ከትንሽ ደረጃ ተነስቶ፤ በፈተናዎች ውስጥ አልፎ እውን የሆነ የስኬት ተሞክሮ፣ ከአስደናቂነቱ ባሻገር ለሌሎች ሰዎች የሚፈጥረው መነሳሳትና ሞራል ከፍ ያለ ዋጋ አለው። እንዲህ ዓይነቶቹ የስኬት ታሪኮች ፅናትን፣ ተስፋ አለመቁረጥንና የታላቅ ዓላማ ባለቤትነትን አጉልተው የሚያሳዩ እንደሆኑ ከብዙ ስኬታማ ሰዎች ታሪክ መገንዘብ ይቻላል።
በመሰል የስኬት መንገድ ያለፉ ስኬታማ ሰዎች ለገጠሟቸው ችግሮች አልተንበረከኩም፤ ባገኟቸው ውጤቶችም ተኩራርተው ጉዟቸውን አላቆሙም። ችግሮችን እንደጥንካሬ መመዘኛ ተመልክተው፣ መሰናክሎችን ድል እያደረጉ ከስኬት ወደ ስኬት የተሸጋገሩም ናቸው። የዛሬው የ‹‹ስኬት›› አምድ ባለታሪክም በዚህ ዓይነት የሕይወት ተሞክሮ ያለፈ ባለተሞክሮ ነው።
ዋልተንጉሥ መጨጊያው ይባላል። የ‹‹ማኅበረ ትጉሃን የእንጨትና ብረታ ብረትና ኮንስትራክሽን ስራ ድርጅት›› መስራችና ስራ አስኪያጅ ነው። በ1972 ዓ.ም የተወለደው ይህ ዋልተንጉሥ፣ ተወልዶ ያደገውም ሰሜን ሸዋ፣ ደራ ወረዳ አካባቢ ነው።
በጎልማሳነት እድሜ ላይ የሚገኘውን ዋልተንጉሥን በሥራ ስኬቱና በእድሜው የአንቱታ ከበሬታ የሚገባው ቢሆንም አንተ ብለን ማውጋቱን ወደናል። ዋልተንጉሥ የሕይወት ፈተናን ማየት የጀመረው በለጋነቱ ነበር። በመጀመሪያ እናቱን ቀጥሎም አባቱን በሞት የተነጠቀው ዋልተንጉሥ፣ በ13 አመቱ ታናናሾቹን የመርዳት ኃላፊነቱን መቀበል ግድ ሆነበት። ለመሥራት ደግሞ ወደ ከተማ መውጣት ነበረበት። ሥራን ሀ ብሎ የጀመረው ጫማ በማሳመር (በመጥረግ) ነው። ጫማ አሳምሮ በሚያገኘው ገቢ፣ እንጀራ እየጋገረ ታናናሾቹን አሳድጓል። ራሱን በትምህርት ለማብቃት ባደረገው ጥረት ስምንተኛ ክፍል ደርሷል።
በዚህ መንገድ ኑሮውን እየገፋ ሳለ ነበር ‹‹ሰዎች ለሰዎች›› (Menschen für Menschen) ከተሰኘው ምግባረ ሰናይ ድርጅት ጋር በ1992 ዓ.ም የመተዋወቅ ዕድሉን ያገኘው። ድርጅቱም የአናፂነትንና የግንባታ ሙያ ክህሎት እንዲያገኝ እገዛ አደረገለት። ድርጅቱ በቀን 25 ብር እየከፈለው ነበር የሙያ ባለቤት ያደረገው። ‹‹ለማደግና ለመለወጥ ያስቻለኝ ‹ሰዎች ለሰዎች ድርጅት› ነው። እዚያ ገብቼ ሙያ መልመዴ ለዚህ አብቅቶኛል›› የሚለው ዋልተንጉሥ፣ ዛሬ ለደረሰበት ስኬት ያበቃውን ድርጅት ውለታም አልዘነጋውም።
ድርጅቱ ውስጥ ሆኖ በቀሰመው እውቀት ሲሰራ ባጠራቀማት ሦስት ሺ ብር በጉንደመስቀል ከተማ፣ ‹‹ማኅበረ ትጉሃን የእንጨት፣ ብረታ ብረት እና ኮንስትራክሽን ስራ ድርጅት››ን በ1995 ዓ.ም በማቋቋም ከእህቱ እመቤት መጨጊያው ጋር በመሆን የእንጨት ስራ ጀመረ። በሂደትም ወንድሞቹን ወደዚሁ ስራ በማስገባት አብረው መሥራቱን ተያያዙት። ወደ ግል ሥራ ከገባ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ነበር ትዳር የመሠረተው። በአካባቢው ላይ በግል በጀመረው የእንጨት ስራ የቆየው ለስምንት ዓመታት ብቻ ነበር። በ2003 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጣ።
ዋልተንጉሥ ወደ አዲስ አበባ የመጣበት ውሳኔው የቆራጥነት፣ የተስፋና የጽናት መገለጫ ተደርጎ የሚቆጠር ነው። ‹‹የቤተ መንግሥት አስተዳደር የሰንበሌጥ ሳር በጨረታ አወዳድሮ መግዛት እንደሚፈልግ የሚገልፅ የጨረታ ማስታወቂያ ‹አዲስ ዘመን› ጋዜጣ ላይ አነበብኩ። ጨረታውን እንደተመለከትኩ ለናሙና የሚሆን ሰንበሌጥ ሳር ይዤ ከደራ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። ‹የሥራ ዘርፍህ የእንጨትና የብረታ ብረት ስራ ስለሆነ፣ ያቀረብከው ለጨረታው ብቁ አይሆንም› ተብዬ የጨረታው ጉዳይ ሳይሳካ ቀረ። ሳር ተሸክሜ ቤተ መንግሥት አካባቢ ስዘዋወር የተመለከቱኝ የቤተ መንግሥቱ ጥበቃ አባላት ይገረሙ ነበር። ጨረታው ባይሳካም እዚሁ ሆኜ ስራ እሰራለሁ እንጂ ወደ ደራ አልመለስም ብዬ በአዲስ አበባ ስራ ለመጀመር ጥረቴን ቀጠልኩ›› በማለት ወደ አዲስ አበባ የመጣበትን አጋጣሚ ያስታውሳል።
አዲስ አበባ ስራ ለመጀመር የቆረጠው ዋልተንጉሥ፣ አዲሱ ገበያ ተብሎ የሚታወቀው አካባቢ ቤት ተከራይቶ ስራ ጀመረ። የመስሪያ እቃዎችን በዱቤ እያፈላለገና በጓደኞቹ ድጋፍና ምክር እየተበረታታ ስራውን በብርታትና በተስፋ ጀመረ። ከተቀጣሪነት ይልቅ የራሱን ስራ በመፍጠር እሳቤ ሦስት ሰራተኞችን በመቅጠር የጀመረው ስራ፤ መልክ እየያዘለትና ስኬት እያገኘበት መጣ።
ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ የእቃ መደርደሪያና ማስቀመጫ (ሎከር) እና ሌሎች የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስን እያመረተ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ለትላልቅ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ጭምር ማቅረቡን ቀጠለበት። ስራውን በተገቢው ጥራትና ከተሰጠው ጊዜ ቀደም ብሎ ማስረከብንም መለያው አደረገ።
ይህ ታታሪነቱ ደግሞ ከተቋማቱ አመኔታን አትርፎለት። ከ40 በላይ ትላልቅ ተቋማት ለስራው ጥረትና ቅልጥፍና ማረጋገጫ የሚሆን የምስክር ወረቀት ሰጥተውታል። ከእነዚህ መካከል አዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ሐረማያ፣ ዋቸሞ፣ ደብረ ታቦር፣ አምቦ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ዲላ፣ ደብረ ብርሃን፣ ድሬዳዋ፣ ባሕር ዳር፣ ሚዛን ቴፒ፣ ሰመራ፣ መቱ እና የኢትዮጵያ ፖሊስ የኒቨርሲቲዎች ይጠቀሳሉ። የዳግማዊ ምኒልክ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን እና የትምህርት ጽሕፈት ቤት፣ የዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የደራ ወረዳ አስተዳደር፣ የፍቼ ከተማ አስተዳደር፣ አጋርፋ ግብርናና ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ እና ኢካፍኮ አክሲዮን ማኅበር ሌሎች የምስክር ወረቀት የሰጡት ተጠቃሽ ተቋማት ናቸው።
የእንጨትና ብረታብረት ስራው ጥሩ መስመር እየያዘለትና ስኬት እያገኘበት ሲመጣ ቤተሰቦቹን አዲስ አበባ በማምጣት ከባለቤቱና ከልጆቹ እንዲሁም ከወንድሞቹ ጋር እየኖረ ስራውን ቀጠለ። ብዙ ደንበኞችን እያፈራ፣ በስራውም የበለጠ ልምድ እያገኘ መጣ።
‹‹ማኅበረ ትጉሃን የእንጨትና ብረታ ብረትና ኮንስትራክሽን ስራ ድርጅት›› በአሁኑ ወቅት ለ40 ሰዎች የስራ እድል የፈጠረና 40 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያለው ምስጉን አምራች ተቋም መሆን ችሏል።
ዋልተንጉሥ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ጉዞው ቀላል እንዳልነበር ያስረዳል። የአሁኑ ስኬቱ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎና ጫናዎችን ተቋቁሞ የተገኘ ድል ነው። ያሳለፋቸውን ጊዜያት ዛሬ ላይ ሆኖ ሲያስታውሳቸው የዛሬው ስኬቱ በቀላሉ እንዳልተገኘ ይገነዘባል። ‹‹ስኬታማ ለመሆን ተግቶ መስራት ያስፈልጋል። እሰራለሁ ብሎ ቃል የገቡትን ስራ በጊዜና በጥራት ለማጠናቀቅ መትጋት ይገባል። ስራን በጥራትና በፍጥነት አጠናቅቆ ማስረከብ የደንበኞችን እምነት ያስገኛል። እኔም ሁልጊዜም ቢሆን በዚህ መርህ እየተመራሁ ይህን መርህ ለመተግበር እጥራለሁ›› በማለት ይገልፃል።
በስራ ሕይወቱ አስፈሪና አስደንጋጭ የሆኑ አጋጣሚዎችንም አልፏል። ለአብነትም ደራ በነበረበት ወቅት ያጋጠመውን እንዲህ ሲል ያስታውሳል። ‹‹ደራ በነበርኩበት ጊዜ ለእንጨት ስራ ግብዓት የሚሆን ዋንዛ የምናመጣው ከገጠር ተሸክመን ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ዋንዛ ለማምጣት ከጓደኞቼ ጋር ዋንዛው ወደሚገኝበት ስፍራ በሌሊት ሄድን። እንጨቱ የሚገኝበት ቦታ ደግሞ ገደላማ ነበር። በዕለቱ በነበረው ኃይለኛ ነጎድጓድ (መብረቅ) ምክንያት እኔና ጓደኞቼ ገደል ልንገባ እግዚአብሔር ነው ያተረፈን›› በማለት ይህ ክስተት እስካሁን ድረስ በጣም ከሚያስገርሙት አጋጣሚዎቹ መካከል አንዱ እንደሆነ ይናገራል።
ለስራው የሚያስፈልጉ የአንዳንድ ግብዓቶች እጥረት፣ የቦታ ጥበት እና በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት ብድር ማግኘት አለመቻል በስራ ሂደት ላይ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል ዋነኞቹ እንደሆኑ የሚናገረው ዋልተንጉሥ፤ ‹‹ለትልልቅ ተቋማት ብዙ ምርቶችን በፍጥነትና በጥራት ለማቅረብ ሰፊ የመስሪያ ቦታ ይፈልጋል። ምርቶቻችንን ለብዙ ተቋማት እንደምናቀርብና በስራውም ጥሩ ውጤት እያገኘን እንደሆነ በመረዳት መንግሥት የቦታና የብድር አቅርቦት ቢያመቻችልን ከዚህ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንችላለን›› በማለት መንግሥት ድጋፍ እንዲያርግላቸው ይጠይቃል።
ዋልተንጉሥ ችግሮችን የምሬትና መሰናክል ምንጭ አድርጎ ከማየት ይልቅ የጥንካሬ መመዘኛና የብቃት መፈተኛ አድርጎም ይመለከታቸዋል። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ‹‹ብዙ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ዋናው ቁም ነገር ለችግሮችና ለፈተናዎች አለመበገርና በፅናት ታግሎ ማሸነፍ ነው›› ብሎ የሚናገረው።
ዋልተንጉሥ ከስራውም ባሻገር በሌላው የሕይወት ዘርፉም በአርዓያነት የሚጠቀስ ስኬት አለው። ባለትዳርና የአራት ልጆች (አንድ ወንድና ሦስት ሴቶች) አባት ነው። ከቤተሰቡ፣ ከጎረቤቶቹ፣ ከስራ ባልደረቦቹ ጋር እጅግ ሰላማዊ የሆነ ግንኙነትና ትብብር አለው። በማኅበራዊ ሕይወቱም ንቁ ተሳትፎ ያደርጋል።
ዋልተንጉሥ የመገልገያ መሳሪያዎችን እየሰራ አቅም ለሌላቸው ተቋማት፣ በተለይም ለትምህርት ቤቶች፣ ያበረክታል። ‹‹እኔ በችግር ውስጥ ስላለፍኩ ሌላውንም መርዳት ተገቢ ነው። ሁሉንም የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው። የተቸገረ ሰው ድጋፍ ቢደረግለት ለውጥ እንደሚያመጣ ስለማውቅና የቻልኩትን ያህል ባደርግ ለኅሊናዬ ደስታን ስለሚሰጠኝ የአቅሜን ያህል በመደገፍ እሳተፋለሁ። ያደረግኩትን ሁሉ ዘርዝሬ መናገር ግን አያስፈልግም›› በማለት መስጠትና ሌሎችን ማገዝ ‹‹እንዲህ አድርጌያለሁ›› ብሎ ከመናገር ይልቅ በትህትና መታጀብ እንዳለበት ምርጫው መሆኑን ጠቁሟል።
ስራዎቹን በፍጥነትና በጥራት ለደንበኞቹ በማቅ ረቡ ካገኛቸው ምስጋናዎችና እውቅናዎች በተጨማሪ የሚጠበቅበትን ግብር በአግባቡ ለመንግሥት የሚከፍል በመሆኑም የገቢዎች መስሪያ ቤት የምስክር ወረቀት ሰጥቶታል።
የ‹‹ማኅበረ ትጉሃን የእንጨት፣ ብረታ ብረትና ኮንስትራክሽን ስራ ድርጅት›› ስራዎች ለደንበኞች ጥራት ያላቸውን ምርቶች በፍጥነት ከማቅረብ ባሻገር፣ ከውጭ ይገቡ የነበሩ የቢሮ እቃዎች በአጭር ጊዜና በተመጣጣኝ ዋጋ በአገር ውስጥ ተመርተው የውጭ ምንዛሬን በማዳን ለአገር ትልቅ ፋይዳ እያበረከቱም ነው። በዚህ ረገድ ዋልተንጉሥ ‹‹ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከውጭ ያስገባቸው የነበሩትን እቃዎች እኛ እዚሁ አገር ውስጥ በጥሩ ሁኔታ በመስራት አቅርበንለታል። ኦዳ ቡልቱ ዩኒቨርሲቲም ከውጭ ሊያስመጣው የነበረውን ምርት እኛ እዚሁ በመስራታችን ተቀባይነት አግኝቷል›› በማለት የድርጅቶቹ ምርቶች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የመተካት አቅም እንዳላቸው ማስመስከራቸውን ያስረዳል።
‹‹ዓላማ ያለው ሰው ትኩረቱን ስራው ላይ ብቻ ያደርጋል›› የሚለው ዋልተንጉሥ፣ ወጣቶች ማድረግ ስለሚገባቸውም ይመክራል። ‹‹ወጣቶች የሚያገኙትን ገንዘብ ማባከን የለባቸውም። ‹ይቺ ምን ታደርግልኛለች?› ከማለት ይልቅ መቆጠብና ለተሻለ ዓላማ ማዋል ይገባቸዋል። ደራ በነበርኩበት ጊዜ ጓደኞቼ ‹ይቺን ገንዘብ መኪና እንግዛባት› ሲሉ እኔ ግን ገንዘቡን እንዳያጠፉትና ቆጥበነው ሌላ ስራ ሰርተን እንደምንለወጥለበት እነግራቸው ነበር። በተጨማሪም ወጣቶች አልባሌ ቦታ መዋል የለባቸውም። የሰው ልጅ ዋነኛ ሀብት ሙያ ስለሆነ የሙያ ባለቤት ለመሆን መትጋት ይጠበቅባቸዋል!›› በማለት ይመክራል።
ዋልተንጉሥ ከትንሽ ተነስቶ ዛሬ ለሚገኝበት ትልቅ ደረጃ መብቃቱ ‹‹የስኬት ጫፍ ላይ ደርሻለሁና ይበቃኛል›› ብሎ እንዲቀመጥ አላደረገውም። ድርጅቱን አሁን ካለበት የተሻለ የማድረግ ዓላማና ርዕይ አለው። ‹‹የወደፊት እቅዳችን ተጨማሪና የተሻሉ ማሽኖችን እንዲሁም መሬት በማግኘት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ የማምረት ኢንቨስትመንት ላይ በስፋት መሰማራት ነው ። ሰፊ ስራ ሰርቼ ሁሉም ሰው የሚጠቀምበትና አገር የሚለውጥ ድርጅት እንዲሆን ምኞቴ ነው›› በማለት ስለወደፊት እቅዱና ዓላማው ይናገራል።
በአንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2015 ዓም