አዲስ አበባ፡- የትራንስፖርት ባለስልጣን የወጪና ገቢ ጭነትን የሚያስተጓጉሉ እንቅፋቶች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ በመሆኑ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ተናቦ በመስራት ችግሮችን ማስወገድ እንደሚገባው የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስገነዘበ።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሄር እንደገለፁት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ለአንድ ሀገር ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በመግ ለጽ የጭነት አገልግሎትን ምርታማነት ለማሳደግ ችግሮችን ለይቶ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል።
ሀገሪቱ በዋናነት ከውጭ የምታስገባቸው እንደ ማዳበሪያ፣ ስንዴ፣ ብረትና ዘይትን የመሳ ሰሉት ምርቶች ከወደብ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የሚያጋጥሙትን እንቅፋቶችና መጓተቶች ለማስቀ ረት ትራንስፖርተሮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተናበው መሥራት እንዳለባቸው ወይዘሮ ሙሉ አስታውቀዋል።
ትራንስፖርት በአግባቡ ካልተጠቀምነው የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ሀገርን ሊጎዳ ይችላል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ዘመናዊነትን የተከተለና አሁን ያለንበትን የለውጥ ሂደት የሚመ ጥን በእውቀት የሚመራ የትራንስፖርት አመራር ሥርዓት ሊኖር ግድ ነው ብለዋል። እየታየ ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን ፈትሾ የህግ ማዕቀፍ ማውጣትና አሰራሮችን ማስተካከል ያስፈ ልጋል ብለዋል።
ከወደብ እቃዎችን የማንሳት እና ወደ ወደብ በፍጥነት የማድረስ አቅምን ለማሳደግ ያለአግባብ የሚቆሙ መኪኖች እንዳይኖሩ የሚያስ ችል እና የምልልሱን ጊዜም ለማሻሻል የሚያግዝ የዲሜሬጅ ህግ ወጥቶ ተግባር ላይ እንደዋለ ወይዘሮ ሙሉ ያስረዳሉ። የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎቱ በ2010 ዓ.ም ከነበረው አፈጻጸም አንጻር መሻሻል የታየበት ቢሆንም አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች እንዳሉበት ተጠቅሷል ፡፡
ከተጠቀሱት ችግሮች ውስጥ የመንገድ ምቾት መጓደል፣ የመጋዘን እጥረት ፣የፍተሻና የስታንዳርድ ደረጃ ውጤት አሰጣጥ ቅልጥፍና ማነስ፣ የተሽከርካሪዎች ማርጀትና የቴክኖሎጂ እጥረት እንደችግር የተጠቀሱ ሲሆን በተለይም የድንበር ተሸጋሪ የደረቅ ጭነት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በየተቋማቱ የሚገጥሟቸው ቢሮክራሲዎች ሥራውን ለማቀላጠፍ እንቅፋት እንደሆኑባቸው ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2011
በእያሱ መሰለ