ልጆች እንዴት ናችሁ? በዚህኛው አምድ ላይ ታዋቂ ፈላስፋዎችን፣ ጀግና የአገር መሪዎች፣ ሳይንቲስቶችን እና ለዓለም ሥልጣኔ የበኩላቸውን ድርሻ የተወጡ ሰዎችን እናስተዋውቃችኋለን። እስቲ ልጆች የሰው ልጅ የሥልጣኔ ጉዞ እዚህ እንዲደርስ ትልቅ ድርሻ አላቸው የምትሏቸውና ከዚህ ቀደም እናንተ ከምታውቋቸው ሰዎች መካከል ጥቂቶቹን አስታውሱ። እኛ ለዛሬ አንድ ሰው መርጠንላችኋል፡፡ ይህ ሰው ታዋቂው ሠዓሊ እና የሥነ ፅሁፍ ሰው ገብረ ክርስቶስ ደስታ ነው፡፡
ገብረ ክርስቶስ ከአባቱ ከአለቃ ደስታ ነገዎ ከእናቱ ከወይዘሮ አፀደ ማርያም ወንድማገኝ በ1924 ዓ.ም በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ሀረር ከተማ ተወለደ፡፡ ገና የስድስት ዓመት ልጅ እያለ ‹‹እናትነት›› ብሎ የሠየማትን የእርሳስ ሥዕል ሠራ፡፡ እዚህ ጋር የህይወት ስጦታው እና ችሎታው ምን እንደሆነ አወቀ፡፡
በኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ አጭር ቆይታው በኢትዮጵያ የጥበብ ዘርፍ ከፍተኛ ዝና ያላቸውን ስመጥሮቹን በተለይ መንግሥቱ ለማንና አፈወርቅ ተክሌን የመተዋወቅ ዕድል አግኝቷል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጥሩ ውጤት ካጠናቀቀ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ሳይንስ ፋካልቲ የተመደበው ገብረ ክርስቶስ ትምህርቱን የተከታተለው ለአጭር ጊዜ ነበር፡፡ የሚወደውን የሥነ ጥበብ ሥራ ለመማር ይህኛውን ለማቋረጥ ተገደደ፡፡
ገብረ ክርስቶስ በውጭ ሀገር ሥነ ጥበብን ለመማር 1949 ወደ ቀድሞዋ ምዕራብ ጀርመን አቀና፡፡ ጀርመን ሀገር በሚገኘው በኮለን የጥበብ ትምህርት ቤት በቆየባቸው አምስት ዓመታት ስለ ሥዕል አሠራር፤ ቅብ አጠቃቀምና ሌሎች የሥዕል መሳሪያዎችና አጠቃቀማቸውን በሚገባ ከማወቁም በላይ በረቂቅ ሥዕል ሥራ ከፍተኛ ዝና የነበራቸውን ምሁራን ለማወቅና ሥራቸውን ለመመልከት እድል ያገኘበት አጋጣሚም ነበር፡፡ ገብረ ክርስቶስ በጀርመን ሀገር እያለ በረቂቅ ሥዕል አሳሳሉ ከታወቀው ሩሲያዊ ዋሲስኪ ካዲስኪና ከሌሎች የአውሮፓ ረቂቅ ሥዕል ጠቢባን ጋር መገናኘቱን ተከትሎ ለረቂቅ ሥዕል ሥራ ከፍተኛ ፍቅር አድሮበታል፡፡
ከኮለኝ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በከፍተኛ ውጤት መመረቁን ተከትሎ በተበረከተለት የሥዕል መሥሪያ ስቱዲዮ የተለያዩ ሥዕሎችን በማዘጋጀት የአንድ ሰው የሥዕል አውደ ርእይ ለማቅረብ ችሏል፡፡
ገብረ ክርስቶስ በይበልጥ የሚታወቀው በሥዕል ሥራዎቹ ቢሆንም ለስሜቱም ቢሆን የጻፋቸው ጥቂት ግን ተወዳጅ የግጥም ሥራዎቹ በኢትዮጵያ በዘርፉ ትልቅ ስም ካላቸው ሰዎች ተርታ አስቀምጠውታል፡፡ ገብረ ክርስቶስ በረቂቅ የሥዕል አቀራረቡ በሀገራችን መነጋገሪያ የሆነውን ያክል ግጥሞቹ የራሳቸው የቃላት አሰላለፍን የሚከተሉና የቤት ዓመታታቸው ቁጥር ከተለመዱት የግጥም ቤቶች የተለዩ መሆናቸው በጥበብ ቤተሰቦች መነጋገሪያ መሆናቸው አልቀረም፡፡ ገብረ ክርስቶስ የተለያዩ ጭብጦችን ነቅሶ የጻፋቸው የግጥም ሥራዎቹ የተለዩና ስሜት የሚኮረኩሩ ከመሆናቸው በላይ የቃላት አመራረጡ እጅግ ግልጽና ቀላል በመሆናቸው ማንኛውም አንባቢ የሚረዳቸው ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2011