በቡናው ዘርፍ በተጠናቀቀው 2014 በጀት አመት ሶስት መቶ ሺ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።ይህ ገቢ በቡና የወጪ ንግድ ታሪክ የመጀመሪያ ለመባልም በቅቷል።
ለተገኘው ስኬት በቡና ሻይ ባለስልጣን ከተከናወኑ በርካታ ተግባሮች መካከል በዘርፉ የተካሄደው ሪፎርም፣ ይህን ተከትሎም በቡና ልማቱም ግብይቱም የተከናወኑ ተግባሮች ይጠቀሳሉ።በተለይ በግብይት በኩል ሰፋፊ ውጤታማ ተግባሮች ተከናውነዋል።ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ብሎ ለማለት ባያስደፍርም፣ የነበሩትን ውስብስብ እና አስቸጋሪ አሰራሮችን መልክ የማስያዝ እና ህግና መመሪያ የተከተለ አሰራር በመዘርጋት በኩል ስኬታማ ስራዎች ተሰርተዋል ማለት የሚያስችል ሁኔታ መኖሩን ባለስልጣኑ ባለፈው ነሀሴ ይዞት ከወጣው መጽሄት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
አማራጭ የግብይት መንገዶች ወደ ስራ መግባት በግብይት በኩል የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አስችሏል።ለአመታት ሲሰራባቸው የቆዩት ሁለት የግብይት አይነቶች ብቻ እንደነበሩ በቡናና ሻይ ባለስልጣን የገበያ ልማትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ታጠቅ ግርማ ይገልጻሉ።እሳቸው እንደሚሉት፤ ቡና ለውጭ ገበያ የሚቀርብባቸው መንገዶች ኮሜርሻልና ስፔሻሊቲ በመባል ይታወቃሉ።ከሀገሪቱ ቡና አብዛኛው ለውጭ ገበያ የሚቀርበው በኮሜርሻሉ መንገድ ነው። ቡና የተለያዩ ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፣ ከደረጃ ሶስት በላይ ያሉት አራተኛና አምሰተኛ ደረጃ ቡናዎች ኮሜርሻል ይባላሉ።እስከ ደረጃ ሶስት ያሉት ደግሞ ስፔሻሊቲ ቡናዎች ናቸው።የስፔሻሊቲው መንገድ አሁን አሁን እየጨመረ መጥቷል፤ ለእዚህም ከጥቂት አመታት ወዲህ በሀገሪቱ በቡና ግብይቱ በኩል የተፈጠሩ አማራጭ ግብይቶች ትልቁን ድርሻ እየተወጡ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ የሚጠቁሙት።
እንደ አቶ ታጠቅ ገለጻ፤ በ2009 አም የቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር አዋጅ የወጣ ሲሆን፣ ይህን ለመተግበር ደግሞ በ2011 አም ደንብ ወጥቷል።ይህ አዋጅና ደንብ ስራ ላይ የዋለው በ2012 ነው። አዋጁ ከቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር አኳያ የተለያዩ ጉዳዮች የተካተቱበት ሲሆን፣ አንዱም አማራጭ የግብይት ስርአትን ተግባራዊ ማድረግን የተመለከተው ነው።አማራጭ ግብይቶቹ የጀመሩትም ከዚህ በኃላ ነው።
ለግብይት የተባሉትን ለማብራራት የቀድሞውን እና ቀጣይ አማራጭ ግብይት ሆኖ የመጣውን በማነጻጻር አቶ ታጠቅ ሲያብራሩ፣ በፊት አርሶ አደር ያመረተውን ቡና ለመሸጥ ያሉት ሁለት አማራጮች ብቻ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።አንዱ አማራጭ ቡናውን ለተደራጀበት ህብረት ስራ ማህበር ማቅረብ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አካባቢው ባለው ገበያ ለቡና አቅራቢው/ ሰፕላየር/ ወይም ለነጋዴ ማቅረብ ነበር ሲሉ ያስታውሳሉ።
ይህ አርሶ አደር ምንም አይነት ቡና ያምርት ፈቅዶና ወዶ ያለግዳጅ በሁለቱ አማራጮች ብቻ ቡናውን አቅርቦ ሲሸጥ ኖሯል።አሁን በተፈጠረለት አማራጭ ገበያ ደግሞ አርሶ አደሩ ገበያ አግኝቶ መሸጥ እስከ ቻለ ድረስ ቀጥታ ለኤክስፓርት ማዋል የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።በተለይ ቀጥታ ከአርሶ አደሩ ጓሮ ቡና የሚፈልጉ ካሉና በተለይ ከአርሶ አደሩ ቡና መግዛት የሚችሉበት ሁኔታ ከተመቻቸ አርሶ አደሩ እንደ ነጋዴ ሳይቆጠር ባንኮችና ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በተሰራው ስራ በቀጥታ መላክ የሚችልበት እድል ተፈጥሮለታል።ለእዚህም የቡናና ሻይ ባለስልጣን ትልቁን ድርሻ ወስዷል።
ይህን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተከትሎ ቀጥታ ቡና ወደ ውጪ ለመላክ ፈቃድ ያወጡ አርሶ አደሮች ከ1500 በላይ ደርሰዋል።በህጉ ማእቀፍ መሰረት ሁለትና ከሁለት ሄክታር በላይ የቡና መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች በእዚህ ግብይት መጠቀም ይችላሉ።በዚህም እስከ መቶ የሚደርሱ አርሶ አደሮች ገበያ ውስጥ ገብተው እየላኩ ናቸው፤፡ ይህ አንዱ አማራጭ ነው።
ይህ አማራጭ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፤ በዚህ አማራጭ የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች ገበያ ለሚፈልጉላቸው ሰዎች ከሚከፍሉት ኮሚሽን ወይም የአገልግሎት ክፍያ ውጪ የኤክስፓርት ዋጋውን ቀጥታ በማግኘት መቶ በመቶ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ ።
የግብይት አማራጩ ግን የአርሶ አደሩን ልምድ፣ እውቀትና ግንዛቤ ይጠይቃል የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ባለስልጣኑ አርሶ አደሮች ይህን ግብይት ለመምራት ትምህርቱም ግንዛቤውም ላይኖራቸው ይችላል በሚል ልጆቻቸውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሙከራዎች እያደረገ ይገኛል።ለአርሶ አደሮቹ ለራሳቸውም በተለያዩ መድረኮች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ተሰርቷል።በዚህ በኩል ተቋሙ በዋናነት አቅም ግንባታ ላይ ይሰራል ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ አቶ ታጠቅ ገለጻ፤ ሁለተኛው የልማት ግብይት ትስስር /አውት ሶርስ ስኪም/ የሚባለው ነው።አርሶ አደሩ ያለማል፤ በአካባቢው ያለው ባለሀብትም ያለማል።ይህ አሰራር አልሚ ባለሀብቶች ባለሀብቶች ልምድ ያላቸው ፣ የገበያ ችግር የሌለባቸው ፣ወደማምረት የመጡ ባለሀብቶች እንደመሆናቸው መጠን የገበያ ችግር የለባቸውም ተብሎ ስለሚታሰብ፣ የአካባቢውን አርሶ አደር በኤክስቴንሽን ስራ፣ በግብአት አቅርቦት እያገዙ የተሻለ መጠንና ጥራት ያለው ምርት በማምረት ለእነሱ በተሻለ ዋጋ እንዲያቀርብ ማድረግ የሚያስችል ስርአት ነው። ይህ የአርሶ አደር ባለሀብት ትስስር በሁለቱም ሙሉ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ነው።
ሶስተኛዎቹ አማራጮች ቡና ቆልተውና ፈጭተውና አሽገው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ናቸው።እነዚህ ድርጅቶች ከአዋጁ በፊት ጥራት ያለው ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና መግዛት አይፈቀድላቸውም ነበር። አሁን ግን ይህን ቡና በቀጥታ ከገበያ እንዲገዙ የሚያስችል ስርአት ተዘርግቶ እየተሰራበት ነው።አምራቹም ጥራት ያለው ቡና ለእነዚህ ድርጅቶች መሸጥ የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሮለታል።
ሌሎችም አማራጭ ግብይቶች አሉ። አርሶ አደሮች አባል ለሆኑበት የህብረት ስራ ማህበራት ቡናቸውን የሚሸጡበት አማራጭ አላቸው።ሴት አርሶ አደሮች ቀጥታ ለሴት ላኪዎች መሸጥ የሚችሉበት አማራጭ ተፈጥሯል።ይህ እየሆነ ያለው ሴት አርሶ አደሮችን ከማበረታታት አንጻር ብቻ አይደለም፤ ሴት ላኪዎችም እንዲሁ የሚፈልጉትን ቡና ከሴት አርሶ አደሮች እንዲገዙ የሚያስችል ሁኔታም ተመቻችቷል።
አርሶ አደሩ ምርቱን እንደ እስከ አሁኑ ሁሉ ለምርት ገበያ አቅርቦም ለላኪዎች መሸጥ እንደሚችል ጠቅሰው፣ በአጠቃላይ ወደ ስድስትና ሰባት አማራጮች ለአርሶ አደሩ እና ለባለሀብቱ የተመቻቹበት ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑን አስታውቀው፣ በቡናው ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችም በራሳቸው ራሳቸውን የቻሉ አማራጮች መሆናቸውን ነው ያመለከቱት፤ ይህ ሁሉ አሁን በግብይቱ ላይ ለተመዘገበው ውጤት የራሱን ሚና እየተጫወተ ይገኛል ይላሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ሌላው ትልቅ አማራጭ አቅራቢ/ ሰፕላይር/ ላይ የተፈጠረው ነው።አቅራቢ ከአርሶ አደር ቀጥታ የሚገዛ አካል እንደመሆኑ መጠን ቀደም ሲል ምርት ገበያ ገብቶ ለላኪ የሚሸጥበት ሁኔታ ነበር ያለው።ስለዚህ አቅራቢው አካባቢው ካለው ገበያ ከአርሶ አደር ይገዛል፤ በዚህም የታጠበም ሆነ ደረቅ ቡናን አዘጋጅቶ በምርት ገበያ በኩል የሚልክበት አግባብ ነበረው።አሁን ግን ሌላ እድል ተጨምሮለታል፤ያለ ሶስተኛ ወገን ማንም ጣልቃ ሳይገባበት ምርቱን በቀጥታ ለላኪ መሸጥ ይችላል። ምርት ገበያ እንዳለ ሆኖ፣ አቅራቢው በቀጥታ ለላኪ መሸጥ የሚችልበት ሌላ አማራጭ ነው የተፈጠረው።
መነሻ ወይም መነጋገሪያ ዋጋዎች ግን በቡናና ሻይ ባለስልጣን ይቀመጣል፤ በዚህ መነሻ ዋጋ ተነጋግረው አቅራቢና ላኪ ይገበያያሉ ማለት ነው።
ምርት ገበያም የራሱን ስራ እየሰራም በተፈጠሩት የተለያዩ አማራጮች ከ95 በመቶ በላይ የቡና ግብይት በቀጥታ ግብይት ተፈጽሟል ማለት ይቻላል።ምርጫው ተቀምጦላቸዋል፤ አስገዳጅ ሁኔታ የለም፤ አቅራቢው ሲፈልግ ምርት ገበያን እንዲጠቀም፣ ሳይፈልግ ደግሞ ለላኪው የሚሸጥበት አግባብ መመቻቸቱ ላኪው የሚፈልገውን ቡና አይነትና የጥራት ደረጃ ተዋውሎ ቀጥታ ከአቅራቢው አንዲያገኝ ነገሮች ተመቻችተዋል፤ ይህ በመሆኑም ምርቱ ከአርሶ አደር ወደ አቅራቢ ከአቅራቢም በቀጥታ ወደ ላኪ እንዲደርስ የሚያደርግ ሁኔታ ተፈጥሯል።
ቡናው በቀጥታና በፍጥነት ላኪው እጅ ገባ ማለት ለኤክስፓርት መጠን እድገት የራሱ ሚና እንዲኖረው ያስችላል ያስችላል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ቫልዩ ቼይን / የግብይት ሰንሰለት/ በጨመረ ቁጥር ላኪው አካል ቶሎ ምርቱን አያገኝም፤ ዋጋ የመጠበቅ፣ ጊዜ የመፍጀት ነገሮች ይኖራሉ፤ የግብይት ሰንሰለቱ /ቫልዩ ቼይኑ/ ባጠረ ቁጥር ጊዜ ያጥራል፣ ምርቱ ቶሎ ላኪዎች እጅ ይገባል፤ ስለዚህ
ምርቱን ቶሎ ማግኘት ለኤክስፓርት የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ሲሉ ያብራራሉ።ለኤክስፕርት እድገቱ ምርቱ ለኤክስፓርት የሚደርስበት አግባብ ወይም ያጠረ የግብይት ሰንሰለት መፈጠሩ አንድ ምክንያት ነው ተብሎ ይወሰዳል ብለዋል።
በፊት አቅራቢ አቅራቢ ብቻ ሆኖ ብቻ ነበር የሚሰራው።በአዲሱ አሰራር አቅራቢው ልምዱን ባከበተ ቁጥር አቅራቢም ላኪም ሆኖ እንዲሰራ ሁኔታው ተመቻችቶለታል።አቅራቢው በሂደት ላኪ መሆን የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።እንደ አርሶ አደሩ 1500 ላኪ ተፈጥሯል ባልልህም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ አቅራቢዎች ወደ ላኪነት ተሸጋግረዋል፤ አቅራቢም ላኪም የመሆን እድሉ ተመቻችቷል ሲሉ አቶ ታጠቅ ያብራራሉ።
በሌላ ገጹ ደግሞ ቀደም ሲል ላኪው ከአቅራቢው ቡና ይገዛ እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁንም መግዛት ይችላል፤ ይህንን ሲፈልግ በምርት ገበያ በኩል መፈጽም ይችላል፤ ሲፈልግ ደግሞ የአቅራቢነትን ሚናም መጫወት ይችላል ሲሉ ላኪው አቅራቢ ሆኖ ሊሰራ የሚችልበት አሰራር መዘርጋቱን ይናገራሉ፤ ላኪው ራሱ የአቅራቢ ፈቃድ አውጥቶ ታች ወርዶ ከአርሶ አደሩ ለላኪ ድርጅቱ ቡና ገዝቶ መላክ ይችላል።
እነዚህ ነገሮች ላኪው ቡናውን ባጠረ ጊዜ እና በሚፈልገው መጠን እንዲያገኝ አስችለውታል ሲሉ ገልጸው፣ በፊት ላኪ አህት ኩባንያ አቅራቢ አንዲከፍት አይፈቀድም ነበር።ህጉ ይገድብ ነበር።ስራውን ግን በህገወጥ መንገድ ይሰሩት አንደነበር ጠቁመዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ይህ የተከለከለው ህገወጥነትን ለመከከላከል ሲባል ነበር፤ ቡና ለኤከስፓርት የሚመረት ነው፤ ሀገር የውጭ ምንዛሬ ትፈልጋለች፤ ላኪው አቅራቢም ሆኖ ሲሰራ ይህን ለማስተዳደር ያስቸግራል የሚል እሳቤ ፊት ነበር።ቡናው ይባክናል የሚል ሀሳብ ነበር፤ አሁን ግን የማስተዳደር አቅም እያደገ፣ በቴክኖሎጂ እየተደገፈ መጥቷል፣ እህት ኩባንያ ከፍቶ እንዲሰራ የተደረገው የማስተዳደር አቅም ስለተገነባና ብዙም የሚፈጠር ችግር አይኖርም የሚባል ደረጃ ላይ ስለተደረሰ ነው ።ይሄ ላኪ ከእህት ኩባንያው ብቻ እንዲገዛ አይደለም የሚደረገው፤፤ ከሌሎች አቅራቢዎችም መግዛት ይችላል፤፤ ላኪው በተለያዩ አማራጮች ምርቱን የሚያገኝበት ሁኔታ መፈጠሩ ምርቱን ቶሎ አንዲያገኝ እንዲልክ በማድረግ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ማለት ይቻላል።
ባለልዩ ጣእም ቡናዎችም የራሳቸው የሆነ ግብይቶች መፍጠራቸውን አቶ ታጠቅ ይጠቅሳሉ።እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በየማህበረሰቡ ዘንድ የኑሮ ደረጃ ልዩነቶች እንዳሉ ይታወቃል።በዚህ ውስጥ የተለያዩ ፍላጎቶች ይፍጠራሉ።ለምሳሌ የወይን መጠጥ የጠጪዎቹን ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ የተለያዩ ደረጃዎች እንዳሉት ይታወቃል።ከፍተኛውን የጥራት ደረጃ የያዘ ወይን የሚጠቀሙት በአኗኗራቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው።ሲዘጋጅም እነሱን ታሳቢ ተደርጎ ነው።ልክ እንደዚያ ሁሉ ጥሩ ጣእም ያላቸውን ቡናዎች የሚጠቀሙ ማህበረሰቦች የኑሮ ደረጃ ከፍ ያለ ነው።ባለልዩ ጣእም ቡናዎች በእነዚህ ማህበረሰቦች በእጅጉ ይፈለጋሉ።የባለ ልዩ ጣእም የቡና ውድድሮች በእዚህ አይነት መንገድ ለቡና ግብይቱ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።
የግብይት አማራጮች እየጨመሩ መምጣት ለውጭ ገበያ የሚላከው ቡና በፍጥነት እንዲቀርብ አስተዋጽኦ እያደረገ ስለመሆኑ ባለፉት ጥቂት አመታት በቡናው ዘርፍ የተመዘገበው ስኬት ያመለክታል።በተያዘው በጀት አመት በቡናው ዘርፍ የተያዘውን 360 ሺህ ቶን ቡና የመላክና ሁለት ቢሊየን ዶላር የማግኘት እቅድ ለማሳካትም እነዚህ የግብይት መንገዶች ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ስለመሆኑ የተመጣበት መንገድም ያመለክታል።በቀጣይም በግብይቶቹ ላይ ጠንክሮ በመስራት የዘርፉን ተጠቃሚነት ማስቀጠል ይገባል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2015