ሰዎች ተለይተው የሚታወቁበት ምክንያቱ ብዙ ነው። አንዱ በቁንጅናው፤ ሌላው ደግሞ በጀግንነቱ የተቀረው ደግሞ በዕውቀቱ … ሊታወቅ ይችላል። አንዱ በስንፍናው፤ አንዱ ደግሞ በአዘጥዛጭነቱ። በሁሉም መስክ እንደዚህ እያሰቡ የልዩነቶችን ምክንያት መለየት ይቻላል። አንዳንዱ ጦር ሲሰብቅ፣ ሌላው ሰላምን ይሰብካል፤ አንዱ አገር ለማዳን ደፋ ቀና ሲል፣ ሌላው ”ምርጥ ዘር” በመዝራት፣ ለግጭትና ጥላቻ መደላድል ለመፍጠር፣ አገር ለማፍረስ ይራወጣል። ዛሬ አየሩን የተቆጣጠረው ደግሞ የዚህ አይነቱ ስራ መሆኑ ለቀባሪ እንደማርዳት ነው፡፡
ደራሲያንን አንድ ከሚያደርጋቸው ”ደራሲ”ነት ባሻገር ልዩነቶቻቸው በርካቶች ሲሆኑ፤ ከዘውግ (ዥነር) ጀምሮ፣ ”ስታየል”ን ጨምሮ ተቆጥሮ አያልቅም። ከቋንቋ አጠቃቀም እስከ ቃላት ምርጫ፤ ከጭብጥ መረጣ እስከ ሴራ አወቃቀር ድረስ ልዩነታቸው ሰፊ ነው፤ ወዘተርፈ። ተክለጻድቅ መኩሪያም እንደ ማንኛውም ደራሲ ሁሉ እራሳቸው ከራሳቸው ጋር ብቻ የሚመሳሰሉ እውቅ፣ ታሪክ አዋቂና አፍቃሪ እናት አገር ደራሲ ናቸው።
ከላይ በጠቀስናቸው ብቻ አይደለም፤ ተክለጻድቅ መኩሪያ በብዙ መንገድ ከብዙዎች ይለያሉ። የቆሙበት መሰረት ቱባው የኢትዮጵያ ታሪክ መሆኑ ቀዳሚ ልዩነታቸው ነው። በዚሁ ታሪክ ላይ የተመሰረተው ቋሚና የማይናወጥ የአገር አንድነት አቋማቸው ሌላውና ቀጣዩ ልዩነታቸው ነው። ”የኢትዮጵያን ታሪክ እንዴት ከተክለፃዲቅ ውጪ ማሰብ ይቻላል?” ይባል ዘንድ ግድ ማሰኘታቸው ከጠቀስናቸው እኩል እሳቸውን ከሌሎች የምንለይበት ”ነጥብ” ሆኖ ይመጣል።
ስለ ዛሬው ባለውለታችን ግለሰባዊ ማንነት ብዙ ተብሏልና ዛሬ በዝርዝር የምናየው አይሆንም። ይሁን እንጂ አንድ መታለፍ የሌለበትን (ከ“ያሠርቱ ምእት፣ የብርዕ ምርት” ተወስዶ ድረ-ገጽ ላይ ለንባብ የበቃ) መሰረታዊ ጉዳይ ቁጭ አድርጎ ማለፍ ግዴታችን ሲሆን እሱም፤
ተክለጻድቅ መኩርያ በ ፲፱፻፮ (1906) ዓ.ም በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ፣ አሳግርት፣ ልዩ ስሙ ”ሳር አምባ” በተባለ ሥፍራ ተወለዱ። ዕድሜያቸው ለትምሕርት ሲደርስ መጀመሪያ ከአባታቸው፣ ቀጥሎም በአጥቢያቸው ባህላዊውን ትምሕርት እስከቅኔ ድረስ ቀስመዋል። ከዚያም አዲስ አበባ መጥተው አሊያንስ ፍራንሴዝ እና ተፈሪ መኮንን ትምሕርት ቤት ገብተው የጊዜውን የትምሕርት ደረጃ ተከታትለው አጠናቅቀዋል። ኢጣልያ አገራችንን በወረረችበት ወቅትም በየካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. ፍጅት ተይዘው ወደ ሶማሌ፣ ደናኔ ተግዘው ለሦስት ዓመታት ታስረዋል። ከነጻነትም መልስ አገራቸውን በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች አገልግለዋል።
“የኢትዮጵያ ታሪክ ከዓፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ” ከሆነው የበኩር ስራቸው ጀምሮ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ርቀው የሄዱት ተክለፃድቅ መኩሪያ ለዚህ ሁሉ መነሻ ምክንያታቸው ደግሞ ቁጭት እንደ ሆነ ራሳቸው መናገራቸው ለሰነድነት በቅቶ የታሪካቸው አካል ሆኖ፤ በማህበራዊ ጉዳይ ላይ “የሰው ጠባይና አብሮ የመኖር ዘዴ”ን በመጻፍ መልካም ማህበረሰብ ግንባታ ላይ አስተዋፅኦዋቸው ጉልህ መሆኑን አስመሰከሩ።
ከላይ እንደ ዘበት ጣል ያደረግነውን እንደ አንድ ራሱን የቻለ ጥያቄ አድርገን እናንሳው። ለመሆኑ ”ተክለጻድቅን ለታሪክ ጸሐፊነት ምን አነሳሳው?” ስንል፤ የምናገኘው ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው የተባሉ ሰው ስለ ተክለጻድቅ በጻፉት መጣጥፍ ላይ፤ የሚከተለውን ብለዋል፡፡
በ1936 ተክለፃዲቅ መኩሪያ የተባለ ጎበዝ በትምህርት ሚኒስትር ውስጥ ይሰራ ነበር። ይህ ወጣት ለታሪክ ልዩ ፍቅር ነበረው። ታዲያ ይህንን የታሪክ ጥማት ለማርካት ወደ ቤተመጻሕፍት ጎራ ብሎ በአማርኛ የተጻፉ የታሪክ መጻሕፍትን ቢያፈላልግም አልተሳካለትም። ቢያገላብጥ ካርሎ ኮንቴ ሮሲኒ፣ ቢገልጥ ፍራንቺስኮ አልቫሬዝ፣ አንቶኒቼሊ ፍራንኮ ወይም ዴል ቦካ ናቸው። ታሪካችን በነጮች ተወሯል። የአገሩ፣ የወንዙ ልጅ የታሪክ ጸሐፊ አንድም የለም።
ለዚህ ብርቱ ወጣት ይህ አሳሳቢ ነው። የራሳችን ታሪክ እኛው መጻፍ አለብን፤ የራሳችንን የቤት ስራ እኛው መስራት አለብን። የታሪክ ጽሑፍ ሊዛባ ይችላል። በተለይ የባእድ ሰዎች ለራሳቸው በሚመቻቸው መልኩ ሊጠመዝዙት ይችላሉ። በዚህ ምክንያት የታሪክ ጽሑፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋል። በውጪ ኃይል ’እንካችሁ፤ ታሪካችሁ ይሄ ነው’ መባልን አንሻም።
ያለው ሆኖ እናገኘዋለን። ወደ ርእሳችን እንመለስ።
ርእሳችን ”የኢትዮጵያ አንድነት”ን ቁልፍ ጉዳዩ አድርጎ እንደመነሳቱ መጠን የምናተኩረውም ዛሬ የምናስታውሳቸው እንግዳችን ያመረቷቸው ከ10 በላይ (ከ15 አመታት በላይ የደከሙበት “የግራኝ አህመድ ወረራ” የተሰኘ መጽሐፋቸው በ155 ምእራፎችና በ840 ገፆች በካርታ፣ በሰንጠረዥ፣ በፎቶግራፍ … መረጃዎች የሞላውን ስራቸውን ጨምሮ፤ እንዲሁም፣ ”ከሞትኹ በኋላ ይታተምልኝ” ያሉትን ግለታሪካቸው (Autobiography)ን ሳይጨምር) ጠብሰቅ ጠብሰቅ ያሉ ስራዎች ላይ ሳይሆን፤ ሶስቱ፤
• አፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት፣
• አፄ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት፣ እና
• አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት፤
ላይ ይሆናል።
እነዚህን፣ ታላላቅ ነገስታቱ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ክብርና ብልፅግና፤ እንዲሁም ስልጣኔና እምነት ያደረጉትን ታላላቅ ተግባራትና ክንውኖች፤ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ፤ እንዲሁም ድክመትና ጥንካሬያአቸውን የከተቡባቸው ትላልቅ የታሪክ መጻሕፍትን፤ በተለይ የማንሳታችን ጉዳይ አቢይ መንስኤው የሶስቱም ማሰሪያ ገመድ ”የኢትዮጵያ አንድነት” መሆኑና ሶስቱም መጻሕፍት ከኢትዮጵያም አልፎ በአለም አቀፍ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራን የያዙ ከመሆናቸው አኳያ ነው።
የሶስቱም ርእሶች ለተጻፉበት ዘመን ምስክሮች ናቸው፤ ሶስቱም ርእሶች መጠነ ርእያቸው ሰፊና ጥልቅ ነው፤ የሶስቱም መጻሕፍት ርእሶች የምን ግዜም የሕዝብ ድምፆች ናቸው፤ ሶስቱም ርእሶች የጸሐፊውን እምነት፣ ርእዮት፣ አቋም፣ ፍላጎት … በሚገባ ያንፀባርቃሉ። ሶስቱም ርእሶች ዘመን ተሻጋሪዎች ናቸው። የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ማንነቶች ናቸው።
በተለይ ዛሬ ላይ ሆነን ስንመዝናቸው ሶስቱም ርእሶች የሰጉት (ስጋት የገባቸው) ነገር ያለ ይመስላል፤ ሶስቱም የትንቢታዊነት (ፕሮፌቲክ) ባህርይ አላቸው። ድሮ ላይ ሆነው ዛሬን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱንም የተለሙ ናቸው። ከመለያየት አንድነት፤ ከመጋጨት መተባበር፤ ከጦርነት ሰላም ወዘተርፈ መሆኑን አስቀድመው ያዩና አይተውም ምክረ ሀሳባቸውን እነሆ ያሉ ናቸው። የተክለፃድቅ መኩሪያ ውለታ እዚህ ድረስ ነው።
ከሶስቱም ግዙፍና በታሪክ ወሳኝ ከሆኑት እነዚህ ስራዎቻቸው የምንረዳው አንድ መሰረታዊ ጉዳይ ቢኖር ተክለጻድቅ ለአንድነት፤ ማለትም ለኢትዮጵያ አንድነት ልዩ ስፍራ መስጠታቸውን ብቻ ሳይሆን የአንድነትን አስፈላጊነት በአንባቢ አእምሮ ውስጥ ለማስረፅ ያላቸውን ብርቱ ፍላጎት ጭምር ነው። እንዲሁም፣ ሰው ከታሪክ ይማር፣ የአሁኑን ያስተካክል፣ የወደፊቱን ከወዲሁ ያቃና ዘንድ የተበረከቱ ናቸው።
ይህ ብቻም አይደለም፤ በኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ ውስጥ የነበሩት መሪዎች ለአገርና ህዝብ አንድነት ምን ያህል ትኩረት ሰጥተው ይሰሩ እንደ ነበር ጭምር፣ ገና ወደ ውስጥ ሳንዘልቅ በርእስ ደረጃ ያስተላለፉት ቁልፍ መልእክት ሆኖ እናገኘዋለን።
አሁንም ”ለተክለጻድቅ መኩሪያ አንድነት ምንድን ነው? ለምንስ መሪዎቹን ይህንን በሚያክል ቁልፍ ቃል ማስተሳሰር ፈለገ፣ ምን ለማለትስ ፈልጎ ነው በአንድነት ጉዳይ ላይ ይህንን ያህል የተጠመደው?” ብለን መልሰን መላልሰን ልንጠይቅ የሚገባን መሰረታዊ ጉዳይ የመሆኑ ነገር እንዳለ ሆኖ፤ ታሪክን ወደ ኋላ ሄደን እንድንመረምር፤ በጭፍንና በጥላቻ፣ በደመነፍስ እንዳንሄድ ጥሩ አጋጣሚን የመፍጠር ተግባሩ ለባለውለታነቱ ሌላው አስተዋፅኦ ነው።
ይህ ብቻም አይደለም፤ አሁን የአገራችን ከፍተኛ ችግርና ቀውስ የአንድነት ችግር መሆኑ ሲታይ የደራሲው ምን ያህል ቀድሞ ሄዶ እንደ ነበር፤ አርቆ ተመልክቶ እንደ ነበር … ተንብዮ እንደ ነበር … ሁሉ እንረዳለን። የማስተማር አቅሙ በራሱ ለተክለጻድቅ መኩሪያ እዚህ መነሳት ከበቂ በላይ የሆነ ምክንያት ነውና ይህ በትውልዶችም የሚቀጥል እንደሚሆን ከወዲሁ መናገር ይቻላል።
”አንድነት፣ በተለይም የኢትዮጵያ አንድነት ለተክለጻድቅ ምኑ ነው?” የሚለውን ብቻ እንመልከት።
ከጠቀስናቸው ሶስት ስራዎቹም ሆነ ሌሎቹ እንደምንረዳው ለተክለጻድቅ አንድነት ማለት አገር ነው፤ አንድነት ማለት ህዝብ ነው፤ አንድነት ማለት የበሳል አመራር ውጤት ነው፤ አንድነት ማለት የአንድ ሕዝብና የአንድ አገር ሁነኛ መገለጫ ነው፤ አንድነት ማለት ሰላም፣ ፍቅር፣ ደስታ … ማለት ነው። አንድነት ታሪክ ነው። ታሪክ ያለ አንድነት እንደማይኖር ሁሉ ታሪክ የሌለው አንድነትም አይኖርም።
ከሶስቱ ስራዎች እንደምንረዳው፣ የመሪዎች ተግባርና ኃላፊነት የአገር አንድነትን ማፅናት ነው፤ ሉአላዊነትን ማስከበር ነው፤ ለአንድነት በአንድነት የቆመ ህዝብ መገንባት ነው፤ ብሔራዊ መንግስት ምስረታ ላይ መበርታት ነው፤ የወከለን ህዝብ በአግባቡ ማገልገል ማለት ነው፤ ከታሪክ ተጠያቂነት ራስን ማፅዳት ነው ….።
ስለ እኝህ፣ በኢትዮጵያ የታሪክ ጥናት ውስጥ ሳይጠቀሱ ስለማይታለፉት ሰውዬ ቀለል ባለ መልኩ ”ኢጣልያ አገራችንን የወረረች ጊዜም በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ፍጅት ተይዘው ወደ ሶማሌ ደናኔ ተግዘው ለሦስት ዓመታት ታስረዋል። ከነጻነትም መልስ አገራቸውን በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች አገልግለዋል።” የሚለውን ይዘን፤ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፤ ስለ አገርና ሕዝቧ አንድነት፤ ስለ ጠላትና ወዳጆቻችን …. አብዝተው መጠበባቸው ላይ ስንደርስበት የአንድነት ሚስጥሩ ወለል ብሎ ከመታየቱም በላይ፤ የታሪክ ጸሐፊውም ለኢትዮጵያ አንድነት ልዩ ትኩረት መስጠታቸውንም እንገነዘባለን። ስለ አንድነት መስበካቸው፤ ስለ አንድነት ማስተማራቸው፤ በተለያዩ ጊዜያት የነበሩ ሶስት መሪዎችን እንደ ሶስቱ ስላሴዎች ”አንድም ሶስትም” በማድረግ በኢትዮጵያ አንድነት ማስተሳሰራቸው ወዘተርፈ ሚስጥሩ ቢገለጥልን እንጂ አይሰወርብንም። (ብሩህ አለምነህ (2010 ዓ.ም) እንደነገረን የፈላስፋው ዘርዐያዕቆብ ሶስቱ ስላሴዎች፡- እግዚአብሄር፣ ተፈጥሮና ልቦና ናቸው።)
እውነትና አንድነት ስሙ መሆናቸውን፤ ያለ እውነት አንድነት ሊኖር እንደማይችል ከስሩ ማስመራቸውን፤ አገሪቱ የእውነት አገር፤ ስር የሰደደ የመንግስትነት ታሪክ ያላት አገር፤ የጀግኖችና ታታሪ ሕዝቦች አገር፤ በጠላት የተከበበችና ተመልካቿ ብዙ የሆነች አገር መሆኗን ወዘተርፈ ለማሳየት አንድነትን ማሰሪያ ገመዳቸው ማድረጋቸው በባለውለታመነት ቢያስመሰግናቸው አይበዛባቸውምና የታሪክ ጥናትን ለአገር ግንባታ ማዋላቸው ታላቅ ተግባር ነው። ”አንድ ከሆንን እንዘልቃለን፤ ከተከፋፈልን ግን እንሰምጣለን” የሚለው የአሁኑ ዘመን ፖለቲከኞች አፍ ሟሟሻ አባባልን እሳቸው አስቀድመው ተረድተው ሌላውም ይረዳው ዘንድ በታሪክ ለውሰውና አሽተው አቅርበውልናልና ተክለጻድቅ ዘመናቸውን የቀደሙ ጸሃፊ ናቸው ብንል ያስኬደናል።
በእነዚህ ጥልቅ የኢትዮጵያን ታሪክ በታቀፉ ሶስት መጻሕፍት ውስጥ ያለው ታሪክ በየርእሶቻቸው ፍንትው ብሎ የወጣ ቢመስልም በእያንዳንዳቸው ጉያ የሁላችንም ታሪክ አለና፤ የአገራችን ታሪክ አለና፤ ባህልና ቱባው እሴታችን አለና፤ ጀግንነታችን ሁሉ አለና … ደራሲው ልክ ሶስቱን ነገስታት ያስተሳሰሩበት አንድነት ለምን ግዜውም ይሰራልና ተክለጻድቅ በተነሱበት ሁሉ ስለ አንድነት ያላቸው አቋምም ሆነ አስተምህሯቸው አብሮ መነሳቱ የግድ ይሆናል ማለት ነው። ባጭሩ፣ በታሪክ ጸሐፊነት ብቻ ያልተወሰኑትና “የሰው ጠባይና አብሮ የመኖር ዘዴ” እና በሚዮቶሎዢያ (mythology) ላይ ያተኮረ “ከጣዖት አምልኮ እስከ ክርስትና” የሚሉም መጽሐፎች ለንባብ ላበቁት ተክለጻድቅ ”አንድነት” ማለት ባለቤት አለው – የኢትዮጵያ ህዝብ። ”አንድነት ለምን?” ብሎ ለጠየቀም መልሱ እዛው አለ – ”ለኢትዮጵያ” የሚል።
ሶስቱ መሪዎች የሚለያዩባቸው፣ በተለያዩ ወገኖች (ዛሬም ጭምር) በክፉም/ደግም የሚጠቀሱባቸው … መለያዎች አሏቸው። በተክለጻድቅ መኩሪያ ቁና የተሰፈሩት ግን ከአንድ መሰረታዊ ጉዳይ አኳያ ብቻ ሲሆን፤ እሱም ”የኢትዮጵያ አንድነት” ነው። በመሆኑም፣ የተክለጻድቅን ስራዎች ከብዙ እይታ አኳያ መፈተሽና አንዳች መደምደሚያ ላይ መድረስ የሚቻል ሲሆን፤ በተለይም ከብሔራዊ መንግስት (Nation-State) መመስረት አኳያ ቢታይ አገራዊና ወቅታዊ ፋይዳን እንደሚያስገኝ መናገር ይቻላል።
ሌላውና የታሪክ ተመራማሪው በአድናቂዎቻቸውና አጠቃላይ አንባቢያን ልብ ውስጥ ሰርስርው እንዲገቡ ካደረጓቸው ምክንያቶች መካከል (የተለያዩ ጥናቶች እንዳመለከቱት)፤
• ታሪክን ከተተበተበበት ልማዳዊ አጻጻፍ ነጻ አውጥተው በሰገላዊ መንገድ መጻፍ በመጀመራቸው፤
• ከአገራዊው መረጃ በተጨማሪ፣ በውጭ ቋንቋ ማለትም በጣልያንኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በእንግሊዝኛ ጭምር ያለውን ሁሉ ተጠቅመው ከስር እስከጫፍ የአገሪቱን ታሪክ በመጻፋቸው፤
• እኒህን ሁሉ መጻሕፍት የጻፉት በመደበኛ የቀለም ትምሕርት ቤት ሳይሰለጥኑ፣ በከፍተኛ የመንግሥት ሥራና ኀላፊነት ተጠምደው፣ ያላቸውን የመዝናኛ ጊዜ ሁሉ ሰውተው … ቁም ነገር በመሥራታቸው፤ እንዲሁም፣
• የእርሳቸው ዘመን የታሪክ ምሁራንም ሆኑ አሁን ያሉት ምሁራን በአብዛኛው የሚፅፉት በውጭ አገር ቋንቋ ሲሆን፤ እሳቸው ግን ለአገራቸው ህዝብ ሊገባው በሚችል መልኩ በአማርኛ በመጻፋቸው፤
• የዛሬን ያላዩት ገብረሕይወት ባይከዳኝ በ”አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” ተጠቃሽ መጽሐፋቸው ”ታሪክን መማር ለሁሉ ሰው ይበጃል፤ የታሪክ ትምህርት ግን የሚጠቅም የእውነተኛ ታሪክ ትምህርት ሲሆን ነው፤ እውነተኛውን ታሪክ ለመጻፍም ቀላል ነገር ኣይደለም፤ የአገራችን ታሪክ ጸሓፊዎች ግን በ’ነዚህ ላይ ኃጢኣት ይሰራሉ፤ በትልቁ ነገር ፈንታ ትንሹን ይመለከታሉ፤ በእውነት መፍረድንም ትተው በኣድልዎ ልባቸውን ያጠብባሉ” ያሉት በአሁኑ ዘመን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ባላነሰ ይጠቀሳል። ተክለጻድቅ ከዚህ አይነቱ ወቀሳ ነፃ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፤ ስራዎቻቸው እጅጉን ተጠቃሽ በመሆናቸው፤
• ከአሥራ አምሥት ዓመታት በላይ የደከሙበት “የግራኝ አሕመድ ወረራ” የተሰኘው መጽሐፋቸው በመቶ አምሳ አምሥት ምዕራፎችና ስምንት መቶ አርባ ገጾች በጽሑፍ፣ በካርታ፣ በሠንጠረዥ፣ በፎቶግራፍ … መረጃዎች ተጠናቅሮ የተሠራ ግዙፍ ሥራ በመሆኑ … በቀዳሚነት ይጠቀሱላቸዋል።
ሰውየው ከጣሊያን ወረራ በኋላ ከ1934 ዓ.ም እስከ 1935 ዓ.ም በመዝገብ ቤት ሹምነትና በሚኒስትር ፀሐፊነት ሰርተዋል። ከ1935-1966 ዓ.ም ደግሞ የምድር ባቡር ዋና ተቆጣጣሪ፣ በፓሪስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዋና ፀሐፊ፣ የጡረታ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር፣ በረዳት ሚኒስትርነት ማዕረግ የብሔራዊ ቤተመዛግብት ወመዘክር ዋና ኃላፊ፣ በሚኒስትር ማዕረግ በእየሩሳሌም ቆንስል፣ በቤልግሬድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገራቸውን አገልግለዋል። የአፄ ኃይለሥላሴ ስርዓት በኃይል ከተወገደ በኋላም በዘመነ ደርግ እስከ 1967 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ የትምህርትና የባሕል ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸውን ታሪካቸው ያወሳል። ከዚያም በጡረታ ተገለሉ።
ታላቁና የታሪክ ሊቁ ተክለጻድቅ መኩሪያ በተወለዱ በሰማንያ ስድስት ዓመታቸው ሐምሌ 16 ቀን 1992 ዓ.ም አረፉ።
ምን ግዜም፣ ስም ከመቃብር በላይ ነው !!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 11/2015 ዓ.ም