
አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመስቀል ደመራ በዓል በከተማዋ ከ2 ሺህ 200 ቦታዎች በላይ ከምንጊዜውም በላይ በደመቀና ባማረ ሁኔታ ትውፊቶቹንና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን ገለጸ።
የከተማ አስተዳደሩ የመስቀል በዓልን በሰላም መጠናቀቅ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ ሁሉም የከተማዋ ነዋሪ በዓሉ የጋራ በዓላችንና ኢትዮጵያን ለዓለም ያስተዋወቀ ነው በማለት በዓሉ ከሃይማኖታዊ ገጽታው ባሻገር የኢትዮጵያ መልካም ገጽታ መገለጫና የኢትዮጵያ ሰላም ወዳድነት ማሳያ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል ብሏል፡፡
ነዋሪው በአብሮነት ለደመራውና ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ሁሉ በማዘጋጀት አካባቢውን በማስዋብ ድንቅ ኢትዮጵያዊ እሴት ጎልቶ እንዲወጣና ከተማችን የኅብረብሔራዊነትና የመተባበር ተምሳሌት መሆኗን አሳይቷል ብሏል አስተዳደሩ በመግለጫው፡፡
እንዲሁም የፀረ ሰላም ኃይሎች የበዓሉን ድባብ ለማጥፋት የሀገራችንን ገፅታ ለማበላሸት የሞት የሽረት ትንቅንቅ ያደረጉበትና አዲስ አበባን የሽብር ማዕከል ለማድረግ ብዙ ሃብት አፍስሰው የሰው ኃይል አሰማርተው ከበዓሉ ቀደም ብለው ሲዘጋጁበት የነበረው የሽብር እቅዳቸው በሕዝቡና በፀጥታ ኃይሉ ትብብር ምኞታቸው ቅዠት ሆኖ መቅረቱን ገልጿል መግለጫው፡፡
በዚህም ፀረ ሰላም ኃይሎችን አጋልጦ በመስጠት በርካታ ተላላኪዎችና ለሽብር ድርጊት ሊውሉ የተዘጋጁ መሣሪያዎች ጭምር በየአካባቢው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
የልዩነትና የመከፋፈል አጀንዳዎችን በማስወገድ በንቃትና በትጋት በአንድነት ተናበንና ተዋህደን ዘላቂ ሰላማችንን ልናረጋግጥ ብሎም እነዚህን ኃይሎች እስከ መጨረሻው ተስፋ ልናስቆርጥ ይገባል ብሏል አስተዳደሩ በመግለጫው።
ፀረ ሰላም ኃይሎች ምንም ቢተባበሩና የፈለገውን ያህል ቢዘጋጁ ከሕዝባችንና ከፀጥታ ኃይላችን ዐይንና ጆሮ የማያመልጡና ለዘላቂ ሰላማችን ስጋት ሊሆኑ እንደማይችሉ በጉልህ ያረጋገጥንበት በዓል ነውም ብሏል አስተዳደሩ፡፡
በመስቀል አደባባይ እና በየአካባቢው የመስቀል ደመራ በዓል በደማቅና ሰላማዊ ሁኔታ ሃይማኖታዊ እሴቱንና ሥርዓቱን ከፍ አድርጎ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ከተማ አስተዳደሩ አመስግኗል፡፡
ለመጪው የኢሬቻ በዓል ትብብራችንና አንድነታችንን ጠብቀን ሳንዘናጋ እጅ ለእጅ ተያይዘን ከተማችንን ዳግም የሰላም አምባ ለማድረግ እንድንነሳ ሲልም ጥሪ አቅርቧል፡፡
በተለይም የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት፣ የወንድማማችነትና እህትማማችነት መንፈስ ተቀብለን በማስተናገድ፣ ፍቅራችንን በማጋራት በአብሮነታችን የኢትዮጵያን ከፍታ ዳግም ልናረጋግጥና የጠላትን ሴራ በአደባባይ ዳግም ልናከሽፍ ይገባል ብሏል መግለጫው፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2015