የ2014 ዓ.ም የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአስራ አንድ የተለያዩ ዘርፎች በሁሉም ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ከ19 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ከሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ሲከናወን ቆይቶ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡
ሲከናወን በቆየው በዚሁ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መንግስትና ህብረተሰቡ ሊያወጡ የሚችሉትን 11 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ወጪ ለማዳን ታቅዶ 14 ቢሊዮን ብር ማዳን ተችሏል፡፡ አገልግሎቱም 40 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ተደራሽ ሆኗል፡፡
የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አሰጣጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥነት እንዲኖረውና በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ለማስቻል የፌደራል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ብሔራዊ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ፖሊሲና የአሰራር ማዕቀፍ እያዘጋጀ ይገኛል፡፡
ፖሊሲና የአሰራር ማዕቀፍ ከማዘጋጀት በዘለለ ታዲያ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በክረምት ብቻ ሳይሆን በበጋ ወቅትም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ብዙዎች ከአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይፈለጋል፡፡ ለዚህም ወጣቱ በበጋ ወቅት ከሚያከናውነው የግል ስራና ትምህርቱ በተጓዳኝ በትርፍ ጊዜው እውቀቱን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማዋል እንዳለበት ይታመናል፡፡
ወጣት ፋጡማ ሃሰን አርሲ ሮቤ ተወልዳ ያደገች ቢሆንም ኑሯዋ አዳማ ከተማ ነው፡፡ በከተማው በክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ውስጥ በመታቀፍ የአቅመ ደካማ ቤቶችን በማደስ፣ ጎዳና ላይ የወደቁ ልጆችን በማንሳትና በመደገፍ በሌሎችም የበጎ ፍቃድ ስራዎች ላይ ስትሳተፍ እንደቆየች ትናገራለች፡፡
‹‹ብዙ ጊዜ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት የተለመደው በክረምት ወቅት ነው›› የምትለው ወጣት ፋጡማ፤ በነዚህ ጥቂት ወራት አገልግሎቱን ለበርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ ስለማይቻል አገልግሎቱን በበጋ ወቅትም ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ትናገራለች፡፡ ወጣቱም ከትምህርትና የስራ ግዜው ላይ ትርፉን ለዚሁ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማዋል እንደሚገባው ታስረዳለች፡፡
ለዚህም ይህን ዘርፍ የሚመሩ የመንግስት አካላትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክፍሎች ስራውን ሊደግፉና ሊያበረታቱ እንደሚገባ ታመለክታለች፡፡ በተመሳሳይ ባለሀብቶችም ወጣቱን ከጎን ሆነው ቢደግፉ አገልግሎቱን በስፋት መስጠት እንደሚቻልም ነው ወጣት ፋጡማ የምታስረዳው፡፡ ይህም በክረምቱ ወቅት ያልተፈቱ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግር ለመፍታት እድል እንደሚሰጥ ትጠቁማለች፡፡
ወጣት ኤልሳ ኃይለ መስቀል የቀድሞው የኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች ስትሆን፤ ከአማራ ክልል ደብረ ብርሃን ከተማ አፄ ዘርዓያእቆብ ክፍለ ከተማ እንደመጣች ትናገራለች፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማ የሴቶች እግር ኳስ ክለብን ከማሰልጠን ውጪ ሙሉ ጊዜዋን ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት እየሰራች እንደምትገኝም ትገልፃለች፡፡ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱን ከአስር አመት በፊት እንደ ጀመረችም ታስረዳለች፡፡
በክረምት ወቅት በደብረ ብርሃን ከተማ ሲከናወን የቆየውን የክረምት ወቅት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በተለይ ደግሞ ከህልውናው ዘመቻ፣ ከደም ልገሳ፣ ከአረጋውያን ቤት ጥገና ጋር በተያያዘ ያለውን ስራ በማስተባበርና በመሳተፍ ላደረገችው አስተዋፅኦ ከፌዴራል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሽልማት እንዳገኘችም ትጠቁማለች፡፡
ከሴቶች ጋር በተገናኘ በከተማዋ ከልጅነቷ ጀምሮ በርካታ ስራዎች ስትሰራ እንደነበርና ሴቶች በስፖርት በተለይ ደግሞ በእግር ኳስ ተሳታፊ እንዲሆኑ ስትሰራ መቆየቷን ተናግራ፤ ሽልማቱ የእርሷ ብቻ ሳይሆን በምትኖርበት አካባቢ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ ለተሳተፉ ሁሉም ወጣቶች መሆኑንም ትገልፃለች፡፡
እርሷ በትኖርበት አካባቢ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በክረምት ብቻ ሳይሆን በበጋም ጭምር እንደሚሰጥ ትናገራለች፡፡ ሆኖም አገልግሎቱ የክረምቱን ያህል እንዳልሆነና በበጋ ሰፊ ጊዜ ስለሚኖር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ትጠቁማለች፡፡ በጎነት ለራስ እንደመሆኑ ወጣቱ በክረምት ወቅት ብቻ ሳይሆን በበጋ ወቅትም የበጎ ፍቃድ ስራዎችን ማከናወን እንዳለበትም ታመለክታለች፡፡ ከዚህ አኳያ እርሷ በምትኖርበት የደብረ ብርሃን ከተማ አፄ ዘርያእቆብ ክፍለ ከተማ የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በበጋውም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ታስረዳለች፡፡
በክረምት ወቅት ትምህርት ስለሚዘጋ አብዛኛውን ወጣት ማግኘት የሚቻለው በዚሁ ወቅት በመሆኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱን በበጋ ወቅት በስፋት ለመስጠት ችግሮች እንደሚያጋጥሙም ወጣት ኤልሳ ጠቅሳ፤ በበጋ ወቅት የወጣቱን በጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሳታፊነት ለማሳደግ ከወዲሁ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉም ታብራራለች፡፡
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚቋረጥ ባለመሆኑና ሁሌም ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ሁሉም ወጣት ትርፍ ጊዜውን ለዚህ በጎ ተግባር ማዋል እንዳለበትም ትምክራለች ወጣት ኤልሳ፡፡ ይህም የበርካታ ህብረተሰበ ክፍሎችን ህይወት የሚያሻሽል መሆኑም ትጠቁማለች፡፡
ወጣት ብሩክ መሰለ የኢትዮጵያ ስካውት ማህበር ስራ አስፈፃሚ ኮሚሽነር ነው፡፡ እርሱ እንደሚለው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት የሚገኝባት ሀገር እንደመሆኗና የክረምት የበጎ ፋቃድ አገልግሎት ደግሞ የሚሰጠው ለጥቂት ወራት በመሆኑ በበጋ ወቅትም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ይህም በክረምት ወቅት የተከናወነውን አገልግሎት በእጥፍ በማሳደግ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ማሳደግ ያስችላል፡፡
ከዚህ አንፃር በመንግስት አካባቢ ያሉ የሚመለከታቸው አካላት በክረምት ወቅት ሲሰሩበት በነበረው ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት በበጋ ወቅትም ስራውን ማከናወን ከቻሉ ወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱን ለመስጠት ወደኋላ አይሉም፡፡ በመንግስት በኩል ያለው ሀብት ውስን በመሆኑና ሁሉንም የህብረተሰብ ችግሮች መፍታት የማይችል በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ወጣቶች በያሉበት አካባቢ አቅማቸው የፈቀደውን አገልግሎት መስጠት አለባቸው፡፡ በክረምት ወራት የነበራቸውን ተነሳሽነትም አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡
በርግጥ የበጋ ወራት የትምህርት ወቅት ቢሆንም ትምህርትን ጠንክሮ መማር በራሱ አንዱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ነው፡፡ ከመደበኛ ትምህርት ውጪ ከፍተኛ የወጣቶች ቁጥር በመኖሩ ይህ ወጣት በማህበረሰቡ ውስጥ ላሉ እያንዳንዱ ችግሮች አቅም በመፈቀደ ሁሉ የሚችለውን ሁሉ ካደረገና ካስተባበረ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን መጥቀም ይቻላል፡፡
ወጣቶች ለማንኛውም ማህበራዊ ጉዳዮች ግንባር ቀደም ምላሽ መስጠት አለባቸው፡፡ በስካውት ማህበርም እያንዳንዱ አባል የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ የስካውት አንዱ መርህም በቀን ቢያንስ አንድ መልካም ተግባር መስራት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በስካውት ማህበር በክረምት ብቻ ያልተወሰነና በማንኛውም ጊዜና በእለት ተእለት ህይወት የሚከናወን ተግባር ነው፡፡
ከዚህ አኳያ ሌሎችም ወጣቶች በክረምት ብቻ ሳይሆን በበጋም ጭምር ከተለመደው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስኮች በተጨማሪ ሌሎች ፈጠራ የታከለባቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዋናው ትርፉ የህሊና እርካት ማግኘት በመሆኑ አቅም በፈቀደ ሁሉ ከሁሉም ወጣት ተግባሩን መፈፀም ያስፈልጋል፡፡
ወጣት ብሩክ እንደሚገልፀው፤ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ የስካውት እንቅስቃሴ አለ፡፡ መንግስት ባስቀመጣቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘርፎች ማለትም የአካባቢ ፅዳት፣ ችግኝ ተከላ፣ ማእድ ማጋራት፣ የሆስፒታል ውስጥ አገልግሎት፣ የቤት ማደስና ግንባታ ላይ ስካውቶች በንቃት በያሉበት አካባቢ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በሴቶች የወር አበባ መጠበቂያ፣ በሰላምና በግጭት ተፈናቃዮች ዙሪያ ፈጠራ የታከለባቸው የበጎ ፍቃድ ስራዎችን አከናውነዋል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደሚገልፁት፤ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ የወጣቶችን ሁለገብ ተሳትፎ ለማጎልበትና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ከሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ አንዱ ሲሆን፤ ወጣቶች ካልባሌ ቦታዎች በመራቅ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ተጠቅመው እንደየአካባቢያቸው ነባራዊ ሁኔታ፣ እንደህብረተሰቡ ፍላጎት በመንግስትና በማህበረሰቡ ያልተሸፈኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክፍተቶችን ለመሙላት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡
የዘንድሮው የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ‹‹ በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ›› በሚል መሪ ቃል ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም በይፋ መጀመሩን ተከትሎ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱም የከተማ አስተዳደሮች ጋር በመተባበር አጠቃላይ ሂደቱን በሀገር አቀፍ ደረጃ በበላይነት ሲያስተባብር ቆይቷል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃም በ2014 ዓ.ም የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት 19 ሚሊዮን ወጣቶችን ለማሳተፍ አቅዶ በሰራው ንቅናቄ 19 ሚሊዮን 800 ሺ ወጣቶችን በማሳተፍ የእቅዱን 105 ከመቶ ማከናወን ችሏል፡፡ በወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎትም በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በወጣቶች ዘንድ ሀገራዊ አንድነት እንዲፈጠርና ትስስሩም እንዲጠናከር ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ 40 ሚሊዮን የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ እቅድ ተይዞ ከ42 ሚሊዮን በላይ ያህሉ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ በተሰጠው የበጎ ፍቃድ አገልግሎትም በመንግስትና በህዝብ ሊወጣ የነበረውን 12 ቢሊዮን ብር የሚገመት አገልግሎትን ለማዳን ታቅዶ 14 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ያህሉን ማዳን ተችሏል፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ በዚሁ የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሳትፈው ውጤታማ ስራዎችን ያከናወኑና ለመርሃግብሩ መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉ ወጣቶች እውቅናና ሽልማት መሰጠቱ በቀጣይ አገልግሎቱ በተጠናከረ መልኩ በበጋ ወቅትም ጭምር እንዲቀጥል መነቃቃትን ይፈጥራል፡፡
ውድ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ሳይሰስቱ ለውጥ በሚያመጡና ጠቃሚ በሆኑ ተግባራት ላይ በማዋል የድርሻቸውን ሲወጡ የነበሩ የበጎ ፍቃድ አምባሳደሮችና ሁሉም የበጎ ፍቃድ ወጣቶች በቀጣይ በርካቶችን ከጎናቸው በማሰለፍ በወሰንና በወራት፣ በባህልና በተለያዩ ሁኔታዎች ሳይገደቡ በየመስኩና በየአቅጣጫው የጀመሯቸውን ሰብአዊ አገልግሎቶች ከክረምቱ ባሻገር በበጋውም ወራት ይበልጥ አጠናከረው ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል፡፡
አስናቀ ፀጋይ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/ 2015 ዓ.ም