አሸባሪው ሕወሓት ባልተገባ ወታደራዊ አካሄድ ሕፃናትን ለውትድርና ማሰለፉ የጭካኔውን ጥግ ያሳየ ቢሆንም፣ የሰብዓዊመብት ተቆርቋሪ ነን የሚሉ አገራት፣ መንግሥታት እና ተቋማት በጉዳዩ ዙሪያ ዝምታን መምረጣቸው አግራሞትን ፈጥሯል። በተለይ በፈርጣማ ክንዷና በልዕለ ኃያልነቷ የምትታወቀው አሜሪካ እና ተቋሞቿ በጉዳዩ ዙሪያ ዝምታን መምረጣቸው በብዙ መልኩ አነጋጋሪ ሆኗል።
ጦርነት መግደልና መሞት ብቻ አይደለም። ዓለምአቀፍ የውጊያ ሥርዓት ያለው ነው። በሁለት ሰላም ፈላጊ ወይም ደግሞ በማሸነፍ ውስጥ ፍላጎታቸውን እውን ለማድረግ በተነሱ ቡድኖችና አገራት መካከል የሚደረግ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ሕግና ደንብ የሚመራም ጭምር ነው። ከዚህ ሕግ ውስጥ አንዱ ሕፃናትን ለጦርነት ማሰለፍን መከልከልን ይካተትበታል።
የአሸባሪው ሕወሓት የጦርነት ስትራቴጂ ግን ከመሠረቱ ዓለም አቀፉን ሕግጋት የጣሰ ሆኖ እናገኘዋለን። ኢትዮጵያ ላይ በከፈታቸው ጦርነቶች ሁሉ ይሄን ዓይነቱን ዓለምአቀፍ ደንብና ሕግጋትን በመጣስ አውሬነቱን በይፋ ሲያሳይ ቆይቷል። በሰሞኑ ጦርነትም ዕድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሱ፣ መሣሪያ ለመሸከም ቀርቶ ጉልበታቸው በወጉ ያልጠና ቦርቀው ያልጨረሱ ሕፃናትን ከእናታቸው ጉያ እየቀማ ለጦርነት ሲያሰለፍ በተለያዩ ማህበራዊ ገጾች ላይ ተመልክተናል። ይሄን ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ አረመኔአዊ ድርጊት እያየ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ዝምታን መምረጡ የቡድኑ ደጋፊነቱን በግልጽ ያሳየ ሆኗል።
ሕወሓት ዛሬ ብቻ ሳይሆን ባለፉት የሥልጣንም ሆነ የጦርነት ዘመኑ በሰብዓዊነት ላይም ሆነ በሌሎች ወገኖች ላይ ይሄ ነው የማይባል ግፍና በደሎችን ፈጽሟል። በተለይ ዓይን ባወጣ መንገድ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሚለኩሳቸው በእብሪት በሚለኩሳቸው ጦርነቶች እንደ አገር ብዙ ኪሳራዎችን ቢያደርስም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የደረሰበት አንዳች ውግዘት የለም። ከዝምታና ዓይቶ እንዳላየ ከመሆን ባለፈ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ ሌሎች ለሰብዓዊነት ቆመናል የሚሉ አካላት ተግባሮቹን ጆሮ ዳባ ብለዋል። አንዳንድ ዓለምአቀፍ የመገናኛ ተቋማትም ከዝምታ አልፈውም ድርጊቱን እንደ አንድ ጀብዱ ከፍ ባለ ድምጽ ሲያስተጋቡለትም ተስተውሏል።
ይህንን እውነታ/ የዓለምአቀፉን ኅብረተሰብ በተለይም የምዕራቡን ዓለም ዝምታ “ኖ ሞር” በሚል ዓለምአቀፋዊ ንቅናቄ መቀልበስ ባይቻል ኖሮ ሊያስከትል ይችል የነበረው አደጋ፤ ከሆነው በላይ እንደሚሆን ለመገመት አይከብድም።
ይህንን የቡድኑን ወንጀል፤ በዜጎች ላይ የተፈጸመን ግፍ፤ ከፍ ባለ ድምጽ በዓለምአቀፍ መድረኮች ያሰሙት ኢትዮጵያዊ አንደበቶች ናቸው። “ኖ ሞር” ሲሉ የሕወሓትን ግፍ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ (የምዕራቡን ዓለም) ዝምታ መስበር የቻሉት የእኛው የራሳችን አንደበቶች ናቸው።
ዛሬም ቢሆን ቡድኑ በዚህ እኩይ ተግባሩ ስለገፋበት፤ ተግባሩን የሚያወግዙ ድምጾች እየተሰሙ ነው። ከነዚህም ውስጥ አንዱ በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህርና የሕግ ምሁር የሆኑት ኢትዮጵያዊው ዓለማየሁ ገብረ ማርያም ናቸው።
ምሁሩ በቲውተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክታቸው ሕወሓት ጡት ያልጠገቡ፣ ሮጠው ያልቦረቁ ጨቅላ ሕፃናትን በማስገደድ ለጦርነት ሲያሰልፍ የባይደንን አስተዳደር በመውቀስ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በበኩላቸው «ሕወሓት ሕፃናትን ለውትድርና እየመለመለ በሕዝብ ማዕበል እየተጠቀመ ይገኛል» ሲሉም ዓለምአቀፉን ኅብረተሰብ በጉዳዩ ዙሪያ ለማንቃት ሞክረዋል። እንደ የዓለም ጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅትን የመሳሰሉና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማት «እውነት ስለሕፃናት ያሳስበናል የምትሉ ከሆነ ይሄን ድርጊት አውግዙ» ሲሉ ጥሪ ቢያቀርቡም ሰሚ ያገኙ አይመስሉም።
በፕሬስ ነፃነት እና በአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋችነታቸው የሚታወቁት ዶክተር ቫን ቴራራ «የሕወሓት እኩይ ድርጊት በአስቸኳይ መቆም አለበት» በማለት የሕወሓትን ድርጊት ካወገዙት ሌላኛዋ ታዋቂ ግለሰብ ናቸው።
«ሕፃናትን ለውትድርና መጠቀም የጦር ወንጀል ከመሆኑም ባለፈ የጭካኔ ተግባርም ነው። በመሆኑም ድርጊቱን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አጥብቆ ሊያወግዘው ይገባል» ሲሉም የሕወሓትን ያልተገባ የአውሬነት ጫፍ አጥብቀው ኮንነዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሕወሓትን ትክክለኛ ማንነት ቢያውቀውም፤ የቡድኑን ወንጀል እያየ እንዳላየ በማለፉ ቡድኑ የልብ ልብ እንዲሰማው ምክንያት ሆኖለታል። ቡድኑ ዛሬም ዓለም አቀፍ ሕግን በጣሰ አካሄድ የሕዝብ ማዕበል በሚል የጦርነት ስትራቴጂ በሰብዓዊነት ላይ ከፍተኛ ወንጀልን እየፈጸመ ይገኛል።
የሕወሓት የክፋት ዒላማና የጥፋት አጀንዳ በግለሰቦች የተናጠል ውግዘት የሚቆም አይደለም። በጉዳዩ ዙሪያም ዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ በአደባባይ እስኪናገር (ከተናገረ) የሚፈጠረው ጥፋት በቀላሉ የሚታሰብ አይደለም። ትውልድ የማጥፋት ያህል የሚታሰብ እና የሚወገዝ ነው።
ኃያላኖቹ እስኪናገሩ፣ ዝምታቸውን እስኪሰብሩ፣ ዓለም በአንድ ድምጽ አሸባሪው ሕወሓት እስክታወግዝ ድረስ ለአገራችን ድምጽ በመሆን የነውረኞችን ሴራ ማክሸፍ ከዜጎች ሁሉ የሚጠበቅ አሁነኛ ተግባር ነው። ጊዜ ልንሰጠው የማይገባ።
ሁሉም ዜጋ በአሸባሪው ሕወሓት በትግራይ ሕፃናት ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ የማውገዝ የሞራል ግዴታ አለበት፤ እነዚህ ዜጎች የነገ አገር ተረካቢዎች የመሆናቸው እውነታ ደግሞ ነገ ላይ የምናስባትን አገር ጎዶሎ እንደሚያደርጋት መዘንጋት የለብንም።
አሸባሪው ቡድን እንደ አገር በመላው ሕዝባችን ላይ፤ እንደ ሕዝብ በትግራይ ወንድሞቻችን ላይ ያልፈጠረው መከራና ስቃይ የለም። ያልዘራው የክፋት ሀሳብ፣ ያረጨው መርዝ የለም። የክፋት ልቦች ፍጻሜ፤ ክፉዎች ነገ እንደሌላቸው ሁሉ ቡድኑ ከክፋቱ ራሱ ቀን ቆጥሮ የእጁን ማግኘቱ የማይቀር ነው ።
በገዛ መንገዱ የሚወድቅበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። በገዛ ግፉ ይወድቃል። የትግራይ እናቶች ለቅሶ፣ በከንቱ የፈሰሰው የትግራይ ወጣቶች ደም ፍርድ ያመጣበታል። ሰላምን ረግጦ ጦርነትን ለናፈቀ፣ አንድነትን ሽሮ፣ ወንድማማችነትን ንቆ ውንብድናን የመረጠ መጨረሻው የከፋ ውድቀት ነው! ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2015 ዓ.ም