በኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት ዘርፉ ላይ ትላልቅ ለውጦች መምጣታቸው ይነገራል። እነዚህ ለውጦችም የመጀመሪያ፣ ሁለተኛ እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መብዛት፤ የተማሪዎች ቁጥር መጨመርና ለሴት ተማሪዎች የሚሰጠው ትኩረት ከፍ ማለት እንደሆነም ይገለጻል። ይሁን እንጂ ቁጥሩ ቢሰፋም ጥራቱ ግን አጠያያቂ እየሆነ እንደሄደ በዘርፉ ያሉ ምሁራን ይናገራሉ። ቤተሰብም ቢሆን የዘወትር ጥያቄው ልጆቻችን በቂ እውቀት እየጨበጡ አይደለም ነው።
ወደ ሥራ ቅጥርም ሲገባ እንዲሁ በቂ እውቀት ጨብጦ የሚወጣው ከስንት አንድ እንደሆነ ቀጣሪዎች ሲናገሩ ይደመጣል። እንዲያውም ለልምምድ ጭምር ወደ ኢንዱስትሪ ተቋማት ሲላኩ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ይሁንታ አናሳ የሆነው ከዚህ አንጻር እንደሆነም ይነሳል። ከጥራቱ ጋር በተያያዘ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ባሉት ክፍሎች ውስጥ ያሉ ተማሪዎች በብዛት የማንበብና የመጻፍ ችግር ያለባቸው እንደሆኑም ትምህርት ሚኒስቴር በሚያወጣቸው መረጃዎች በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር።
በመሆኑም ይህንን መፍትሄ መስጠት የውዴታ ግዴታ ነውና እንደ አገር በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ በርካታ ማሻሻያዎች ተደርጎ ወደሥራ ተገብቷል።
አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ በርካታ ማሻሻያዎችን የያዘ ሲሆን፤ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ላሉ የክፍል ደረጃዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት እንዲሰጥ ያስችላል። ከሰባተኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ያሉት ደግሞ ሁሉም ተማሪ በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲማር ይደረጋል። በእርግጥ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ያሉት ተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ መማር ግዴታቸው ነው። እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዲሰጣቸው ሥርዓቱ ያዛል። ከዚያም በተጨማሪ ሦስተኛ ክፍል ላይ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተጨማሪ ቋንቋዎችን ጭምር ለማስተማርና የእርስ በእርስ ትስስርን ለማጥበቅ የሚተገበር ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ የሚሰጥ የአጎራባች ቋንቋዎች ትምህርት አለ። ማለትም በክልሎች ውስጥ በርካታ ቋንቋ ይነገራልና የሚቀርበውንና በስፋት የሚነገረውን ተጨማሪ ቋንቋ በመምረጥ ተማሪዎቹ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዲወስዱ የሚያደርግበት አካሄድ ነው።
ሌላው በቀድመው የትምህርት ሥርዓት 10ኛ ክፍል ይሰጥ የነበረው አገራዊ የመልቀቂያ ፈተና እንዲቀር ተደርጓል። አጠቃላይ ፈተና በክልል ደረጃ ስድስተኛ ክፍል እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ስምንተኛ እና 12ኛ ክፍል እንዲሆን ተወስኗል። ከዚህ ቀደም ሦስት ዓመት የነበረው የተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ቆይታ ደግሞ ዝቅተኛው አራት ዓመት እንዲሆን ተደርጓል። ለሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች በመጀመሪያ ዓመት ከሚሠጡ ትምህርቶች ውስጥ እንደ ጂኦግራፊ፣ አንትሮፖሎጂ፣ ሶሺዮሎጂና ሥነ-ምግባር የመሳሰሉት ይካተታሉም ይላል።
የኢትዮጵያ ትምህርት ዘርፍ ጥራት ብቻ ሳይሆን ከሥርዓት እስከ አፈጻጸሙ ድረስ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑ ይነሳል። ማለትም እስከዛሬ በነበረው የማስተማር ሥርዓት ውስጥ የተማሪዎች ሥነምግባርን በአግባቡ ሊቀርጽ የሚችል ነገር አልነበረም በማለት አንዳንዶች መገለጫ ያስቀምጣሉ።ከዚያ ይልቅ ትምህርቱ ትኩረቱን ያደርግ የነበረው ፖለቲካ ላይ ነው የሚሉም አሉ። ለዚህም ማሳያው በሥነምግባር ስም የሚሰጠው የሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት ነው፤ ይህንን የትምህርት ሥርዓት ለማስተካከል እውቀትና ባህል፤ ግብረገብና ታሪክን ትውልዱ እንዲያውቁም አዲሱ የትምህርት ሥርዓት ዕድል ይሰጣል።
የፍኖተ ካርታ ተሰርቶ የትምህርት ሥርዓት አተገባበሩ ተፈትሾ በአዲስ መልክ ለመሥራት ሲታቀድ ብዙ ስኬቶችን ለማምጣት እንደሆነ በሙከራ ትግበራ አጀማመር፣ በተዘጋጁት የማስተማሪያ መጽሐፍትና በትምህርት አሰጣጥ ዙሪያ የአሰልጣኞች ሥልጠና በደብረብርሃን ከተማ በተከናወነበት ወቅት በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ ትምህርት ማበልፀጊያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ቴዎድሮስ ሸዋረገጥ ተናግረዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሥርዓተ ትምህርት ሪፎርሙ ግድ ነው። ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የሥርዓተ ትምህርት ሰነዶች የሚያካትታቸው የተማሪ ባህሪያት፣ የይዘት ፍሰት መርሀ ትምህርትና ሌሎች ዝግጅቶች ተከናውነው አምስት ዓመታትን በፈጀው ጊዜ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ ተደርጎ በሙከራ ደረጃ ተገብቶበታል።
በ2014 የትምህርት ዘመን በመላ አገሪቱ በተመረጡ 589 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአዲሱ የሥርዓተ ትምህርት የመማር ማስተማር የሙከራ ትግበራ ሲከናወን ቆይቷል። በ2015 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ከሙከራ በመውጣት በመላ አገሪቱ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ይተገበራል። በዚሁ ዓመት በተመረጡ 80 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የማስተማር የሙከራ ትግበራው ይከናወናል። ለዚህም የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሐፍት ዝግጅት እንዲሁም ስለ ትምህርት ሥርዓቱ የተለያዩ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ያስረዳሉ።
ፍኖተ ካርታው የተሻሻለውና አዲስ ሥርዓተ ትምህርት የተዘጋጀው በትምህርት ሥርዓቱ የመማር ማስተማሩን የጥራት ደረጃ ለማሻሻል፣ እንዲሁም ሙያዊ ግዴታውን በብቃት የሚወጣ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የትምህርት ማኅበረሰብ ለመፍጠር እንደሆነ የሚያነሱት ዶክተር ቴዎድሮስ፤ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ግብረ ገብነት፣ አገር በቀል ዕውቀቶች፣ ሙያና የቀለም ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ተግባር፣ ጥናትና ምርምር ትኩረት ተደርጎባቸው እንዲሰጡ ይሆናል።
ይህ ደግሞ ተማሪዎች የአገር በቀል እውቀት እንዲኖራቸው፤የግብረገብባለቤትእንዲሆኑ ያስችላቸዋል። በተጨማሪም የሥራና ተግባር ትምህርት ተካቶ ስለሚሰጣቸው የራሳቸውን ሥራ በራሳቸው እንዲፈጥሩ ዕድል ይፈጥርላቸዋል። ከተቀጣሪነት ተላቀው የራሳቸውን ገቢ የሚያመነጩ ተማሪዎች እንዲሆኑም ያደርጋቸዋል።
በ2002 ዓ.ም ተከልሶ እስከዛሬ ስንጠቀምበት የነበረው ሥርዓተ ትምህርት ብዙ ተግዳሮቶች ያሉበት እንደነበር የሚገልጹት ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ሥርዓተ ትምህርት ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ ዛፉ አብርሃ ናቸው። ለአብነት ካነሷቸው መካከልም የትምህርት ዓይነቶች መታጨቅ፤ የይዘት ስብጥሩ ክፍተት፤ ለተማሪዎች የሚሰጠው ይዘት ከብዶ መታየት፤ ተማሪ ተኮር አፈጻጸሞች ደካማ መሆን፤ የአገር በቀል እውቀትን ያላካተተ፤ ሥራና ትምህርትን ያላገናኘ፤ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ያላገናዘበ፤ የ21ኛው ክፍለዘመን ክህሎቶችን ያላካተተ፤ ተግባርና ትምህርትን ወደ አንድ አምጥቶ ዜጋን ከመቅረጽ አንጻር ያለውን ክፍተት ያልደፈነ መሆኑና መሰል ነገሮች ዳግም ሥርዓቱን ለማሻሻል ማስገደዱን ነው።
የሥርዓተ ትምህርቱን ማዕቀፍ በመያዝ ሦስት ትልልቅ ሥርዓተ ትምህርት ሰነዶችን እንደ አገር የትምህርቱን ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ መዘጋጀቱን የሚናገሩት ወይዘሮ ዛፉ፤ የመጀመሪያው የይዘት ፍሰት ሲሆን ሁለተኛው የብቃት መለኪያው ነው ፤ ሦስተኛው ደግሞ መርሃ ትምህርቱ ነው። እናም እነዚህን አካቶ የመማር ማስተማር ሥርዓቱ ይከናወናል።
የአዲሱ የትምህርት ዘመን መስከረም ዘጠኝ ሲጀመር ብዙ ዝግጅቶች ተከናውነውና ስልጠናዎች ተሰጥተው ነው። ይሁን እንጂ አሁንም ቀሪ ሥራዎች ያሉበት እንደሆነ የሚገልጹት ኃላፊዋ፤ በትምህርት አጀማመሩና የሥርዓተ ትምህርት ክለሳው ላይ ዓመታት የተቆጠሩበት ነው። ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉበትና ብዙ ጉልበትና ገንዘብ ፈሶበታል። ስለሆነም ትግበራው እርሱን በሚመጥን መልኩ የሚከወን ይሆናል ብለዋል።
አተገባበሩ አሁንም ብዙ መሻሻሎችን የሚጠይቅና በሂደት ነገሮች እየታዩ የሚታረሙ እንደሆነ የሚያነሱት ወይዘሮ ዛፉ፤ ሙሉ ለሙሉ የሚተገበርባቸው የክፍል ደረጃዎች እንዳሉ ሁሉ በዚህ ዓመት በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የማይካተቱም ይኖራሉ፤ ለምሳሌ 11ኛ እና 12ኛ ክፍሎችን እዚህ ላይ ማንሳት ይቻላል። ስለሆነም ሙከራቸውን የሚጀምሩት በ2016 ዓ.ም እንደሚሆን ይናገራሉ።
አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ የግልም ሆኑ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ቢተገበሩም በኤምባሲዎች በሚተዳደሩ ዓለም አቀፍና የማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች ላይ ተግባራዊ አይሆንም ብለዋል። እዚህ ላይ ግን ከትምህርት ሚኒስቴር እውቅና ውጪ ራሳቸውን ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ነን ያሉትን የማይጨምር እንደሆነ አስገንዝበዋል።
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፤ ሥርዓተ ትምህርቱ በዚህ ዓመት ሙሉ እና የሙከራ ትግበራ ከተደረገበት በኋላ በ2016 ዓ.ም የሚኖሩ ችግሮችን በማስተካከልና የማዳበሪያ ሃሳቦችን በመጨመር ሙሉ ለሙሉ ወደ ትግበራ የሚገባ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው። ለምሳሌ የዘጠነኛና የአስረኛ ክፍል መጻሕፍት ዝግጅት፣ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ የተመረጡ አምስት የትምህርት ዓይነቶችን ዝግጅት ማድረግ ነው። ህትመትና ስርጭቱን በመለከተ ለውጪ አካል በመስጠት ተማሪዎቹ በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ትምህርቱን እንዲከታተሉ ለማድረግ ተሞክሯል። ሥራውም በሂደት ላይ ይገኛል።
የመጽሐፍ ዝግጅቱ ሦስት ዓመታትን የፈጀ ነው ያሉት ኃላፊዋ ምክንያቱ ደግሞ ቀደም ሲል የነበሩት ክፍተቶች እንዳይደገሙ ለማድረግ ነው። ለአብነትም ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል የሚሰጠው የግብረገብ ትምህርት ተጠቃሽ ነው። በተጨማሪም የማህበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ ውህድ የሆነ ትምህርት ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ለመስጠት የሚያስችል መጸሐፍ መዘጋጀቱ በማስፈለጉ እንደሆነ ተናግረው ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል በተናጠል ይሰጡ የነበሩ የሳይንስ ትምህርቶች አጠቃላይ ትምህርት በማለት ወደ አንድ እንዲመጡ ሆኗል፤ ጂኦግራፊና ታሪክም ተቀናጅተው የሚሰጡበት ሁኔታ መመቻቸቱም ሌላው ትልቅ ጊዜ የተሰጠበት ዋና ምክንያት ስለመሆኑ ያነሳሉ።
የሙያ ትምህርትም ሰባትና ስምንተኛ ክፍል እንዲሁም 11ኛ እና 12ኛ ክፍሎች ላይ የሚሰጥበት ሁኔታም በሥርዓተ ትምህርት ደረጃ መዘጋጀቱ እንደአንድ ልዩ ትኩረት ከተሰጠው መካከል መሆኑን ይናገራሉ።
ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን የትምህርት መጽሐፍት ክልሎች በራሳቸው ባህልና አካባቢያዊ ሁኔታ ቃኝተው በማዘጋጀት ወደ ትግበራ እንደሚያስገቡት የገለጹት ኃላፊዋ፤ ህትመቱን በተመለከተ ሙሉ ለሙሉ ሳይሆን ለማስተማር በሚጠቅም ልክ ብቻ ይደረጋል። ምክንያቱም ብዙ መሻሻሎችን የሚጠይቅና ግብዓቶች የሚያስፈልጉት በመሆኑ በሂደት ላይ የሚቆይ እንደሚሆንም አስረድተዋል። በተለይ ደግሞ የዘጠነኛና የአስረኛ ክፍል መማሪያ መጽሐፍትን በተመለከተ ሙከራው እየተከናወነበት በትምህርት ሚኒስቴር ድረ ገጽ ላይ ይለቀቅና ሁሉም እንዲተቸው እንደሚደረግም አስረድተዋል።
የትምህርት ዘመኑም ሆነ የሥርዓተ ትምህርቱ አተገባበር በሁሉም አካባቢዎች በእኩል ደረጃ ሊጀመር እንደማይችል የገለጹት ደግሞ የትምህርት ፕሮግራሞች ጥራትና ማሻሻል መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሐንስ ወጋሶ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት፤ በተለይም ጦርነቱ ባለባቸው አካባቢዎች በርካታ ችግሮች በመኖራቸው ይህንን ለማድረግ ያዳግታል። በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ትምህርት ቤት ወድሟል፤ ትምህርት ቤቶች ተዘርፈው ለማስተማር የሚችሉበት ቁመና ላይ አይደሉም። በተመሳሳይ ተረጋግቶ የመኖር ሁኔታውም ገና ብዙ መሥራትን ይጠይቃል። ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ተግባራትን በአፋጣኝ በመከወን በተቻለ መልኩ ለማስጀመር ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ሰላምና መረጋጋት ጭምር ባለባቸው አጎራባች ከተሞች ላይ የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማከናወን የማያስችሉ ችግሮች እንዳሉ የሚያነሱት ሥራ አስፈጻሚው፤ ብዙ ተፈናቃዮች ትምህርት ቤቶች ላይ ተጠልለዋል። እነርሱን ደግሞ ምቹ ሁኔታ ሳይፈጥሩ ማስወጣት አይቻልም። ስለሆነም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር በመሥራት ሰላምና መረጋጋት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ላይ ሰዎቹን በማስፈርና ትምህርት ቤቶችን በማስለቀቅ እንዲሁም መግባት ያለባቸውን ቁሳቁሶች በማስገባትና ለመማር ማስተማር ምቹ በማድረግ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ትምህርቱ እንደሚጀመር ያስረዳሉ።
አጠቃላይ ሁኔታውን በተሳለጠ መልኩ ለማከናወን ያግዝ ዘንድ ከዛሬ ጀምሮ የትምህርት አገልግሎቱን የሚሰጡ 34 ሺ ትምህርት ቤቶች መዘጋጀታቸውን ያነሱት ሥራ አስፈጸሚው፤ ለዚህም 16 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2015 ዓ.ም