
አዲስ አበባ:- ኢትዮጵያውያን በመስቀል ደመራ በዓል ያሳዩትን የመከባበር፣ የመተማመን፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የመተሳሰብ ባህልን ሊያጠናክሩ እና ወላጆች ልጆቻቸውን በመልካም መክረው ሊያሳድጉ እንደሚገባ የክርስትና እምነት ተከታዮች ገለጹ።
የ2015 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል ትናንት በመስቀል አደባባይ በድምቀት ተከብሯል። በበዓሉ የታደሙት አባ ተስፋ ስላሴ ወልደማርያም፤ ወላጆች ልጆቻቸውን በመልካም መክረው፣ ፈሪሃ እግዚአብሄር እንዲያድርባቸው፣ታላላቆቻቸውን የሚያከብሩ እንዲሆኑ ሊያስተምሯቸው ይገባል ብለዋል።
ትውልዱ ከመስቀል ደመራ በዓል መፋቀር፣ መከባበርን መማር እንዳለበትም ነው የተናገሩት። ‹‹መስቀል ሰላም ማለት ነው። ሰላምን የምናስታውስበት፣የምንሰብክበት፣ ትዕግስትን የምንማርበት ነው›› ብለዋል። እርስ በእርስ በመፈቃቀር፣ ትዕዛዛቱን በመፈጸምና በተግባቦት መኖር እንደሚገባም አባ ተስፋ ስላሴ አመልክተዋል።
‹‹ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ውጭ በመሆናችን፣ ግለኝነት በመሰልጠኑ፣ አብሮነት በመጥፋቱ አሁን ለተፈጠረው ችግር ምክንያት ሆኗል›› በማለት ጠቁመው፤ አብሮነት ከጠፋ መራራቅ ይፈጠራል፣ በመራራቅ ውስጥም መጨካከን አለ እነዚህን በማስወገድ እርስ በእርስ መዋደድ ያስፈልጋል ብለዋል።
የበዓሉ ታዳሚ መምህር መክብብ ገብረማርያም በበኩላቸው፤ ይህ ቱባ ባሕል እንዳይጠፋና እንዳይበረዝ የኢትዮጵያ ነገሥታት፣ የሃይማኖት አባቶች መስዋዕትነት ከፍለው ጠብቀው ለትውልድ ያስተላለፉት መሆኑን አስታውሰዋል።
በዓሉ ለዓለም፣ ለአፍሪካውያንና ለኢትዮጵያውያን ብርሃን እና ክብር መሆኑን ነው የገለጹት። የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቁመዋል። ይህ ወቅት ብርሃን የሚታይበት፣ አዕዋፋት የሚያዜሙበት፣ ጫካ ውስጥ የቆዩ እንስሳት የሚወጡበት፣ የሰው ልጆች እርስ በእርስ የሚገናኙበት፣ እርቅ የሚፈጸምበት የትውልድ መደሰቻ በዓል መሆኑንም ተናግረዋል።
ደመራው የሰላምና የአንድነት ምሳሌ ነው። በዓሉ አንድነትን ያሳያል፣ ይህ ደግሞ ለአፍሪካውያንና ለዓለም ምሳሌ የሚያደርግ መሆኑን ነው መምህር መክብብ የገለጹት። ኢትዮጵያ የሰላም፣ የአንድነት እና የፍቅር ምሳሌ ናት። ይህ አንድነት ደግሞ የሚገለጸው በደመራው ብርሃን ነው ብለዋል። በበዓሉ ወቅትም አባቶች ተሰብስበው ለዓለም ሰላም መስፈን ጸሎት የሚያደርጉበት እንደመሆኑ ሕዝቡ የሰላም አምባሳደር መሆን አለበት ሲሉ ጥሪ አቀርበዋል።

ወይዘሮ ማርታ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የሰንበት ተማሪዎቹ በሙሉ ዝማሬና ወረብ በማቅረብ በዓሉን በድምቀት ማክበራቸውን ጠቁመዋል። በርካታ የእምነቱ ተከታዮችም ሆኑ ሌሎችም በአንድነት ተሰባስበው በመተማመንና በመከባበር የሚያከብሩት፣ የእርስ በእርስ ግንኙነትን የሚያጠናክር የአንድነት በዓል መሆኑንም ነው የገለጹት።
የመስቀል ደመራ በዓልም ሆነ ጥምቀትና ሌሎች የአደባባይ በዓላት ከሃይማኖታዊ በዓልነታቸው ባሻገር በዩኔስኮ የተመዘገቡ በመሆኑ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድትታወቅ እንደሚያግዝ፣ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን በማድረግ የገቢ ምንጭ እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2015 ዓ.ም