-ፒተር አብረሃምስ (1919 -2017)
አፓርታይድ እንዲሁ እንዳልተገረሰሰ ይታወቃል። ከልጅ እስካዋቂ፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ … ዋጋ ከፍለውበታል። ሕይወታቸውን ቤዛ ያደረጉትን ቤቱ ይቁጠራቸው እንጂ ሌላ ምንም ማለት አይቻልም።
የዘር አገዛዝ የሆነውን አፓርታይድ (በደቡብ አፍሪካ እስከ 1994 ድረስ የነበረው የዘር ልዩነት ስርዓት) ከስሩ መንግሎ ለመጣል ቀላል አልነበረም። ቀላል አለመሆኑም የሚታወቀው የፈጃቸው መራራ የትግል አመታትና እስካሁንም በወጉ ያልደረቀው የግፍ ስርአቱና የያስከፈለው ዋጋ ነው። ስለ አፓርታይድ (ትርጉሙ ”መለያየት” ማለት ነው) ይህችን ካልን በቂ ሆኖ፤ ለመገርሰሱ ምክንያት ከሆኑት ወደ አንዱ፣ ወደ ዛሬው የመንፈስ እንግዳችን ፒተር አብራሃምስ እንሂድና የተወሰኑ ሃሳቦችን እናንሳ።
ወደ ዋናው ርእሰ ጉዳይ ከመሄዳችን በፊት ግን ጥቂት ስለ አፍሪካ ሥነጽሑፍ እናውራ።
በመሰረቱ የአፍሪካ ሥነጽሑፍ (African Literature) ራሱን ችሎ በመጠናት ላይ ያለ የጥናት መስክ ሲሆን፤ ልክ እንደ ሌሎቹ ሁሉ የራሱ የሆነ ፍልስፍናና አተያይ ያለው መስክ ነው።
ይህ መስክ (በጉዳዩ ላይ ገፋ አድርገው የሄዱትን፣ የዶ/ር መላክነህ መንግሥቱን ስራዎች፣ ለምሳሌ Map of African Literature ይመልከቱ) በርካታ የአፍሪካ ሥነጽሑፋዊ ስራዎችን የሚመለከት ሲሆን፤ አንዱና ዋናውም የደቡብ አፍሪካ ሥነጽሑፍን የሚመለከተው Apartheid Literature (ትርጓሜውም They chronicled or satirized state-enforced racism and explored the possibilities of resistance)፣ የመንግስት መራሹን ዘረኝነትና ዘረኛ ተግባራት የሚሰንድ፣ ዘንዶም ለህዝብ የሚያጋልጥ፣ በተግባራቱም የሚሳለቅ፤ እንዲሁም ከዚህ አስከፊ የዘረኝነት ስርአት መውጫ መንገዶቹና የተቃውሞ ስልተቶቹ ምን ምን እደሆኑ የሚያመላክት ነው።
በመሆኑም፣ የPeter Abrahams ስራዎችንም ከዚሁ አኳያ መገንዘብ ይገባል። የደቡብ አፍሪካዊያን ድምፅ በመባል የሚታወቀውንና በአማረ ማሞ ”እሪ በይ አገሬ” በሚል የተተረጎመውን፣ የአለን ፔተንን ”Cry, the Beloved Country”ንም እዚህ ቦታ ላይ መጥቀስ ግድ ይሆናል። (ከድህረ አፓርታይድ በኋላ የደቡብ አፍሪካ ሥነጽሑፍ ማርሹን ቀይሮ በእርቅና መልሶ ግንባታ ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ጥናቶች እያመላከቱ ነው።)
ስራዎቹን ለመገንዘብ ያግዘን ዘንድ ስለ አፍሪካ ሥነጽሑፍ ይህችን ያህል ካልን፣ ወደ ፒተር እንመለስ። ፒተር አብረሀምስ ይባላል። ማርች 3 1919 ነው የተወለደው። ሙሉ ስሙ Peter Henry Abrahams (በብዕር ስሙ Spencer Quinn) ሲሆን፤ የዘር ሀረጉ ከኢትዮጵያ ይመዘዛል። (ማለትም፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ነው።)
በስደት ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄደው ከነበሩት ኢትዮጵያዊ አባቱ ፒተር ሄንሪ (Peter Henry Abrahams Deras) እና ከፈረንሳዊ/አፍሪካዊት እናቱ የተወለደው ፒተር የትውልድ ስፍራው እዛው ደቡብ አፍሪካ፣ ጆሀንስፐርግ አካባቢ (Vrededorp የምትባል ስፍራ) ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊ አባቱን በሞት የተነጠቀው ገና በልጅነቱ ነበር። ለጊዜው ዝርዝሩን አቆይተን ወደ ስራና ህይወቱ እናምራ።
በሀገሪቱ ውስጥ 21 በመቶ የሆኑ (የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች ነው የሚባሉት)፣ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ስልጣንን በመያዝ የአገሩን ባለቤት ሲጨቁኑ የኖሩበት፤ ዜጎች በገዛ አገራቸው ሰጨቆኑ የኖሩበት የነበረ መሆኑ ለፒተር አብረሃስ የብዕር ተጋድሎ (በ1910 የተመሰረተው የደቡብ አፍሪካ ኅብረት፤ የምልክት መሪው ኔልሰን ማንዴላ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ) መቀስቀስ ምክንያት እንደ ነበር ይታወቃል። በመሆኑም አጠቃላይ ሥነጽሑፋዊ ምርቱ መዕከላዊ (ዐቢይ) ጭብጥ ይህንኑ አስከፊ ስርአት ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡን በማንቃት፣ ፍትህና ርትእን በመስበክ … በስርአቱ ላይ እንዲነሳና እንዲወገድ ሲያደርጉ ፀረ-አፓርታይድ ታጋዮች መካከል ከቆዩት አንዱ ነበር።
”የ20ኛው ክፍለ ዘመን እውቅ ጸሐፊና ጋዜጠኛ” መሆኑ የተመሰከረለት ፒተር አብረሃምስ የተለያየ ዜግነት ካላቸው ወላጆቹ መወለዱ ለበኋላ ማንነቱ፣ ለፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግሉና ፀረ-አፓርታይድ አቋሙ መሰረት (mulatto background) እንደሆነው ይነገራል።
የእነ ሄንድሪክ ቨርዎርድ (ከ1958-66 የብሔራዊ ፓርቲ መሪ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረ እና የአፓርታይድ ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ ቁልፍ ሚና የነበረው) ማስፈራሪያ እንኳን ያልበገረው ፒተር በሃያኛው ክፍለ ዘመን በደቡብ አፍሪካ ለተስፋፋውና ለየት ያለ የዘር-ሶሻል ርዕዮተ ዓለምን ለሚያራምደው አፓርታይድ ያለው ጥላቻ በስሜት ሳይሆን በምክንያት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፣ በስራዎቹ በብዙዎች ከጀፍተኛ አድናቆትን የያተረፈ ሲሆን፤ ለዚህም ከሁሉም ቀዳሚ ተጠቃሽና ተፅእኖ ፈጣሪ (seminal novel) በሆነው በMine Boy (1946) ስራው ውስጥ የሚያራምደው ሰውን መሰረት ያደረገ አስተሳሰቡና ሁሉም ጨቋኙም ተጨቋኙም ራሱን እንዲያይ ያደረገበት አቀራረቡ ነው።
ስፔንሰር ክዊን (ከላይ ይመልከቱ) ”A Wreath for Udomo”ም እንዲሁ በ2ኛነት ደረጃ ታዋቂና ተወዳጅ ስራው መሆኑ ተመስክሮለታል። በተለይ ስራዎቹ ዘረኝነትን፣ ፖለቲካን ….. (የደቡብ አፍሪካ ሥነፅሁፍ አቢይ ጭብጡ racial segregation and political and economic discrimination against nonwhites መሆኑን ያስታውሷል) የሚያብጠለጥሉና የሚያጋልጡ እንደ መሆናቸው መጠን የመላው ደቡብ አፍሪካዊያን ድምፅ ሆነው እስከ ማገልገል መዝለቃቸው ይታወቃል።
በዚህ ተወዳጅና አብዝቶም ተጠቃኝ ስራው ጥቁር (ወይም ባንቱ)፣ ቀለም (የተቀላቀለ)፣ ህንድ እና ነጭ ሰሜን አፍሪካውያን … ልዩነት የነበረውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስርአት/ልዩነት ያስከተለውን አፓርታይድ በምክንያት አጋልጧል፣ ተችቷል፤ ”መቀጠል የሌለበት” መሆኑን አስቀምጧል፤ ሊወገድ ይገባዋል” ሲልም እቅጩን ተናግሯል።
ይህ፣ በ1900ዎቹ፣ ከቦር ጦርነት በኋላ በደቡብ አፍሪካ የተጀመረውን የዘር ልዩነት አንድ በአንድ እየቆጠረ በማጋለጥ የተሳካለት ፒተር በአንድ ወይም በሁለት ስራዎች የተገደበ፤ በርካታ (ወንጀል፣ ፖለቲካ፣ ፀረ-አፓርታይድ …) መጻሕፍትን ለንባብ ያበቃ ብርቱ ሰው ብቻ ሳይሆን፤ ያለ መቋረጥ በጋዜጦች ላይ በሚያወጣቸው ጽሑፎቹም ታዋቂነትን አትርፏል። አፓርታይድን ከስሩ ፈንግሎ ለመጣል የራሱን የማይተካ ድርሻ ተወጥቷል።
ባልተቋረጠ ሁኔታ ሥነፅሁፋዊ ምርቶቹን ለአለም ሲያበረክት የቆየው ፒተር፣ በአሁኑ ሰአት ሳይቀር፣ ከአማዞን ጀምሮ የአለምን የመጽሑፍት ገበያ የተቆጣጠሩት ስራዎች በርካቶች ሲሆኑ፤
Oblivion, The Tutor, The Fury of Rachel Monette, Hard Rain, The Fan, Crying Wolf, The Right Side (በSpencer Quinn ብእር ስሙ የፃፈው), the Echo Falls Mysteries for children, … ጥቂቶቹ ናቸው።
‘አፍሪካንስ’ ቋንቋ በትምህርት ቤት ውስጥ ጥቅም ላይ መዋሉን ከተቃወሙ ጥቁር ተማሪዎች ውስጥ አንዱ የሆነው፤ እአአ በ1976 በስዌቶ በተካሄደ ዐመፅ ወቅት በፖሊስ እጅ በተገደለው የ12 አመት ታዳጊ ሄክተር ፒተርሰን የተሰየመውና የፀረ-አፓርታይድ ትግል ወቅት የነበሩ ቁልፍ ክንዋኔዎችን የሚያወሳው ሙዚየም የዘመነ አፓርታይድን ግፍና ዘረኛ ማንነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መሆኑን መዛግብት ይመሰክራሉ። ይህ ሙዚየም ካካተታቸው ታሪኮች መካከል የፒተር አብረሃምስ ስራዎች ጥቂቶቹ ናቸው።
ይህ ሙዚየም በከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀር የሚጎበኝ ሲሆን፤ በቅርቡ የአሜሪካው ብሊንከን ደቡብ አፍሪካን ከሩሲያና ቻይና ነጥለው ወደ ራሳቸው ለማምጣት (ባይሳካም) ባደረጉት ጉዞ እንዲጎበኙ የተጋበዙት ይህንኑ ሙዚየም ሲሆን፤ በወቅቱም “የሄክቶር ታሪክ ጎልቶ የሚሰማን ነው ምክንያቱም እኛም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የራሳችን የነፃነት እና እኩልነት ትግል አለን። የደቡብ አፍሪካ ታሪክ ልዩ ነው ነገር ግን ደግሞ በጥልቅ ጎልቶ እንዲሰማ የሚያደርግ በርካታ ተመሳሳይ ነገሮችም አሉን።” ማለታቸው ተዘግቧል።
እንደነ ማንዴላ (ንጉስ ኃይለ ሥላሴ ለማንዴላ ሽጉጥ መሸለማቸውን፣ ሽጉጡም ደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ሙዚየም የሚገኝ መሆኑን ልብ ይሏል)፣ ደቡብ አፍሪካ በተለይም በፀረ-አፓርታይድ ትግል መሪነታቸው የሚታወቁት ዴዝሞን ቱቱ፤ አልበርት ሉቱሊ፣ ዎልተር ሲሱሉ እና የመሰሉት የቀድሞ የኤኤንሲ አባላት ሁሉ፤ ከአፓርታይድ ነፃ የሆነች ደቡብ አፍሪካን በመፍጠሩ እንቅስቃሴ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ፒተር አብረሃምስ የቀለም ልዩነትና የነጮች የበላይነት እንዲያከትም ሌት ተቀን የሰራ፤ ያለ ፍርሀትም የተጋፈጠ፤ ኢ-ፍትሃዊነትን፣ የጎሳ ዘረኝነትን በአገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም የታገለ የብዕር ጀግና ነው።
በዘመነ አፓርታይድ ምን ምን ተግባራት ተፈፅመው ነበር፣ ፒተርንም ሆነ ሌሎች ደራሲያንን ለዚህ (ለAnti-Apartheid Movement) ያበቃቸው ምንድን ነው? ብሎ ለጠየቀ ምላሹ፤
… የዘር ጋብቻ በወንጀል ተፈርዶበታል። … ጥቁሮች ደቡብ አፍሪካዊያን ንብረት ሊኖራቸው አልቻለም። … ትምህርት በቀለም (በነጭና ነጥቁር) ተለያይቷል። … በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ሰዎች በዘር ተከፋፍለዋል። … የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ፓርቲ እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል። ንብረት (መሬትን ጨምሮ) በጥቂት ነጮች መዳፍ ስር ወድቋል። ወዘተርፈ …. (ለተጨማሪ ”Writing South Africa Literature, Apartheid, and Democracy, 1970–1995” መመልከት ጠቃሚ ነው።)
የሚል ሲሆን፤ የብዕር አለቆቹን፣ እነ ፒተር፣ አሌክስ ላጉማና የመሳሰሉትን ወደዚህ አይነቱ የብዕር ተቃውሞ ያስገባቸውም ይሄው ነው። (ወደ እኛም አገር ስንመጣ የሥነጽሑፍ ስራዎቻችን ዘመናቸውን ነው የሚመስሉት። አሁን አሁን ግራ አጋቢ ሆኑ እንጂ፣ ለምሳሌ በጣሊያን ወረራ ጊዜ የተሰሩትን ማየት ይቻላል።)
ምንም እንኳን አንዳንድ በወቅቱ፣ በመጨረሻው ሰአት የተፃፉ ሰነዶች ”በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት እ.ኤ.አ. በ1990 እና 1993 ተከታታይ ድርድሮች እና በዲ ክለርክ መንግስት በአንድ ወገን እርምጃዎች ተጠናቀቀ።” ይበሉ እንጂ፣ አፓርታይድን ገዝግዘው የጣሉት ብዕረኞች መሆናቸው የታወቀ ነው። ይህንን ለማረጋገጥ ደግሞ ከብዙዎቹ አንዱና ቀዳሚ የሆነውን፣ የፒተር አብረሃምስን ስራዎች መመልከቱ በቂ ማሳያ ይሆናል።
ወደ ማጠቃለያችን ከመሄዳችን በፊት የአፍሪካን ሥነፅሁፍ ልዩ መገለጫ እንመልከት፤ ከዛ ውስጭም የደቡብ አፍሪካን ድርሻ እንይ።
የደቡብ አፍሪካ ደራሲያን ስንል ፀረ አፓርታይድ ትግል የሚያካሂዱና ከየትኛውም አይነት ቀለም (ዘር) የሆኑትን ሲሆን፤ ተወላጆቹ (South African Black Authors የሚሏቸው)ም አሉ። እንደውም፣ እንደሚጠበቀውም፣ አብዛኞቹም እነዚሁ ተወላጆች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥም፣ ልክ እንደ ፒተር አብርሃምስ ሁሉ፣ ግንባር ቀደሞች (Sol Plaatje, Zakes Mda, Kopano Matlwa, Zukiswa Wanner, Pumla Gqola እና ሌሎችም) አሉ። (በአፍሪካ ሥነፅሁፍ ውስጥ የቹና አቼቤን Things Fall Apart የ1ኛነት ስፍራን ልብ ይሏል።)
በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ህልውናውን ያረጋገጠውና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከፍተኛ መሻሻልን ያሳየው በደቡብ አፍሪካ ሥነፅሁፍ ውስጥ በአቢይ ርእስነት ትኩረት የሚደረግባቸው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ባህላዊ … ጉዳዮች ሲሆኑ፤ እነሱም እራሱ አፓርታይድን ጨምሮ እሱ ያስከተላቸውን መዘዞች ሁሉ (Apartheid, Negritude, Assimilation, Racism, lack of education, dual identity of the mixed people etc) ናቸው።
እንደ አጠቃላይ የአፍሪካ ሥነጽሑፍ አቢይ ትኩረት ማህበራዊ (በተለይም ባህል ላይ)፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ሲሆን እነዚህ በተን ተደርገው ሲታዩ ደግሞ በርካታ (slave narratives, protests against colonization, calls for independence, African pride, hope for the future, and dissent) ናቸው። ይህ የጋራ ባህርይና ልዩ ትኩረት አሰጣጥ ዝም ብሎ በአጋጣሚ የሆነ ሳይሆን፤ የጋራ ጠላት የሆነው ቅኝ አገዛዝ ያመጣው የጋራ ስሜት፣ የጋራ አቋም፣ የጋራ አስተሳሰብና የጋራ መፍትሄ ፍለጋ ነው። የደቡብ አፍሪካ ሥነጽሑፍም ይህንኑ የሚጋራ ሲሆን፣ የዛሬው የአምዳችን ”እንግዳ”ም ሆነ፣ የገጣሚ ሎሬት Keorapetse William Kgositsile (South Africa’s National Poet Laureate) ስራዎች ከዚሁ የተቀዱ እንደ መሆናቸው መጠን ይህንኑ ሲያስተጋቡ እንመለከታለን።
በመጨረሻም፣ በ97 አመት (3 ማርች 1919 – 18 ጃንዋሪ 2017) እድሜው ከዚህ አለም በሞት የተለየው የዛሬው የባለውለታችን አምድ ተስተናጋጅ፣ ፒተር አንረሃምስ ለተወለደባት አገሩ ደቡብ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን የነጭ የበላይነትን በመቃወምና የርትእና ፍትህን አስፈላጊና አይቀሬነት፤ ስለ ዲሞክራሲ፣ እኩልነትና ነፃነት በማስተማር እድሜውን አሳልፏል። እንደ ማንኛውም ትውልደ ኢትዮጵያዊ አገሩን (ኢትዮጵያን)ም በስራዎቹና በእሱ ጠንካራ ማንነት አማካኝነት አስጠርቷል። በመሆኑም፣ ደቡብ አፍሪካዊያን ብቻ ሳይሆኑ፤ መላው ጥቁር ህዝብ ብቻ ሳይሆን፣ መላው የፍትህና ርትእ ደጋፊ፤ አፍቃሬ ዲሞክራሲና አቀንቃኝ ሁሌም ሲያነሳው ይኖራል። በተለይ የነጮቹን ሴራና ራስ ወዳድነትን መሰረት ያደረገ ስግብግብነት፤ ኢፍትሀዊነት የሚያውቅ ሁሌም ከፒተር አብረሀምስ ጋር እንደሚሆን አያጠራጥርም።
በመጨረሻው መጨረሻ፤
ይህ ጽሑፍ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ፒተር አብረሀምስን ለማስታወስ ያህል የተዘጋጀ እንጂ እሱን ይገልፀዋል ማለት አይቻልም። በመሆኑም፣ ፒተርን የበለጠ ለመረዳት ብዙ መሄድ ያስፈልጋል እንጂ፣ እዚህች ገፅ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ ሙሉ ፒተርን ይገልፃል የሚል ማጠቃለያ የለም።
አለማችን የፒተር አብረሀምስን አይነት ሰዎች ያብዛላት።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2015