ትውልዱም ሆነ እድገቱ እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ምስራቅ በርና ቦሌ በተባሉ ትምህርት ቤቶች ነው የተማረው። በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በቢዝነስ ማኔጅመንት የትምህርት መስክ መማር ቢጀምርም ክፍያውን መክፈል ባለመቻሉ ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገደደ። ከልጅነቱ ጀምሮ ለበጎ ስራ አገልግሎት ልዩ ፍቅር ያለው ይህ ወጣት በበጎ ስራ በሚሳተፍበት የወጣት ማህበር አማካኝነት ሳውዲስታር በተባለ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ በሩዝ እርሻ ላይ ለሁለት ዓመታት ያህል ጋምቤላ ክልል ሰርቷል።
የጋምቤላ ቆይታው ለእፅዋትና ለአረንጓዴ ልማት ስራ ልዩ ፍቅር ይበልጥ እንዲያዳብር ምክንያት ሆነለት። እናም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ጓደኞቹን በማስተባበር በበጎ አድራጎት ይሰራ የነበረውን አካባቢን የማስዋብና የእፅዋት ስራን ወደ ቢዝነስ በመቀየር ውጤት ማምጣት ቻለ። በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በርካታ የመንገድ አካፋዮችና የመንገድ ዳርቻዎችን በማስዋብ በከተማ አስተዳደሩና በማህረሰቡ ተቀባይነቱን አሳደገ። በአሁኑ ወቅት ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ዋርካ የመናፈሻ ስራና የእፀዋት ማዕከል በመክፈት ከስድስት ያላነሱ የልማት ጣቢያዎችን ማፍራት ችሏል። ይህ ወጣት ለ20 ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር የዜግነት ግዴታውን በመወጣት ላይ ይገኛል። ከወጣት የአረንጓዴ አሻራ ባለራዕይ እንዳለ ተሰማ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- ወደዚህ ሥራ የገባህበትን አጋጣሚ አስታውሰንና ውይይታችንን እንጀምር?
ወጣት እንዳለ፡- ይህንን ስራ ከመጀመሬ በፊት የወጣት ማህበር እያለሁ ጀምሮ ወጣቶችን በማስተባበር በከተማችን የተለያዩ አካባቢዎች ችግኞችን እንተክል፤ ከተማም የማስዋብ ስራ እንሰራ ነበር። በተለይ ክረምት ላይ በርካታ የችግኝ ተከላ ስራዎችን እንሰራ ነበር። ያ ነው እያደገ መጥቶ ለአረንጓዴ ልማት ልዩ ቦታና ትኩረት እንድሰጥ ያደረገኝ። በተለይም እንደምታስታውሽው የባቡር መንገድ ዝርጋታው ሲጠናቀቅ የባቡር መስመሩን ተከትሎ ምንም አይነት እፅዋት አልነበሩም፤ እኛም ይህንን በማየት የተለያዩ ችግኞችን በበጎ ፈቃድ ሰዎችን በማስተባበር መትከል ጀመርን። በአካባቢው ያሉ ተቋማትና ባለሃብቶችን እያስተባበርን ችግኞችን መትከል ጀመርን።
በመሰረቱ አረንጓዴ ልማት በብዛት የሚሰራው በመንግስታዊ ድርጅቶች አማካኝነት ነው። ሆኖም በእኛ የወጣት ማህበር የበጎ ፍቃድ መርሃ ግብር ውስጥ በክረምት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚሰሩ ስራዎች መካከል አንዱ የችግኝ መትከል፤ መንከባከብና አካባቢን ማስዋብ ስራ ነው። በክረምት ላይ በብዛት ተማሪዎችን የክረምት ትምህርት እናስተምራለን፤ እኔ እንዳውም እዚህ ላይም ለረጅም ጊዜ አስተባባሪ ነበርኩኝ። ከማስተማሩ ጎን ለጎን ግን በየሳምንቱ እየወጣን ችግኝ እንተከል ነበር። በኋላ ላይ ይህ ስራችን እየሰፋ ሄደና የባቡር መስመርን ተከትሎ ችግኝ በበጎ ፈቃድ እንዲተከል ከፍተኛ ስራ ሰርተናል።
በተለይ ከመገናኛ እስከ መስቀል አደባባይ ድረስ ለማልማት ከክፍለ ከተሞች ጋር በውል ቦታውን ወስደን ወደ ስራ ገባን። እናም ለእፅዋት የነበረን ፍቅር እነዚህ እንቅስቃዎቻችን ጋር ተዳምሮ የበለጠ እንዲዳብር አድርጎታል ብዬ ነው የማምነው። መጀመሪያ ላይ እንደጊዜ ማሳለፊያም ብጠቀምበትም፤ ከሁሉ በላይ የተወለድንባትና ያደግናባትን ከተማ እንደስሟ ውብ ማድረግ በራሱ ትልቅ እሴት ነው የፈጠረልኝ። እንዳልኩሽ ደግሞ ፈቃደኛ የሆኑ ተቋማት ደግሞ ድጋፍ ሲያደርጉልን የበለጠ እየተበረታታን መጣን። በተለይ አንዳንድ ሆቴሎችና ድርጅቶች የምንሰራውን ስራ እያዩ እፅዋቱ እስከሚያድግ ድረስ የሚያስፈልገውን ወጪ ይሸፍኑልን ነበር።
በዚህ ሁኔታ ነበር ከአረንጓዴ ልማት ስራ የበለጠ መቆራኘቱ የመጣው። ከዚያ በኋላ ነው መንግስት የስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ሲሰጥ እኛም የበጎ አድራጎት ስራና ወደ ቢዝነስ የቀየርነው። በተለይ ፓርኮችንና አደባባዮችን ለማልማት ህጋዊ ሆነን ተደራጅተን ወደ ስራ ገባን። በነገራችን ላይ ችግኞቹን ተክለን እስኪያድጉ ድረስ ከጥቃት ለመከላከል የምንሰራው ብረት ላይ የድርጅቶችን ማስታወቂያ እናስቀምጣለን። ይህም የሚረዱን ድርጅቶች እኛን ከማገዝ ጎን ለጎን እነሱም የተቋማቸውን ስም ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል ፈጥሮላቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ወጣቶች ዲግሪ ይዞ ወደ እንደዚህ አይነት ስራ መስራት አይፈልጉም፤ አንተ በዚህ ሙያ ላይ ስትሰማራ ቶሎ ገቢ የማይገኝበት መሆኑ አላሰጋህም?
ወጣት እንዳለ፡– ልክ ነሽ፤ ለብዙዎች ከባድ ነው፤ እንዳልሽውም ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በቢዝነስ ማኔጅመንት ዲግሪ ይዤያለሁ፤ ነገር ግን ከተመረኩኝ በኋላ ስራ ለማግኘት ሁኔታዎች ምቹ አልነበሩም። ሲጀመርም ደግሞ ተቀጥሮ የመስራት ፍላጎት አልነበረኝም። የራሴን ስራ ለመፍጠር ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ። ወጣት ማህበር በቆየሁበት ጊዜ የፈጠረልኝ አንዱ ምቹ ሁኔታ የተለያዩ ስልጠናዎችን ማግኘት ነው። በእነዚያ ስልጠናዎች የራሴን ስራ እንድጀምር ከፍተኛ መነሳሳት ፈጥሮብኛል። ከእኔ አልፎ እንዳውም ለሌሎች ወጣቶች ስራ ለመፍጠር ነበር ህልሜ። ከዚያ በኋላ ከመቀጠሩ ይልቅ በትንሹም ቢሆን የራስን ስራ መጀመር የተሻለ እንደሆነ ደጋግሜ አስብ ነበር።
ሳውዲስታርም በነበርኩበት ጊዜም ጥሩ ተከፋይ ብሆንም ተቀጥሮ መስራት እንዴት ፈታኝ እንደሆነ አይቻለሁ፤ በአጠቃላይ ተቀጥሮ መስራት ከእኔ ህልምና ፍላጎት ውጭ ነበር። ለዚህ ነው ወስኜ ትቼው በመምጣት የራሴን ስራ መስራት የጀመርኩት። በነገራችን ላይ ሳውዲ ስታር ራሱ የስራ እድል እንዲፈጥርልኝ ያደረኩት እኔው ራሴ ነኝ። በማሽን ስራ ስልጠና ወስጄ ስለነበር ለእኔና ለጓደኞቼ ስራ እንዲፈጠርልን በደብዳቤ አመልክቼ ነው ስራውን ያገኘሁት።
ጋምቤላ ለሁለት ዓመት ከቆየሁ በኋላ ወደራሴ ስራ መግባት እንዳለብኝ ራሴን አሳምኜና ሌሎች ወጣቶችን አስተባብሬ የጀመርኩት። ከአረንጓዴ ልማት ስራው ጎን ለጎን የህትመት ስራ እንሰራለን። ስንጀመር የተከልነው ችግኝ በብዛት ይረጋገጥብንና ይቆረጥብን ነበር፤ በመሆኑም የችግኞቻችንን ሕይወት ለመታደግ ብረቱንና የማስታወቂያ ህትመት ወደ መስራቱም ገባን። ባለሃብቶች ማስታወቂያቸውን በአደባባዮቹ እያስቀመጡ እንዲያለሙ ማድረግ ጀመርን።
አዲስ ዘመን፡- ከሰራኋቸው የከተማዋ ማስዋብ ስራዎች መካከል ጥቂቶቹን ብትጠቅስልን?
ወጣት እንዳለ፡- አሁን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመስራት ላይ እንገኛለን፤ በተለይ የአፍሪካ ህብረት አካባቢ ያለውን የመንገድ አካፋይን የማስዋብ ስራ እየሰራን ነው። የዚህም መንገድ የማስዋብ ፕሮጀክት አጠቃላይ ስፋት ወደ አምስት ሺ ካሬ ቦታ ሲሆን ሃላፊነቱን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወስደን ነው የምንከባከበው። ጥላሁን አደባባይንም እንዲሁ ከይርጋ ሃይሌ ቤተሰብ ጋር በመተባበር እነሱ ወጪውን ሸፍነው አልምተን አስረክበናል። እንደዚሁም ጉምሩክ ኮሚሽንን፤ የኢንቨስመንት ቢሮን የመሳሰሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማትንም በእፅዋት የማስዋብ ስራ እንሰራለን። ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርም ጋር በጋራ የምንሰራቸው ስራዎች አሉ።
ይህንን ስራ ስንጀምር ግን ትልቅ መነሻ የሆነን ከመገናኛ እስከ ሃይሌ ህንፃ የሰራነው የማስዋብና የአረጓዴ ልማት ስራችን ነው። በዚህ አጋጣሚ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ስራችንን ስንጀምር ከሁሉም በፊት ድጋፍ ያደረገልን በመሆኑ ላመሰግነው እወዳለሁ። የሚገርምሽ ያንን ካፒታል እንደመነሻ ይዘን ነው ሌሎችን ስራ የቀጠልነው። በተጨማሪም ከባቡር መስመሩን ተከትሎ ከቦሌና ከየካ ክፍለ ከተማ ጋር በመተባበር አልምተናል። በተመሳሳይ ቂርቆስ ላይ ደግሞ ከኡራኤል ጀምረን እስከ ሜክሲኮ ድረስ፤ ስቴዲየምና መስቀል ፍላወርና ከኡራኤል እስከ አትላስ ያሉ መንገዶችን እንዲሁ አስውበናል።
አዲስ ዘመን፡- በተለይ ከለውጡ መምጣት ጋር ተያይዞ መንግስት ለአረንገዴ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ይታወቃል፤ በዚህ ስራ የእናንተ አስተዋፅኦ ምንድን ነው?
ወጣት እንዳለ፡- እንዳልኩሽ እኛ ከለውጡ በፊትም ነው በበጎ ፍቃድ ከተማችንን ስናለማና ስናስውብ የነበረው። እኛ ይህንን ስራ በበጎ ፈቃድ ስንጀምር በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር፤ ሰዎች ችግኞችን ይረግጡብን ነበር፤ ተቀባይነቱም አልነበረንም። ከ2010 ዓ.ም በኋላ ግን አገራዊ ስሜት ተፈጠረ። በተለይ ከአረንጓዴ አሻራ ጋር ተያይዞ የመትከል ፍላጎት፤ ለእፅዋት ያለው ፍቅር እያደገና ጥቅሙን በተጨባጭ የሚያየው ነገር ሆነ። በተለይ መሪዎቻችን ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ህብረተሰቡን ያነቃቁበት እና ያንን ተከትሎ ለእኛም ጥሩ ምቹ ሁነታዎች ተፈጠሩ።
አሁን ላይ ህብረተሰቡ አረንጓዴ አሻራን በየአካባቢውና በየቤቱ መተግበር ጀምሯል። ከመንግስት ተቋማት ባሻገር የግል ድርጅቶችም ተቋማቸውን በእፅዋት የማስዋብ ስራ እየተበራከተ መጥቷል። በተለይ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፕሮጀክቶች እየተመለከተ ሁሉም የየራሱን አካባቢ የማሳመር ፍላጎት በጣም ጨምሯል። ይህንን ያልኩሽ ደግሞ አካባቢው ላይ ያለውን ፍላጎት ገበያው ላይ ስለምናውቅ ነው። እኛም ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እፅዋቶችን እያቀረብን ነው ያለነው። የተለያዩ የመንገድ አካፋዮችንም ከተቋማት ጋር በመተባበር እያሳመርን ነው የምንገኘው። ከዚህም ባሻገር ምን አይነት እጽዋት ለአካበቢው ምቹ እንደሆነ ከማማከርና ስልጠናዎችን ከመስጠት ጀምሮ እንክብካቤ በማድረግ ሂደት ውስጥም ሰፊ እንቅስቃሴ ነው እያደረግን ያለነው። የሕብረተሰቡም ጥያቄ በዚያው ልክ ነው እያደገ የመጣው።
አዲስ ዘመን፡- ለምን ያህል ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ችላችኋል? የድርጅታችሁ አቅምስ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?
ወጣት እንዳለ፡- በአሁኑ ወቅት 20 ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ችለናል። አሁን ላይ የእኛ ካፒታል እፅዋቶቻችን ናቸው፤ ሆኖም የአፍሪካ ህብረት አካባቢ ያለውን ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ወደ ስድስት ሳይቶች አሉን። በተጨማሪም በርካታ የግለሰብ ተቋማትንና ጊቢዎችን እንከባከባለን። በዚህም አቅማችን ይበልጥ እያጎለበትን ነው የምንገኘው። አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እንደመሆንዋ መጠን ለሁሉም የምትመችና ማራኪ ከተማ ለማድረግ የበኩላችንን ጥረት እያደረግን ነው። በተለይ በዚህ ዓመት ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል። ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የመንግስት በጀት ፈሶባቸው አደባባዮች ይለሙ ነበር፤ ነገር ግን አመቱን ሙሉ በቂ እንክብካቤ ስለማያጎኙና የውሃ እጥረት በመኖሩ ተመልሰው የሚጠፉበት ሁኔታ ነበር። እኛ ይህንን ችግር በዘላቂነት ከመፍታት አንፃር ትልቅ እቅድ ይዘን ነው እየሰራን ያለነው። ከመንግስትም አንዳንድ ድጋፎች ካገኘን የበለጠ ለመስራት ነው ያሰብነው። ምክንያቱም ችግኞችን መትከል ብቻ ከተማችንን በዘላቂነት ማስዋብ አይቻልም፤ ደግሞ የመጨረሻ ግብ ሊሆን አይችልም።
በቀጣይም በዘርፉ በተለይ በላንድስኬፕ ላይ የተሻለ ተቋም የመፍጠር አላማ ነው ያለኝ። በተጨማሪም ደግሞ በአገራችን ውስጥ ትልቅ የሆነ እፅዋቶችን ነርሰሪ የመገንባት እቅድ አለን። ፈጣሪ ከረዳን በአጭር ጊዜ ውስጥ በዘርፉ ከፍተኛ የስራ እድል የሚፈጥር ድርጅት መሆን ነው መሻታችን።
በመሰረቱ አካባቢን ማስዋብ ስራ ብቻ ሳይሆን ጥበብ ነው። አዲስ አበባ ደግሞ የዓለም የዲፕሎማት መቀመጫ ከሚባሉት ከተሞች መካከል እንደመሆንዋ ከሌሎቹ ጋር ለማቀራረብ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል። በተለይ የአፍሪካ መዲናነቷን የሚያስጠብቅ ፓርኮች፤ መዝናኛዎች፣ የመንገድ አካፋዬች፣ አረንጓዴ ቦታዎች ሊኖሯት ይገባል። ያንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ የተሻለ አቅምና ፍላጎት ያላቸው አካላት ለዘርፉ እድል በመስጠት ነው ብዬ አምናሁ።
በተለይ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ይህንን እድል ከመፍጠር አኳያ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ባይ ነኝ። በየኛ በኩል ምቹ ሁኔታው ከተፈጠረልን አዲስ አበባ ላይ ትልቅ ፓርክ የመገንባት እቅድ አለን።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ሙያ ውስጥ ያጋጠሙ ፈታኝ አጋጣሚዎች ምን ነበሩ? አሁንስ ለስራችሁ ተግዳሮት የሆነባችሁ ጉዳይ ምንድን ነው?
ወጣት እንዳለ፡- ከዚህ ቀደም በበጎ ፈቃድ ስንሰራ የምናደርጋቸው ጥረቶች እንደመልካም ጎን ታይቶ ድጋፍ እንኳን ቢቀር የምንሰራውን ስራ እውቅና መስጠት አስቸጋሪ ነው። የምንሰራው ለአገር ጥቅም ስለመሆኑ ከመንግስት አካልም ሆነ ማህበረሰቡ የሚረዳ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ችግኞችን ተክለን ተንከባክበን ስናሳድግ ሌላ አላማ እንዳለን የሚያስብ አለ። የበጎ አድራጎት ስራውን ወደ ቢዝነስ ቀይረን ስንሰራም በተለይ የመንግስት ተቋማትን ለማሳመን ትልቅ ተግዳሮት ነው የሆነው። ስራ ማግኘትም በጣም ከባድ ነበር። አሁንም ድረስ እየተፈተንበትና ትልቅ ራስ ምታት የሆነብን ነገር ውሃ ማግኘት ነው። የምንተክለው ተክል በውሃ እጦት ምክንያት ይደርቃል። በጄሪካን ውሃ እየተሸከምን ነው የተከልናቸውን አትክልቶች የምናጠጣው። አሁንም ክረምት ላይ ጥሩ ሰርተናል፤ ግን በጋው ሲመጣ ይደርቅብናል ብለን እንፈራለን።
በሌላ በኩል ደግሞ የአገራችን ባንኮች ትልቅ ሃሳብና ጥሩ ፕሮጀክት ላለው ወጣት ብድር የሚሰጡበት አሰራር አለመኖሩ ወደፊት ላሰብነው ትልቅ ፕሮጀክትም ሆነ አሁን እየሰራን ላለነው ስራ እንቅፋት ሆኖብናል። በተለይም በዘርፉ ላሰብናቸው ትልልቅ ስራዎች የተለያዩ ባንኮችን ብናኳኳም በጎ የሆነ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። በመሆኑም የአገራችን ባንኮች ኮላተራል ማስያዝ ለማይችል ግን ደግሞ ችግር ፈቺ የሆነ ሃሳብ ላለው ዜጋ ምቹ ሁኔታ ሊፈጥሩ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ዲግሪ ይዘው የመንግስት ስራ ለሚጠብቁ ወጣቶች የምታስተላልፈው መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥህ?
ወጣት እንዳለ፡- እኔ ለወጣቱ የማስተላለፈው ዋነኛ መልዕክት ከጠባቂነት እንዲወጡ ነው። የተማረው ለመቀጠር ብቻ ነው ብሎ የሚያስብ ጥቂት የማይባል ወጣት አለ። ይህ አስተሳሰብ ግን አሁን ባለው ሁኔታ ሊሆን የሚችል አይደለም። ከዚያ ይልቅ ወጣቱ ችግር ፈቺ ሊሆን ነው የሚገባው። በተማሩት ሙያ ስራ እስከሚገኙ ድረስ አካባቢያቸው ላይ ያሉትን እድሎች መጠቀም ይገባቸዋል። በመሆኑም ማንኛውንም ስራ ሳይንቁ መስራት አለባቸው። ወጣቱ በአካባቢው ምቹ ያልሆነውንም ጭምር ምቹ ለማድረግ መጣር አለበት የሚል መልዕክት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ።
ወጣት እንዳለ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2015