በአሁኑ ወቅት በየትኛው የምሽት ክበብ ጎራ የሚል ሰው የእሱን ሙዚቃ ወጣት ድምጻውያን ሲያዜሙት ይሰማል፡፡ አሁን የተስፋፋው የተለያዩ ሙዚቃዎችን እየቀነጨቡ በአዲስ መልክ መጫወት ላይም ከማይቀሩት ሙዚቃዎች መካከል ዋነኛው የእሱ ሙዚቃ ነው፡፡ ልዩ በሆነ አዘፋፈኑ እና ነፍስ ባላቸው ሙዚቃዎቹ እናውቀዋለን፡፡ አበበ ተካ።፡ በዛሬው የዝነኞች ገፅ አምዳችን በተለያዩ ጊዜያት ስለ እሱ ከተሰሩ ዘገባዎች መርጠን ልናስታውሰው ወደድን፡፡
ትውልድና እድገቱ ጎንደር ከተማ ውስጥ ነው። ከልጅነቱ ነው ከሙዚቃ ጋር በፍቅር የወደቀው፡፡ በልጅነቱ የህንድ ፊልሞችን እያየ በፊልሙ ላይ ያሉ ሙዚቃዎችን እያጠና ሲያዜም ጓደኞቹ ዙሪያውን ከብበው ያዳምጡት ነበር፡፡ ገና የ10 ዓመት ልጅ እያለም በቀድሞው የከፍተኛ ኪነት ውስጥ አባል ሆኖ ሙዚቃ ይጫወት ነበር፡፡ ‹‹የ10 ዓመት ልጅ ሆኜ ነው ሙዚቃን ከታላላቅ አርቲስቶች ጋር የጀመርኩት። ወገራ አውራጃ ዳባት ከተማ የሚባል አባቴ ለስራ ከጎንደር ተዛውረው ወደዛ ሲሄዱ እኔን ነበር ይዘው የሄዱት፡፡ በዚያ ጊዜ ነው ሙዚቃን መስራት የጀመርኩት›› ይላል፡፡ ገና በ12 ዓመት እድሜው
ሰፊው ህዝብ በሙሉ ያለከው በሀገር
ተነሳ በአንድነት እንድንተባበር
የሚለውን የራሱን ድርሰት ሰርቶ ለህዝብ አቅርቦ የድምጽ ብቃት ብቻ ሳይሆን የደራሲነት ክህሎት ባለቤትነቱንም አረጋግጧል፡፡ ከዚያም በኋላ በ1978 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ውስጥ በ603ኛ ኮር የኪነት ቡድን ውስጥ በመቀላቀል ሙዚቃ መስራቱን ቀጥሏል፡፡ በዚሁ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ሙዚቃ ብቻ ሳይሆን ግብረ ገብን እና መልካም ስነ ምግባርን ማዳበሩንም ይናገራል፡፡ ‹‹ውትድርና ማለት አንድ ታላቅ ትምህርት ቤት ማለት ነው፡፡ ስርአት ወዳለው ሕይወት ራስህን የምትቀይርበት አንደኛው ቦታ ውትድርና ነው። ከሙዚቃው ጋር የውትድርናውን ሳይንስም አብሬ ተምሬያለሁ›› በማለት ይነገራል፡፡ ይህ የውትድርና ኪነት ግን ለአበበ የሙዚቃ ብቻ ሳይሆን የትዳሩም ጥንስስ የተጠነሰሰበት ነው፡፡ የዚሁ የኪነት ቡድን ተወዛዋዥ አባል የነበረችውን እና የሙያ ባልደረባው የነበረችውን ብሎም የዘፈነላትን እና ያለቀሰላትን እታገኝ ሙላትንም ያገኘው እዚሁ ነው። በኋላ ላይ ከእሷ ጋር መለያየቱንም በማስመልከትም ነው መከፋቱን እና የውስጡን መጎዳት በዜማ የገለጸው። ‹‹ሙዚቃ በፍቅር ውስጥ ሆነህ ስትሰራው እና እንዲሁ ስትሰራው በጣም ልዩነት አለው፡፡ ፍቅር ስልህ ደግሞ ከአብሮ መኖር በላይ በመለያየት ውስጥ ስትሆን ነው ፍቅርን የምታገኘው፡፡ ከባለቤቴ ጋር ከተያየሁ በኋላ የማላውቃቸው የተደበቁ ጥበቦች ሁሉ ከኔ ላይ ወጡ ማለት ነው፡፡ በውስጥህ ያለው እንዲገለጽ የግዴታ መታመም አለብህ በሆነ ነገር›› ይላል፡፡
አርቲስት አበበ ተካ በ603ኛ ኮር ውስጥ የሙዚቃ መሰረቱን ቢጥልም የውትድርናው ሀላፊነት በኪነት ቡድን ውስጥ ያለውን ሀላፊነት እየገደበው ሲመጣ ከውትድርና ጠፍቶ አመለጠ፡፡ እናም ሙሉ ጊዜውን ለሙዚቃ ሰጥቶ በሚወደው ሙያ ለውጥን ያመጣው በምሽት ክበቦች ውስጥ በመስራቱ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ አበበ አዲስ አበባ ውስጥ ኮንኮርድ እና ኦሪዮን በተሰኙ ምሽት ክበቦች ውስጥ በሰፊው ሰርቷል። ከላፎንቴኖች ጋር አብሮ የምሽት ክበብ ቢመሰርቱም ከአንድ ቀን በላይ አብሯቸው እንዳልሰራ ያስታውሳል።
በ1982 ዓ.ም የሰራው የመጀመሪያ አልበሙ በተለያዩ ምክንያቶች በህዝብ ዘንድ በሰፊው አለመደመጡን አበበ ያስታውሳል፡፡ ይሄው አልበም ከወጣ ከ4 ዓመታት በኋላ ነው በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያገኘው ‹‹ሰው ጥሩ›› የተሰኘውን አልበም ለህዝብ ጆሮ ያቀረበው፡፡ ‹‹የዚህ ስራ ውጤት የጓደኞቼ ታላቅ ጥረት ነው፡፡ በተለይ አበበ ብርሃኔ፤ ሙሉጌታ ተስፋዬ እና ጸጋዬ ደቦጭ ማለት ነው፡፡ የእነሱ ውጤት ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ ልጅነት የሚያጠቃው ሰው፤ ጓደኛ የሚወድ ፤ ከሙያው በላይ አንዳንዴ ጓደኝነት የሚያጠቃው ሰው ነኝና በምክር እና በመደጋገፍ ነው እዚህ የደረስኩት›› ይላል ስለ አልበሙ ሲያወራ፡፡
አበበ ስራዎቹን በመድረክ ሲያቀርብ ራሱንና ውስጡን በማዳመጥ ጆሮውን ይዞ አይኑን ጨፍኖ በማዜም ይታወቃል፡፡ ይህ የተመስጦ ዘዬ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ እንዳለው አርቲስት አበበ ይናገራል። ‹‹አንድ ጆሮህን በምትይዝበት ጊዜ ጭንቅላትህ ላይ ነው ድምጽ ያለው፡፡ እና የራስህን ድምጽ ደግመህ ስለማትሰማው ያለመንሸራተት እድል አለህ፡፡ ልክ ከሳውንድ ሚክሰሩ ወጥቶ የምትሰማው ነው የሚመስለው፡፡ ሌላው አይኔን በምጭፍንበት ጊዜ አለማየትህ የሚሰበስበው ብዙ ነገር አለው››፡፡
አበበ ተካ ባህር ተሸግሮ አሜሪካ የገባው ከእሱ ቀድማ አሜሪካ የገባችውን ያዜመላትን ሚስቱን ለማግኘት ነበር፡፡ ያም ሆኖ አሜሪካ እሱ እንደጠበቀው አልጋ በአልጋ ሆና አልጠበቀችውም፡፡ ገና እሱ ዋሽንግተን ዲሲን እንደረገጠ ለእስር ተዳረገ፡፡ በእስር ቤት ቆይታው ደግሞ ሙዚቃን የሀሳቡ መገለጫ የብቸኝነቱ መግፊያ አድርጓት ቆይቷል፡፡ አርቲስት አበበ ተካ ከእስር ቤት ብዙ መማሩን ያስታውሳል፡፡ ‹‹እስር ቤት ማለት ከፍለህ የማትማርበት ትምህርት ቤት ማለት ነው፡፡ እና ወደዚህ አገር ስመጣ ያጋጠመኝ እስር ነበር፡፡ ምናልባት የመጀመሪያዋ ሌሊት ነበረች በሞት እና በሕይወት መካከል የነበርኩት። ምናልባት የዚያን ቀን ሞት መጥቶ ቢጠይቀኝ ወደ ሞት እሄድ ነበር። ነገር ግን ከአንድ ቀን በኋላ እስር ቤትን እንደ ቤቴ አየሁት። በወቅቱ አምስት ዓመት ነበር የተፈረደው ነገር ግን ባለኝ ስነ ምግባር በዓመት ከሁለት ወር ከእስር ቤት ተለቅቄያለሁ›› በማለት ወቅቱን ያስታውሳል፡፡
ከእስር ቤት እንደወጣም በሎስ አንጀለስ ከተማ በሚገኙ የምሽት ክበቦች ውስጥ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ከዚያም ወደ ዋሽንግተን ሲቲ እና አካባቢዋ በማቅናት በዲሲ በሜሪላንድ እና በቨርጂኒያ የምሽት ክበቦች ውስጥ ሰርቷል፡፡ የሶስት ልጆች አባት የሆነው አበበ ተካን በተመለከተ የአድናቂዎቹ የሁልጊዜም ጥያቄ አዳዲስ ስራዎችን ይዘህ የምትመጣው መቼ ነው የሚል ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት አሞኛል ብዬ የተሰኘ ነጠላ ዜማ ለቅቆ የነበረ ሲሆን በህዝብ ዘንድም በጣሙን ተወድዶለት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የጤና እክል አጋጥሞት የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ጤናው ተስተካክሏል፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2015 ዓ.ም