የዛሬው ባለውለታችን ሰው ሁለገብ ናቸው። እዚህ ሲሏቸው እዛ፤ እዛ ሲሏቸው ደግሞ እዚህ ይገኛሉ። በመሆኑም፣ እኛም ሁለገብነታቸውን ተገንዝበን በፈርጅ በፈርጁ ልንገልፃቸው፣ ስራዎቻቸውን በአይነት በአይነት ልናይላቸው ወደድን። እርግጥ ነው እኚህ የዛሬው የ ”ባለውለታዎቻችን” ተስተዋሽ ሁለገብ ሰው በአሁኑ ትውልድ ብዙም አይታወቁም። እሳቸው አይታወቁ እንጂ ዛሬ የምንመለከታቸው ስራዎቻቸው ግን በእያንዳንዳችን በሚባል ደረጃ የእለት ተእለት እንቅስቃሴና አኗኗር ዘይቤ ውስጥ ያለሟቋረጥ ቦታ አለው። አስተዋፅኦዋቸውም ጉልህ ነው።
እኚህ የዛሬው የገፁ ተስተናጋጅ ብዙ አይባልላቸው እንጂ በብዙዎች በሚፈለጉ ሰነዶች ላይ ግን ተገቢውን ስፍራ ይዘው የምናገኛቸው ሲሆን፤ Encyclopaedia aethiopic እና ሌሎችም ላይ ሕይወትና ስራዎቻቸው ሰፍረው ይገኛሉ። (በቋንቋ ክፍተት ምክንያት መረዳት ያልቻልነውና ድረ-ገፅ ላይ የሚገኘው ” አምባሳደር ተፈሪ ሻረው ብኸፊሉ እንክዝከሩ!”ም ሌላው ስለ ተፈሪ ሻረው የተፃፈ ነው።)
አቶ ተፈሪ ከአፍሪካ እግር ኳስ አባት ይድነቃቸው ተሰማ ጋር ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው ለእግር ኳሳችን በመልፋታቸው ምክንያት በተለይ በቀድምቶቹ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ በሚገባ ይታወቃሉ፤ ይጠቀሳሉም።
አቶ ተፈሪ ሻረው በማህበራዊ አገልግሎቱ በኩልም በዚህ መልክ ገለፅናቸው እንጂ በፖለቲካውም አሉበት።
አቶ ተፈሪ በፖለቲካው መስክ ያላቸው ሚናም ሆነ ተሳትፎ ይህ ነው ብሎ ቁልጭ ባለ መልክ መግለፅ የሚቻል አይደለም። የዚህ ችግር ዋናው መንስኤ ደግሞ የመረጃ እጦት ሲሆን፤ እንደ ነገሩም ያገኘናቸው ምንጮች እንደሚያሳዩት ከሆነ የፖለቲካ ሰብእናቸው አወዛጋቢ ነው። በተለይ ከንጉሱ ጋር እሳትና ጭድ ናቸው ይባላል።
አምባሳደር ተፈሪ ሻረው በዲፕሎማሲው መስክ አገራቸውን አገልግለዋል። ይሁን እንጂ ይህም (ከመቼ እስከ መቼን ጨምሮ) ያስመዘገቧቸውን ድሎችም ይሁን ያበረከቱትን አስተዋፅኦ እንካችሁ የሚሉ መረጃዎች የሉም። ምናልባት ከዚህ ፅሁፍ በኋላ አቶ ተፈሪ ሻረውን የተመለከቱ መረጃዎች በእጃቸው ያሉ ሰዎች ያካፍሉናል ተብሎ ይጠበቃል።
ሰውየውና ሁለገብነታቸው በአንድ አካባቢ የተወሰኑ አይደሉም። እነ ጋሽ በቀለ ሞላን በሚያስታውሰን መልኩ ካሉበት፣ ከጀመሩበት አካባቢም ወጥተዋል። ለዚህ ማስረጃችን ደግሞ ከወደ ጅማ የተገኘው መረጃ ነውና ዝቅ ብለን የምናየው ይሆናል።
ተፈሪና አምቦ ጠበል
ከአፍሪካ 1ኛ፣ ከዓለም 10ኛ፣ ዓመታዊ አማካይ ገቢው ከ3 ቢሊዮን ዩኤስዲ በላይ የሆነው አልኮል አልባ መጠጦች አምራች ኩባንያ (ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግ) እንደገለፀውና allafrica.com ለንባብ እንዳበቃው በ1931 በአምቦ ከተማ የመጀመሪያውን፣ አምቦ የማእድን ውሃ (Ambo Mineral Water) በሚል መለያ (brand) የሚታወቀውን የአምቦ ውሃ (በተፈሪ ምክንያትም በአለም “oldest modern mineral water” በሚል ይታወቅ ዘንድ ግድ ብሏል) ማምረቻ ፋብሪካ የመሰረቱት (የከፈቱት) ነጋዴው (businessman ይላቸዋል) ተፈሪ ሻረው ናቸው።
የአምቦ ውሃ ፋብሪካ በአሁኑ ሰአት አቅሙን ከሶስት እጥፍ በላይ ለማሳደግ ከውጭ ባለሀብቶች ጋር መስራት በማስፈለጉ ያ ተደርጎ፣ በፊት በሰአት 12 ሺህ ጠርሙስ የነበረው ከ2009 ጀምሮ በሰአት 40ሺህ እንዲያመርት ሆኗል። እኤአ በ2017 CCBA ከገዛው ጀምሮ ስያሜው Ambo Mineral Water S.C ሆኗል። ንብረትነቱም የCoca-Cola Beverages Africa ነው። ከተወረሰበት 1975 (እአአ) ጀምሮ እስከ ኢህአዴግ አገሪቷን እስከተቆጣጠረበት ጊዜ ድረስ የህዝብ ሀብት (public companies) ከሆኑት አንዱ የነበረው፣ ይህ የኢትዮጵያ ምልክት (”Ethiopian Icon” ይሉታል) የሆነው አምቦ (ጠበል) ውሃ (ልክ እንደ ቡናችን ሁሉ) ተወዳጅነቱ፣ ተመራጭነቱና ተፈላጊነቱ የትም ሲሆን በተለይም በኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳን፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ፣ እንግሊዝ፣ ስዊድን፣ ዩናይትድ ስቴስትስ፣ ቶሮንቶ እና ካናዳ ሕይወት ያለ እሱ ባዶ ነች።
ውድነቱም የዛኑ ያህል ሲሆን፤ ለምሳሌ፡- ኒው ዮርክ ሬስቶራንቶች ውስጥ ከየትኛውም ለስላሳ መጠጥ በላይ የሚሸጠው ($6 በጠርሙስ) የእኛው አምቦ ውሃ ነው። ይህንን ስንመለከት፣ ያኔ የአቶ ተፈሪ የቢዝነስ ምርጫ የሚደነቅ ሆኖ እናገኘዋለን። (በነገራችን ላይ፣ በአሁኑ ሰአት 106 የፕላስቲክ ውሃ አምራች ኩባንያዎች እንዳሉ ያውቃሉ? ለጠቅላላ እውቀት እንጂ ከአምቦ ጋር እያነፃፀርናቸው አይደለም።)
ተፈሪና አረንቻታ
አቶ ተፈሪ ሻረው አረንቻታን በተመለከተም ያው እንደ አምቦ ውሃው (ጠበል) ሲሆን፤ ከመጀመሪያዎቹ የፋብሪካ ባለቤቶችና ባለሀብቶች አንዱና በንጉሰ-ነገሥቱ ዘመን ለስላሳ መጠጥ ፋብሪካ የሆነውን አረንቻታ የከፈቱ ባለሀብት ነበሩ።
የመጀመሪያው የሀገራችን የለሥላሳ መጠጥ ፋብሪካ በአቶ ተፈሪ ሻረው የተከፈተው የአረንቻታ ፋብሪካ ነበር። በፊት የተወዳጁና ስመ ጥሩ አምቦ ባለ ጋዝ ውሃ ቀደምት ባለቤት እሳቸው እንደ ነበሩት ሁሉ አረንቻታ ማምረቱም የእሳቸውና በእሳቸው የተጀመረ ነው። በዘመኑ የሁሉም ለስላሳ መጠጦች ዋጋ አስር ሳንቲም ነበር። (እአአ በ1959 አዲስ አበባ፣ ሁለተኛ ቅርንጫፉን በ1965 ድሬዳዋ ላይ የከፈተው፤ በ1975 የተወረሰው Ethiopian Bottling Share Company ባይወረስ ኖሮ ዛሬ የት በተደረሰ፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪም በሆንን ነበር።)
ተፈሪና ጅማ
አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ተመስገን ወርቁ የተባሉ ሰው ስለ ጅማ ቀደምትነት (የዛሬን አያድርገውና በማለት የተፃፈ) በፃፉት የቁጭት ጽሑፍ ላይ የሚከተለው አረፍተ ነገር ሰፍሮ ይገኛል። ጅማ የለስላሳ መጠጥ (ተፈሪ ሻረው አረንቻታ) ፋብሪካ በነበራት ጊዜ ከጥቂት “ከተማዎች በስተቀር በሌሎች ብዙ ቦታዎች የሚኖሩት ዘመዶቻችን አረቄና ጠላ ነበር የሚጠጡት፤ … ግፋ ቢል ጠጅ። ስለዚህም ከጽሑፉ በግልፅ እንደምንረዳው አቶ ተፈሪ ሻረው ከአዲስ አበባም አልፈው ለከተሞች እድገት፣ ሥልጣኔና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ የነበሩ መሆኑን ነው።
ተፈሪና ስፖርት
በ1940 ዓ.ም የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ በማህበር ተቋቋመ። በዚህ ጊዜ አልጋወራሽ የክለቡ የበላይ ጠባቂ ሲሆኑ አቶ ገብረሥላሴ ኦዳ ፕሬዝዳንት፤ አቶ ተፈሪ ሻረው እና አቶ ጌታሁን አየለ ምክትል ፕሬዝዳንት፤ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ዋና ጸሐፊ ሆነው ተመርጠዋል።
ግንቦት 15 ቀን 1950 የአምቦ ውሃ ባለቤት አቶ ተፈሪ ሻረው ለስድስት ወር የሚቆይ ፑልፒ (ከጣፋጭ ፍሬዎች የሚሰራ) በተባለው መጠጥ ላይ በሳጥን የአምስት ሳንቲም እርዳታ ለማድረግ ወስኖ አስተላለፈ። ደጋፊውና ተማሪው ፑልፒኑን ሲጠጣ ጊዮርጊስን እየረዳ እንደሆነ እንዲያስብ ነው። ባለቤቱ ተፈሪ ሻረው በዓመቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ። በዚያኑ ዓመት ደግሞ ዞማ ኮላ ከተባለ መጠጥ አስር ሳንቲም ለአንድ ወር ፈቀደ። ግንቦት 12 ቀን 2008 ዓ.ም የጊዮርጊስ ቡድን ለ12 ጊዜ የፕሪሚመር ሊጉን ዋንጫ ያገኘበት እለት ነው። (ግጥምጥሞሹን ልብ ይሏል።)
ገነነው መኩሪያ (ሊብሮ) እንደሚለው፤ የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ የልብ ደጋፊ የነበሩት እና የቅዱስ ጊዮርጊስን ክለብን በፕሬዝዳንት (በ1951 ዓ.ም) ለመምራት የተመረጡት አቶ_ተፈሪ_ሻረው ናቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ታሪካዊ ቀለማት ቀይና_ቢጫ እንዲሆን ያደረጉት።
ተፈሪና ፖለቲካ
ከድረ-ገጽ (https://am.sewasew.com) ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ራስ መስፍን ስለሺ በጣም ያቀርቧቸው እና በቅርበት ይከታተሏቸው የነበሩት ተፈሪ ሻረው በራሳቸው በራስ ስለሺ አማካኝነት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ድርጅት ውስጥ ትልቅ ሃላፊነት ተሰጥቷቸው ተሹመው ነበር። ይህ ድርጅት በጽህፈት ሚኒስትሩ በእነ ጸሐፌ ትዕዛዝ ወ/ጊዮርጊስ ወ/ዮሐንስ ሳይቀር በጥርጣሬና በጥላቻ የሚታይ ነበር። በዚህም ምክንያት ተፈሪ ሻረው ጸሐፌ ትዕዛዙን ጨምሮ በመኳንንቱ ዘንድ በጥሩ ዓይን የሚታዩ ሰው አልነበሩም።
ለስፖርት፣ ሙዚቃ … ፍቅር የነበራቸውና በአንድ ወቅት ለሚኒስቴርነት ሊሾሙ ታጭተው የነበሩት ተፈሪ ሻረው ሹመቱ ቀርቶ በቁም እስር ከቤታቸው እንዲቆዩ ተደረጉ። ከትንሽ ጊዜ በኋላም፣ ከዓይን የራቀ ከልብ ይርቃል (“ካብ ዓይኒ ዝገለለ ካብ ልቢ ገለለ!” በማለት የወቅቱ ጸሐፊና የመረጃ ምንጫችን ይገልፀዋል) በሚለው መሰረት፣ ከተከታይና ደጋፊዎቻቸው ይለያዩ ዘንድ በአምባሳደርነት ወደ ስዊድን ተላኩ።
ስዊድን በአምባሳደርነት በሚሰሩበት ወቅት የ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ሲሞከር ተፈሪ ከመፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች ጎን ቆሙ። “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ጨቋኝ ነው፤ ንጉሡም የአገሪቱን ሀብት ዘርፈው ለግላቸው እያከማቹ ነው” ሲሉም ተናገሩ። (በዚህ ወቅት ደራሲና ተርጓሚ ሳህለሥላሴም እዛ ነበሩና ይህንኑ የአምባሳደሩን ሃሳብ ይደግፉ እንደ ነበር በአንድ ወቅት ተናግረዋል) በዚህም ምክንያት ከነበሩበት ኃላፊነት እንዲነሱ ተደረገ።
ተፈሪና የአንበሳ አውቶቡስ
በ1940ዎቹ (በመስከረም ወር) በንጉሳዊ ቤተሰቦች ሽርክና የአዲስ አበባ ከተማ ”አንበሳ አውቶቡስ ድርጅት” ተቋቋመ። አንበሳ አውቶቡስ መጀመሪያ ሲቋቋም የአውቶቡሶቹ ቀለም አረንጓዴ ነበር፤ ከዚያ አረንጓዴ ቢጫ ሆነ። አሁን ያለውን የአንበሳ የከተማ ባስ ቀለማት (ቀይ እና ቢጫው) የተከሉት ተፈሪ ሻረው ናቸው። (ከላይ ስለ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ አርማ ቀለም ያነሳነውን ያስታውሷል።)
ድጋፍና ትብብር
በሙያቸው በውትድርናው መስክ እስከ ሻለቃ ማእረግ የደረሱትና አሳዳሚ ናቸው በሚል ምክንያት ወደ ሲቪል እንዲቀየሩ የተደረጉት አቶ ተፈሪ ሻረው በማሕበራዊ አገልግሎት (በጎ አድራጎት) ዘርፍም በብዙዎች የሚታወቁ ሲሆን፤ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ነዳያንን ገንዘባቸው እስኪያልቅ የሚለግሱ፣ ለደሀ አዛኝ፣ በመሀል ፒያሳ የሚገኙ ሙዚቀኞችንና ባንዶችን ከማበረታታት ባለፈ በገንዘብ የሚደግፉ፣ ወጣቶችን ለስራ የሚያነሳሱና የሚያበረታቱ፣ በስፖርቱም ዘርፍ (ከላይ ይመልከቱ) እንዲሁ የሚያደርጉ …. ሰው ናቸው። በባህሪያቸውም ቁጡነትንና ሩህሩህነትን አጣምረው የያዙ መሆናቸው ይነገርላቸዋል።
ተፈሪና ስደት
በስዊድን ከአምባሳደርነታቸው ከተነሱ በኋላ ለ16 ዓመታት (14 የሚሉም አሉ) ወደ አገር ቤት ሳይመለሱ እዛው ስዊድን አገር ቆዩ። ደርግ ሥልጣን ከያዘ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ወደ አገራቸው ተመለሱ። ብዙም ሳይቆዩ በ1970 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ከላይ በመግቢያችን ስለ አቶ ተፈሪ ሻረው ብዙም መረጃ እንዳላገኘን ጠቅሰናል። በወጉ የሰነደ ቀርቶ የጋዜጣ ላይ ጽሑፎችን እንኳን ማግኘት አልተቻለም። ይሁን እንጂ በቋንቋ ክፍተት ምክንያት ባልተረዳነው (የተወሰነውን በመተርጎም የተባበረንን የትግርኛ ክፍል እናመሰግናለን)፣ ቆየት ካለና ርእሱን ከላይ በጠቀስነው ጽሑፍ ውስጥ የአቶ ተፈሪን ማንነት (ሩህሩህነት፣ እንደስማቸው በሁሉም የሚፈሩ መሆናቸውን …)፤ ከባለቤታቸው ጋር ተከታትለው መሞታቸውን፣ በጎ አድራጊነታቸውን፣ አርአያነታቸውን፣ በተራማጅ አስተሳሰባቸው ምክንያት በባለሥልጣናት የማይወደዱ መሆናቸውን …፤በማለት ስለ አቶ ተፈሪ የሚያብራሩ አንቀፆች መኖራቸውን መጠቆም እንፈልጋለን።
በመጨረሻም፣ የዚህ አምድ ዐብይ ዓላማ ለአገርና ወገን መልካም ሰርተው ያለፉትን ማስታወስ ነው። በመሆኑም ዛሬ በተማረው የሕብረተሰብ ክፍል ሳይቀር ተጽዕኖ ፈጣሪውን፣ በማሕበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ከፍተኛ ተሳትፎና አስተዋፅኦ የሚያደርጉትን …፤ በእናታቸው ከዓድዋ፣ በአባታቸው ከወልቃይት አካባቢ የተወለዱትን አቶ ተፈሪ ሻረውንና ስራዎቻቸውን፤ እንዲሁም አስተዋፅኦዎቻቸውን አንስተናል። ይህ ስለ ባለውለታችን በቂ ነው ማለት ባንችልም። በመሆኑም ወደ ፊት ለሚደረጉ ጥረትና ጥናቶች አጋዥ እንደሚሆን ግን መጠራጠር አይቻልም። ቢያንስ መነሻ ስለመሆኑ ደፍሮ መናገር ይቻላልና እንጠቀምባቸው። ሰላም!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2015