ወጣት ይድነቃቸው ተረፈ ትውልድና እድገቱ በደብረብርሃን ከተማ ነው። የመጀመሪያ ዲግሪውን በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ከደብረብርሃን ዩኒቨር ሲቲ አግኝቷል። ሁለተኛውን ዲግሪውን ደግሞ በማኔጅመንት ተቀብሏል። በተማረባቸው የትምህርት መስኮች በተለያዩ የግልና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ተቀጥሮ አገልግሏል።
በግሉ የማቀዝቀዣና የድራፍት ማሽኖች ጥገና ስራም ሰርቷል።በቀበሌ አካባቢ በሚካሄዱ የወጣቶች እንቅስቃሴዎች ውስጥም ንቁ ተሳታፊ ነበር።የማነቃቂያ ፕሮግራሞችንም ሰርቷል።በስነተዋልዶ ጤናና በፀረ ኤች አይቪ ኤድስ ክበቦች ውስጥም በንቃት ተሳትፏል።
‹‹ከፍታ›› ስለተሰኘው ፕሮጀክት መረጃው ቢኖረውም ጉዳዩን ቀለል አድርጎ ሲመለከተው እንደነበር የሚናገረው ወጣት ይድነቃቸው ስለከፍታ ምንነት በተመለከተ እርሱን ጨምሮ ለሌሎች የደብረብርሃን ወጣቶች ገለፃ ሲደረግ ስለፕሮጀክቱ ምንነት በጥልቀት እንደተረዳ ይገልፃል። በተለይ ደግሞ ታለንት ዩዝ አሶሴሽን ወጣቱ ማህረሰብ ከድንጋይ ወርዋሪነት ወደ ድንጋይ ደርዳሪነት እናምጣው፤ ድንጋይ ለመወርወር ምክንያት የሆነውን እንቅረፍለት የሚለው ሃሳብ ይበልጡን እንደሳበውና ወደዚህ ፕሮጀክት ለመግባት እንደገፋፋው ያስረዳል። በአሁኑ ግዜ ደግሞ የደብረብረሃን ከፍታ ወጣቶች ህብረት ጥምረትና የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ተቋም ሊቀመንበር መሆኑን ይገልፃል።
እንደ ወጣት ይድነቃቸው ማብራሪያ የከፍታ ፕሮጀክት እንደ ደብረብርሃን ከተማ ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ተመስርቷል።ሲመሰረትም ከክፍለ ከተማ ጀምሮ ከተለያዩ ክበቦች የተውጣጡ፣ ማህበረሰቡን የሚወክሉና አካል ጉዳተኛ ወጣቶች የተካተቱበት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል።ከ103 የወጣት ክበቦች ውስጥ የተውጣጣ 11 ውህደት በመፍጠር ፕሮጀክቱ ተጀምሯል።
‹‹ከፍታ›› ፕሮጀክቱ ይፋ እንደሆነ ስለምንነቱና ስለሚሰራባቸው ስራዎች እንዲብራራ ተደርጓል። በመቀጠልም በውህደት ጥምረት ማህበሩ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ከፍታን በተመለከተ የያዙትን እውቀት ለሌሎች ወጣቶች አሳውቀዋል። ይህንንም ለማሳካት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴዎች ተዳርገዋል።ወጣቱ የከፍታ ፅንሰ ሃሳብን ከተረዳ በኋላ ወደ 24 ያህል የሚሆኑ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንዲያገኝ ተደርጓል።
በኋላ ላይ ደግሞ በከፍታ ፕሮጀክት ውስጥ አዲስ ፅንሰ ሀሳብ መጣና የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ተጀመረ። ይህ የገንዘብ ተቋም ለወጣቱ የገንዘብ ቁጠባና ብድር በማመቻቸቱ ለወጣቱ ተጨማሪ የስራ እድል ፈጥሯል። በተለይ ደግሞ ወጣቱ የተለያዩ የቢዝነስ ሃሳቦች ቢኖሩትም የመስሪያ ገንዘብ ስለማይኖረው ወደ ተግባር ለመግባት ይቸገር ነበር። በከተማዋ ውስጥ ሌሎች የገንዘብ ቁጠባና ብድር ተቋማት ቢኖሩ እንኳን ገንዘብ ለመበደር ማስያዣ ስለሚጠይቁ አብዛኞቹ ወጣቶች ገንዘቡን ማግኘት አይችሉም።ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ የከፍታ ፕሮጀክት በዚሁ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ተቋም አንድ ወጣት ከሌላኛው ጋር እንዲጣመርና ዋስ እንዲሆን በማድረግ የብድር አገገልግሎት እንዲያገኙ አክሲዎን መሸጥ ተጀመረ።
የአንድ አክሲዎን ዋጋ 250 ብር እንዲሆንና ወጣቱ ዝቅተኛውን አራት የአክሲዎን ዋጋ እንዲገዛ ተደረገ።ወራሃዊ ቁጠባ 300 እንዲሆንም ተወሰነ። በዚህም ለበርካታ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች 50 ሺ ብር የሚሆን አክሲዎን ተሸጠ።በአሁኑ ግዜ ደግሞ ከ150 ሺ በላይ አክሲዎን ተሸጧል።ይህ ጠቃሚ መሆኑን ተረዱ ወጣቶችም የገንዘብ ተቋምን መቀላቀል ጀመሩ። በቅርቡ ደግሞ ቢሮ በመከራይቱ ተቋሙ ሙሉ ስራውን ይጀምራል።
ወጣት ይድነቃቸውም ከሰኔ 24 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ፕሮጀክቱን መቀላቀሉን ተናግሮ፤ በዚህ ፕሮጀክት ታቅፈው የሚሰሩ ወጣቶች 4 ሺ መድ ረሳቸውን ይጠቁማል። የገንዘብ ብድርና ቁጠባ አገልግሎቱን በተመለከተ ደግሞ ከ200 ሺ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች አክሲዎን በመግዛት ላይ እንደሚገኙ ያመለክታል። ወጣቶቹ አክሲዎን ከገዙ በኋላ በትንሹ 300 ብር በወር እየቆጠቡ መስራት ለሚፈልጓቸው ማንኛውም የቢዝነስ አይነቶች አራት እጥፍ ብድር የሚያገኙ ይሆናል።
በአሁኑ ግዜ ልክ እንደሌሎቹ ወጣቶቹ ሁሉ እርሱም በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ በመታቀፍና የራሱን ሀሳብ በማመንጨት ወደ ቢዝነስ ለመግባት ሃሳብ እንዳለውም ጠቁሞ በተለይ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ተቋሙ ሙሉ በሙሉ ስራውን ሲጀምር ሃሳቡን ወደ ተግባር ለመለወጥ ትልቅ እድል እንደሚፈጥርለት ተማምኗል። አክሲዎን በመግዛቱ ደግሞ ሀሳቡን ከጫፍ ለማድረስ አንድ እርምጃ አንዳንደረደረው ይገልፃል።
ልክ እንደ እርሱ ሁሉ ሌሎችም ወጣቶች በእንዲህ አይነቱ ፕሮጀክት ውስጥ ገብተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቅድሚያ ራሳቸውን ሊለውጡ የሚችሉ አጋጣሚዎችን መጠቀም እንደሚኖርባቸው ይመክራል።የንቁ ዜጋ መገለጫውም ይኸው ነው ይላል።
ታለንት ዩዝ አሶሴሽን በተሰኘው አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ የፕሮግራም ማናጀር አቶ ኤርሚያስ አሰፋ እንደሚናገሩት ድርጅቱ በዋናነት ወጣቶች ላይ አተኩሮ የሚሰራ ሲሆን ከተቋቋመ ሀያ አመታትን አስቆጥሯል። በነዚህ አመታት ውስጥ በተለይ በወጣቶች የስነ ተዋልዶ ጤናና በሌሎች አጠቃላይ የጤና ጉዳዮች ተደራሽነትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አገልግሎቶች ላይ ሰፋፊ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ወጣቶችን ወካይ የሆኑ ስርአቶችን በመዘርጋትም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚህም እድሜያቸው ከ15 እስከ 29 የሚሆኑ በርካታ ወጣቶችን በተለያዩ ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንዲያገኙ አድርጓል። አዲስ አበባን ጨምሮ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አማራና አፋር ክልሎች ላይ ወጣት ተኮር ስራዎችን አከናውኗል።
በአሁኑ ግዜ ደግሞ ድርጅቱ ‹‹ከፍታ›› የተሰኘ ለአምስት አመት የሚቆይ ትልቅ ፕሮጀክት ጀምሯል። ፕሮጀክቱም በዩ ኤ ስ ኤድ የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወን ሲሆን አዲስ አበባ እና ደብረብረሃን ላይ 460 ሺ ወጣቶችን ተደራሽ በማድረግ እየተተገበረ ይገኛል። ፕሮጀክቱ ተግባራዊ መሆን ከጀመረም ሁለት አመት አስቆጥሯል።
በዚሁ ፕሮጀክት ለወጣቶች ተደራሽ የሚሆኑ የጤና አገልግሎቶችን በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በወጣት ማዕከላት፣ በጤና ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጡ ይገኛሉ። ለወጣቶች ተደራሽነት ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አገልግሎቶችም በብድርና ቁጠባና በአቅም ግንባታና የህይወት ክህሎት ስልጠናዎች በነዚሁ ማእከላት እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው።
ፕሮጀክቱ ወጣቶች በተቀናጀ መልኩ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የሚያስችል ሲሆን ሁለት መሰረታዊ ግቦችን ይዟል። የመጀመሪያው ግብ ወጣቶች ዲሞክራሲያዊ በሆነና እነሱን በሚወክል መድረክ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ነው። ለዚህም ወጣቶቹ በተለያዩ ፍላጎቶቻው ለአብነትም በስፖርት፣ በስነ ጥበብ፣ በቴክኖሎጂና በሌሎችም ጉዳዮች እንዲደራጁ በመለየት፣ በመመዝገብና በማሰልጠን የወጣት ማህበራት ጥምረት በማቋቋም እርስበርስ የሚረዳዱበት፣ ሀሳብ የሚለዋወጡበት፣ በወጣቶች ጉዳዮች ላይ ድምፃቸውን የሚያሰሙበትና በአገራቸው ጉዳይ ላይ የሚወያዩበት መድረክ ተፈጥሯል።
በዚሁ መሰረት በደብረብርሃን ከተማ አንድ የወጣቶች ጥምረት ተቋሟል። በአዲስ አበባም በሰባት ክፍለ ከተሞች ማለትም በየካ፣ ለሚ ኩራ፣ ጉለሌ፣ አዲስ ከተማ፣ አራዳ፣ ልደታና ቂርቆስ ክፍለከተሞች ላይ ሁለት የወጣት ጥምረቶች ተቋቁመዋል።
ሁለተኛው ግብ ፈጠራ የታከለበትና ወጣት መር የፈንድ ማግኛ መንገዶችን መፍጠር ሲሆን ይህም በወጣቶች የሚመራ ሲሆን ወጣቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ስልጠናዎችና የብድርና ቁጠባ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።
እንደ አቶ ኤርሚያስ ማብራሪያ እነዚህን ሁለት መሰረታዊ ግቦች ዕውን ለማድረግ ደግሞ ሶስት ደጋፊ ግቦች አሉ። አንደኛው /youth capacity for advocacy and agency/ ሲሆን በወጣቶች ጉዳይ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ኢኮኖሚና ውክልና ላይ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ አቅማቸውን ማጎልበት፣ ራሳቸውን በማውጣት ለማህበረሰቡና ለመንግስት እንዲያቀርቡ ያስችላቸዋል። በዚህ ላይ የአደቮኬሲ፣ አጀንዳ ሴቲንግ፣ ሲቪክ ኢንጌጅመንት ስልጠናዎች ወጣቶቹ እንዲያገኙ ይደረጋል።
ይህም ወጣቶች በማህረሰባቸው ውስጥ ያሉ ችግሮችን ነቅሰው አውጥተው ለማህበረሰባቸው መልሰው ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።የተቸገሩ አዛውንቶችን እንዲያግዙ፣ ያረጁ ቤቶቻውን እንዲያድሱ፣ የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን እንዲደግፉ፤ እንዲጠግኑና በመሰል ስራዎች ወጣቶች ከችግር ፈጣሪነት ወደ መፍትሄ አካልነት እንዲሸጋገሩ የሚያደርግ ነው።
ሁለተኛው አዳዲስ የኢኮኖሚ እድሎችን በተለይ ተቀጥረው መስራት ለማይፈልጉ ወጣቶች ስራ መፍጠር ሲሆን እነዚህን ወጣቶች በመለየት የቢዝነስ ክህሎት፣ የኢንተርፕሪነርሺፕ፣ የብድርና ቁጠባ አገልግሎቶችን እንዴት ማግኘትና መጠቀም እንደሚችሉ፣ የህይወት ክህሎት፣ የሲቪክ ተሳትፎና ሌሎችም ስልጠናዎች እንዲሰጣቸው ይደረጋል።
በመቀጠል ደግሞ ወጣቶች ብድርና ቁጠባ እንዲያገኙ በዚሁ ፕሮጀክት በተቋቋመው ‹‹ዩዝ ኢምፓ ወርመንት ፈንድ›› በቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል። ዚህም በደብረ ብርሃን ከተማ አንድ ትልቅ የወጣቶች የብድርና ቁጠባ ህብረት ስራ ማህበር ተቋቁማል። በሀአሁኑ ግዜም ማህበሩ ተደራጅቶ ሼር እየሸጠ ይገኛል።
አባላት ከዚህ ፈንድ ከሚያገኙት ብቻ ሳይሆን ራሳቸው በሚቆጥቡት ገንዘብ ለትምህርት፣ ለቢዝነስና ለተለያዩ ለሚፈልጓቸው አገልግሎቶች ብድር መበደር ይችላሉ።ተቀጥረው መስራት ለሚፈልጉ ወጣቶች ደግሞ በተቀጠሩበት የስራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ፣ ስራ መፈለግና ሲቪ ማዘጋጀት እንዲችሉ ስልጠናዎች ይሰጣቸዋል።
የስራ እድል እንዲመቻችላቸውም ይደረጋል። ለአብነትም ለዳሸን ባንክ ከ300 በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን ማስቀጠር ተችሏል።የኢንተርፕረነርሺፕ አገልግሎቶችም ለወጣቶቹ እንዲመቻች ይደረጋል። በፍቃደኝነት ስራ እንዲለማመዱ የሚደረግበት ሁኔታም ይመቻቻል። የስራ ፍለጋ ክህሎታቸውን በማዳበር ስራ ራሳቸው ፈልገው የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲኖርም ስልጠናዎች ይሰጣቸዋል። ለዚህም ድርጅቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከተግባረ ዕድ ኮሌጅና ደረጃ ዶት ኮም ከተሰኘ የኦንላይን ፕላትፎርም ጋር አብሮ ይሰራል።በቅርቡ 53 ቀጣሪ ኩባንያዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የተሳተፉበት ቀጣሪ ከተቀጣሪ የተገናኘበት ፕሮግራም ተዘጋጅቷል።
ሶስተኛው እነዚህን አገልግሎቶች ለወጣቶቹ ተደራሽ ለማድረግ ድርጅቱ የለያቸው የወጣት ማእከላት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የጤና ተቋማት፣ የብድርና ቁጠባ ተቋማትንና የማህበራዊ ሚዲያውን ይጠቀማል።በተጨማሪም የወጣት ማእከላትና የጤና ተቋማትን በመረከብ ለወጣቶቹ ምቹና ሳቢ እንዲሆኑ ይታደሳሉ።ለወጣት ሴቶችና ለአካል ጉዳተኞችም ተደራሽ እንዲሆኑ ተደርገው ይሰራሉ።ለዚህም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከተግባረ እድ ኮሌጅ ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ወደ ስራ ሊገባ ነው።
አቶ ኤርሚያስ እንደሚሉት አዲስ አበባ ተግባረ እድ ኮሌጅ ውስጥ ለሚገኙ ከ7 ሺ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች ተሰጥቷቸዋል።ሰልጣኞችንም ወደነዚህ ጥምረቶች በማምጣት የቁጠባና ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ስራዎች ይሰራሉ።
በሚነድፉት ፕሮጀክቶች ውስጥ በትንሹ 50 ከመቶ ያህሉ ሴቶች እንዲሆኑ ተደርጎ እየተሰራ ነው። ከዚህ ፕሮጀክት 6 ከመቶ ተጠቃሚነት ደግሞ ለአካል ጉዳተኞች ተሰጥቷል።
‹‹ከፍታ›› ፕሮጀክት በ17 የአገሪቱ ከተሞች ተግባራዊ እየሆነ የሚገኝ ሲሆን ታለንት ዩዝ አሶሴሽን ደግሞ አገልግሎቱን በአዲስ አበባና ደብረ ብረሃን ከተማ ይሰጣል፤ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆንም በሌሎች አካባዎች ላይ ይሰራል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓም