በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ እያጋጠመ ባለው የዋጋ መናር የተነሳ በህብረተሰቡ ላይ የኑሮ ጫና እየተፈጠረ ነው:: ከምግብ ሸቀጦች ጀምሮ በአልባሳት፣ በቤትና በቢሮ ዕቃዎች እንዲሁም በተለያዩ የግንባታ ዕቃዎች ላይ በሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ሸማቹ እያማረረ ነው:: መንግሥት ገበያን ለማረጋጋት በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል:: በተለይ ደግሞ በሲሚንቶ ምርት ላይ የሚስተዋለው የተጋነነ የመሸጫ ዋጋና የምርት አቅርቦት አለመኖር ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል::
ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የሲሚንቶ ዋጋ መናርና የአቅርቦት እጥረት በተመለከተ የተለያዩ አካላትን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበናል:: በአዲስ አበባ መገናኛ አካባቢ በሚገኙ የሲሚንቶ መሸጫ ሱቆች ያለውን የገበያ ሁኔታ እንደቃኘነው፤ለወትሮው በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የሚርመሰመሱበትና መተላለፊያ መንገድ የማይገኝበት ይህ የሲሚንቶ መሸጫ አካባቢ እኛ በሥፍራው በተገኘንበት ወቅት ከወትሮው በተለየ መልኩ ጭር ብሏል:: የገበያተኛው እንቅስቃሴ ቀንሷል:: አብዛኞቹ የሲሚንቶ መሸጫ ሱቆችም ዝግ ነበሩ:: ሱቃቸውን የከፈቱ ቢኖሩም የሲሚንቶ ምርት አልነበራቸውም:: በሲሚንቶ መሸጫ ደጃፎቹ ላይ ብዛት ያላቸው ከባድ የጭነት ተሸከርካሪዎች ቆመዋል:: አሽከርካሪዎች፣ጫኝና አውራጆች ያለሥራ መቀመጣቸው የሲሚንቶ ንግድ መቀዛቀዝን ያሳያል:: ምክንያቱን ለማወቅ ከመካከላቸው ለማነጋገር ፈልገን በተናጠል ሀሳብ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም:: በአንድ ድምጽ መንግሥት ባወጣው መመሪያ መሰረት ሲሚንቶ አግኝተው መሸጥ እንዳልቻሉና በዚህም እየተቸገሩ እንደሆነ ነው የገለጹት::
በዚሁ ሥፍራ ያገኘናቸው የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት በመሥጠት ሥራ ላይ የተሰማሩት አሽከርካሪ አቶ ሰለሞን ከበደ በሰጡት ሀሳብ፣መንግሥት እየናረ ያለውን የሲሚንቶ ገበያ ለማረጋጋት በተለያየ ጊዜ የሚያወጣቸው መመሪያዎች ስለመኖራቸው ጠቅሰው፣መመሪያው ግን ከሲሚንቶ ነጋዴው በተጨማሪ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎችን፣ጫኝና አውራጆችን እየጎዳ መሆኑንና እነዚህ አገልግሎት ሰጭዎች ከሶስት ወራት በላይ ያለሥራ ለመቀመጥ መገደዳቸውን አስረድተዋል:: እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ቀደም ሲል በነበረው አሰራር አንድ ሰው ከማምረቻው እስከ ሁለት መቶ ኩንታል ሲሚንቶ መግዛት ይችል ነበር:: በመካከል ላይ መንግሥት የሲሚንቶ ፋብሪካዎችንና ነጋዴውን የሚያገናኝ ወኪሎች (ኤጀንቶች) በማቋቋም ግብይቱ በወኪሎቹ አማካኝነት እንዲከናወን አደረገ:: ወኪሎቹ በተመጣጣኝ ዋጋ በበቂ ሁኔታ እያቀረቡ ባለመሆናቸው የሲሚንቶ ገበያው ቀላል ሊሆን አልቻለም:: ይህ ደግሞ በዘርፉ በተለያየ አገልግሎት ላይ የሚገኘውን ጎድቶታል:: አቶ ሰለሞን መንግሥት ያወጣውን ህግ ተግባራዊ በማያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጅ መውሰድ ተገቢ መሆኑን ቢያምኑም ነጋዴው ሲሚንቶ ባላገኘበት ሁኔታ ህግ ማውጣት ግን ተገቢ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ::
ለሲሚንቶ ገበያ አለመረጋጋት ሌላው ምክንያት የምርት አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም መሆኑን ያነሱት አቶ ሰለሞን፤ መንግሥት ፋብሪካዎችን መደገፍና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል:: እንደ አቶ ሰለሞን ማብራሪያ ለሲሚንቶ ምርት ዋናው ግብዓት የከሰል ድንጋይ ነው:: ይህ ግብአት ደግሞ በሀገር ውስጥ በስፋት ይገኛል:: መንግሥት ግብአቱ ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ በማመቻቸት ችግሩን መቅረፍ ይኖርበታል::
ዋጋውን በተመለከተም እንደየሲሚንቶው አይነት የሚለያይ መሆኑን በመግለጽ፤ ዳንጎቴ ተፈላጊ በመሆኑ ከፍ ባለ ዋጋ እንደሚሸጥ ጠቅሰው፤ መንግሥት አንድ ኩንታል ሲሚንቶ በሰባት መቶ ብር እንዲሸጥ ተመን ያወጣ ቢሆንም፣ገበያ ላይ በአንድ ሺ አምስት መቶ ብር እንኳን ማግኘት እንደማይቻል ነው የተናገሩት:: የማከፋፈል ሚና ያለው ጅንአድ የተባለው ድርጅት በምን ሁኔታ እንደሚያከፋፍል በመከታተልና ቁጥጥር በማድረግ ገበያውን ማረጋጋት እንደሚያስፈልግ ሀሳብ ሰጥተዋል::
የአቡቀለም ኮንስትራክሽን ሥራ አስኪያጅ፣የዲዛይን ማማከርና የግንባታ ሥራዎችን እንዲሁም የግንባታ ቁጥጥር ሥራ የሚሰሩት ኢንጅነር ደሳለኝ ከበደ፤በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ የግንባታ ዕቃዎች እንደማንኛውም ምርት የገበያ አለመረጋጋት ይታይበታል:: የገበያ አለመረጋጋቱ ደግሞ ኮንትራከተሮች ቃላቸውን ጠብቀው ግንባታ እንዳያከናውኑ ከማድረግ ባለፈ ለኪሳራ በመዳረጉ የተለያዩ ፕጀክቶች ሥራ እንዳይፋጠንና ሥራውም በወቅቱ እንዳይጠናቀቅ ያደርጋል:: ይህ ደግሞ በሀገር ሀብት ላይ ብክነት ያስከትላል:: ገበያው እየተመራበት ያለው መንገድ ጤናማ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል:: ተጠቃሚው የሚፈልገውን ምርት በቀጥታ አያገኝም፤ ቢያገኝም ያለደረሰኝ እንዲገዛ ይገደዳል:: ይህ ደግሞ ከዘርፉ የሚገኘውን የግብር ገቢ ያሳጣል:: እየሆነ ያለው ይህ ነው:: በሲሚንቶ ግብይት ላይ የሚስተዋለው ችግር ዘርፈ ብዙ ነው ይላሉ::
በተለያዩ ምክንያቶች የሲሚንቶ እጥረት በአገሪቷ ላይ ስለመኖሩ የታዘቡት ኢንጅነር ደሳለኝ፤ መንግሥት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተለያዩ መመሪያዎችን ቢያወጣም የሲሚንቶ ገበያን ሊያረጋጋ እንዳልቻለና በዚህ ምክንያትም በርካታ ሥራዎች እየተስተጓጎሉ መሆናቸውን ተናግረዋል:: የሲሚንቶ ግብይት ችግር ላይ ሲወድቅ የአሸዋ፣ የብረት፣ የጠጠርና የሰው ኃይልም ጭምር ከሥራ ውጭ እንዲሆኑ የሚያደረግ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮች አብረው ይፈጠራሉ:: ስለዚህ የሲሚንቶ ግብይት ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በባለሙያ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል:: መንግሥት በቅርቡ በሲሚንቶ ገበያ ላይ ያወጣው መመሪያ በባለሙያ የተጠና ስለመሆኑ ጥርጣሬ እንዳላቸው የሚናገሩት ኢንጅነር ደሳለኝ፤ ለአብነትም መመሪያው ለአንድ ቤተሰብ 15 ኩንታል ሲሚንቶ ብቻ ይፈቅዳል:: ነገር ግን ሲሚንቶ በቤተሰብ ብዛት ሳይሆን፣በፕሮጀክት የሚለካ ነው ብለዋል::
እንደርሳቸው ገለጻ፣15 ኩንታል ሲሚንቶ ሊሠራ የሚችለው ሥራ በጣም ትንሽ ነው:: 15 ኩንታል ሲሚንቶ አገሪቷ አሁን እያከናወነች ካለው ትላልቅ ፕሮጀክቶች አንጻር አቅርቦቱ በቂ አይደለም:: ዋጋውን በተመለከተም ፋብሪካዎች አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከአምስት መቶ እስከ ስድስት መቶ ብር ነው የሚሸጡት:: ይሁን እንጂ ገበያው ላይ መንግሥት ባወጣው የዋጋ ተመን እየተሸጠ አይደለም:: በመሆኑም ከፋብሪካዎች በላይ በንግድ ሰንሰለት ውስጥ መሀል ላይ ያሉት ደላሎች ተጠቃሚ ሲሆኑ፣መጨረሻ ላይ ያለው ገዢው ደግሞ በከፍተኛ መጠን ተጎጂ ይሆኗል::
ኢንጅነር ደሳለኝ፤ በዘርፉ እየተስተዋለ ያለውን ችግር ለመቅረፍና የሲሚንቶ ገበያን ለማረጋጋት መፍትሔ ይሆናል ያሉትን ሃሳብ ሲያካፍሉም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ቀዳሚው መፍትሔ እንደሆነ አስገንዝበዋል:: ለዚህም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲስፋፋና በብዛት ማምረት እንዲችሉ ማበረታታት አስፈላጊ እንደሆነ በመመክር በተለይም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አነስተኛ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል:: እነዚህን አነስተኛ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግና ምርቱን በማብዛት ገበያውን ማረጋጋት ይቻል ይሆናል እንጂ በየጊዜው በሚወጣ የገበያ ቁጥጥርና መመሪያ ውጤት ማምጣት አይቻልም ብለዋል::
ለሲሚንቶ ምርት ዋና ዋና ግብዓቶች ናቸው የሚባሉት ጅብሰም፣ የድንጋይ ከሰልና ሌሎችም በአገር ውስጥ ስለመኖራቸው የጠቀሱት ኢንጅነር ደሳለኝ፤ የኃይል አቅርቦትን በተመለከተም የዓባይ ግድብ ኃይል እያመነጨ እንደሆነ አንስተው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር እያወጡ ህንጻ የሚገነቡ ሰዎችን ወደ ሲሚንቶ ፋብሪካ ማምጣት ያስፈልጋል:: እነዚህን ጥሬ ዕቃዎች ተጠቅመው ሲሚንቶ ፋብሪካ መገንባት ቢችሉና ከአገር አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ መትረፍ እንደሚቻል ተናግረው የመንግሥት ትኩረት መሆን ያለበት ምርቱን ማብዛት ላይ ነው ብለዋል::
የሲሚንቶ ዋጋ ረጅምና ጤናማ ባልሆነ የግብይት ሰንሰለት አማካኝነት ያለአግባብ እየናረ ስለመሆኑና በዚህም ምክንያት በአገራዊና ማህበረሰባዊ እድገት ላይ ፋይዳ ያላቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች ተስተጓጉለዋል:: በመሆኑም ሰንሰለቱን ለማሳጠርና ገበያውን ለማረጋጋት በሚል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ በየደረጃው ካሉ የንግድ ዘርፍ መዋቅሮችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል::
መንግሥት በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ የሚያደርገው ቁጥጥርና ክትትል ምን ውጤት አስገኘ፤ የተወሰዱ እርምጃዎችስ እንደምን ያሉ ናቸው፤ አሁን ያለው የሲሚንቶ ገበያስ እንዴት እየተመራ ነው ስንል ላነሳነው ጥያቄም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ቁምነገር እውነቱ፤ የሲሚንቶ ገበያን ለማረጋጋት በሚል ከሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ መመሪያ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባቱን አስታውሰው፤ በመመሪያው አተገባባርም መንግሥት እጁን በማስገባት ፋብሪካዎችም በመንግሥት መመሪያ እንዲገዙ ሆኖ ዋጋ አቅርበው መመሪያው ተግባራዊ መሆን እንደቻለ አስረድተዋል::
ይሁንና መመሪያውን ተግባራዊ ማድረግ ያልቻሉና በአቋራጭ መክበር የሚፈልጉ የፋብሪካ ባለቤቶችን ጨምሮ አንዳንድ አከፋፋዮች በመኖራቸው የሲሚንቶ ገበያ መረጋጋት እንዳልቻለ አንስተው፤ ማህበረሰቡ ሲሚንቶን በተጋነነ ዋጋ እየገዛ እንደሆነ ነው የተናገሩት:: መንግሥት ያወጣውን መመሪያ ተግባራዊ ማድርግ ያልቻሉትንም ግብረኃይል ተቋቁሞ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እየተወሰደ ስለመሆኑ ያነሱት ኃላፊዋ፤ ከሰሞኑ ብቻ በሶስት ክፍለ ከተሞች ላይ በተደረገ ቁጥጥርና ክትትል 22 ሺ ኩንታል ሲሚንቶ ተወርሶ መንግሥት ባወጣው የሲሚንቶ ዋጋ ተሽጦ ለመንግሥት ገቢ መደረጉን ተናግረዋል:: ከዚህ በተጨማሪም የታሸገባቸውና እርምጃ የተወሰደባቸው ፋብሪካዎች ስለመኖራቸውና ግብረኃይሉ መሰል ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ አንስተዋል::
አሁን ያለውን የሲሚንቶ ገበያ አስመልክተውም እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ከምርት እጥረት ጋር ተያይዞ የመጣ እንዳልሆነና የመንግሥትን መመሪያ ጠብቀውና ተከትለው የሚሠሩት ጥቂቶች በመሆናቸው ያነሱት ኃላፊዋ፤ ለአብነትም እንደ አዲስ አበባ ከተማ መመሪያውን በጠበቀ መንገድ በሁለት ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ማከፋፈያዎች ብቻ እንደሚከፋፈል ነው ያስታወሱት:: እነዚህ ማከፋፈያዎችም ፒያሳ የሚገኘው ኤግልድ ኮርፖሬሽንና የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ናቸው::
ከእነዚህ ሁለት አከፋፋዮች ውጭ ማንም ነጋዴ እንደፈለገ ሲሚንቶ መሸጥ የተከለከለ እንደሆነ መመሪያው ያዛል:: ነገር ግን የተፈቀደላቸውና የመንግሥትን መመሪያ መሠረት በማድረግ ለሚሸጡት ቅደም ተከተሉን በጠበቀ መንገድ እንዲሸጡ ተደርጓል:: ይህም ማለት የመንግሥትና የግል አልሚዎችን ግንባታ እየፈጸሙ ላሉት ቀጥታ ከፋብሪካ በር ላይ እንዲገዙ ነው የተደረገው:: ምክንያቱም በርካታ ግንባታዎች በሲሚንቶ እጥረት በየቦታው እየተስተጓጎሉ በመሆናቸው ነው::
በቁጥር አነስተኛ መጠን ያለው ሲሚንቶን ለሚፈልጉ ተጠቃሚዎች ማለትም ለቀብርና መሰል ጉዳዮች ግለሰቦች ሲፈልጉ ሲሚንቶ እንዳያጡ ባልተጋነነ ዋጋ እንዲያገኙ የተዘጋጁ መሸጫ ቦታዎች በየአካባቢው ይገኛሉ:: ነገር ግን በእነዚህ አካባቢዎች የሚቀርበው የሲሚንቶ ዋጋ እጅግ የተጋነነ ስለመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ እየደረሰው ሲሆን፤ መረጃውን መሰረት በማድረግም ጥቆማው በተሰጠባቸው አካባቢዎች በመዘዋወር የእርምት እርምጃ መወሰዱንና በቀጣይም ቁጥጥሩና ክትትሉ በከፍተኛ ሁኔታ አጠናክሮ በማስቀጠል ገበያውን ለማረጋጋት ይሠራል ብለዋል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2 ቀን 2015 ዓ.ም