ስፔናዊው የታሪክ ተመራማሪ ስፔኖዛም ‹‹ሰላም ከጤናማ አዕምሮ የሚፈልቅ ምንጭ ነው›› ይለዋል፡፡ በርግጥም ሰላም ከጤነኛ አዕምሮ ወይም ክፋት ካላሸነፈው ቅን አዕምሮ የሚመነጭ አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ ቅን አስተሳሰብ ከምንጩ ኮለል ብሎ ይፈስ ዘንድ ደግሞ ሁላችንም ኃላፊነታችን እልፍ ነው።
ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሰዎች ሲገናኙ ቅድሚያ ስለ ሰላማቸው የሚጠያየቁት፡፡ ጠዋት ከእንቅላፋቸው ተነስተው «በሰላም አውለኝ»፤ ማታ «በሰላም ያዋልከኝ በሰላም አሳድረኝ» ብለው ምስጋናቸውን የሚገልጹትም የሰላምን ትልቅ ዋጋ በመረዳታቸው ነው፡፡ ሁሉም ሰው ሰላም በህይወቱ ላይ ትልቅ ውድ ዋጋ ያለው ነገር መሆኑን ይገነዘባል፤ ለሰላምም ዘብ ይቆማል፡፡
በአንፃሩ ደግሞ ሰላም ለማደፍረስ የሚተጉ አይጠፉም፡፡ በእነዚህ ዓይነት ሰዎች የተነሳ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ ህዝቦች ሰላምና መረጋጋት እንዲርቃቸውና በአንጻሩ ጦርነት፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ ሽብርተኝነትና ወንጀል ተንሰራፍተው የሰዎችን ዕለታዊ ኑሮ እንዲታወክ ምክንያት ሆነዋል፡፡
በዓለማችን በሰላም እጦት ምክንያት የሚሊዮኖች ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ተከስቷል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰላም እጦት ምክንያት በየዓመቱ 13 ነጥብ 6 ትሪሊየን ዶላር ኪሳራ እየደረሰ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሶሪያ፣ የመን፣ ኢራቅና ደቡብ ሱዳን በሰላም እጦት ምክንያት እየተናጡ ከሚገኙ ሀገራት ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ በተለይም ሶሪያና የመን በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል፡፡
ዓለማችን በሰላም እጦት ሳቢያ ዳግም እንዳያገግሙ ሆነው የፈራረሱትን ከተሞች በውስጧ ይዛ ትውልድ ይማርባቸው ዘንድ ማሳያ አድርጋቸዋለች፡፡ በሰላም እጦት ሳቢያ የሚደርሰውን ሰብዓዊ ጉዳት ለመረዳት እሩቅ ሳንሄድ የኛው ወገኖች ለስደት መሸጋገሪያ አድርገው ይጓዙባት የነበረችው የመንን ማሰብ በቂ ነው፡፡ የመናውያን በፈራረሰችው ሀገራቸው ትቢያ ስር ተቀብረው ታሪክ በዘግናኝነቱ የከተበውን ጦርነት ለታሪክ ፀሐፊያንና ነጋሪዎች አሳልፈው ሰጥተዋል።
ሶርያዊያን ከሚወዷት ከተማቸው ፍርስራሽ ስር ፈራርሰው የቀሩትን ዘመዶቻቸውን ከማስታወስና ከማዘን ይልቅ ጀርባቸውን ለሀገራቸው ሰጥተው ስደትን ብቸኛው አማራጭ አድርገዋል፡፡ በመድፍ አረር ከመዳፈን የተረፉትም ቢሆኑ በራሳቸው ላይ ፈርደው እግሬ አውጪኝ ብለው የተሰደዱትን በርሃው ይቁጠራቸው፡፡ በፈጣሪ ድጋፍ የመነመነች ህይወታቸውን ብቻ ይዘው የተሰደዱትም ቢሆኑ ነፍሳቸውን ለማቆየት ብቻ የሰው ፊት እየገረፋቸው እጃቸውን ለልመና ዘርግተዋል፡፡ በሀገራችን ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ የዕርዳታ እጃቸውን የዘረጉ ሶርያዊያንን ማየት የጦርነትን አስከፊነት ለማሠተዋል በቂ አብነት ነው፡፡ ብልህ ከሌሎች ጉዳት ይማራል የሚባለውም ለዚሁ አይደል።
ሁላችንም በሰላም መደፍረስ የሚፈጠረውን ጉዳት ከማንም በላይ እንረዳዋለን። አሁን ሰላምን ለማስከበር የምንደራደርበት ጊዜም አይደለም፡፡ ህልውናችን በሙሉ በሰላማችን ውስጥ ነው ያለው፡፡ ሰላም ዋጋው እጅግ ብዙና በቁጥር የማይሰፈር በመሆኑ መንግሥት የሰላም ሚኒስቴርን አቋቁሞ ስለሰላም እየዘመረ፣ ስለሰላም እየሰበከ፣ ለሰላም ዘብ እንደ ቆመ የሚያመላክቱ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሰላምን ፋይዳ አግዝፈው በሚያሳዩ ሁነቶችና ሰላምን የሚያውኩ አስተሳሰቦችን ቀድሞ በመመከት ረገድ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ጅምር የአንድ ወቅት ሁነት ሳይሆን ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ላይ ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር «ኪነጥበብ ለሰላም» በሚል መሪ ሃሳብ የተከናወነው ሀገር አቀፍ ውይይት ተገቢ እንደነበር ለመረዳት ይቻላል፡፡ ኪነ ጥበብና ሰላም ድንበር የለሽ ህዝባዊ ትስስር አላቸው፡፡ የኪነ ጥበብ ሰዎች የጋራ መግባቢያ ቋንቋ አላቸው፡፡ ኪነ ጥበብ በጋራ ያግባባል፤ በጋራ ያኖራል፤ ያስተዋውቃል፡፡ ምክንያቱም ኪነ ጥበብ ድንበር የለውምና፡፡
የኪነ ጥበብ ሰው ስለ ሰላም መሪ መሆን አለበት፡፡ ከያኒ ስለሰላም ማነሳሳት አለበት፡፡ ኪነ ጥበብ ከመንግሥት ኃይል በላይ የሆነ ጉልበት አለው፡፡ ግጭት ቢነሳ መንግሥታት ግጭቱን ማስቆም ይችሉ ይሆናል፤ ኪነ ጥበብ ግን ግጭቱ እንዳይነሳ ማድረግ ይችላል፡፡ መንግሥታት ግጭቶችን በኃይል ሊያስቆሙ ይችላሉ ፤ ኪነ ጥበብ ግን በአስተሳሰብ ለውጥ ነው ሰላምን ሊያመጣ የሚችለው፡፡
የጥበብ ሰዎች ሰላምን ከአየር ጋር ያመሳስሉታል፡፡ ያለ አየር መኖር አይቻልም፤ ግን የአየርን ጥቅም የምናውቀው ስናጣው ብቻ ነው፡፡ አየርን እየተጠቀምን ጠፍቶ ካላየነው በስተቀር በአየር የምንኖር ሁሉ አይመስለንም። ሰላምም እንደዚያው ነው፡፡ ሰላም ትዝ የሚለን ሰላም ሲጠፋ በሚያጋጥመን ችግር ነው፡፡ መንግሥትም የጥበብ ሰዎችን ችግር ሲከሰትና ሰላም ሲደፈርስ ስለ ሰላም እንዲሰብኩ ከመቀስቀስ ይልቅ ቀድሞ አስተሳሰብ ላይ እንዲሠሩ ሊደግፋቸው ይገባል፡፡ ኪነጥበብ ስለሰላም ልትጮህ፣ ስለሰላም ልትዘምር፤ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ስለሰላም ድምፃቸውን ከፍ አድረገው ሊያስተጋቡ ይገባል፡፡