የአንድ አገር እድገት በብዙ መንገድ ሊለካ ይችላል። ቁሳዊ ሃብት ከሚዛናዊ ምጣኔ ሃብት ጋር ተደምሮ አንዱ የሃያልነት መለኪያ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። ከዚያ ባለፈ የሰው ሃብት ልማት፣ የተፈጥሮ ሃብትና ሌሎች መሰል ጉዳዮች የእድገትና ብልፅግና መስፈርቶች መሆናቸው ይጠቀሳል።
ከሁሉም በላይ ግን በልዩ ልዩ ዘርፎች እውቀቱንና ጉልበቱን አውጥቶ መስራት የሚችል ወጣት ሃይል ሲኖር የአገር ተስፋዋ ይለመልማል። መንግስት እነዚህን ሁሉ በአንድነት ማቀናጀትና በብቃት መምራት ሲችል ሁለንተናዊ ለውጥና እድገት እንደተመዘገበም ይቆጠራል።
በኢትዮጵያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ከአገሪቱ ህዝብ 70 በመቶ የሚሆነው መስራት የሚችል ወጣት ሀይል ነው። ይህን ሃይል በተለያየ እውቀት በማነፅና ወደ ስራ በማሰማራት አስደማሚ ፈጣን እድገት ማስመዝገብ ይቻላል። አጋጣሚውን ለመጠቀም ደግሞ አገሪቷን እየመራ የሚገኘው መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይጠበቅበታል። ከዚህ ውስጥ አንዱ ሃላፊነት ወጣቱን ሃይል በብዛት በእውቀትና በተለያዩ ችሎታዎች መቅረፅ ነው። በሚሰማራባቸው ዘርፎች ላይ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ማከናወንንም ይጠይቃል። ቀዳሚው እና አንገብጋቢው ጉዳይ ግን እውቀትን ማስታጠቅና ዝግጁ ማድረግ ነው።
ወጣቶች ብሩህ አእምሯቸውን ተጠቅመው እውቀት እንዲጨብጡ ለማስቻል ጠንካራ የትምህርት ፖሊሲ ቀርፆ ከማስተማር ባሻገር ቁሳዊ በሆነው ጉዳይ ላይም ትኩረት ማድረግ ያሻል። ከዚህ ውስጥ አንዱ ምቹ የመማሪያ ቦታ ማዘጋጀት ነው። ይህ ሲባል የመሰረተ ልማት ዘርፉን ጠንካራ በማድረግ ግንባታዎችን ማከናወንን ይጠይቃል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለትምህርትና ሙያዊ ስልጠናዎች በፖሊሲ የተደገፈ ትኩረት በመስጠት ታዳጊዎችና ወጣቶች በክህሎት የዳበረ ችሎታ ኖሯቸው አገር እንዲጠቅሙ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል። ለዚህ እንዲረዳ በዘርፉ ልዩ ልዩ መሰረተ ልማቶችን እየገነባ ነው። ለመጀመሪያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፤ የግሉ ዘርፍ ብቻ ይሰራበት የነበረው የአጸደ ህጻናት ትምህርት ቤቶች ጉዳይ በመንግስት በኩል ይሰራበት ጀምሯል።
የልማት ማህበራት አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ከፍተው እያስተማሩ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሴቶች እንዲሁም የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው እያስተማሩ ይገኛሉ። በዚህም ተማሪዎች ትምህርታቸውን ብቻ እንዲያስቡ በማድረግ በትምህርቱ ዘርፍ ላይ ለውጥ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ነው።
በርካታ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአገሪቱ ተከፍተው እየሰሩ ሲሆን፣ ሰሞኑን ደግሞ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶችና ታዳጊዎችን ተቀብሎ ተሰጥኦዋቸውን የሚያጎለብት የልህቀት ማእከል ተመርቋል።
በአዲስ አበባ ግንባታው ተካሂዶ በቅርቡ ተመርቆ እየተጎበኘ ያለው የሳይንስ ሙዚየም ከዚህ አኳያ ሊጠቀስ የሚችል መሰረተ ልማት ነው። ሙዚየሙ ወጣቶች ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ፣ እውቀትን እንዲቀስሙና ከህልማቸው ጋር በቀጥታ ተገናኝተው ያሰቡትን እንዲያሳኩ የሚያግዝ መሆኑን መመስከር ይቻላል።
ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ የሚያግዝ የትምህርት መሰረተ ልማት ከትናንት በስቲያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቋል። ዛሬ በዚሁ የመሰረተ ልማት አምድ ላይ ልንዳስሰው የወደድነው ይህ ትምህርት ቤት የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ይህን የልዩ ተሰጥኦ ማበልጸጊያ ትምህርት ቤት መርቀው ሲከፍቱ “ኢትዮጵያ የብሩህ አቅሞችና ተሰጥኦዎች ባለቤት ምድር ናት። ባለ ተሰጥኦ ታዳጊዎችና ወጣቶች ክህሎታቸውን እያዳበሩ፣ አገራቸውን በቴክኖሎጂ ከበለጸጉ አገራት ተርታ እንዲያሰልፉ፣ እንደ ቡራዩ የተሰጥኦ ማበልጸጊያ ትምህርት ቤት ያሉ የተሰጥኦ ማዕከላትን ማብዛት ይገባል” በማለት በትምህርት መሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ በቀጣይ ሌሎች በርካታ ስራዎች መሰራት እንደሚገባቸውና መንግስትም ለዚያ ዝግጁ እንደሆነ ገልፀዋል።
“ኢትዮጵያ የምትቀየረው ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎችን የሚያበረታቱና የሚደግፉ ማዕከላት ሲስፋፉ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ የልዩ ተሰጥኦ ትምህርት ቤት የተለየ የፈጠራ ሃሳብና ክህሎት ያላቸው ወጣቶችና ታዳጊዎች ለአገር ጥቅም ከፍተኛ ሚና እንዲያበረክቱ ያስችላል ብለዋል። አገር የሚቀየረው በወሬ ሳይሆን በፈጠራ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህ ባለ ልዩ ተሰጥኦዎች የፈጠራ ሃሳባቸውን ወደ ተግባር የሚቀይሩበትና የሚያበለጽጉበት አውድ መፍጠር አስፈላጊ ነው። ይህን ማድረግ ሲቻልም እነሱም ይጠቀማሉ፤ እኛም እንደ አገር እናተርፋለን ብለዋል።
“ዓለማችን በቴክኖሎጂ መጥቃለች። አገራችን ኢትዮጵያም ቴክኖሎጂ ከሚያስገኛቸው እንደ ኢኮኖሚ ካሉ ትሩፋቶች ተጠቃሚ ለመሆን፣ በዘርፉ የላቀ ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎችን ማፍራቷ ግድ ነው›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ትምህርት ቤቱ ከየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚመጡ ወጣቶች ተሰጥኦቸውን የሚያጎለብቱበት እንደሚሆንም አስታውቀዋል። የትምህርት ቤቱ ግንባታ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ በልዩ ልዩ መንገድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የአካባቢው ነዋሪዎችም ምስጋና አቅርበዋል። “የምንተባበር፤ የምንደማመጥ፤ በዘር በሃይማኖት የማንገፋፋ ስንሆን አገራችንን በቀላሉ ማሳደግ እንችላለን›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሃሳብ ልዩነት ሳይገድበን አገራችንን በትብብር ማሳደግና ማበልጸግ ይኖርብናል ሲሉ አስገንዝበዋል። ‹‹በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ነገር ይቆጫል፤ ትግራይ ሰላም ትሆናለች፣ ከትግራይ ወንድሞቻችን በጋራ የምናለማበት ጊዜ ቅርብ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ››ሲሉም አስታውቀዋል።
ጥቂት እውነታዎች ስለ ማእከሉ
የልዩ ተሰጥኦ ትምህርት ቤቱን ለመገንባት 708 ሚሊዮን 693 ሺህ ብር ወጪ ተደርጎበታል ። ይህ ትምህርት ቤት እስከ አንድ ሺህ ባለተሰጦዎችን ተቀብሎ የማስተማር አቅም አለው። ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ በ 10 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ይሆናል። ከትናንት በስቲያ የተመረቀው በአምስት ነጥብ አራት ሄክታር ላይ ያረፈው ፕሮጀከት ነው።
ትምህርት ቤቱ የባለተሰጥኦዎች ማደሪያ፣ የመመገቢያ አዳራሽ፣ የአስተዳደር ህንጻዎች፣ የህክምና ማዕከል፣ መማሪያ ክፍሎችና ቤተ ሙከራዎችን አካቶ የያዘ ነው። አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉት አስፈላጊ ቁሳቁስ የተሟሉለት ሲሆን፣ መጽሐፍት ፣ ኮምፒውተሮች፣ የቤተ ሙከራ ዕቃዎችንና ሌሎች አስፈላጊ ዕቃዎች አቀናጅቶ የያዘ ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስለ ማእከሉ
መንግሥት የቴክኖሎጂ ፈጠራን በከፍተኛ ደረጃ ለማበረታታት የተግባር ሥራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች አሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ክህሎት ያላቸውን ታዳጊዎችና ወጣቶች መደገፍ የሚያስችል “የክህሎት ማእከል” ወይም የታለንት ልማት ግንባታ ማድረግ ነው። ከዚህ አንፃር ደግሞ በከፊል ተጠናቆ የተመረቀውና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘው የቡራዩ የታለንት/ተሰጥኦ ልማት ማእክል ፕሮጀክት ይጠቀሳል። ማእከሉ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ በሳይንስና ቴክኖሎጂው የፈጠራ ዘርፍ ልዩ ተሰጦ ያላቸው ወጣቶችን በብዛት ለማፍራት አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት እሙን ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አቶ በለጠ ሞላን ጨምሮ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮች ቀዳሚ አጀንዳቸው በማድረግ የታለንት ልማት ኢንስቲትዩቱ ከፊል ግንባታ ተጠናቆ እስከተመረቀበት ጊዜ ድረስ ያለበትን ደረጃ በተደጋጋሚ ጉብኝተውታል።
የአይሲቲ ልማትና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ ዓሊ ስለ ግንባታው በተናገሩበት ወቅት “የኛ ሥራ ቴክኖሎጂ ማበልጸግ ብቻም ሳይሆን ተሰጥኦዎችን ማበልጸግም በመሆኑ መሰል ተቋማት መጀመራቸው ሊበረታታ ይገባል” በማለት የመሰረተ ልማት ግንባታውን አስፈላጊነት አስታውቀዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አቶ በለጠ ሞላ የግንባታ ፕሮጀክቱ ግዙፍነትና ሊያሳካው የታለመለት ዓላማም ትልቅ መሆኑን አንስተዋል። በተጨማሪም ፕሮጀክቱ አገራዊ ፋይዳ ያለው እንደመሆኑና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ዜጎች ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳይንስ፣ በኢንጂነሪግና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ተሰጧቸውን የሚያሳድጉበት መሆኑን ጠቁመዋል። መሰል ተቋማት ዓለምአቀፍ አሰራርን ተከትለው በቀዳሚነት መቋቋምና ከነገም ተበድረን ልናሳካቸው ከሚገቡ ማዕከላት ቅድሚያ የሚሰጣቸውና ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሁሉም ዜጋ ሊደግፋቸው እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
“በዓለም አቀፍ ደረጃ የተረጋገጡ ፋይዳቸው ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ፕሮጀክቶች ውጥናቸው ከማንም ቢሆን በትኩረት ፈጽመን ልናሳካቸው እና ለላቀ አገራዊና ሕዝባዊ ጥቅም ልናውላቸው እንደሚገባ ይታመናል” ያሉት አቶ በለጠ፤ መሰል ተቋማት በየክልሎች እንዲስፋፉ ለማድረግ እንዲቻል ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል። ከወዲሁ በትብብር አቅዶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመግባትም ከሚመለከታቸው ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት ዝግጅት መደረጉንም አመልክተዋል።
እንደ መውጫ
የሰው ልጅ ስልጣኔ ምድር ላይ በሚያሳርፈው በጎ አሻራ በቀዳሚነት ይገለፃል። ለሺህ ዘመናት የዓለማችንን የመዘመን መንገድ የበየኑና ከቀሪው ፍጥረት የሰውን ልጅ ልዩ አድርገው ያመላከቱ የሰው ልጅ አሻራውን ያሳረፈባቸውን አያሌ ህንጻዎችን መጥቀስ ይቻላል። ከነዚህ ውስጥ የሚጠቀሰው ደግሞ የሰው ልጅ በተሰጠው የማሰላሰልና በህብረት የመስራት አቅሙ ምክንያት እስካሁን ድረስ ለምስክርነት የቆሙ የህንፃ ጥበቦቹን መጥቀስ ብቻ ይበቃል።
የሮማውያንን የህንፃ ጥበብ እና የመንገድ ግንባታ ለማድነቅ የግዴታ በዚያን ዘመን ብቻ መወለድ ላያስፈልግ ይቻላል። ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነው፤ 2000 ዓመታትን ዘልቀው እንኳን የእነዚያ ጥበበኞች አሻራዎች ያረፉባቸው ስራዎች ዛሬም ምስክር ናቸውና። የንጉስ ላሊበላን ተአምራዊ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ትናንት ስለነበርን ሳይሆን ዛሬም ድረስ ያለምንም እንከን አጠገባችን በመሆናቸው የሰው ልጅ ረቂቅ ክህሎት ምድራችንን በበጎ መልኩ ቀይሮ ለትውልድ የማሻገር ብቃት እንድናስተውል አድርጎናል።
ዛሬ ላይ ዓለማችን ተቀይራለች። መለወጥ ብቻ ሳይሆን የፉክክር መድረክ ሆናለች። መሰረተ ልማቶች ለቁጥር በሚታክት መልኩ ተገንብተዋል። ምድራችን በሰዎች ድንቅ የመፍጠር አቅም አጊጣለች። አገራት በየራሳቸው ቀለም አብበው ምቹ የመኖሪያ አካባቢዎችን ፈጥረዋል።
ትውልድ የራሱን ኖሮ ለመጪው ትውልድ የሚያሻግራቸው አያሌ ቅርሶችም እንደ ምድር አሸዋ የበዙ ሆነዋል። አሁን በምድር ላይ ምን ተሰራ ሳይሆን እኔ ምን አይነት አሻራ አሳረፍኩ የሚለው የበለጠ የሚያፎካክር ጉዳይ ነው። የታፈረና የተከበረ አገር ለመፍጠር አንዱ መንገድ በሉአላዊ ግዛት ውስጥ የሚተገበር የላቀ የመሰረተ ልማት ግንባታ ቀዳሚው መስፈርት ይይዛል።
ሁላችንም ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ አሻራ ማኖር ያስፈልገናል። መንግስት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እያከናወነ ነው። ይህን በጎ ዓላማ መደገፍ፣ ክፍተቶች ሲኖሩም ነቅሶ ማውጣት ወደፊት ለሚሰሩ መሰል ተግባራት ጠቀሜታ ይኖረዋል እያልን የዛሬውን ሃሳባችንን እዚህ ላይ እንቋጭ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2015