አሶሳ፡- የቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሞ ህዝቦችን በልማት የሚያስተሳስር የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተሠራ መሆኑ ተጠቆመ።በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል ከሦስት ወር በፊት ተከስቶ የነበረው ችግር ተፈትቶ አንጻራዊ የሆነ ሰላም መፈጠሩም ተመልክቷል፡፡
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) 29ኛውን የምስረታ በዓል ‹‹መደማመጥና ማስተዋል የወደፊት ስኬት መሰረት ነው›› በሚል መሪ ቃል ትናንት በአሶሳ ምክር ቤት አዳራሽ ከአጋር ድርጅቶች፣ ከድርጅቱ አባላትና ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በፓናል ውይይትና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
በበዓሉ ላይ የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቲ ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት፣ ሁለቱን ክልሎች በልማት የሚያስተሳስርና የልማት ጥያቄን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሥራ ለመሥራት የኦሮሚያ ክልል 11 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ ነቀምት ውስጥ የፕሮጀክት ቢሮ አቋቁሟል።
እንደ ዶክተር ግርማ ገለጻ፤ የክልሉ መንግሥት ይህን ያደረገበት አብይ ምክንያትም የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብና ለዘመናት የቆየውን የህዝቡን የልማት ፍላጎት ለመመለስ በማሰብ ነው።
ከሦስት ወር በፊት በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ችግርና የሰላም እጦት ከነበረው ስፋት አንጻር በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍታት ተችሏል ያሉት ዶክተር ግርማ፣ ህዝቡ ወደነበረበት ሰላማዊ ኑሮ ሙሉ ለሙሉ እንዲመለስ ለማድረግ ሁለቱ ክልሎች በመግባባት እየሠሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ በተሰሩት ሥራዎችም ሥራ አቋርጠው የነበሩ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ሥራቸውና ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን አስረድተዋል።ከሁለት ሳምንት በፊት ከ38ሺ በላይ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችም ወደነበሩበት መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሌ ሀሰን በበኩላቸው፣ የኦሮሞ ተወላጆች ከአምስቱ ብሔረሰብ ተወላጆች ጋር የነበራቸው የረጅም ዘመን የአብሮነት ታሪክ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለዚህም ከኦሮሚያ ክልል መስተዳድር ጋር በጋራ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ በኦሮሚኛ ቋንቋ ትምህርት እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ይነሳ የነበረው ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን እና ይህም በ2012 ዓ.ም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ አሻድሌ ሀሰን፣ ለወጣቶችን የሥራ ዕድል ለመፍጠር ክልሉ ያለውን ሰፊ መሬትና ሌሎች ሀብቶችን በመፈተሽ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል።
በዛሬ ዕለት የቤኒሻንጉልና የኦሮሚያ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች በተገኙበት የጋራ ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 /2011
ለምለም መንግስቱ