
አዲስ አበባ፤ ህዝቦች በሃይማኖት፣ በብሄርና በጎሳ ሳይከፋፈሉ ተግባብተው በአንድነት እንዲኖሩ ማድረግ እንደሚገባ የአገር አቀፍ የሰላም አምባሳደር እናቶች አሳሰቡ ፡፡
‹‹እናት እንዳታለቅስ፣ ሰላም በኢትዮጵያ ይስፈን›› የሚል መልዕክት በማንገብ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ሰላምን በመስበክ ላይ የሚገኙት አምባሳደር እናቶች ትናንት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት በመገኘት የሰላም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃን አጀንዳ እየቀረጹ ሰላምን ለማስፈን የበኩላቸውን ጥረት እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በየክልሉ እየተዘዋወሩ ስለ ሰላም እየሰበኩ የሚገኙ እናቶችን፤ የሰላም ጉዳይ ትልቅ ዋጋ ያለው መሆኑን አመልክተው እንደ ኢትዮጵያ የተለያየ መልክ፣ ቋንቋ፣ፍላጎት፣ ሃይማኖት፣ ብሄር ብሄረሰብ ላለው አገር ሰላም በጣም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ ሰላምን ለማስፈን እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል፡፡
ሰላም የማስፈኑ ሥራ በጣም አሳሳቢ መሆኑን የተናገሩት አቶ ለማ፤ አሁንም መጠኑና ቁጥሩ ቢቀንስም በየቦታው ሰዎች እየሞቱ፣ እየተፈናቀሉና በየአካባቢው የሚገኙት አንድነትን የሚያለያዩ መሆናቸው እንደሚያሳስብ ገልጸዋል፡፡ የአገር እድገትና የዴሞክራሲ ግንባታ የሚኖረው ሰላም ሲሰፍን መሆኑን ጠቁመው ሁሉም ኅብረተሰብ ለሰላም መስፈን እንዲተባበርም ጠይቀዋል፡፡
የፖለቲካ ሥራ ህዝብን ማቀራረብና አገርን ማሳደግ እንዳለበት በመግለጽ፤ ህዝብን፣ ቤተሰብንና ማህበረሰብን የሚያለያይ ፖለቲከ ወንጀል በመሆኑ ሊወገዝ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ምሁራንና የሃይማኖት አባቶች ማኅበረሰብን በማስተማር ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ ማህበራዊ ድረ ገጽ አብሮነትንና ሰላምን የሚያውክ መረጃዎች እንዳይተላለፉበት፣ መልካም ስነ ምግባር ያለው ትውልድ እንዲታነጽ መሰራት እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡
የሰላም አምባሳደር እናቶች 21 አባላትን ያቀፈው የልዑካን ቡድኑ ዛሬ 14ኛ ቀናትን አስቆጥሯል፡፡ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ሲሆን፤ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በመገኘት ሰላም እንዲሰፍን ድርሻቸውን እየተወጡ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2011
በዘላለም ግዛው