የኢሬቻ በዓል ከገዳ ሥርዓት ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው ይገለጻል።ገዳ ደግሞ ለኦሮሞ ማኅበረሰብ ምን እንደሆነ መናገር ለቀባሪው እንደማርዳት ነው።እናም በዚህ ውስጥ ሆኖ ብዙዎችን ያስተሳሰረው ኢሬቻ ለኦሮሞ ማህበረሰብ ብዙ ነገሩ ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል።ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ በሁለት ቦታዎች ላይ በድምቀት የሚከበር በዓል ሆኗል።ክብረበዓሉ ከመስቀል በዓል በኋላ ባሉት ቅዳሜ እና እሁድ የሚከበር ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ፤ በቢሾፍቱ ከተማ ደግሞ ሆራ ሃር-ሰዲ እየተባለም ይከበራል።
ኢሬቻ በዚህ ውስጥ ግን በርካታ መሰናክሎችን ያሳለፈ የአደባባይ በዓል ነው።ማለትም በ2008 ዓ.ም ብዙዎችን ለሞት የዳረገ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ሆኖም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአሉ በደመቀ ሁኔታ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡የእርስ በእርስ ትስስርን ከማጎልበቱም በላይ ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር በኩልም በዓሉ የራሱን በጎ ጎን እያሳረፈ ይገኛል፡፡
ይህ አኩሪ በዓል ለራሳቸው የፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል የተለያዩ ወገኖች ቢሞክሩም ኢሬቻ በየአመቱ እየደመቀና እየጎመራ ህዝብ በአል በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ወጣቶችም በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሲወጡ እየተስተዋሉ ነው፡፡የዘንድረውም የኢሬቻ በአለም ባህላዊ ትርፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ወጣቶች እያደረጉት ያለውን ጥረት ምን መልክ እንዳለው ከኦሮምያ ክልል የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እንዲሁም የኦሮምያ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ከድር እንዳልካቸው ጋር ቆይታ አድርገናል።እርሳቸው ያሉንንም እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ኢሬቻ ማለት ምን ማለት ነው፤ አገራዊ አንድምታውስ ምንን ያመላክታል?
አቶ ከድር፡- ኢሬቻ እንደ ኦሮሞ ማህበረሰብ በርካታ ትርጉሞች የሚሰጡት በዓል ነው።ለአብነት ኢሬቻ የምስጋና በዓል ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ምድር እና ሰማይን ለፈጠረው ፈጣሪው ዋቃ ምስጋናውን ለማድረስ የሚጠቀምበት ነው።ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም መሸጋገራቸው ነው።ከጨላማው ማለትም ከክረምቱ ወደ በጋው ወይም ብርሃኑ በመሻገራቸው በዓሉን መሰረት አድርገው አምላካቸውን ያመሰግኑበታል።
ኢሬቻ ማለት ዋቃ (ፈጣሪ) የፈጠረውን ማመስገን እንደማለትም ይወሰዳል።ስለዚህም ይህንን በዓል እድሜ ገደብ ሳይኖር፣ መልክና ቁመና ሳይወስን ፤ የገንዘብ መጠን ልዩነት ሳይደረግበት፤ ባለስልጣኑ ከተገዢው ሳይለይ ሁሉም በእኩል ደረጃ የሚያከብረውና ለአምላኩ ምስጋና የሚያቀርብበት ነው።
በሌላ በኩል ኢሬቻ የዘመን መለወጫ በዓልም ተደርጎ ይወሰዳል።የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በማለፉ በኢሬቻ ቀን ይደሰታል።ምክንያቱም በክረምት ወራት ተራርቆ ሳይገናኝ የቆየ ዘመድ አዝማድ መስከረምን አሳቦ ይገናኛል። ሕዝቡም ክረምቱን ስላሳለፍክልንና አዲስ ዘመንን ስለሰጠኸን እናመሰግንሃለን ይሉበታል።
ኢሬቻ የሰላም እና እርቅ ቀንም ነው።የኦሮሞ ሕዝብ ፈጣሪውን እያመሰገነ ለመላው የሰው ልጅ ሰላምና ደኅንነት ከፈጣሪው ይለምንበታል።ልመና ደግሞ የሚከናወነው በንጹህ ልብ በመሆኑ በወቅቱ የተጣላ መታረቁ ግድ ነው። ሰላም ማውረድ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው።እናም ተበዳይ ሳይቀር ቂሙን ትቶ በነጻ ልቦና ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ዕለት ነው።
አንዳንዶች ደግሞ ኢሬቻ ማለት መስማማት፣ አንድነት፣ እርቅ ማለት ነው ይሉታል። ይህ ምሳሌነቱ ደግሞ አገራዊ አንድምታውን በሚገባ ያሳየናል።ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት ተስማምቶና ተግባብቶ መኖር ነው፤ ኢትዮጵያዊነት አብሮ መብላትና ተሰባስቦ መደሰት ነው።ኢትዮጵያዊነት ይቅር ባይነት፤ በፍቅር መኖርም ነው።ያለው የሌለውን ደግሞ የሚያሻግርበት፤ ችግርን በአብሮነት ለመፍታት የሚረባረብበትም ነው።ስለዚህም የኢሬቻን አገራዊ አንድምታ በዚህ ውስጥ እንመለከተዋለን ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢሬቻን ባህላዊ ነው፤ መንፈሳዊም ነው፤ ኑሮም ይሆናል ይባላል።ምክንያቱ ምንድነው?
አቶ ከድር፡- ምክንያቱ በአንድ ነገር ብቻ የሚገለጽ አይደለም።በስርዓትና በአተገባበር ጭምር የሚብራራ ነው።ለአብነት ኢሬቻ የምስጋና ቀን ነው ስንል መንፈሳዊነቱን በደንብ ያሳየናል። ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ራሳቸውን የማይገዙ ሰዎች በኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ ይታረማሉ።ምክንያቱም ወደቦታው ለማምራትና አምላካቸውን ለመለመን ሲያስቡ የተጣሉትን ይታረቃሉ፤ ክፉ መንፈሳቸውን አራግፈው ንጹህ ልቦናቸውን ይዘው ይመጣሉ።
ወደ ባህላዊነቱ ስንመጣ ደግሞ ኢትዮጵያዊነቱ ከቡና አፈላሉ ይጀምራል።አዲስ የደረሰ የባቄላና የአተር እሸት ተቆልቶ ለቡና ቁርስ ይቀርብበታል። የኦኮሌ ስርአት ማለትም ለመጀመሪያ ጊዜ የወለዱ ከብቶችን ለመመረቅ የሚከበር ስርአትም በዚህ ውስጥ ይከናወናል።ጊደሮች ወተታቸው ተጠራቅሞ፣ ግማሹ ተንጦ፣ ቅቤው ወጥቶ፣ ግማሹ እርጎ፣ ግማሹ አይብ ተደርጎ ቅንጬ ተሰርቶ፣ ዘመድአዝማድ ተሰብስቦ ከተመረቀ በኋላ ይበላል።.በዚህ ውስጥ ደግሞ መሰባሰቡ፣ ደስታን መጋራቱ፣ አዲስ ሰብልና ወላድ መመስገኑ፤ መልካሙን ነገር አብሮ መጋራቱ በሙሉ ባህል ነው።
ኢሬቻ ማለት ማምለክ እና ማመስገን ማለት ነው የሚሉም አሉ።ይሄን ስላደረግህልኝ፣ ከክረምት ወደ በጋ (ብራ) ስላሸጋገርከኝ አመሠግናለሁ እየተባለ ፈጣሪ የሚመሰገንበት ነው።ኢሬቻ ሠፊ አገልግሎቶች አሉት።መነሻውም በጣም የራቀ ነው።ለአብነት በእርጥብ ሣር ይወከላል።ይህ ማለት ደግሞ ኢሬቻ የልምላሜ ነጸብራቅ ነው።ለጋብቻ ጥያቄ ሳይቀር እርጥብ ሣር ለአገልግሎት የሚውለው ለዚህ ነው።
ሌላው ኢሬቻ የምትለዋ ቃል የምትወክለው ሣር ወይም አበባን እንደሆነም ይነገራል።ምክንያቱ ደግሞ መልካም ነገር አብሳሪነትን የሚያስረዳ ነው።በኦሮሞ ባህል እርጥብ ሳር የያዘ ሰው ኢሬቻ የሚሄድ ሰው ነው።ለጋብቻ የሚጠይቅ ሰው ሳይቀር እርጥብ ሳር የሚይዘውም ከዚህ የተነሳ ነው።ስለዚህም ይህም ባህል ነው።እድምተኞቹ “መሬሆ” የሚለውን የምስጋና መዝሙር በአንድነት እያሠሙ ለአምላካቸው ምስጋና የሚያቀርቡበትም ሌላው ባህላዊ ክዋኔ ነው።በተመሳሳይ ህዝቡ የፈለገውን ባህላዊ ጭፈራ እየጨፈረ የሚያከብረውም ባህል ነው፡፡
ኢሬቻ ኑሮው ነው ሲባል በሚከበርበት ጊዜ ብቻ ማየት ይቻላል።ሁለት ጊዜ በዓሉን ወዶ ያከብረዋል።የመጀመሪያው መልካ (በውሃ አካል ዳርቻ) የሚከበረው ሲሆን፤ የምስጋና በዓሉም ነው።ለተደረገለት ሁሉ አምላኩን ያመሰግናል።ሁለተኛው በዓመቱ አጋማሽ ላይ የሚከበረው ሲሆን፤ ኢሬቻ ቱሉ (በተራራማ ቦታ) የሚከበረው ነው። ይህ በዓል ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ፈጣሪውን የሚለምንበት ነው። በበጋው የፀሐይ ሃሩር ሰው እና ከብት በሚቃጠልበት ጊዜ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ እንዲዘንብ የኦሮሞ ሕዝብ ወደ ተራራ ወጥቶ ፈጣሪውን ይለምናል። ይህን ተራራ የፈጠርክ ፈጣሪ ወቅቱን የሰላም አድርግልን፣ የሰላም ዝናብ አዝንብልን፣ ጎርፍን ያዝልን፣ የተዘራው ፍሬ እንዲያፈራ እንለምንሃለን” ይላል።ይህንን ተከትሎም ኢሬቻ ባህላዊ ነው፤ መንፈሳዊ ነው አለያም ኑሮው ነው እንዲባል አስችሎታል።
አዲስ ዘመን፡- ኢሬቻ ለኦሮሞ ምኑ ነው?
አቶ ከድር፡- ኢሬቻ ለኦሮሞ ሕዝብ የሰላም ምልክቱ ነው።አምላኩን ማመስገኛው፤ ከአገሬው ሰው ጋር መገናኛው፣ ደስታውን መግለጫው፤ ቂምና በቀልን መርሻው፣ በአዲስ ተስፋ ቀጣዩን ዘመን መመልከቻው በአጠቃላይ ተስፋውን ለማለምለም የሚነሳበት በዓሉ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አኳያ ኢሬቻ በኦሮሞ ወጣቶች ዘንድ እንዴት ይታያል?
አቶ ከድር፡- ከወጣቶች ምልከታ አንጻር ኢሬቻን በብዙ በኩል መተንተን ይቻላል።ከገዳ አንጻር ብቻ ብናነሳው በርካታ ባህላዊና ትውፊታዊ የሆነ መልዕክትን ያዘለ ነው።ማለትም በየደረጃው የተለየ ተልዕኮ አለውና በዚያ ውስጥ የሚማራቸውን ነገሮች የሚተገብርበት በዓል ነው።ለምሳሌ ፎሌነቱ የእድሜ እርከኑን ብቻ ሳይሆን አብሮ የሚሰጠው ተልዕኮም አለው።ኢሬቻም እንዲሁ ከዚህ የተቀዳ ነገር ስለሆነ ብዙ ነገር እንደሚሰጠው ያውቃል።እናም ኢሬቻ በወጣቱ ዘንድ የሚታየው ራስን መግዢያው፤ እርቅን ማበልጸጊያው፤ ባህሉን ማጎልበቻው፤ አዲስ ተስፋውን ማያው፤ አምላኩን ማክበሪያው ነው።
ከዚያ ባሻገር ወጣቱ ለኢሬቻ ሲወጣ ነጻና በፍቅር ተሞልቶ ስለሚሆን በዓሉን የአንድነት፣ የመቻቻልና የሰላም ተምሳሌት እንደሆነ ያራጋግጣል።ሌላው ኢትዮጵያዊነቱን የሚያይበት መድረክም ስለሆነ አብዝቶ አገሩን እንዲወድ የማድረጊያ በዓል እንደሆነም ያስባል።የማህበረሰቡ አንድ አካል በመሆኑ ማህበረሰቡ የሚሰማውን ሁሉ ያደርጋል፤ ይኖርበታልምም።የሚሰማውም ይኸው አይነት ስሜት ነው።ምልከታውም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም።አውራ በዓሉ አድርጎት ያከብረዋል፤ ያስቀጥለዋልም።
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት መራሹ ስርዓት በኦሮሞ ህዝብ ላይ ሲያደርሳቸው የነበሩ ግፎችና በደሎች እንዴት ይታወሳሉ?
አቶ ከድር፡- ይህንን በቃላት መግለጽ እጅግ ከባድ ነው።ምክንያቱም ህወሓት በሰው ልጅ ላይ ቁማር የሚጫወት ጨካኝ ቡድን ነው።ፖለቲካ ጥቅሙን እንጂ ማንንም የማያስቀድምም ነው።በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ያደረሰው በደልም በዚህ ደረጃ የሚገለጽ ነው።ሥራው አገር ማፍረስ ስለሆነም ባህልን ሲያጠለሽ፣ የተሳሳቱ ትርክቶችን ሲያሰፋና ሕዝብን ከሕዝብ ፣ማህበረሰብን ከማህበረሰብ ሲያጋጭ ኖሯል።አሁንም ከድርጊቱ አልተቆጠበም።ተደጋጋሚ ጦርነቶችን የምናየውም በዚህ ምክንያት ነው።በአጠቃላይ እርሱ ሰላም ጠል ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በ2008 ዓ.ም በቢሾፍቱ በነበረው ኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ በነበረው የኢህአዴግ ስርዓት አማካኝነት በርካታ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።ያን አሰቃቂ ጊዜ እንዴት ያስታውሱታል?
አቶ ከድር፡– በሌሎች አገሮች አይደለም እንደዚህ አይነት መልካም ነገር መስበኪያ በዓላት የሌላቸውን እንኳን ፈጥረው ለሌሎች ለማሳወቅ ይጥራሉ።የሌላቸውን ታሪክ ታሪክ አለን በማለትም ገንዘብ ያደርጉታል።እኛ ጋር ግን እነዚህ በዓላት የጸብ ምንጭ ሲሆኑ ይስተዋላሉ።ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አንድ ነው።ጠላት ማለትም እንደ ህውሓትና ሸኔ አይነቶች ገንዘባቸውን የሚያገኙት ታሪክን በማጥፋት፣ የሕዝብን ሰላም በማደፍረስ ነው።ስለዚህም መልካሙን በዓሎቻችንን ለራሳቸው ጥቅም ያውሉታል።ብጥብጥ አስነስተውም ይህንን አድርገናል ይሉበታል።የ2008ቱም የሆነው ይኸው ነው።
የኦሮሞን ሕዝብ ተሰባስቦ በዓሉን በሰላም እንዳያከብር የመስበርና የማሸማቀቅ ሥራ ለመሥራት ሞክሯል።ግን ሕዝቡ በቀላሉ የሚሰበር አይደለም፤ የሚሸማቀቅም እንዲሁ።ብዙ መሰዋዕትነት ቢከፈልም ኢሬቻ በደመቀ መልኩ እንዲከበር አድርጎታል እንጂ።
ሕወሓትም ሆነ ኦነግ ሸኔ አሁንም ይተኛሉ ተብሎ አይታመንም።መሞከራቸው አይቀርም።ነገር ግን መቼም አይሳካላቸውም።በዓሉን ለማጠልሸት እንደ ገቢ ምንጭ እድሉ እንዲጠቀምበት ማንም አይፈቅድለትም።ምክንያቱም በሥራቸው ዛሬ ሁሉም አውቋቸዋል፤ ነቅቶባቸዋልም።ስለዚህም ነቅቶ እንደሚጠብቃቸው እርግጠኛ ነኝ።በተለይም የኦሮሞ ሕዝብ ይህንን እንዲያሳካ መቼም አይፈቅድለትም።ወጣቱም ቢሆን በዚህ ደረጃ ተዘጋጅቷል።ሰላምን ለማይፈልግ ሰው ማንም ቦታ አይሰጠውም።
አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ስቃይና መከራ ሲዘሩ የነበሩ ሰዎች አሁን የኦሮሞ ህዝብ ጠበቃ ሆነው ቀርበዋል፡፡ለእነዚህ አካላት የምታስተላልፈው መልዕክት ምንድን ነው?
አቶ ከድር፡- የሀሰት ፕሮፓጋንዳው ገና ከመስቀል በፊት የጀመረ ነው።ይህ ደግሞ የአደባባይ በዓላትን የማጠልሸትና እንዳይከበሩ ማድረግ ላይ ያተኮረ ነው። ነገር ግን የመስቀል በዓል ምንም አይነት ችግር ሳይፈጠርበት በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በኦሮምያ ክልል ጭምር በመጡ ወጣቶች ሥራ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሆኗል።ኢሬቻም ይህንኑ አይነት አከባበር ይኖረዋል።ይሁን እንጂ የማህበረሰቡ ርብርብ ግድ ያስፈልገዋል።የመጀመሪያው የሀሰት ወሬዎችን አልሰማም ማለት ሲሆን፤ ሌላው በነቂስ ወጥቶ የበዓሉ ድምቀት መሆን ነው።
ጠላት የሚመጣው አገር ወደድና የኦሮሞ ተቆርቋሪ መስሎ ነው።ይህንን የሚያወጣው ደግሞ አስተባባሪው ብቻ ሳይሆን ምልከታው ሰፊ የሆነው ሕዝብ ነው።ስለዚህም ሁሉም ሰው በመተባበር ይህንን የሰላም ምልክት የሆነ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ሊያደርገው ይገባል።የበአሉ ታዳሚዎች ልዩ እንቅስቃሴዎችን ካዩ ለጸጥታ አካሉ ወይም ለተመረጡት ፎሌዎች ወዲያውኑ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል።የጥፋት ኃይሎችን ሀሳብ ላለማስፈጸም መጣር ይገባልም።ይህንን አይነት ተግባር እንፈጽማለን የሚሉም ቢሆኑ ለማንም የሚጠቅም ተግባር አይደለምና ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል። ኢሬቻ ለፊኒፍኔ ስጋት ሳይሆን ትልቅ የገቢ ምንጭና ውበት ስለሆነ እንደ አገር ጥቅም አስቦ መስራቱ ለሁሉም ሰው ያገለግላል።
አዲስ ዘመን፡- ኢሬቻ በሰላም እንዲጠናቀቅ በኦሮምያ ወጣቶች ማህበር ዘንድ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል።በተለይም ሰላም ከማስከበርና በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከማድረግ አኳያ?
አቶ ከድር፡- ይህ በዓል ሌሎች ክልሎች ብቻ ሳይሆኑ ከጎረቤት አገር ጭምር ሰዎች መጥተው የሚታደሙበት ነው።ሰፊውና ብዙ ሕዝብ ያለበት የኦሮምያ ክልልም ታላቅ በዓሉ ስለሆነ ይታደምበታል።ስለዚህም በርካቶችን ሰብስቦ የሚያወዳጅ በመሆኑ በርካታ በርካታ መስተጋብሮች ይኖራሉ።የመጡ እንግዶችን ጭምር በአግባቡ አስተናግዶ መመለስ ይገባል።ለዚህ ደግሞ አንድ ሺህ ፎሌዎችን መልምለን ተልዕኮ በመስጠት ዝግጅታችንን አጠናቀናል።
ከዚያ ባሻገር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ለመስራትም በእነርሱ በኩል ወጣቶች ተመልምለው ተዘጋጅተዋል።ስለዚህም በዓሉን በሰላም ለማጠናቀቅ በሁለቱም በኩል በቂ ዝግጅት ተደርጓል።ከጸጥታ አካሉ ጋርም በቅርበት ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል።ይህ ደግሞ ቀደም ብሎ በመስቀል በዓልም የታየ ነው።ስለሆነም በኢሬቻም የሚደገም ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ኢሬቻ ሰላም እንደሆነ ማረጋገጥ ያለበት ወጣቱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ከኢሬቻም በኋላ በርካታ በዓላት አሉንና የወጣቶች ሚና በምን መልኩ መታየት አለበት?
አቶ ከድር፡- የአደባባይ በዓላት የገቢ ምንጭ፣ የውበት እና የማንነትን መግለጫ ናቸው።ጥቅሞቻችንን በምን መልኩ እንደምናገኝ የሚያመላክቱ አቅጣጫ ጠቋሚም ናቸው።ስለሆነም ወጣቱ ሊጠቀምባቸው ይገባል።በተለይም አፍላ እድሜ ላይ በመሆኑ የሥራ እድሎችን ጭምር ያይባቸዋል፤ ይሰራባቸውና ይለወጥባቸዋልም።በዚህ ውስጥ ደግሞ አገርን ማስጠራት ጭምርን ያመጣባቸዋል።እናም ጥቅሙ ብዙ ነውና ሁሉም መልካም ጎናቸውን አይቶ ካላቸው በረከት መቋደስ ይገበዋል።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
አቶ ከድር፡- በዓላት የማንም ግለሰብ ወይም ብሔር ብቻ አይደሉም።የሁሉም ሕዝብ ናቸው።ይህንን ማስከበርና ማክበር ያለበትም አካል አንድ አይደለም።ሁሉም ለበዓሉ ስኬታማነትና በሰላም መጠናቀቅ የበኩሉን ማበርከት አለበት።ምክንያቱም ሰላማዊ የሆነ ክብረበዓል ሲኖር ሰውም አገርም ይጠቀማል።ስለዚህም ኢሬቻን ለማክበር ወደቦታው የሚሄደው ብቻ ሳይሆኑ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ያሉ ለበዓሉ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው።ይህንን ካደረጉ ደግሞ ጎንለጎን የሚጠቀሙበትን ነገር ይዘረጋሉ።ለምሳሌ፡- ለበዓሉ የመጣው ታዳሚ በምግብና መሰል ነገሮች የከተማዋን ገቢ ከፍ ማድረግ ይቻላል።እናም ይህ እየታሰበ ለበዓሉ ስኬት ሁሉም በጋራ መሰራት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡ ስለሰጡን ማብራሪያ እጅግ አድረገን እናመሰግናለን።
አቶ ከድር፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2015 ዓ.ም