በመዶሻና በኩርንችት ሚስማር ተከብቤ፣ የሰባት ሰዐቷ ጸሀይ አንጸባርቃብኝ፣ በላብ ቸፈፍ ተጠምቄ፣ መሬቱን በጥፍሮቼ ቆንጥጨ፣ ተረከዜ ላይ ተደላድዬ ቁጢጥ ብያለው..ባለፈው ሁለት ሳምንት ቅናሽ ሆኖ ሳገኘው ጥሩ መስሎኝ የገዛሁትን ሶሉ የለቀቀብኝን የቻይና ጫማ እየጠገንኩ። አይ ቻይና እላለው በልቤ። በስራ አጥ ወገቤ አጠራቅሜ የገዛሁት ብልጭልጭ ጫማዬ በሳምንቱ አይሆኑ ሆኖ ሳገኘው። እንደ እኔ በዚች ምድር ላይ ቻይናን የረገመ ሰው ያለ አይመስለኝም። ቻይና እንዴት ሰለጠነች ብሎ ለጠየቀኝ የምመልሰው አንድ መልስ አለኝ በብልጠትና በወርቅ ቀለም የተሸለመ አመዳይ እየሸጠች የከበረች የሚል። እንዲህ እንደ እኔ በወርቃማ አሸንጉሊት ተታሎ ብኩን የሆነ ብቻ ነው ቻይናን የሚያውቃት። ብዙ ቀን እንዲህ እንደ አሁኑ ለምስራቅ ደፍ ግንባሬን ሰጥቼ፣ ተረከዜ ላይ ቁጢጥ ብዬ ስፍገመገም አያቴ ምን እየሰራህ ነው ብላኝ ታውቃለች። ምን እየሰራህ ነው ስትለኝ.. ሳምንት የገዛሁት ጫማዬ ሶሉ ወልቆ እሱን እየጠገንኩ ነው ብላት የምትሆነው መሆን ስለሚያስፈራኝ እዋሻት ነበር።
ቻይና ጋፍ ጫማ ብቻ አይደለም የሸጠችልኝ ውሸትንም ነው አብራ የሸጠችልኝ። አያቴን ዋሽቻት የማላውቀው ልጅ ከዛ ጫማ በኋላ ውሸት ጀመርኩ። የቻይና ግፍ መች ይሆን በድሀ ሀገራት ላይ የሚያበቃው? ብዬ ሳልጨርስ የአያቴን እልልታ ከሳሎን ሰማሁት። አያቴ በሆነ ባልሆነው እልል እንዳለች ነው። ዛሬ ከነጋ እንኳን ሰባት ጊዜ እልል ስትል ሰምቻታለው። ልብሳችንን እየበላች መከራ ያሳየችን የቤታችን አይጥ በወጥመድ መያዧን ስታይ እልል ብላ ነበር። የዛሬ ወር የቤታችንን ቄብ ዶሮ የዛሬ ሳምንት ደግሞ የቤታችንን መጫት ዶሮ ከነአራስ ልጆቿ የሰለቀጠው የጎረቤታችን የጋሽ ታፈሰ ጉልቤ ድመት በመርዝ መሞቱን ስነግራት እልል ብላ ነበር። ማዶ ተሻግራ ያለችው የታላቅ እህቷ ነፍሰ ጡር ላም በሰላም መገላገሏን ስትሰማ እልል ብላ ነበር። የቤታችንን ጣሪያ እየዞረ ከጋሽ ታፈሰ ድመት የተረፉትን ጫጩቶች የሚቀላውጠው ጭልፊት ባልታወቀ ምክንያት መሰዋቱን ስትሰማ እልል ብላ ነበር። አሁን ደግሞ በምን እንደሆነ እንጃ እልል ስትል ሰማኋት። አያቴ መደሰቻ አታጣም። አፏ ለእልልታም ሆነ ለእርግማን ቅርብ ነው። እኛ ቤት ውስጥ በእማዬ እልልታ ሁሌም ሰርግ ሁሌም መልስ አለ።
ወዲያው ጉርምርምታዋን ሰማሁት..በጉርምርምታዋ ውስጥ ስሜ ይሰማኛል። አሽሙርና ለበጣ የቀላቀለ ጉርምርምታ። አያቴ ብዙ አይነት ሴት ናት። እልል ባለች አፏ እርግማን ይቀናታል። አሜን ባለች አንደበቷ ሀሜት ምሷ ነው። ትላንትን እያስታወሰች፣ አምናን እየመለሰች መራገም፣ መነጫነጭ ልማዷ ነው። አልቀየማትም.. ወንድነቴ እንደፈለገች መሆኛዋ ነው። ራሴን ለሀሳቧ፣ ለምኞቷ፣ ለእርግማንና እልልታዋ አሳልፌ የሰጠሁ ሰው ነኝ።
ማረፊያዋ ነኝ..የነጻነቷ ወደብ። እንደ እኔ እንደፈለገች የምትሆንበት ምንም የላትም። እኔም እንደፈለገች ስለምትሆንብኝ ደስ ይለኛል። በአፌ በብልጭልጭ ቀለም ጎድ የሰራችኝን ቻይናን እየረገምኩ በጆሮዬ ደግሞ ስሜን የቀላቀለ የአያቴን እልልታ እያደመጥኩ በሁለት አለም ውስጥ እዋልላለው። ለብዙ ሰዐት ተረከዜ ላይ ቁጢጥ ማለቴ ህመም ስለፈጠረብኝ መቁነጥነጥ ጀመርኩ። መቁነጥነጥ ብቻ አይደለም ሚዛን እየሳትኩ ወዲያ ወዲህ መዋዠቅ ጀመርኩ። ብዙ ሳልቆይ ቂጤ ላይ በሳሳው ሱሪያ መሬት ላይ ተዘረፈጥኩ። መሬት ቻለችኝ። እንደ መሬት ቻይ ምን አለ? መሬት እኔን መቻሏ ገረመኝ። ያን ሁሉ ድካሜን፣ ያን ሁሉ አበሳዬን መቻሏ መሬት ምን ያክል ቻይ እንደሆነች ደረስኩበት። እኛ የሰው ልጆች እኮ በሀጢያታችን፣ በበደላችን፣ በክፋታችን ማንም የማይችለን ነበረን..መሬት ግን ቻለችን።
አያቴ ከእልልታዋ ጋብ ስትል በትሯን ተመርኩዛ ወዳለሁበት ደጅ ወጣች። ድምጽዋን ሰውራ፣ ኮቴዋን አጥፍታ ድንገት አጠገቤ ሳያት ድንግጥ ነበር ያልኩት። ከድንጋጤዬ የተነሳ ጫማዬ ላይ ባለምኩት መዶሻ እጄን ልቀጠቅጠው ምንም አልቀረኝ ነበር። ቶሎ አላየኋትም። ሁሉ ነገሬ ጫማዬ ላይ ስለነበር ከዛ እስከዚህ እስክትደርስ ኮቴዋ ለጆሮዬ ባዕድ ነበር። በሰባት ሰዐቷ ጀምበር የተሳለ በእርጅና ያጎነበሰ ጥላዋ ሲያርፍብኝ ነበር ቀና ያልኩት።
ለጎኔ በቀረበ..ትከሻዬን በሚተሻሽ አቀማመጥ አጠገቤ መጥታ ተቀመጠች። እንደፈለገች ልትሆንብኝ እየተዘጋጀች መሰለኝ። አይኖቿ እንደፈለጉ ሊሆኑብኝ በትዝብት ሲያስተውሉኝ ቀና ባልኩበት አንድ ጊዜ አስተዋልኳቸው።
ባቀረቀርኩበት ጫማዬን እየቀጠቀጥኩ ‹ደሞ ምን ተገኘ? አልኳት የእልልታዋን ሚስጢር እንድትነግረኝ በመሻት።
‹አይ አንተ እንዳው ምን ይበጅህ ይሆን? አለችኝ።
‹ደሞ ምን አደረኩ? አልኩ ደንገጥ ብዬ..ካጎነበስኩበት ቀና እያልኩ።
‹ማናት ያቺ..እይ..ስሟ ጠፋብኝ..መርፌ ወጊ ዶፍተር ልትሆን ነው አሉ። አንተ ሰፈር ውስጥ አውደልድል። አለችኝ። እንደፈለጉ በሚሆኑብኝ አይኖቿ እየነቆረችኝ።
ተመርቄ ቤት ቁጭ በማለቴ እንደሆነ ስለገባኝ ‹ታዲያ እኔ ምን ላድርግ..ስራ አጥቼ እኮ ነው› አልኳት።
‹እዲያ መልስ እማ ታውቅበታለህ። ቤት ቁጭ ብለህ እያውደለደልክ ስራው ከየት ነው የሚገኘው? መጀመሪያ ከቤት መች ወጣህና..
‹ቆይ ማናት ዶፍተር የምትሆነው? ስል በአያቴ አማርኛ አያቴን ጠየኳት።
‹ያቺ የጎረቤታችን የጋሽ ሳህለ ልጅ ናታ..› አለችኝ።
‹ማን..ርብቃ? እንደዛሬ ጮኬ የማውቅ አይመስለኝም።
‹አዎ ናት..ምን ያስጮህሀል ታዲያ? ስትል ቆጣ አለች። ቡርቃ ናት ቡርቄ ስሟም አይያዝልኝ..ዶክተር ልትሆን ነው አሉ›አለችኝ።
‹እሷ በፍጹም ዶክተር አትሆንም። አይደለም ዶክተር ልትሆን ቀርቶ ታማ ዶክተር ፊት መቅረብ የማይገባት ሴት ናት።› አልኩ ሽንጤን ገትሬ።
‹ለምንድነው የማትሆነው? አንተ እንኳን አውደልዳዩ ማነው የምትለው ሆነህ የለ እንዴ? ድግሪ ጭነህ የለ?
‹ቆይ ዱክትርና መናገርና መስማት ለማይችሉ በነጻ መታደል ጀመረ እንዴ? ስል ድምጼን ከፍ አድርጌ ተናገርኩ።
‹ምንድነው የምትቀባዠረው! መርፌ ወጊ ልትሆን ነው ነው ያልኩህ እኮ›
‹እኔስ እሱ አይደል የገረመኝ..› አልኩ ድምጼን ሰልቤ። በአያቴ አይኖች ላይ ወደ ትላንት እየተረማመድኩ።
በርብቃ ዱክትርና ሀሳብ ዘፈቀኝ። ያኔ ጊቢ ተማሪ እያለሁ ከዶርም ጓደኞቼ ጋር አብረን ተቀምጠን ሳለ ስልኬ የርብቃን አንድ መልዕክት ተቀብሎ ነበር..‹ሀይ ማክቤል..Can l help you? ምን ማለት ነው እባክህ ትርጉሙን ንገረኝ የሚል መልዕክት። ይቺ ሴት ዶክተር ልትሆን ነው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2015 ዓ.ም