አገራት በተለያዩና ባፈሯቸው ሀብቶች (ተፈጥሯዊም ይሁን ሰው ሠራሽ) ይታወቃሉ። ዜጎቻቸው በሠሯቸው ሥራዎች ወይ ከፍ፤ ወይም ደግሞ ዝቅ ሊሉ ይችላሉ። በጀግኖቻቸው “ሌጋሲ” ታፍረውና ተከብረው ይኖራሉ። ፈላስፎቻቸው ባራመዷቸው ፍልስፍናዎች ይፈረጃሉ። ባላቸው ተፈጥሯዊ አቀማመጥም ሆነ በአየር ንብረታቸው ይለያሉ። ባፈሯቸው ምሁራን፣ ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎችም እንደዛው። በሥነጽሑፍ ሥራዎቻቸው ደረጃ ይወጣላቸዋል። ባይሆን ኖሮ ብዙዎቹን ባላወቅናቸው፤ በቀላሉም ባልለየናቸም ነበር። በቀላሉም አስተምህሯቸውን ባልቀሰምን ነበር።
ሼክስፒር ሲባል ጀርመንን እሚያስብ፤ ሂትለር ሲባል አእምሮው ፈጥኖ አሜሪካዊነቱ ላይ የሚሄድ … ሰው አለ ለማለት እንደሚቸግር ሁሉ፤ ኤሚል ዞላን እንግሊዛዊ፤ ዊትማንን ፈረንሳዊ ብሎ ደረቱን ነፍቶ የሚሟገት ሰው ማግኘት ይቸግራል። (እዚህ ላይ “ሰው” ስንል የሚመለከተውን ሰው እንጂ ሁሉንም ሰው እያልን እንዳልሆነ ማስታወስ ይገባናል።) ከዚህ የምንገነዘበው የመግቢያ አንቀፃችን ትክክል መሆኑን ነውና እንቀጥል።
በብዙዎች ዘንድ ናይጄሪያ የሳይንቲስቶች ምድር (ላንድ ኦፍ ሳይንቲስትስ) በሚል ትታወቃለች። ይህንን በሚያክል ባለሀብትነቷ ትታወቅ እንጂ የሀብቷ ተጠቃሚ ባለመሆኗም ያንኑ ያህል ትወቀሳለች። “ለምን?» ቢሉ፤ በሙሉ ሊያስብል በሚችል ደረጃ የሷ ባለመሆናቸውና በተለይ የአሜሪካ የምርምር ማዕከላትን ያጨናነቁት ትውልደ ናይጄሪያዊ ሳይንቲስቶች በመሆናቸው ነው። “ምክንያት?” ካሉም፣ ምክንያቱን ለገንዘብ ሲባል ወደ ሰለጠኑት ዓለማት የሚደረግ ስደት ሆኖ ያገኙታል። ወደ ራሳችን እንመለስ።
ኢትዮጵያ ጥንታዊትና የራሷም የሆነ አገር በቀል ዕውቀት ያላት አገር ነች። ምናልባት በብዙ ሁኔታዎች ከፍ ብላ ትታይ ይሆናል እንጂ ከብዙዎች ጋር ስትታይ ደፍረው ከጎኗ ሊቆሙ የሚችሉ አገራት ትንሽ ናቸው። ብልጫዋ፣ ልክ እንደ ዕድሜዋ ሁሉ፣ ብዙ ነው። ያላትን ሀብት ከመቁጠር የሌላትን መቁጠሩ ይቀላል። ያፈራቻቸውን ሙያና ባለሙያዎች ከማሰብ “ምን ያላፈራችው አለ?” ብሎ መመራመር ይቀላል። የዛሬው ባለውለታችን ደግሞ አንዱና ቀዳሚው ኢትዮጵያ ያፈራችው ፈላስፋ ነውና ወደ’ዛው፤ ወደ ወልደ ሕይወት እንሂድ።
በአንድ ግዙፍ ሰብእና በመሸፈኑ ምክንያት ነው መሰል ወልደሕይወት በብዙዎቻችን ብዙም አይታወቅም። ምናልባትም እዛው፣ በአካዳሚው ደብርና አካባቢው ስሙ ሊነሳ ይችል ይሆናል እንጂ፤ በጥቂት ጉዳዩን ፈልፍለው ለማውጣት በሚጥሩ ሰዎች አካባቢ ይጠቀስ ይሆናል እንጂ ….. በአንድ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋነቱ ሕዝብ ያውቀዋል የሚል አቋም የሚይዝ ሰው አይገኝም። አይደለም ሥራዎቹን፣ እስከ እራሱም መኖሩን የሚያውቁ ብዙዎች አይደሉም።
እርግጥ ነው ወልደሕይወት (ምትኩ) የፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ ተማሪ ነበር። ወልደሕይወት በዚሁ በተማሪነትና የዘርዓያዕቆብ ተከታይነቱ (በነካ ጣል ነካ ጣልም ቢሆን) ይታወቃል። በተለይ በእነ ብሩህ ዓለምነህ አካባቢ እንደ አንድ አቢይ ርእሰ ጉዳይ ተወስዶ ተፈትሿል። ከማንም በላይ ደግሞ፣ እንደ እነ ክላውድ ሰምነር (ስለእኝህ ምሁር አዲስ ዘመን፣ ረቡዕ ሐምሌ 27 ቀን 2014 ዓ.ም፣ ገጽ 23ን ይመለከቷል) በውጭዎቹ ዘንድ በሚገባ ይታወቃል። (እስከዛው፣ ሰምነር የዘርዓያዕቆብን ፍልስፍና ከፈረንሳዊው የአውሮፓ ዘመናዊ ፍልስፍና መስራች ሬኔ ዴካርት (Rene Descartes) ሥራ ጋር በማነጻጸር፣ ኢትዮጵያ በፍልስፍና ታሪክ ውስጥ የነበራትን ሚና፤ በፍልስፍናው ያላትን ቀዳሚነት ለተቀረው ዓለም አጉልቶ አሳይቷል።የሚለውን መያዙ ጥሩ ነው።)
አርስቶትል የፕሌቶ መምህር እንደ ነበረው ሁሉ፤ የዛሬው ባለውለታችን፣ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው፣ በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን የሕይወት ታሪኩንና የፍልስፍና ሥራውን ብራና ዳምጦ፣ ቀለም በጥብጦ፣ በመጻፍ ያቆየልን ኢትዮጵያዊ አመክኗዊ (rational) ፈላስፋ የሆነው፤ የፈላስፋው ዘርዓያዕቀብ (1599-1692) ደቀ-መዝሙር ነው። ብሩህ አለምነህ እንደሚነግረን ከሆነ ወልደሕይወት ከዘርዓያዕቆብ ጋር ከ1626 – 1685 ዓ.ም ድረስ ለ59 ዓመታት በእንፍራንዝ፣ ደቡብ ጎንደር አንድ ላይ የኖረ ሲሆን፣ ፍልስፍናንና የሃይማኖት ትምህርትንም ከዘርዓያዕቆብ ተምሯል።
(ብሩህ ዓለምነህ “ለቅዱስ ያሬድ ይህ ዓለም በመላ ልክ እንደ አንድ ትልቅ ማህሌት (ሲንፎኒ) ነው፤ ፍጥረታት ሁሉ በአንድነት በዜማ የሚያመሰግኑበት ሲንፎኒ፡- ይህም ማለት ቅዱስ ያሬድ ተፈጥሮን የሚገነዘበው በቀለሙ፣ በልስላሴው አሊያም በቅርፁ ሳይሆን በድምፁ ነው – ፈጣሪውን በሚያመሰግንበት ዜማው ነው።ለዚህም ነው “ደምፀ እገሪሁ ለዝናም” (የዝናብ እግሩ ተሰማ) ያለው – ዜማን ከዝናብ ድምፅ ፈልቅቆ ሲያወጣ!!! የ6ኛው ክ/ዘ ባህል እንደዚህም ዓይነት አስደናቂ ሰው ፈጥሯል፡፡” በማለት በአንድ ጽሑፉ ላይ ማስፈሩን ማስታወሱ፣ ቢያንስ ያ ክፍለ ዘመን ምን እንደሚመስል ለመገንዘብ ጠቃሚ መሆኑን በቅንፍ አስቀምጠን ብናልፍ ጠቃሚ ይመስለናል።)
ወልደሕይወት ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ እንዲሉ እንኳን ባይሆን፤ የአስተማሪውን ፈለግ በመከተል ስመ ጥር ፈላስፋ ለመሆን የበቃ ሰው ነው (እንደ የፍልስፍና መምህሩና የአዲስ አድማሱ አምደኛ ፍቃዱ ቀነኒሣ የዘርዓ ያዕቆብና የተማሪው ወልደሕይወት ሐተታዎች፤ በይዘታቸውም ሆነ በአቀራረባቸው ተመሳሳይነት አላቸው)። ከዚያ በፊት ሁለቱ ተለያይተው ሊጠቀሱ በማይችሉ ፈላስፎች ምክንያት ስለ ዘርዓያዕቆብ ሳያነሱ ማለፍ አይቻልምና ባጭሩ ስለ’ሱ (ከትምህርት ጋር በተያያዘ) አንድ ነገር ብለን እንለፍ።
በትምህርት ላይ አብዮት ያካሄደ፣ የትምህርት አብዮተኛ ነበር። ለዚህም “ዘርዓያዕቆብ አክሱም ላይ ወንበር ዘርግቶ ሲያስተምር “ማጥመቅ’ የሚለውን ሃይማኖታዊውን የትምህርት ዓላማ፡ ወገንተኛ ሳይሆኑ “መመርመርና መጠየቅ” በሚለው ተካው፤ ”ማነብነብ” የሚለውን የማስተማሪያ ዘዴ ደግሞ ”መወያየትና መከራከር” በሚለው ዘዴ ለወጠው። ይሄ ነው የዘርዓያዕቆብ የትምህርት አብዮት!!!” ተብሎ በጥናትና ምርምር ሥራዎች ውስጥ የተጠቀሰለትን ማየት ነው። (እዚህ ጋ ከሶቅራጥስ የማስተማር ዘዴ (ሶቅራቲክ ሜተድ) ጋር በማያያዝ የተጠኑ ጥናቶች በርካቶች ሲሆኑ፤ በጉዳዩ ላይ የበለጠ ግንዛቤ ለመያዝ እነሱን ማንበብ ጠቃሚ ነው።)
የሁለቱን ዘመን ለመረዳት «ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት በ17ኛው ክ/ዘ ያገኙት ማህበረሰብ በቁሳዊ ሐብቱ የደኸዬ፣ በዓለማዊ ሕይወቱም እጅግ የተጎሳቆለ ነው፡፡» የሚለውን የብሩህ ዓለምነህን አስተያየት ይዘን፤ ስለቀንዲልነታቸው «የኢትዮጵያ የጽሑፍ ፍልስፍና ከጥበብ (wisdom) ሥራዎች ወደ አመክኖአዊ (rational)፤ ከውርስ ትርጉም ወደ ወጥ (original) ሥራነት ለመሸጋገሩ ህያው ምስክሮች ናቸውና – የዘርዓያዕቆብ (ወርቅዬ) እና የተማሪው የወልደሕይወት (ምትኩ) ሐተታዎች (philosophical treatise) ” የሚለውን አስምረንበት ውይይታችንን እንቀጥል፡፡
የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና መሠረት በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው የሃይማኖቶች አለመግባ ባትና ክርክር ነው። ዘርዓያዕቆብ እንደ ፈላስፋ በሃማኖታዊ ሥርዓትና ትምህርት ውስጥ ነው ያደገው። ”ሐተታ” በተሰኘ ሥራው ውስጥም ሀሳቡን ሲያዳብር ፈጣሪ የፍልስፍና ጉዞውን እንዲያቀናለት በመጠየቅ ነው። ሐተታ ውስጥ ዘርዓያዕቆብ እንደሚነግረን ሁሉን በፈጠረ ፈጣሪና ለሰው ልጅ ሕገ ልቦና በሰጠ አምላክ ስም በሕይወቴ የገጠሙኝን ነገሮች በዚች መጽሐፌ ውስጥ አቀርባለሁ በማለት ነው።(ፋሲል መርአዊ ስምነር 1976ን ጠቅሶ እንዳሰፈረው።)ጥናቱ”በመሠረታዊነት ዘርዓያዕቆብ የማህበረሰባዊ ፍትህና የግለሰብ ተፈጥሮ ላይ ሲያተኩር፣ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ደግሞ የመንግሥት አወቃቀርና የሕዝብ አስተዳደር ላይ ለማተኮር ሞክረዋል፡፡” ማለቱንም ልብ ይሏል።
ስለ ሁለቱ፤
ክለሳ ድርሳናችን እንደሚያመለክተው፣ ካህናቱ መንፈሳዊ ሕይወት (ከተፈጥሮ ሕግ ጋር መስማማት) እና ዓለማዊ ሕይወት ተጫራቾች አለመሆናቸውን በማስተማር ሕዝቡ ከወደቀበት የጉስቁልና ሕይወት እንዲያንሰራራ ማድረግ ይችሉ ነበር።ሆኖም ግን ካህናቱ ይሄንን ነገር ማድረግ ባለመቻላቸው የእነዚህን ሃይማኖታዊ ልሂቃን ሸክም ለመሸከም የመጡት ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት ናቸው።
የአፄ ቴዎድሮስን የዘመናዊነት ፕሮጀክት ሊሸከም የሚችለው ነባሩ ሃይማኖታዊ ትምህርት ሳይሆን የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት የሥነ ሰብዕ ትምህርት ብቻ ነው። የእነዚህ ፈላስፎች የባህልና የእምነት ፍተሻ የአብርሆት ዘመንን በማምጣት በኋላ ላይ አፄ ቴዎድሮስ ላይ ለሚያመረው የዘመናዊነት ፕሮጀክት አስቀድሞ የባህል መደላድል የመፍጠር አቅም ነበረው።በመሆኑም የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት አዲሱና መሠረታዊ ፍልስፍና የሰው ልጅ መንፈሳዊ ከፍታን የሚያመጣው የተደላደለ ቁሳዊ መሠረት ሲኖረው ነው!” የሚል ነው፡፡
ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርዓያዕቆብ “ሐተታ” የተሰኘውን የፍልስፍና መንገድ በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የሃይማኖት ግጭትና አለመግባባት እንደመፍትሄ አድርጎ ለማስቀመጥ ይጥራል። በዚህ ፍልስፍና ውስ ጥም ከፈጣሪ ህልውና፣ የእውነት ተፈጥሮ፣ በዓለም ላይ ያለውን ግጭትና መንስኤው እና የሥነምግባር ፍል ስፍና ለማዳበር ይሞክራል።
የኢትዮጵያ ፍልስፍና በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ የሚካተት ነው።ይሄንን ዘውግ የመሠረቱት ፈላስፎቻችን ደግሞ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት ናቸው። (ፍልስፍናንና ሃይማኖትን በማጣመር ለመጀመሪያ ጊዜ ወንበር የዘረጋው ግን ዘርዓያዕቆብ ነው። ለዚህም ነው ወልደ ሕይወት ከሌሎች የአገራችን ሊቃውንቶች ለየት ያለ ሐሳብ ይዞ የመጣው፡፡)
የወልደሕይወት ፍልስፍና የዘርዓያዕቆብ ቅጥያ ነው። ሆኖም ግን ከዘርዓያዕቆብ ወደ ወልደ ሕይወት የተደረገው ሽግግር ዕድገትም ምልሰትም አለው።(ብሩህ ይህንን “ሽግግሩ ዕድገት አለው” የምንለው ከስፋት እና ከአቀራረብ (Scope and method) — ከሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች ብዛት፣ ስፋትና የማስተማር ሥነ ዘዴ አንፃር ሲሆን፤ “ሽግግሩ ምልሰት አለው” የምንለው ደግሞ ከይዘትና ከአዲስነት (Content and originality) — ከርዕሰ ጉዳዮቹ ጥንካሬና ከአዲስነት አንፃር ነው፡፡” በማለት ያብራራዋል።)
ዘርዓያዕቆብ ያላነሳቸው ሆኖም ግን በወልደ ሕይወት ብቻ የተነሱ ሐሳቦችም አሉ። ለምሳሌ፡- ስለ ሕፃናት አስተዳደግ፣ ስለ አለባበስ፣ ስለ ፍቺ፣ ስለ ስልጣንና የመንግሥት ሹመት፣ ስለ መላዕክት እንዲሁም ስለ ሴቶች የወሲብ ስሜት እርካታ ፅፏል።(ወልደ ሕይወት ይሄንን የየጓዳችንን ገመና ነው ወደ አደባባይ አውጥቶ እንወያይበት ያለው። ዘርዓያዕቆብ ስለ ሴቶች መብት የተከራከረ ቢሆንም የስሜቷን ነገር ግን ረስቶት ነበረ፤ ይሄንን ክፍተት ያሟላውና የሴቶችን ጥያቄ ምልዑ ያደረገው ወልደ ሕይወት ነው፡፡)
“ቅጥያ ነው” ካለ በኋላ ወልደ ሕይወት ስለ ስልጣንና የመንግሥት ሹመት ማንሳቱ በዘርዓያዕቆብ የተጀመረው የኢትዮጵያ ፍልስፍና ገና የመጀመሪያው ትውልድ ላይ አድማሱን እያሰፋ ከሃይማኖታዊና ከማህበራዊ ትችቶች ወደ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የመስፋት አዝማሚያ መጀመሩን የሚያሳይ ነው፡፡
ከርዕሰ ጉዳዮች ስፋትና ብዛት አንፃር ወልደ ሕይወት የዘርዓያዕቆብን ፍልስፍና ይበልጥ አስፋፍቶታል። የሐተታዎቻቸውን የምዕራፍ ብዛት ብንመለከት እንኳን የወልደ ሕይወት መጽሐፍ ከዘርዓያዕቆብ በ20 ምዕራፎች ይበልጣል፤ የዘርዓያዕቆብ ሐተታ 15 ምዕራፎች ሲኖሩት፣ የወልደ ሕይወት ሐተታ ግን 35 ምዕራፎች አሉት። በምዕራፎቹ ብዛት ልክም ወልደ ሕይወት የሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች ሰፊና ብዛት ያላቸው ናቸው።ለምሳሌ ስለ ጤና እንክብካቤ፣ ስለ ሥራና ተግባረዕድ (የእጅ ሙያ)፣ ስለ ጋብቻና ምንኩስና፣ ስለ አመጋገብና ፆም፣ ስለ በይነ ዲሲፕሊን ትምህርቶች አስፈላጊነት (ከአንድ ቀኖናዊ ትምህርት መውጣት እንዳለብን) እንዲሁም እምነትን፣ አፈታሪክንና ልማድን ስለ መፈተሽ ዘርዓያዕቆብ አስቀድሞ የፃፈባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ቢሆኑም ወልደሕይወት ግን ይበልጥ አስፋፍቷቸዋል፡፡
ወደ ወልደሕይወት እንመለስ፤
በክላውድ ሰምነር አማካኝነት ስለ ወልደሕይወትም ሆነ ስለ“ሀተታ ወልደሕይወት” ሥራው በሚገባ ተብራርቶ ለዓለም ቀርቧል። (ከሰምነር ሥራዎች፣ በተለይም Classical Ethiopian Philosophy የሚለውን ይመለከቷል።)
የ“ፍልስፍና ፩” እና “ፍልስፍና ፪”” መጻሕፍት ደራሲ ብሩህ ዓለምነህ በአንድ ወቅት “የተዘነጋው ወልደ ሕይወት” በሚል ርእስ አዲስ አድማስ ላይ ባስነበበን ጽሑፍ እንደነገረን ከሆነ፤
“– ወልደ ሕይወት “ሌባና ቀማኛ” የሚለው ፊውዳላዊውን የገባር ሥርዓት ነው።በኢትዮጵያ የልሒቃን ታሪክ ውስጥ የገባሩን ሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ የተቸው ወልደሕይወት ነው – በ17ኛው ክ/ዘመን።ከወልደሕይወት 200 ዓመታት በኋላ የመጡት አፄ ቴዎድሮስ ሰፋፊ የመሬት ይዞታዎችን ለጭሰኞች በማከፋፈል የገባሩን ሕዝብ ሸክም ለማቃለል ሙከራ አድርገው ነበር፡፡–”
የወልደሕይወት አቀራረብ ከመምህሩ ለየት ያለ ሲሆን፤ አቀራረቡን ለየት የሚያደርገው በመጽሐፍ ቅዱስ የሚታወቁ ሐሳቦችን ሲፅፋቸው የአብዛኛዎቹን ማሳመኛቸውን ከእምነት ወደ አመክንዮ እየቀየረ መሆኑ ነው። ይሄም ተግባሩ የሚያስደንቀው ነው፤ እንደ ኦገስቲንና አኳይነስ ትንታኔዎችን የሠሩት በዚህ መልኩ ነበር፡፡
በፍልስፍና ሕይወቱ ወልደሕይወት በሁለት ነገሮች አብዝቶ ይመሰጣል፤ የመጀመሪያው በማስተማር ሥነ ዘዴው ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ፣ ሥራና የእጅ ሙያ ላይ ያለው ፅኑ አቋም ነው። (የመሬት ከበርቴው የጭሰኛውን ጉልበት በሚበዘበዝባት ፊውዳላዊት ኢትዮጵያ፣ የእጅ ሙያ መሰደቢያ በሆነባት ፊውዳላዊት ኢትዮጵያ፣ የጉልበት ሥራ ለመኳንንት ልጆች አይገባም በሚባልባት ፊውዳላዊት ኢትዮጵያ ላይ ወልደ ሕይወት ስለ እጅ ሙያ (በሐተታው ምዕራፍ 18 ላይ) የፃፈው ነገር እጅግ አስደናቂ ነው፡፡) ብሩህ ይህንን የወልደሕይወትን አስተያየት አስመልክተው ሰምነር “በፊውዳላዊት ኢትዮጵያ የሥራ ባህል ላይ የተሰነዘረ አብዮታዊ ሐሳብ” ማለታቸውንም አስፍሯል።
በ“ሌባና ቀማኛ” ሥራው አማካኝነት በዛ (በ17ኛው ክ/ዘ) የገባሩን ሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ የተቸው ወልደሕይወት ነው።(ከወልደሕይወት 200 ዓመታት በኋላ የመጡት አፄ ቴዎድሮስ ሰፋፊ የመሬት ይዞታዎችን ለጭሰኞች በማከፋፈል የገባሩን ሕዝብ ሸክም ለማቃለል ሙከራ አድርገው ነበር።)
ከወልደ ሕይወት 260 ዓመታት በኋላ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ በ20ኛው ክ/ዘ መጀመሪያ ላይ እነ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ፣ በጅሮንድ ተ/ሐዋርያት ተ/ማርያም እና ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ሲሆኑ፤ የመሬት ጉዳይ አገሪቱ አሁንም ድረስ ልትሻገረው ያልቻለችው መሆኑንና የ1966ቱ “የመሬት ላራሹ“ አብዮትም እንዳልፈታው ብሩህ ትዝብቱን ያክልበታል።
በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ የአዋቂዎች (በአገር በቀሉም በዘመናዊውም) ምድር ነች። (ምናልባት ያ የአዋቂዎች ምድርነቷ እየቀነሰ መጥቷል፤ የዩኒቨርሲቲዎቻችንና ምሩቃኖቻችን ቁጥር እየጨመረ በመጣበት በዚህ ዘመን ጭራሹንም እየመነመነ … መጣ የሚለው የአስተያየት ሰጪዎች አስተያየት ቆም ካላደረገን በስተቀር) ኢትዮጵያ የአዋቂዎች ምድር ነበረች። ይህ ደግሞ ከራሷም አልፎ ለዓለሙ ሁሉ ተርፎ እንደነበር ማስረጃዎች ሞልተዋል። ከእነዚህ ለዓለም ከተረፉት እውቀቶችና ፍልስፍናዎች መካከል አንዱ ይሄው የወልደሕይወት ፍልስፍና ነውና ባለውለታነቱ ድንበር የለውም። ለዛሬ በዚሁ አበቃን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2015 ዓ.ም