ሰኘው ግብረ-ሰናይ ድርጅት ስፓይሮሊና (spirulina) የተሰኘ አልሚ ምግብ በማምረት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለሚሰቃዩ ህፃናትና ነፍሰጡር እናቶች በነፃ ሊያቀርብ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ቀደም ሲል በውድ ዋጋ ከውጭ ሲገባ የነበረውን ተመሳሳይ ምርት እንደሚተካና የውጭ ምንዛሪንም እንደሚቀንስ ገልጿል፡፡
ድርጅቱ ምርምሩን በሚያካሂድበት የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ መኖሪያ ግቢ የሙከራ ሥራውን ትናንት ለጋዜጠኞች ባስጎበኘበት ወቅት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ማሞ እንደገለፁት፣ ስፓይሮሊና /spirulina/ የተሰኘውን የተመጣጠነ አልሚ ምግብ በዘመናዊ መንገድ በማምረት ችግሩ ላለባቸው በነፃ ለማከፋፈል ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በምግብ እጥረት ለተጎዱ ህፃናትና ነፍሰጡር ሴቶች የሚሆን የሙከራ ምርት በምርምር ማእከሉ ተሰርቶ ውጤታማነቱ መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡ ስፓይሮሊና /spirulina/ የተሰኘውን አልሚ ምግብ ለማምረት ለምግብነት የሚውሉ የአልጌ ዝርያዎችን ከእስራኤል አገር በማስመጣትና ውሃ በተሞሉ ገንዳዎች ውስጥ በማሳደግ አልጌዎቹን ሰብስቦ በእንክብል አልያም በዱቄት መልክ በማዘጋጀት እንደሚሰራ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ አልሚ ምግቡ በርካታ ንጥረ ነገሮችን የያዘ በመሆኑ በምግብ እጥረት ለተጠቁ ህፃናትና ነፍሰጡር ሴቶች ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡
ምግቡን በአገር ውስጥ ማምረትና ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻል ከሆነም ቀደም ሲል ለአንድ ኪሎ ግራም ስፓይሮሊና /spirulina/ የሚወጣውን 60 የአሜሪካን ዶላር ማስቀረት እንደሚችል ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል። የምርቱን ጠቀሜታና ፍላጎት አስመልክቶ የጤና ሚኒስትር፣የኢትዮጵያ የምግብ መድኃኒትና ጤና አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተግባራዊ ሊሆን የሚችልና ሊበረታታ የሚገባ መሆኑን እንዳረጋገጡም ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡
በቀጣይ ኢትዮጵያም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአልሚ ምግብ ተቋም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ታዛቢ ምክር ቤት ያዘጋጁትን ስምምነት እንደፈረመች በጋምቤላ የማምረት ሥራው እንደሚጀመር ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥም ምርት መስጠት እንደሚጀምርና የክልሉ መንግሥትም 40 ሄክታር መሬት ለፕሮግራሙ እንዳመቻቸም አመልክተዋል፡፡
«ጥሩ ዘር ኢትዮጵያ ለአፍሪካ» ግብረ ሰናይ ድርጅት በእናቶችና ህፃናት ጤና፣ በተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት፣ በወጣቶችና ሴቶች የአቅም ግንባታ ዘርፍ ላይ በአፋር፣ በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከመንግሥትና የልማት ማህበራት ጋር እየሰራ የሚገኝ መሆኑም ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2011
አስናቀ ፀጋዬ