የወንዶች ጸጉር እንክብካቤና ቁርጥ ቀድሞ በቤተመንግስትና በከፍተኛ ባለስልጣናት እንደተጀመረ ይነገራል፡፡ ነገስታትና የነገስታት ልጆች ጸጉራቸውን በተለየ መልኩ አሳምረውና አበጅተው ህዝብ ፊት ይቀርቡ እንደነበርም የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ይህ የጸጉር ቁርጥ ልምድም ቀስ በቀስ ከቤተ መንግስት በመውጣት ወደ ማህበረሰብ ወርዶ በርካቶች ዘንድ ደርሷል፡፡
በተለይ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃና 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በተለያየ አይነትና ምርጫ በተለይ ወንዶች ረገድ በስፊው ታይቷል፡፡ ወንዶች ጸጉራቸውን ተስተካክለውና አስተካክለው ውበትን ተላብሰው መታየት ጀምረዋል፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ላይ ወታደሮች ይቆረጡት የነበረው የጸጉር ቁርጥም ለብዙ ዓመታት የበርካታ ወንዶች ምርጫ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ዛሬ ላይ ፋሽን መልከ ብዙ ሆኗል፡፡ የወንዶችን የጸጉር ቁርጥ ዘመኑ ባፈራቸው መሳሪያዎች ታግዞ ማስዋብ ቀላል ሆኗል፡፡ ወንዶችም ጸጉር መድመቂያና ውበት መሆኑን ተገንዝበዋል፡፡ ለጸጉር አቆራረጣቸውም ልዩ ትኩረት መስጠት ጀምረዋል፡፡
በርካቶችም ከዘመንና ወቅት ጋር፣ለበዓላትና ለአዘቦት ቀን ለተለያየ ጊዜና ቦታም ሁኔታው የሚፈቅደውና እንዳሉበት ስፍራ የተለመደ መልክና ቀለም ያለው የጸጉር አቆራረጥ ‹‹ስታይል” ምርጫቸው ሲያደርጉ እያስተዋልን እንገኛለን፡፡
,ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት በራሳቸው የጸጉር አሰራር ፋሽን ሲከተሉ ኖረዋል፡፡ ጥንት ወጣቶች ጸጉራቸውን አጎፍረው አንዳንዴም ሹሩባ ተሰርተው ይታዩ ነበር፡፡ የህፃናትና ታዳጊዎች ቁንጮ እንዲሁም የነገስታቱ ሹሩቧም ለዚህ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ዛሬ ላይ በየመንደሩ በዘመናዊ መልክ እየተለመዱ የመጡ የጸጉር አሰራር ፋሽኖች፤ ትላንት ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ይዋቡባቸው ከነበሩት የጸጉር አሰራሮች ጋር እጅጉን የተቀራረበ መሆኑን ማየት ይችላል፡፡ለዚህም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ዛሬም ድረስ ሳይቋረጡ ያሉት የጸጉር ማስዋብና እንክብካቤዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ለዘመናት የአፋር ወንዶች ጸጉራቸው በተለያየ ዕፅዋት በመንከባከብ በመጠቅለልና ወዛማና አንፀባራቂ እንዲሆን የማድረግ ጥበብ ዛሬም ድረስ ከተሜዎች መጠነኛ ለውጥ በማድረግ በፋሽንነት ይተገብሩታል፡፡
አሁን ላይ ለጸጉራቸው ልዩ ትኩረት የሰጡት ወንዶች ጸጉራቸውን ዘመኑ ባፈራቸው የተለያዩ ማሽኖችና የጸጉር ቁርጥ መስሪያ ቁሳቁሶች በመታገዝ በውበት ባለሙያዎች ወይም የጸጉር አስተካካዮች ይዋባሉ፡፡ ወንዶቹ ከሌሎች ተመልክተው አልያም ጸጉር ቤት ገብተው የሚፈልጉትን የጸጉር አስተካካይ ለባለሙያዎቹ በመንገር ይዋባሉ፡፡
ሰይድ አክመል ይባላል፡፡ደንበኞቹን በፈለጉት እና ወቅቱ ባመጣቸው መሳሪያዎች በመጠቀም ላለፉት 4 ዓመታት በጸጉር አስተካካይነት ሙያ እየሰራ ይገኛል። በሙያው በቆየባቸው ዓመታትም በየወቅቱ የተለያየ ፋሽን ያላቸው የጸጉር ቁርጦች ቢኖሩም በአብዛኛው በወንዶች ዘንድ የሚመረጠው የፀጉር ቁርጥ ግን ተመሳሳይ መሆኑን ይናገራል፡፡
የጸጉር ቁርጥ አይነቶቹ በእድሜ እና በሰዎቹ ፍላጎት የሚወሰን መሆኑን የሚናገረው ሰይድ፤ በተለይ ህጻናቱ በራሳቸው ምርጫ የሚስተካከሉት አልፎ አልፎ ቢሆንም በአብዛኛው ግን በወላጆቻቸው ምርጫ ላይ ተመስርተው መሆኑንም ይገልፃል፡፡ ብዙዎች በተለይ በእድሜ ገፋ ያሉት አንድ ቁጥር ወይም ኖርማል የተሰኘው ቁርጥ እንደሚመርጡ ይናገራል፡፡
እንደ ሰይድ ገለፃ፣ በበርካታ ወጣቶች ዘንድ እንደ ፋሽንነት የሚወሰደውና የሚወደደው ‹‹ፍሪዝ›› የሚባለው አይነት ነው፡፡ ከስር ዙሪያውን ምልጥ ተደርጎ ወይም በጣም በአጭሩ ተቆርጦ ከፍ እያለ ሲሄድ ጥቁረቱ እየጨመረ ሙሉ በሙሉ በመተውና ቀንሶ በማስተካከል ብቻ በተለያዩ ቅባቶች ጸጉሩን መጠቅለል (መፈረዝ) ነው፡፡
ሰይድ፣ከፍሪዝ ባሻገር አዲስና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተመለከቱትን የጸጉር ቁርጥ አይነት ምርጫቻቸው የሆነ ደንበኞችም አሉት፡፡ከተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችና ድረ ገጾች በተመለከቱት የጸጉር ቁርጥ መስተካከልም እየተለመደ መቷል፡፡ በተለይ ቅርፆችና ምስሎች በጸጉራቸው ላይ በተለየ መልኩ እንዲሳልላቸው ወይም በልዩ ሁኔታ እንዲሰራላቸው የሚፈልጉም በርካታ መሆናቸው ናቸው፡፡
በተለያዩ ፀጉር ማስተካከያ ቤቶች ውስጥም በፎቶግራፍ በተደገደ መልኩ የጸጉር ቁርጦች ስታየል በ‹‹ሜኖ›› መልክ ይሰቀላል፡፡ሰይድ እንደሚያስረዳው፣ የጸጉር ቁርጦቹ አይነትና እና ስያሜ ከቦታ ቦታ እንዲሁም ከቤት ቤት ይለያያል፡፡
ከዋና ዋናዎቹ የጸጉር ቁርጥ አይነቶች መካከልም ፓንክ (በወጣቶች የሚመረጥ)፣ የላኛው የጸጉር ክፍል ሳይነካ ከስር ብቻ ማስተካከልና ቅርጹን ማስተካከል(ፍሪዝ)፣ዜሮ በአንድ ቁጥርና በሁለት ቁጥር(የማስተካከያ ማሽን ጥርሶች ናቸው) መካከለኛ አጭር ቁርጥ፣ አፍሮ(ቀደም ሲል በብዛት የነበረና አሁንም አልፎ አልፎ ያለ)፣ ጆንትራ ቮልታ፣ ባላቶሊ የተለመዱና ጎልተው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
‹‹የወንዶች ጸጉር ቁርጥ በዘመናት ሂደት ውስጥ እየተለዋወጠ አንዴ ፋሽን ሆኖ ቆይቶ እየጠፋ መልሶ ከመጠነኛ ለውጥ ጋር የሚመጣ ነው የሚለው››ባለሙያው፣አንድ የጸጉር ቁርጥ አይነት ለበርካታ አመታት ፋሽን ሆኖ ሊቆይ እንደሚችልና የሴቶቹን ያህል በዘመን ሂደት ውስጥ የጎላ ለውጥ ሲኖረው እንደማይታይም ይጠቅሳል፡፡
ሰይድ እንደሚያስረዳው፣ወንዶች የሚቆረጡት የጸጉር ቁርጥ እንደ እድሜያቸው ምርጫቸውም የተለያየ ነው፡፡በየጊዜው የሚለመዱ የጸጉር ቆረጣ ስልቶች ወይም ፋሽኖች በአብዛኛው በወጣቱ ዘንድ ይዘወተራሉ፡፡ እድሜያቸው ከፍ ያሉትና በአነስተኛ የእድሜ ደረጃ የሚገኙ ወንዶች በአንፃሩ የተለመደና ብዙም ወጣ ያላለ አቆራረጥን ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡
የጸጉር አቆራረጥ ስልቶች በእድሜ እንደሚለያይ ሁሉ ወቅት ወይም ክረምትና በጋን መሰረት አድርጎም ሊመረጥ ወይም ሊወሰን ይችላል፡፡ክረምት ላይ አሳጥሮ መቁረጥ ይቀንሳል፡፡ከዚህ ይልቅ ጸጉር ባለበት መንከባከብና ቅርጹን ማስተካከል በብዙዎች ይዘወተራል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በጋ ላይ አሳጥሮ በተለያየ ቅርጽ መሰራትን ብዙዎች ያዘወትራሉ፡፡ይህም የብርድና የሙቀት ወቅት መሆን የሚፈጥረው ምርጫ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ውስጥ የወንዶች የውበት ሳሎኖች ውስጥ የፀጉር ቁርጥ ዋጋ ከ40 ብር እስከ 300 ብር ይገኛል፡፡ ለዋጋው መለያየትም እንደየ ቤቱ የፀጉር ማስተካከያ መሳሪያዎች ጥራት፣ የውበት ሳሎኖቹ የሚገኙባቸው ቦታና የፀጉር አስተካካዮች ልምድ መሰረት ያደረገ እንደሆነም መረዳት ይቻላል፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2015