣ የሚያዳምጡት እያዳመጡ፣ የሚመለከቱት እየተመለከቱ ፤ ቴክኖሎጂዎችን የሚፈቱትና የሚገጥሙትም ሲፈቱና ሲገጥሙ እኛም ተመልክተናል። ሙዚየሙ ለወጣቶችና ታዳጊዎች ብቻ ሳይሆን ለመላ ተማሪዎችና ምሁራንም የተበረከተ ትልቅ የምርምር ማእከልና ስጦታ ነው ማለት ይቻላል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም ወሳኝ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2015