ማንም ይሁን ማን አካባቢ አለው። የትም ሄደ የት ዞሮ ዞሮ … ነው ነገሩ። ምንም ዓይነት ሀብት ይትርፍ ይትረፍረፍ … መጨረሻው «አኝከህ አኝከህ ወደ ዘመድህ ዋጥ» ከመሆን አይዘልም። ይህ እንግዲህ በቅን ልቦና፤ በአገልጋይነት መንፈስ ስንረዳው ነው። እናብራራው።
ይህ ጉዳይ ይብራራ ከተባለ ወሰኑ እስከ ዲያስፖራው ድረስ ይዘልቃል። እንተንትነው ከተባለም ወደ አዳም እና ሄዋን ድረስ ማረጉ አይቀርም። ይሁን እንጂ፣ ከተነሳንበት ርእሰ ጉዳይ፤ አንጻር በአካባቢያቸው ተወልደው፣ እዛው አድገው፣ እዛው ተድረውና ተኩለው እዛው በማገልገል ላይ ያሉትን፤ የዛሬው እንግዳችንን ብቻ ይዘን መዝለቅ ወደናል፡፡
እንዳልነው፣ የዛሬው እንግዳችን ወጣቶች ናቸው፤ ቆይታ ያደረግነውና መረጃ ያገኘነውም በተወካያቸው ወጣት አማካኝነት ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ሁሉም በተወካይ ይገለፃል ከሚል ነው።
ወጣት እንዳልካቸው ታምራት ይባላል። ተወልዶ ያደገው በኦሮሚያ ክልል ጎዋ ዎርኮ ቀበሌ ነው። የዛሬው ቀን እንግዳ ያደረግነው እንዳልካቸው (በተፈጥሮው መሆኑ ያስታውቃል) የልጅ አዋቂ፣ ንቁ፣ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ሲበዛም ተግባቢ ነው። ስለ’ሱ የጠየቅናቸው ሁሉ እንደ ነገሩን በሰዎች ተወዳጅ ብቻም ሳይሆን ተመራጭ ነው። ሥራውን ያስኬደዋል ብቻ ሳይሆን ሥራው ራሱ ይሄድለታል። ሰዎችን ላስተባብርና ወደ መልካም ነገር ላምጣ ብሎ ሲነሳም ከሱ ቀድመው የልቡን ነው የሚያደርሱለት። ባጭሩ፣ እንዳልካቸው ታምራት ለሥራ የተፈጠረ የሥራ ሰው ነው። ማህበራዊነት ውስጡ ነው። ተግባቢነት ዕጣ ክፍሉ ነው። ፍጥነት የራሱ ነው። ስኬት አምልጦት አያውቅም። ማገልገል ተፈጥሮው ሲሆን፤ የተቸገሩትን መድረስ እርካታው፤ መመረቅ ትፍህስቱ ነው።
እንዳልካቸው እንዳጫወተን ከሆነ ገና ብዙ የሚቀረው፤ ብዙ እቅድ፤ ከፍ ያለ ተስፋና ራቅ ያለ ራእይ ያለው ወጣት ሲሆን፤ ድርጅታቸውም በዚሁ አቅጣጫ እየሄደ ነው። «አካባቢን፣ ያሳደገን ማህበረሰብ ከማገልገልና ከመመረቅ (ምርቃት ከማግኘት) በላይ ምን አለ» የሚለው እንዳልካቸው በሥራው ዓለም ያጋጠመውን መልካምና ፈታኝ ሁኔታዎች ሁሉ ወደ አጋጣሚ በመቀየር የእድገት መሰላል ማድረግ ላይ ያተኩራል እንጂ ተደናቅፎ አይወድቅም።
ከድርጅታቸው (Abraham and friends Agrochemicals Shop)) ባለድርሻ አካላት አንዱና የበጀትና እቅድ ዘርፉን የሚመራውና «እንዳልካቸው ጎበዝ ነው። ይህ ሁሉ ስኬትና ማህበራዊ አገልግሎት የእሱ ውጤት ነው። ለሌሎች አርአያነቱም እንደዛው» ሲል የእንዳልካቸውን ጥረትና ስኬት የሚናገረው ወጣት አብርሃም ታምራትም ነው፡፡ በስልክ ያነጋገርናቸው የድርጅቱ ተጠቃሚና የጎዋ ወርኮ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ተረፈ ሀብቴ የሚመሰክሩት ይህንኑ ነው።
ስለ ድርጅቱ ጠንሳሽ፣ መስራችና አስተባባሪ እንዳልካቸው ይህንን ያህል ካልን፣ ስለ አጠቃላይ ሥራውና ድርጅቱ ጠይቀነው ያጫወተንን እናካፍል።
አዲስ ዘመን፡- ሥራ እንዴት ነው?
እንዳልካቸው፡- ሥራ ጥሩ ነው። በጣም ጥሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ድርጅታችሁ መች ነው የተቋቋመው፤ ያቋቋማችሁት?
እንዳልካቸው፡- በ2007 አ.ም።
አዲስ ዘመን፡- የድርጅታችሁ መቋቋም ዋና አላማው ምንድን ነው?
እንዳልካቸው፡- ስናቋቁመው ዋና አላማችን የአካባቢያችንን የግብርና ግብአት ተጠቃሚ ኅብረተሰብ፣ በተለይም አርሶ አደሩን ከብዝበዛ መከላከል ነው። ከብዝበዛ መከላከል ሲባል ከከተማ እየመጡ እዚህ ለገበሬው የግብርና ግብአቶችን የሚሸጡ ነበሩ። እነዚህ ነጋዴዎች ዋጋቸው ጤነኛ አልነበረም። የ100 ብሩን 300 እና 400 ብር ነበር ለአርሶ አደሩ የሚሸጡት። ይህ ነገር በጣም ያናድደን ነበር። በመሆኑም «ለምን እኛ ለገበሬው አናቀርብለትም?» የሚል ነገር መጣብን። በቃ፣ ከዚያ ከዚህም ከዛም ብለን፣ ከራሳችንም አድርገንና ተበዳድረን ጀመርነው።
አዲስ ዘመን፡- ስትጀምሩ መነሻ ካፒታላችሁ ስንት ብር ነበር?
እንዳልካቸው፡- 47ሺህ ብር።
አዲስ ዘመን፡- ምን ምን በማቅረብ ነው ሥራችሁን የጀመራችሁት?
እንዳልካቸው፡- ወሳኝ የሆኑ የግብርና ምርቶችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ነበር የጀመርነው። ወሳኝ ሲባል እንደ አረም ማጥፊያ፣ የችግኝ ፍሬዎች እና ሌሎችም። በተለይ የዘር ሰዓት ሲደርስ ለዚያ ወቅት የሚያስፈልጉትን ስለምናውቃቸው እነሱን ነበር የምናቀርበው። እራሳችን ግብርና ውስጥ ስላለን ይህንን ማወቅ አይቸግርንም ነበር። ለዚያም ነው «መሸወድ የለብንም፤ አርሶ አደሩም መበላት የለበትም» ብለን የገባንበት።
አዲስ ዘመን፡- ለመደብራችሁ የሚሆነውን አቅርቦት ከየት ነው ታገኙ የነበረው?
እንዳልካቸው፡- በወቅቱ በማፈላለግ ነበር የምናገኘው። ደብረ ዘይት፣ አዲስ አበባ … ሰው እየጠየቅን ነበር ገዝተን የምናመጣው። አሁን ያ ችግር ተፈትቷል።
አዲስ ዘመን፡- በምን መንገድ ተፈታ?
እንዳልካቸው፡- አሁን ሁሉ ነገር እንደ ያኔው አይደለም። ሥራችን በሚመለከተው ሁሉ ታውቆ አስፈላጊው እገዛ እየተደረገልን ነው። የወረዳው (በኦሮሚያ የምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ አድአ ወረዳ) የግብርና ባለሙያዎች የቅርብ ክትትልና እገዛ ያደርጉልናል። ምክርና አስተያየታቸውን ይሰጡናል። ኦዲት ያደርጉናል። የግብርና ግብአቶችን በተገቢው ዋጋ ገዝተን የምናመጣበትን ሁኔታ አመቻችተውልናል። በነጋዴዎች እንዳንበዘበዝ አድርገውናል። ይህ ደግሞ ለእኛ ትልቅ እገዛ ነው። ይህ እገዛ ደግሞ በብዙ መልኩ ከእኛም አልፎ ለአርሶ አደሩ ትልቅ እርዳታና እገዛ ነው። ለአገርም ቢሆን እንደዛው።
ለአርሶ አደሩ በመስክና በኮምፒዩተር የተደገፈ የምክር አገልግሎት እንሰጣለን። በሠርቶ ማሳያ የተደገፈ ነው። እራሳችን ገበሬዎች፣ ከገበሬው የወጣን ስለሆንንና ስለምናውቀው በተግባር ሞክረነው አዋጭ ሆኖ ካላገኘው ለአርሶ አደሩ አንሸጥም። አዋጭ ሆኖ ስናገኘው ብቻ ነው የምንሸጥለትና እንዲጠቀምበት የምናበረታታው። ሁሉ ነገራችን፤ የምንሠራቸው ሥራዎች በሙሉ ዋስትና አላቸው። ይህ ደግሞ ውጤታማ አድርጎን፣ ተአማኒነትን ፈጥሮልን አይተነዋል። አርሶ አደሩም ተጠቃሚ ሲሆን ተመልክተናል። ቤት ለቤት፣ ማለትም በግል በሚደረግ ግንኙነት ሁሉ ከአርሶ አደሩ ጋር ስለምንነጋገር ችግሮችን በቀላሉ ነው የምንፈታው።
ልጆቹ ስለሆንን በማሀላችን ምንም ዓይነት የተግባቦትም ሆነ መተማመን ችግር የለም። ይህ እራሱ አንዱ ማሳያ ነው። ከቸገረው ሲያገኝ የሚከፍለው የዱቤ አገልግሎት እንሰጣለን። ብዙውን ጊዜ በስልክ ሁሉ ነው የምንጨርሰው፤ «የት ጋ ነህ፣ የት ልምጣ፣ የት እንገናኝ፣ ይሄ … አለህ ወይ፣ ዋጋው ስንት ነው …?» እና የመሳሰሉትን የምንጨርሰው በአብዛኛው በስልክና በማህበራዊ ሕይወት መስተጋብር ውስጥ ነው። ለቅሶም ሆነ ሌላ ቦታ ስንገናኝ ስለ ጉዳዩ እናወራለን። ደብረ ዘይት ወይም አዲስ አበባ ሄዶ የሚያጠፋውን ጊዜ፣ ጉልበት፣ ገንዘብ … እንዲቆጥብ ዕድሉን እዚሁ ፈጥረንለታል፤ አሠራራችን ሁሉ በሙሉ ዋስትና ላይ የተመሠረተ ነው። ይህም ራሱ ለእኛ አንዱ ደስታና እርካታችን ሲሆን፤ እያገለገልን ነው ብለንም እናስባለን። አዝመራ በሚሰበሰብበት ጊዜም የምንሠራቸው ወሳኝ ሥራዎች አሉ። የውቂያ ማሽኖች ስላሉን በየአርሶ አደሩ ደጅ እየሄድን ውቂያ እንወቃለን። በተለይ ጤፍ እና ስንዴ እኛ ነን የምንወቃው። በዚህም ምን ያህል የአርሶ አደሩን ድካም እንደቀነስን አይተነዋል። ሁለት ቀን የሚፈጅበትን ነው እኛ በሰዓታት ሠርተን የምንጨርስለት። በዚህ ደግሞ አርሶ አደሩ ምን ያህል ደስተኛ እንደሆነ ሁሌም ነው የሚነግረን።
ሌላም አለ። እንደሚታወቀው ይህ አካባቢ ከክረምቱ በተጨማሪ አመቱን ሙሉ የመስኖ ሥራ አለ። አገሩ የተባረከ አገር ስለሆነ ሁሌም እርጥብና ምርታማ ነው። ሁሉም ዓይነት ምርቶች አሉ። አትክልት በየዓይነቱ ነው። ወደ ማዶ፣ ጎዋ ወርኮ ቀበሌ እንኳን ብትሄድ የአትክልት ዓይነቶችን በሙሉ ታገኛለህ። ስፍራው ለምለም ነው ብቻ ሳይሆን ገነት ነው ማለት ይቻላል። እዚህ ጎዲኖም እንደዛው። አልተሠራበትም እንጂ ቢሠራበት የትና የት ባስገኘ ነበር። ልልህ የፈለኩት፣ በዚያው ልክ የእኛም ሥራ አለ። ልክ ለክረምቱ እንደምንሠራው ሁሉ ለመስኖውም እናቀርባለን።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን በማድረጋችሁ ምን ያገኛችሁት ነገር አለ፤ ማለትም የተጠቃሚው ኅብረተሰብ ምላሽ ምን ይመስላል?
እንዳልካቸው፡- በእኛ በኩል የሕዝቡ ምላሽ ያው እንደ ነገርኩ ነው፤ በጣም ደስተኛ ነው። ሁል ጊዜ ምርቃት ነው። ሁል ጊዜ ምስጋና ነው። እኛ ከሁሉም የሚያስደስተን ደግሞ ምርቃቱ ነው። እንደ ምርቃቱ የሚያስደስተን ምንም የለም። ሕዝቡ ሲመርቅህ ከልቡ ነው። የእውነቱን ነው። ለችግሬ ደረስክልኝ ብሎ ሲመርቅህ አንተም ደስ ይልሃል። ካለው ከፍሎ፤ ከሌለው ቀስ ብሎ የሚከፍለውን ግብአት ስለሚወስድ ልክ እንደ ራሱ ቤት ነው የሚቆጥረው። ደግሞም ነው። ካስፈለገም፣ እንደ ሰውየው የገቢ ሁኔታ አይተን ከመጣበት ቀንሰን ሁሉ እንሸጥለታለን።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ አገልግሎታችሁ ከሌላ አካላት ያገኛችሁት ድጋፍ ወይም ማበረታቻ አለ?
እንዳልካቸው፡- አዎ፣ አለ። በመጀመሪያ ድጋፍም ሆነ እገዛ ያገኘነው፣ ቅድም እንዳልኩህ ከወረዳው የግብርና ባለሙያዎች ነው። ከምክር አገልግሎት ጀምሮ ስልጠና ድረስ የዘለቀ አገልግሎትን አግኝተናል። ከዚያም በላይ ደግሞ ባሳየነው ጥረት፣ በምንሰጠው አገልግሎትና ባስመዘገብነው ከፍተኛ ውጤት አዳማ (ናዝሬት) ላይ ተጋብዘን ከፍተኛውን የሜዳልያ ሽልማት አግኝተናል። እገዛው በብዙ መልኩ ነው። እዚህ የደረስነው በእነሱ ድጋፍ ስለሆነ ይህ እንደሚቀጥልም እርግጠኞች ነን።
አሜሪካዊው የልማት ድርጅት (“ዩኤስኤይድ” የሚባለው) እየቀጠለ የሚሄድ የመጀመሪያ ዙር ድጋፍና እርዳታ አድርጎልናል። ለምሳሌ፣ ይህ የምታየው በአብዛኛው በእነሱ ድጋፍ የተገኘ ነው። እዚህ ድረስ በመምጣት ማቀዝቀዣ፣ ባለ መስታወት መደርደሪያ፣ የግድግዳ ቀለም፣ ኮርኒስ፣ ትልቅ ማከማቻ፣ በፀሐይ ኃይል የሚሠራ ሶላር፣ ቁም ሳጥን፣ ላፕቶፕ፣ መደርደሪያ ….፤ እንዲሁም ከመደብሩ ውጪ ያለውን በራፍ በአስፋልት ማሳመርና ሌሎች ድጋፎችን ሁሉ አድርገውልናል። ይህ ለእኛ ትልቅ ማበረታቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ካፒታላችሁ እንምጣ። ቅድም በ47ሺህ ብር መነሳታችሁን ነግረኸኛል። አሁን ስንት ደርሳችኋል?
እንዳልካቸው፡- 3, 000, 000.00 (ሦስት ሚሊዮን ብር)
አዲስ ዘመን፡- የወደ ፊት እቅዳችሁ ምንድን ነው?
እንዳልካቸው፡- አሁን ያለነው በትንሹ (ማይክሮ) ደረጃ ነው። እቅዳችን ወደ ላይ መሄድ ነው። ከዚህ መውጣትን አቅደን ነው እየሠራን ያለነው። ለዚህም እንዲያግዘን ያቀድን፤ ያቀድነውንም ያሳወቅን ሲሆን፤ የተለያዩ ብድርና ድጋፎች እንዲመቻቹልን ጠይቀናል። ከእነዚህም አንዱ ትራክተር እንዲሰጠን ወረዳውን የጠየቅነው ነው። እስካሁን ምላሽ አላገኘንም። ምላሽ እናገኛለን ብለን ግን እንጠብቃለን። ሌሎች ነገሮችም እንደዚያው ይመቻቹልናል ብለንም እናስባለን። ይህ ከሆነ በየአርሷደሩ መንደር፣ እርሻ ቦታና በሚሠራበት ሁሉ እየሄድን ለመሥራት ነው ያቀድነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደው እዚህ ደረጃ እስክትደርሱ ምንም ያጋጠማችሁ ችግር የለም? ሁሉ ነገር አልጋ ባልጋ ነበር ማለት ይቻላል?
እንዳልካቸው፡- (ሳቅ) አለ እንጂ፤ በጣም አለ። ዋናውና ደስ የሚለውም እሱን አልፎ እዚህ መድረሱ ነው። ያመነን ሰው ሁሉ አልነበረም። «እነዚህ ልጆች ትምህርት የላቸው፤ እንዴት እንደዚህ ሊደፍሩ ቻሉ?» ተብለን ሁሉ ነበር። ይህ ምንም ማለት አይደለም፤ ይጠበቃል። በመንግሥትም በኩል እንደዚያው ነበር። ከብዙ ፈተናና ማረጋገጥ በኋላ ነው ትክክለኛነታችን፤ አገልጋይነታችን ተረጋግጦ ለእውቅናና ድጋፍ የደረስነው። ጥያቄህን መልሼው ከሆነ የነበረው ሁኔታ ይህንን ይመስል ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ከማኅበረሰቡ ሌላስ የምትሰጡት ማህበራዊ አገልግሎት አለ? እንደው፣ ካለ በሚል ነው።
እንዳልካቸው፡- አዎ፤ በሚገባ አለ። ለሥራ ጉጉ የሆኑ፣ የሥራ ፍቅርና ተነሳሽነት፤ ታታሪና ራእይ ያላቸውን ወጣቶች እንቀርባቸዋለን። ቀርበንም እናግዛቸዋለን። ወደ ሥራ እንዲገቡ እናበረታታቸዋለን። የምንችለውን እያደረግንም እናቋቁማቸዋለን። እስካሁንም ሁለት ወጣቶች እራሳቸውን ችለው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ እየቀጠሉ ከሚሄዱት ተግባሮቻችን አንዱ ነውና የሚቆም አይደለም። ሌላው በቅጥርም የሥራ ዕድል የመፍጠሩ ጉዳይ ሲሆን፤ ይህም እየሰፋ የሚሄድ እንደሚሆን መገመት አይቸግርም።
አዲስ ዘመን፡- እናንተ ወጣቶች ናችሁ። በራሳችሁ ተነሳሽነትም ወደ ሥራ ገብታችሁ እዚህ ደርሳችኋል። ከዚህ አኳያ ለሌሎች ወጣቶች ምን መልዕክት ታስተላልፋላችሁ?
እንዳልካቸው፡- እርግጥ ነው፤ እኛ በራሳችን ተነሳሽነት እዚህ ደርሰናል። ተነሳሽነቱም የመነጨው ላሳደገን ማኅበረሰብ፣ አርሶ አደሩ ከመቆርቆር ነው። ያ ማለት ደግሞ፣ እኛም የአርሶ አደሩ ልጅና አካል በመሆናችን ለራስ ከመቆርቆርም ጭምር ማለት ነው። ከዚህ ተነስተን እዚህ ደርሰናል። ወደ ፊት ደግሞ ከዚህ የበለጠ ለመሄድ አስበንና አልመን እየሠራን ነው። እግዚአብሔር ከፈቀደ ሁሉንም እቅዳችንን እናሳካለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ከዚህ አኳያ ለወጣቱ የማስተላለፈው መልዕክት፣ በቃ ወደ ሥራ እንግባ ነው። በአካባቢው የሚሠራ ሥራ ሞልቷል። አካባቢው ለም ነው። አልተነካም። ሌላው ጋ የቸገረው ውሃ ነው። ያ እዚህ ሞልቶ እየፈሰሰ ነው። በመሆኑም ልንሠራ ይገባል። በአሁኑ ጊዜ መሥራት ነው የሚያስፈልገው።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጠኸን ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
እንዳልካቸው፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2015 ዓ.ም