የረጅም ርቀት የምንጊዜም ምርጡ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በአለም ምርጥ ከተባሉት የጎዳና ላይ ውድድሮች አንዱ የሆነው የዴልሂ ግማሽ ማራቶን አምባሳደር ተደርጎ መመረጡ ይታወቃል። ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ አምባሳደር ሆኖ በመመረጡ ደስተኛ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ ነገ ውድድሩ ሲጀመርም በህንድ መዲና ኒው ዴልሂ ተገኝቶ የሩጫው ተሳታፊዎችን እንደሚያበረታታ የአገሪቱ የስፖርት መጽሄት ባስነበበው ሰፊ ዘገባ ገልጿል።
ኃይሌ አምባሳደር በሆነበት በዚህ እውቅ የጎዳና ላይ ውድድር ሌላኛው ጀግና ኢትዮጵያዊ አትሌት ሙክታር ኢድሪስ የውድድሩ ድምቀት እንደሚሆን አዘጋጆቹ የገለጹ ሲሆን፤ በግማሽ ማራቶን ውድድር ቁንጮ የሆነ የአለማችን አትሌቶች በሚያደርጉት ብርቱ ፉክክር የአሸናፊነት ግምት ከተሰጣቸው ኮከቦች አንዱ ሆኗል።
የሁለት የአለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች የአምስት ሺ ሜትር ቻምፒዮኑ ሙክታር በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች በሚደምቀው የግማሽ ማራቶን ውድድር አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የሚፎካከር ሲሆን፤ ቀዳሚዎቹን ደረጃዎች ይዘው የሚያጠናቅቁ አትሌቶች ከተዘጋጀላቸው 268 ሺ ዶላር ሽልማት እንደሚቋደስ ይጠበቃል።
ፈጣን ሰአት በሚመዘገብበት በዚህ ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ የሚሳተፈው ሙክታር ለመጀመሪያ ጊዜ በ2020 በተወዳደረበት ወቅት 59:04 የሆነ ፈጣን ሰአት ማስመዝገቡ ይታወሳል። በዚያ ውድድር አራት አትሌቶች የቦታውን የቀድሞ ክብረወሰን ሲያሻሽሉ ሙክታር አንዱ የነበረ ሲሆን፤ በሽርፍራፊ ሰከንዶች ተቀድሞ አራተኛ ደረጃን ይዞ ነበር ያጠናቀቀው።
“በተፈጥሮዬ እስከ ሶስት ባለው ደረጃ ውስጥ ለማጠናቀቅ ነው የምወዳደረው” በማለት በመጀመሪያ የዴልሂ ግማሽ ማራቶን ውድድሩ ሶስተኛ ሆኖ ባለማጠናቀቁ ቁጭት እንዳደረበት የጠቆመው ሙክታር፤ ዘንድሮ ግን በጥሩ ብቃት ላይ እንደሚገኝና ለዚሁ ውድድር ትኩረት ሰጥቶ ሲዘጋጅ እንደቆየ ተናግሯል። ሙክታር አክሎም የነገውን ፈተና ደስተኛ ሆኖ ለመጋፈጥ እንደተዘጋጀ ገልጿል።
በውድድሩ ከሙክታር ጋር ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁ በርካታ አትሌቶች ቢኖሩም ዩጋንዳዊው ኮከብ ጃኮብ ኪፕሊሞ የተሰጠው ትኩረት ከሁሉም የተለየ ነው። ይህ የርቀቱ ባለክብረወሰን አትሌት ግማሽ ማራቶንን ከ58 ደቂቃ በታች ሶስት ጊዜ ማጠናቀቅ የቻለ እንደመሆኑ የተለየ ትኩረት ቢሰጠው አይገርምም። የ2021 የበርሊን ግማሽ ማራቶን አሸናፊው ኬንያዊ አትሌት ፌሊክስ ኪፕኮይች ሌላኛው ጠንካራ ተፎካካሪ አትሌት ሲሆን ኢትዮጵያዊው ጫላ ረጋሳም ትኩረት ካገኙ አትሌቶች አንዱ ነው። ይህ ወጣት አትሌት ባለፈው አመት በባርሴሎና ግማሽ ማራቶን ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ያስመዘገበው 59:10 የራሱ ፈጣን ሲሆን የማራቶን ኮከቡ ኬንያዊ በ2019 ቬና ላይ አርባ ሁለት ኪሎ ሜትርን በ1:59 ሲያጠናቅቅ ስኬታማ አሯሯጭ ከነበሩት አትሌቶች አንዱ እንደነበር ይታወሳል።
በሴቶች መካከል በሚካሄደው ውድድር የአለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የሶስት ሺ ሜትር አሸናፊዋ ለምለም ኃይሉ ለአሸናፊነት ከሚጠበቁ አትሌቶች አንዷ ነች። ባለፈው የአለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኦሪገን ላይ በሜዳሊያ ከደመቁ አትሌቶች አንዷ የነበረችው የሃያ አንድ አመቷ ለምለም የግማሽ ማራቶን ውድድርን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የምትሮጠው። ያም ሆኖ ባለፉት ሁለት የውድድር አመቶች በ1500እና በ3ሺ ሜትር ወጥ በሆነ አቋም ከአንድ እስከ ሶስት ባለው ደረጃ ውስጥ የማጠናቀቅ አቅም ያላት አትሌት በመሆኗ በነገው ውድድር ትኩረት ሊሰጣት ችሏል። ከለምለም በተጨማሪ የቤንጋሉሩ 10 ኪሎ ሜትር ውድድር አሸናፊዋ ኬንያዊት ኢሪን ቺፕታይ ጠንካራ ተፎካካሪ ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል። ይህች አትሌት ባለፈው የበርሊን ግማሽ ማራቶን 58:57 በሆነ ፈጣን ሰአት ማሸነፍ እንደቻለች ይታወቃል።
ከተዘጋጀው አጠቃላይ 268 ሺ ዶላር ሽልማት ውስጥ በሁለቱም ጾታ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች እያንዳንዳቸው የሃያ ሰባት ሺ ዶላር ተሸላሚ እንደሚሆኑ ከውድድሩ አዘጋጆች የተገኘው መረጃ ያመለክታል። እስከ አስር ባለው ደረጃ ውስጥ የሚያጠናቅቁ አትሌቶችም እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙ ይሆናል። በተጨማሪም የውድድሩን ክብረወሰን ማሻሻል የቻሉ አትሌቶች የአስራ ሁለት ሺ ዶላር ጉርሻ ተዘጋጅቶላቸዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/ 2015 ዓ.ም