ከስድስት ዓመታት በፊት ‹‹ታሪኩ ማንደፍሮና ጓደኞቻቸው ህብረት ሽርክና ማህበር›› ሲመሰረት ያለስራ የሚውሉ እጆችን አስተባብሮ ለመልካም ውጤት የማብቃት ዓላማ ላይ ተመስርቶ ነው። የእህል በረንዳና አካባቢው ወጣቶች ቀደም ሲል ያለ አንዳች ስራ ተቀምጠው መዋል ብርቃቸው አልነበረም። እንዲህ መሆኑ በርካቶች አልባሌ ቦታ እንዲገኙና ለተለያዩ ሱሶች እንዲጋለጡ ማድረጉ አልቀረም፡፡
እውነታውን በቅርብ ሆነው የሚያስተውሉ ጥቂት የአካባቢው ፍሬዎች ታዲያ ይህ ታሪክ በበጎ ይቀየር ዘንድ በብርቱ ይመክሩ ያዙ። አካባቢያቸው ከመላው አገሪቱ እህል በኩንታል እየተጫነ የሚዘረገፍበት ስፍራ ነው። ይህን ተከትሎም በየቀኑ በሚሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ዝውውር ሲካሄድበት ይውላል፡፡
ሶስቱ ወጣቶቸ በብርቱ ሲመክሩበት የቆዩትን ቁምነር ለብቻቸው አልያዙትም። ከወረዳው አስተዳደሮች ጋር ጊዜ ወስደው ተወያዩበት። ዓላማቸውን በወጉ የተረዱት አካላትም የሚሉትን ሰምተው ከሀሳባቸው ሊጣመሩ ወደዱ። ወጣቶች ከዚህ ይሁንታ በኋላ ጊዜ መውሰድ አልፈለጉም። በቁጥር ሰባ የሚሆኑ ፈቃደኛ ወጣቶችን አስተባብረው የመኪና ፓርኪንግ ሥራን ጀመሩ። ጅምር ተግባሩ እንቅስቃሴው ሲፋጠን ከእርምጃቸው ያልተጣመሩ ጥቂቶች ከመንገድ ሊቀሩ ግድ አለ። ውሎ አድሮ ስልሳ አራት ወጣቶች በሀሳብና ፍላጎት የተጣመሩበት የሽርክና ማህበር አንድነቱን አጎልብቶ በመንገዱ ቀጠለ፡፡
ማንደፍሮ በዳዳ የታሪኩ ማንደፍሮና ጓደኞቻቸው ኅብረት ሽርክና ማህበር ሰብሰቢ ነው። ማህበሩ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከኮሚኒቲ ፖሊሲንግ ጋር በሕብረት እንደሚሰራ ይናገራል። የማህበሩ አባላት በየወሩ ከሚያገኙት ገቢ በመቆጠብ ለአካባቢያቸው ነዋሪዎች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦም የበርካቶችን ጎን ደግፏል።
በአካባቢው ‹‹የድሀ ድሀ›› በሚል ተለይተው የሚታወቁ ወገኖች የመኖር አቅማቸው በእጅጉ ደካማ የሚባል ነው። በርካቶችም በዕድሜ መግፋት፣ በገቢ ማነስና በሕመም ምክንያት የሚንገላቱ ናቸው። የሽርክና ማህበሩ አባላት እነዚህን ወገኖች እያዩ ዝም ማለትን አልፈለጉም። በየወሩ ከአባላቱ ተቆጥቦ ከሚገኝ ገቢ የምግብ ፍጆታን በማቅረብ፣ ቤታቸውን በማደስና በመጠገን፣ እንዲሁም የትምህርት መሳሪያና አልባሳት ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ተገቢውን ድጋፍ በማሟላት ሕብረተሰቡን በበጎ ፈቃድ ያገለግላሉ፡፡
ማህበሩ በፈታኙ የኮሮና ዘመን አቅማቸው ለደከመ የዕድሜ ባለጸጎች ድጋፉን ከማድረግ አልተቆጠበም። ይህን በጎነት የሚያውቁ በርካቶች ታዲያ ለችግሮቻቸው መፍትሄ የሚያደርጉት የታሪኩ ማንደፍሮና ጓደኞቻቸው ማህበርን ሆኗል። አቅማቸው የተፈተነ፣ ችግራቸው የበዛ፣ ሸክማቸው የከበደ ሁሉ ወደ ወጣቶቹ ቀረብ ብለው መፍትሄውን ይሻሉ፡፡
ማኅበሩ የተትረፈረፈ ገቢና ሀብት ባይኖረውም የወገኖቹን ችግር ለማዳመጥ ጆሮው የሰፋ ነው። ሁሌም የአቅሙን ለመስጠት ወደኋላ አይልምና የበርካቶችን ዕንባ አብሷል። እንዲህ በመሆኑ የተለየ ትርፍና ዋጋ የለውም። ሁሌም ቢሆን የማህበሩ አባላት ንጹህ ክፍያ ከውጤት በኋላ የሚገኝ የህሊና እርካታና የመንፈስ ጥንካሬ ነው።
ሰብሳቢው ማንደፍሮ በዳዳ እንደሚለውም በወጣቶቹ እንቅስቃሴ የቀደመው የአካባቢው ክፉ ስም በበጎ ተለውጧል። ቀደም ሲል በእህል በረንዳና አካባቢው በርካታ ወንጀሎች ይፈጸሙ ነበር። በጠራራ ጸሀይ ማጅራት እየተመታ ዝርፊያ ይካሄዳል፣ ገበያተኛው በዘራፊዎች እየተዋከበ ይጭበረበራል። እህል ጭነው የሚመጡ ሾፌሮችና መኪኖቻቸው በሰላም ገብተው ለመውጣት ታላቅ ስጋት ነበራቸው፡፡
ዛሬ ግን ያለፈው ታሪክ በ‹‹ነበር›› ተሸኝቷል። ይህን ይፈጽሙ የነበሩ ወጣቶች በድርጊትና በአመለካከታቸው ተቀይረው አካባቢያቸውን ለውጠዋል። ከራሳቸው አልፈውም ለሌሎች ጭምር ተርፈዋል። አሁን ስራ እንጂ ወንጀል ይሉት እንደማይበጅ የሚያስረዱ ወጣቶች ጥቂቶች አይደሉም። በመስራት መቀየር፣ በጎውን በማሰብ በጎ መሆንን በተግባር የሚያሳዩ በርካቶች ናቸው፡፡
ወጣቶቹ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት በማስከበር በኩል ደጀንነታቸውን ያሳያሉ። ለዚህም ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ውጤታማ አድርጓቸዋል።
የአካባቢው የስራ ባህርይ ከተለያዩ ክልሎች ተነስቶ መዳረሻውን አዲስ አበባ እህል በረንዳ ላይ ያሳርጋል። ይህ አይነቱ ማካለል ደግሞ ሁሌም በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚታይ ላይሆን ይቸላል። አንዳንዴ እህል ጭነው የሚገቡ መኪኖች ከጥርጣሬ ዓይን የራቁ አይሆኑም። ከጭነት ባሻገር ሊያዘዋውሩ የሚችሉት ጉዳይ አይታወቅምና መኪኖቹን ከአሽከርካሪዎቹ መጠራጠር የተለመደ ይሆናል፡፡
ይህ አይነቱ ስጋት ይኖራል ተብሎ በታሰበ ጊዜም የማህበሩ አባላት እይታ ከሌሎች ዓይኖች ይለያል። ወጣቶቹ ከፖሊስ ባልተናነሰ እርምጃ በልዩ ትኩረት ለአካባቢያቸው ደህንነት ይንቀሳቀሳሉ። ይህኔ ብርታታቸው በተግባር፣ ውጤታቸው በማሳያ ይፈተሻል። ወጣት ማንደፍሮ እንደሚለውም ወንጀልን ለመከላከል ከፖሊስ ጋር ተቀኛጅቶ መስራቱ የላቀ አስተዋጽኦ አለው። በአንዳንዶች ዘንድ ግን ቅንጅቱ በበጎ ላይታይ ይችላል። ከመስራት ይልቅ መቀመጥን የሚወዱ ጥቂቶች በጎውን በክፉ እያባዙ መልካም ስምን ማጠልሸትና ሰውን ዝቅ ማድረግ ልማዳቸው ነው። ጥቅሙን አሳምረው የሚያውቁት ብርቱ ወጣቶች ግን ከጀመሩት ስራ ወደኋላ አይመለሱም። እንደውም በብርታት ጠንክረው ወደፊት ለመራመድ አጋጣሚውን ይጠቀሙበታል፡፡
ወጣት ማንደፍሮ አንደሚለውም፤ ይህ አይነቱ አጋጣሚ በስራቸው መሀል ከሚገጥማቸው ፈተናዎች ውስጥ አንዱ ነው። እነሱ ግን በድካማቸው መልካም ፍሬን በማግኘታቸው ከማንም በላይ ደስተኞች ሆነዋል። ትናንት ስደትን ያስቡ የነበሩ፣ ተስፋ ቆርጠው በቁዘማ የተቀመጡ፤ በሱስ ተጠምደው ከአልባሌ የዋሉ ሁሉ ዛሬ ታሪካቸው ተቀይሯል፡፡
በማህበሩ ካሉት ግማሽ በላይ የሚሆኑት አባላት ትዳር ይዘው ቤተሰብ መስርተዋል። ይህ የሆነው ኃላፊነትን ስለተማሩና የእኔ የሚሉት መተዳደሪያን ስላገኙ ነው። ወጣት ማንደፍሮ እንደሚያረጋግጠውም በእህል በረንዳና አካባቢው ከተደራጁት መካከል የመጀመሪያውና ግንባር ቀደሙ የእነሱ ማህበር ነው። አሁን ላይ ፈለጋቸውን የተከተሉ ሌሎች ሰድስት አቻ ማህበራትም በተመሳሳይ ዓላማ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ማህበራቱ በአብዛኛው ከእስር የተፈቱና ከስደት የተመለሱ ወጣቶችን ያቀፉ ናቸው። የእነ ማንደፍሮ ማህበር ራስን ችሎ ከመተዳደር ባለፈ ለሌሎች ሰዎች ጭምር የስራ ዕድል በመፍጠር የደሞዝ ተከፋይ ማድረግ ችሏል፡፡
የማህበሩ አባላት በየሶስትወሩ በበጎፈቃደኝነት የደም ልገሳ ያካሂዳሉ። በሰላም ማስከበር ዘመቻው ወቅትም ግንባር ድረስ በመጓዛ የአቅማችውን አበርክተዋል። አባላቱ ሁሌም መንደር ሰፈሩን በጽዳት ለማስዋብ የሚያህላቸው የለም። አካባቢው ድህነት ያጠቃውና ከፍተኛ ለውጥን የሚሻ በመሆኑ ስራ ጠፍቶ አያውቅም። ማህበሩ በየጊዜው በሚያከናውነው ጠንካራ እንቅስቃሴም የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
አንዳንዴ በአካባቢው ህሊናን የሚፈትን አቅምን የሚገዳደር ጉዳይ ሊያጋጥም ይችላል። እንዲህ በሆነ ጊዜም የማህበሩ አባላት በበጎነት መንቀሳቀስ ልማዳቸው ነው። በአንድ ወቅት በአካባቢያቸው የምትኖርና በጥንካሬዋ የምትታወቅ አንዲት ሴት የኩላሊት ህመም ገጥሟት አልጋ ትይዛለች፡፤ ይህን የተረዱት ወጣቶች ታዲያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የመኖሪያ ቤትና የህክምና እርዳታ እንድታገኝ ያደርጋሉ። ህይወቷ እስከሚያልፍም በእንክብካቤ እንድትቆይ ያግዟታል፡፡
በየጊዜው ይህ አይነቱን እውነታ የሚያስተውለው የአካባቢው ነዋሪ ትናንት የሆነበትን ክፉ ታሪክ አያስብም። ይልቁንም ዛሬ ለችግሩ ፈጥነው በሚደርሱት ወጣት ልጆቹ አመኔታን አሳድሯል። ወጣቶቹም ቢሆኑ አካባቢያቸውን በፍቅርና በስራ ትጋት መለወጥ በመቻላቸው የህሊና እረፍትን እንዲያገኙ ሆነዋል። ወደፊትም ያሰቡትን ከግብ ለማድረስ በፍጥነታቸው ልክ ለመሮጥ ዝግጁ ናቸው።
ወጣት ታሪኩ አስራት የማህበሩ ምክትል ስራ አስኪያጅ ነው። ታሪኩ በተለይ የአካባቢን ደህንነት በማስጠበቅ ሂደት ያለው እንቅስቃሴ በመግባባት እንደሚሰራ ይናገራል። አካባቢው ተወልደው ያደጉበት አንደመሆኑ ማን ምን እንደሚሰራ ለማወቅ ርቀው አይጓዙም። የእያንዳንዱን ውሎና የግል ባህርይ ጠንቅቀው ለማወቅ አብሮነታቸውን ብቻውን በቂ ነው።
ታሪኩ ወጣቶቹ ተጣምረው በመስረታቸው ያገኙት ውጤት ለተሻለ ለውጥ እንዳበቃቸው ይናገራል። ይህ ሂደት በአነስተኛና ጥቃቅን አደረጃጀት ሽግግሩን ለማቀላጠፍ ጭምር አግዟቸዋል። አካባቢው ከስጋት ያልራቀ እንደነበር የሚያስታውሰው ታሪኩ ዛሬ ላይ ወጣቱ ከራሱ አልፎ ለህብረተሰቡ መኖር እችላለሁ ብሎ አስኪተማመን ለውጥ መገኘቱ ያኮራዋል ፡፡
እነ ታሪኩና ጓደኞቻቸው በዚህ ማህበር ከመደራጀታቸው አስቀድሞ ከሾፌሮች ጋር በመግባባት አንዳንድ ስራዎችን ይከውኑ ነበር። ይህ ራስን የመርዳት ሂደት ግን በበጎ የሚተረጎም ሳይሆን ቀርቶ ወጣቶቹን ባልተገባ ስም በማሳደድ በወንጀል ጭምር እስከማስጠየቅ ያደርስ እንደነበር ታሪኩ ያስታውሳል፡፡
እንዲህ መሆኑ በወቅቱ ትምህርታቸውን ጨርሰው እንጀራን ለሚሹ ወጣቶች ሆድ ሲያስብሳቸው ቆይ ቷል። በኋላ ግን ክፉ አጋጣሚው ለበጎ እልህና ቁጭት አነሳስቶ በማህበር እንዲደራጁ ምክንያት ሆነ፡፡
ዛሬ ላይ የማህበሩ አባላት በአነስተኛና ጥቃቅን አደረጃጀት ባገኙት ሽግግር ህጋዊ ቢሮና ሰፊውን ስራ ተረክበው ፈጣን ርምጃ ላይ ይገኛሉ። ትናንት በእነሱ መንገድ የተጓዙ አቻ ማህበራት ዛሬ ወደተሻለ ጎዳና አልፈው ነገን በልጦ ለመገኘት በሩጫ ላይ ናቸው። በጓደኛሞቹ ስያሜ የተዋቀረው ማህበርም እነሱ ያለፉበትን መንገድ ተከትሎ ቀድሟቸው ለመሄድ ሌት ተቀን እየተጋ ይገኛል፡፡
ወጣት ታሪኩም ስለ ነገው ሕልማቸው ሲያወጋ የኢንዱስትሪውን መንገድ ለመከተል መዘጋጀታቸውን ይናገራል። ከታሰበው ደረጃ ላይ ለመድረስም አሁን ያሉበት እንቅስቃሴና የስራ ፍላጎት መሰረት እንደሚሆን ሲናገር በእርግጠኝነት ነው። ከሁሉም ማህበራት በከፍተኛ የአባላት ቁጥር የሚንቀሳቀሰው ማህበራቸው ነገን ዕውን ለማድረግ ክንደ ብርቱና ዓላማ ሰፊ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
ወጣት ቤዛ ደሞዜ ማህበሩ በወር ደሞዝ ቀጥሮ ከሚያሰራቸው ሰራተኞች መካከል አንዷ ነች። ቤዛ የአካባቢው ልጅ ነች። በማህበሩ በሂሳብ ተቀባይነት የምታገለግለውም በወር ደሞዝ ተቀጥራ ነው። ወጣቷ የስራ ዕድል ተፈጥሮላት ራሷንና ቤተሰቦቿን ማስተዳደር መቻሏ ከልብ ያኮራታል፡፡
ወጣት ንጉስ አድነው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የወረዳ አራት ህብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ነው። ጽህፈት ቤቱ በበጋና የክረምት አገልግሎቶች የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ይናገራል። አካባቢው የእህል በረንዳ እንደመሆኑ በተለያዩ የስራ አማራጮች የመሰማራት ዕድልን ይፈጥራል።
ወጣት ንጉስ እንደሚለውም ለአካባቢው ይህ አይነቱ አጋጣሚ መኖር ለነዋሪው ጸጋ ነው ተብሎ ይታመናል። ይሁን እንጂ ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ወጣቶችን በማህበር አደራጅቶ ተጠቃሚዎች ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ የጽህፈት ቤቱ አንዱ መገለጫ ነው፡፡
የአካባቢው ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ከሚያገኙት ገቢ ለበጎ ፈቃድ ተግባር ማዋላቸው በርካቶችን እንደጠቀመ ወጣት ንጉስ ይመሰክራል። በአካባቢው የመኖሪያ ቤት እድሳት ለሚደረግላቸው ወገኖች እገዛ ከሚያደርጉት መሀልም በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ዋንኞቹ ናቸው። የአካባቢው ነዋሪ ዎች ስራው በበጎ ፈቃደኞቹ ልጆቻቸው መከወኑ የበለጠ ያኮራቸዋል፡፡
በእህል በረንዳና አካባቢው የሚታየው የመረዳዳት ባህል አብሮ ከመኖር የመነጨ ስሜት በመሆኑ ሁሌም እንደ ባህል የተለመደ ሂደት ነው። በርካታ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ለመከወን የወጣቶች መልካምነት ወሳኝ መሆኑን የሚናገረው ኃላፊ ወጣቶቹ ራሳቸውን ከመርዳት አልፈው ለሌላው መጥቀም መቻላቸው ለአካባቢው ታላቅ ለውጥ እንደሆነ ይገልፃል። ወጣቱ በሙሉ አቅምና ፍላጎት የሚንቀሳቀሱ ሂደት ነገን በተስፋ ለመሻገር ለሚኖረው ሂደት አንድ እርምጃን የሚያራምድ ጉዞ መሆኑንም ወጣት ንጉስ በድምቀት ያሳምርበታል፡፡
ያልባከነው የወጣቶቹ ዕድሜ ጉልበትን ከፍላጎት አጣምሮ ለስራ ሲተጋ ይውላል። ትናንት በክፉ ይወሳ የነበረ ማንነትም ዛሬ በስራ ተፈትኖ ወርቅ የመሆኑን እውነት እያስመሰከረ ይገኛል። ይህ ታሪክ ለብዙዎቹ መሰል ወጣቶች መሰረት ይሆናልና ተምሳሌትነቱን ‹‹እነሆ!›› ብለነዋል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መስከረም 13/2015 ዓ.ም