አዲስ አበባ፡- አገር አቋራጭ መንገዶችን ምቹ በማድረግ ተሸከርካሪዎች ከኢትዮጵያ አልፈው ወደተለያዩ የአፍሪካ አገራት መግባት የሚችሉበት አሠራር በቀጣይ ሁለት ዓመታት ተግባራዊ እንደሚሆን የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ኢንጅነር ሕይወት ሞሲሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በ2020 መድረስ ያለባት አህጉራዊ ትስስርን የሚያግዘው ይህ ፕሮጀክት በዓለም ባንክ በተገኘ የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የተጀመረ ነው።
ፕሮጀክቱ ዘንድሮ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ አጠቃላይ የሰባት ዓመታት ዕድሜም እንዳለው ሚኒስትር ዲኤታዋ ገልፀዋል።በዚህም በቀጣይ ሁለት ዓመታት ለማጠናቀቅ ለታሰበው ሥራ አገሪቱ በሕጎቿ ሁሉ ተግባራቱን በማካተት አሠራር መዘርጋት ይጠበቅባታልም ብለዋል፡፡
እንደሚኒስትር ዲኤታዋ ገለፃ፤ ሥራው ተሸከርካሪዎቹ ክብደታቸው፣ መጠናቸው፣ ያሉበት ደረጃ ሁሉ የተሻለ እንዲሆን የሚጠይቅ ሲሆን፤ እያንዳንዱ የተሽከርካሪ አካል ደረጃውን የጠበቀ እንዲሁም ለመንዳት የሚያስችል መመዘኛን ያሟሉ መሆናቸው የተረጋገጡና ከተሽከርካሪ መለያ ታርጋ ጀምሮ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ተሸከርካሪዎች በአገሪቱ እንዲኖሩም ያስችላል ብለዋል።ለአብነት መጥረጊያ የሌለው ተሽከርካሪ መሄድ እንደማይችል ጠቅሰዋል።
መንገዶቹን ተነባቢ ማድረግና ተሽከርካሪዎች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ማስቻል በሁሉም ላይ በተሟላ ሁኔታ መተግበር ቢያዳግት እንኳ አገር በሚያቋርጡ ተሽከርካሪዎች ላይ ግን ተግባራዊ እንደሚሆንም ሚኒስትር ዲኤታዋ ጠቁመዋል።
ከተሸከርካሪዎች ጎን ለጎን የመንገዶች ጥራትና ስፋታቸው ጭምር ደረጃውን የጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ከዚህም ባሻገር ጠቋሚ ምልክቶች ዓለም አቀፍ የትራንስፖርት መግባቢያ ቋንቋና መመዘኛዎችን እንዲሁም ደረጃዎችን ሊያሟሉ ይገባቸዋል፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ መንገዶች ያሉበት ደረጃ ስለሚታወቅ ዋና ዋና ኮሪደሮች እንደተመረጡ አብራርተዋል፡፡
በሱዳን በኩል እስከ ኬንያ፣ ከጅቡቲ እስከ ደቡብ ሱዳንና ወደሌሎች ጎረቤት አገራት የሚያመሩ ዋና ዋና የገቢና ወጪ ገበያ ትራንክ ኮሪደሮች መኖራቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ አንስተዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ በአምስት ትራንክ ኮሪደሮች ላይ መሥራት ተጀምሯል፡፡ በትንሹ በእነዚህ ዋና ዋና መገናኛ መስመሮች ላይ የሚጀመረው ሥራም አጠቃላይ ወደሁሉም የአገሪቱ ክልል መንገዶችና ወደየአካባቢው የመንገድ ላይ ስርዓቶች ተግባራዊ ይሆናል፡፡ በተያያዘ ሕብረተሰቡ እንደ ተሽከርካሪ አማራጭ የሚገለገልባቸው ዘዴዎች ሁሉ ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ መጓጓዝ የሚችለው ተናባቢ መንገዶች ሲኖሩ በመሆኑ በዚህም ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የአሽከርካሪ፣ የተሸከ ርካሪ፣ የመንጃ ፍቃድ አሰጣጥ፣ ሕገወጥነትን ለመከላከል፣ የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት በመዘርጋት በአንድ ቋት እንዲሆኑ ለማድረግ፣ አገር አቀፍ አሠራር ለማመቻት፣ በቴክኖሎጂ ለመደገፍና ዓለም አቀፍ መመዘኛውን እንዲያሟላ ያግዛል፡፡ ለዚህም ባለፉት ሦሥት ዓመታት አገር አቀፍ ምስሉ ምን እንደሚመስል በሚያመላክት መልኩ መሠረታዊ የአርክቴክቸር ሥራው የተጠና ሲሆን፤ በመላ አገሪቱ ከ200 በላይ ወረዳዎችም ይተሳሰራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት መሟላት ያለባቸው ዋና ዋና ግብዓቶች ምንድን ናቸው? የሚለው አልቆ የግዢ ሂደት ውስጥ መገባቱንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ሥልጠናን ጨምሮ ሰባት የሚደርሱ የተለያዩ ፕሮግራሞች መኖራውንና ከዓለም አቀፉ ሕጎች ጋር የተጣጣመ እንዲሆንም የማናበብ ሥራውን ጎን ለጎን እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህ በተሰጠው ሁለት ዓመት ውስጥም የሥራ ድርሻ ላይ በማካተት ሁሉም ባለድርሻ አካል ገብቶት ለተግባራዊነቱ ሊተጋ እንደሚገባም ኢንጂኒየር ሕይወት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 /2011
ፍዮሪ ተወልደ