የኢትዮጵያ ትምህርት ዘርፍ ከሥርዓት እስከ አፈጻጸሙ ድረስ ከፍተቶች እንዳሉበት በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል። የባለሙያዎችም የዘወትር ጥያቄ እንደሆነ ይስተዋላል። ምክንያቱም በዘረፉ የሚታየው የሥርዓት እና የአፈጻጸም ክፍተቶች ኢትዮጵያውያንን ብዙ ዋጋ እያስከፈሏት ነው። አሁን ላለችበትና እየገጠማት ላለው ችግርም የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ይህ ክፍተት የሞላበት አፈጻጸም እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።
እስከዛሬ በነበረው የማስተማር ሥርዓት ውስጥ ሥነምግባር የሚባል ነገር አልነበረም። ከዚያ ይልቅ ትምህርቱ ትኩረት ያደርግ የነበረው ፖለቲካ ላይ ነው። ለዚህም ማሳያው በሥነምግባር ስም የሚሰጠው የሥ-ነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት ሲሆን፤ ዋና ዓላማውም ፖለቲካው ትምህርቱ ላይ እንዴት ኃይል እንዳለው ማሳየት ላይ ያነጣጠረ ነው። ይህ ደግሞ የትምህርት ሥርዓቱን ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል አድርጎታል። ሥርዓቱን በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ ሥርዓቱ በአፈጻጸም ረገድ የፖለቲካ መጠቀሚያ ወይም የፖለቲካ ጥገኛ እንዲሆን በር ከፍቶለታል።
ዘርፉን ካለበት ችግር ለማውጣት ትምህርት ለሙያተኞች መተው እና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አሠራር መከተል ምርጫ ብቻ ሳይሆን ግዴታ ቢሆንም ያም ሲደረግ አይስተዋልም። አሁን አሁን ግን ነገሮች እየተቀየሩ የመጡ ይመስላሉ። ከነበረው ችግርም ለመውጣት አንዳንድ እርምጃዎች ተጀምረዋል። ለምሳሌ፡- ፍኖተ ካርታ ተሰርቶ የትምህርት ሥርዓት አተገባበሩ ተፈትሾ በአዲስ መልክ ለመሥራት መታቀዱ አንዱ ነው። እስከዛሬ የታዩትን ችግሮች ይቀርፋል ተብሎ ታምኖበታልም።
ይህንን ተስፋ የተጣለበት ፍኖተ ካርታ ለመተግበር ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ሽርጉድ ከማለት አልፈው የሙከራ ተግባራቸውን እያጧጧፉ ነው። ከሙከራ ወጥተው ሙሉ ለሙሉ ወደሥራው ለመግባትም 2015 ዓ.ምን የሚጠብቁ ጥቂቶች አይደሉም። አዲሱ የትምህርት ዘመን በአዲሱ የሥርዓተ ትምህርት ትግበራ የሚጀመርበት ነው። እናም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ይህንን ተቀብለው በሙከራ ደረጃ ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ያው ጦርነት ከነበረባቸው በስተቀር።
እንደ ኢዜአ ዘገባ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በአገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ 80 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሙከራ ትግበራ ለመጀመር ዝግጅት ተጠናቋል። በሙከራ ትግበራ አጀማመር፣ በተዘጋጁት የማስተማሪያ መጽሀፍትና በትምህርት አሰጣጥ ዙሪያ የአሰልጣኞች ሥልጠና በደብረ ብርሃን ከተማ ተከናውኗል። በዚህ ወቅትም በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ ትምህርት ማበልፀጊያ መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ቴዎድሮስ ሸዋርገጥ እንዳሉት፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሥርዓተ ትምህርት ሪፎርሙ ግድ ነውና ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የሥርዓተ ትምህርት ሰነዶች የሚያካትታቸው የተማሪ ባህሪያት፣ የይዘት ፍሰት መርሀ ትምህርትና ሌሎች ዝግጅቶች ሲከናወኑ ቆይተዋል። በ2014 የትምህርት ዘመን በመላ ሀገሪቱ በተመረጡ 589 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአዲሱ የሥርዓተ ትምህርት የመማር ማስተማር የሙከራ ትግበራ ሲከናወን ቆይቷል።
ዶክተር ቴዎድሮስ፤ ከመስከረም ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮም እንዲሁ ከሙከራ በመውጣት በመላ ሀገሪቱ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ይተገበራል። በሁለተኛ ደረጃ ዘጠነኛና አስረኛ ክፍሎች ደግሞ በተመረጡ 80 ትምህርት ቤቶች የሙከራ ትግበራ ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል። ለዚህም የመማሪያና ማስተማሪያ መፅሀፍት ዝግጅት መደረጉን ያስረዳሉ። በ2016 ዓ.ም 11ኛና 12 ክፍል በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መስጠት እንደሚጀምር ጠቅሰው፤ ለዚህ ተግባር እውን መሆንም ከክልሎች ለተውጣጡ የትምህርት ባለሙያዎችና በሙከራ ትግበራ ለሚጀምሩ ትምህርት ቤቶች የአሰልጣኞች ሥልጠና እንደተሰጠ አስረድተዋል።
ከዚህ በፊት የነበረው የትምህርትና ሥልጠና አሰጣጥ አጠቃላይ እውቀት ላይ ያተኮረ በመሆኑ የጥራት አግባብነት ችግር ነበረበት። በመሆኑም በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተቃኝቶ እንዲተገበር ይሆናል። ተማሪዎች ሀገር በቀል እውቀት እንዲኖራቸው የግብረ ገብና የሥነ- ምግባር ትምህርትን ጨምሮ የሥራና ተግባር ትምህርት ያካተተ በመሆኑ ብዙ ውጤት የሚታይበት ይሆናልም ብለዋል።
ይህንን አቅጣጫ ተከትለው ሥራቸውን ከጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አንዱ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ በ55 ትምህርት ቤቶች ላይ በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ ይገኛል። ሥርዓተ ትምህርቱን በ2015 የትምህርት ዘመን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም በቢሮው ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላት በኩል አስረድቷል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ ትምህርት ሚኒስቴር በ2015 የትምህርት ዘመን በተመረጡ ትምህርት ቤቶች የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የሙከራ ትግበራ እንደሚጀመር አስታውቋል። ስለሆነም እንደ ከተማ አስተዳደር አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የትምህርት ጥራትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ግብረ ገብነት፣ አገር በቀል እውቀት፣ ሙያና የቀለም ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ተግባር፣ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የመንገድ ደህንነትና ሌሎች ትምህርቶችን ባካተተ መልኩ እንዲሰጥ ይደረጋል።
በ2015 የትምህርት ዘመን ደግሞ ሥርዓተ ትምህርቱን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ለመተግበር ዝግጅት ተጠናቋል። በሙከራ ትግበራው ወቅት ትምህርት በአግባቡ መድረሱ ይረጋገጣል። ይህ ተሞክሮ ደግሞ ከዚህ ቀደሙ በነበሩት የተለያዩ ሥራዎች የታየና ብዙ መሻሻሎችን ያሳየ በመሆኑ ውጤታማ ያደርገናል። ለአብነት የ2013 የትምህርት ዘመን ኮቪድ-19ኝን በመከላከል መማር ማስተማሩ የተካሄደበትና ውጤት ማስመዝገብ የተቻለበት አንዱ ማሳያ ነው። በተመሳሳይ የተማሪዎቸ ምገባ፣ የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት ለትምህርት ውጤት መሻሻል አስተዋፅኦ ማበርከቱም ሌላው የሚጀመሩ አዳዲስ አሰራሮች ውጤት እንደሚያመጣ የሚያመላክት ነው። እናም በእነዚህና መሰል ተግባራት የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥና መድገም ከቀነሰ እንዲሁም ጥራት ያለው ትምህር መስጠት ከተቻለ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ደግሞ የተሻለ ውጤት እንደሚመጣም እናምናለንና ጠንክረን የምንሰራ ይሆናል።
ሌላው አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት መተግበር ከጀመሩት መካከል የኦሮሚያ ክልል ሲሆን፤ ሥርዓት ትምህርቱ ትውልድን በዕውቀት፣ ሙያና ክህሎት ለማነፅ ትኩረት ያደረገ እንዲሁም የመማር ማስተማር ሂደቱ ተማሪ-ተኮር እንዲሆን የሚያስችል በመሆኑ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የአይሲቲ እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ እንደሚሰጥ በኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ዳይሬክተር ደረጀ ታደሰ ተገልጾ ነበር። በ2014 ዓ.ም ደግሞ በክልሉ ባሉ 75 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ እንደተተገበረም አስረድተዋል።
የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የመማሪያ መጽሀፍቶችና የመምህራን ማስተማሪያ ሞጁሎች መዘጋጀታቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በኦሮሚያ ክልል በሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከመስከረም 09/ 2015 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚተገበርም የተዘገቡ ዜናዎች ያመላክታሉ።
ሌላው አዲሱን የሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ካስጀመሩ ክልሎች መካከል የደቡብ ክልል ሲሆን፤ የትምህርት ሥርዓቱ በ 161 ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ይተገበራል ብሎ እቅድ ይዟል። በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የትምህርት ሥርዓቱ በክልሉ ሀገር በቀል ዕውቀት ላይ ትኩረት አድርጎ የተዘጋጀ በመሆኑና ለሙያና ምርታማነት፣ ለሥራ ፈጠራ፣ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያለው አስተዋዕጾ ከፍ ያለ በመሆኑ ከሙከራው ባለፈ ሙሉ ለሙሉ ወደሥራው እንዲገባ ይፈለጋል። በዚህም በሙከራ ደረጃ ባለፈው የትምህርት ዘመን በተለያዩ ቋንቋዎች በተዘጋጁ መጻህፍት በ115 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ሲተገበር ቆይቷል። አሁንም በ2015 የትምህርት ዘመን በክልሉ ሙሉ ለሙሉ ይጀመራል። ለዚህ ደግሞ እንደ ክልል ዘርፉን የመደገፍ ሥራ ይሰራል። ከዚህ ባሻገር የፖለቲካ አመራሩ እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትም የክልሉን የትምህርት ገጽታ ለመቀየር የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት አለበትና መነሳሳት ለመፍጠር ይሞከራል።
የመጨረሻ ያደረግነውና ልናነሳው የወደድነው ክልል የአማራ ክልልን ሲሆን፤ እርሱም እንደሌሎቹ ክልሎች የአዲሱን የትምህርት ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ካሳዬ አባተ እንደገለጹትም፤ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ለማስተማር ዝግጅት ተጠናቋል። በክልል ደረጃም የማስተማሪያ መጽሀፍት ተዘጋጅቷል። በዚህም በተመረጡ 44 የአንደኛና በ17 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት በሙከራ ደረጃ ለመተግበር ዝግጅት ተደርጓል። በትምህርት ቤቶቹ በሚጀመረው አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ከ77 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ። እናም የሙከራ ትግበራው በኅዳር 2014 ዓ.ም ይጀመራል። ክልሉ ይህንን ቢልም ወደ ተግባሩ ለመግባት ግን የነበረበት ቁመና እንደፈተነው ማንም ይረዳዋል።
በእርግጥ የትምህርት ዘርፉ ቀደም ሲልም ብዙ ችግሮች ነበሩበት። አንዱ ከፖለቲካ ጥገኝነት በአግባቡ አለመላቀቁ ሲሆን፤ ሌላው በኮቪድ-19ኝ የተፈተነ መሆኑ ነው። ከዚያ ይባስ ብሎ ደግሞ የሰሜኑ ጦርነት ሁሉንም የባሰ አደረገው። የዚህን ጊዜ ደግሞ አማራና አፋር ክልሎች በተለየ ሁኔታ እንዲጎዱ ሆነዋል። በክልሎቹ በሺዎች የሚቆጠሩ የትምህርት ተቋማት በሕወሓት ታጣቂዎች ወድመዋል። የትምህርት ቁሳቁሶችም ተዘርፈዋል። የመፈናቀልና የሞት አደጋም እንዲሁ ቀላል አልነበረም። ስለሆነም በዘርፉ የተጀመረውን የማሻሻያ ጅማሮ ከግብ ለማድረስ እንዲቸገሩ አድርጓቸዋል።
እንደሚታወቀው ትምህርት በዓለም ላይ ለሚታዩ ለውጦች ጉልህ ሚና የሚጫወት፣ ለዕድገትና ለለውጥ ቀዳሚ መሠረት ነው። ትምህርትን በአግባቡ የተጠቀሙ እና ውጤታማ የትምህርት ሥርዓት የተከተሉ የዓለም አገራት በተለያዩ ዘርፎች ቀዳሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። የትምህርት ዓላማ ዕውቀትን ማስጨበጥ እና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሁለንተናዊ ዕድገት ማምጣት እንደሆነ ግልጽ ነው። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ታምኖ ወደተግባር ቢገባም አንዳንዶች ትግበራውን እውን እንዳያደርጉ ግን እንቅፋት ገጥሟቸዋል።
በችግሩም በትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለው ማሕበረሰብ መቅሰም ያለበትን ተገቢ ዕውቀት አግኝቶ መውጣት ሲገባው ራስን ማዳን ላይ ብቻ አተኩሮ እንዲቆይ አስገድዶታል። ይሁን እንጂ በአለው አጋጣሚ ሁሉ ትምህርቱ ወደ ሙከራው እንዲገባ ይደረጋል መባሉ ተሰምቷል። ምክንያቱም ከጦርነቱ ጎን ለጎን የማስተማር ሥራው ሳይቋረጥ ሲያካሂድ እንደነበር ይታወቃል። እናም ችግሩ ያጋጠማቸውን ቦታዎች የተለየ ድጋፍ በማድረግ ወደ ሙከራ ተግባራቸው እንዲገቡ ማገዝ ያስፈልጋል። ያ ካልሆነ ግን ልዩነቶች ይፈጠሩና ትምህርት ሁሉንም የሀገራችንን ችግሮችና ጉድለቶች መሙላቱ እንዳይችል ይሆናሉ። ስለሆነም ተገቢነቱ፣ ጥራቱ፣ ችግሮቹና ጉድለቶቹ ላይ አይቶ መተጋገዝ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው ሳንል አናልፍም።
ለትውስታ
የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ ካርታው የተሻሻለው የትምህርት ሥርዓት የመማር ማስተማሩን የጥራት ደረጃ ለማሻሻል፣ እንዲሁም ሙያዊ ግዴታውን በብቃት የሚወጣ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የትምህርት ማሕበረሰብ መፍጠር የሚያስችል መሆኑ ስለታመነበት ነው። በዚህም መሰረት በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ግብረ ገብነት፣ አገር በቀል ዕውቀት፣ ሙያና የቀለም ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ተግባር፣ ጥናትና ምርምር ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች ሲሆኑ፣ ቅደመ አንደኛ ደረጃ፣ አንደኛ ደረጃ፣ መካከለኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ተከፋፍሏል።
በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ማሻሻያ ተደርጎባቸው ተግባራዊ እየተደረጉ ከሚገኙ መሻሻያዎች መካከል፣ ከ 1 እስከ 6ኛ ክፍል ላሉ የክፍል ደረጃዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት እንዲሰጥ፣ ከ 7እስከ 12ኛ ክፍል ሁሉም ተማሪ በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲማር እና ከ 1እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ እንግሊዝኛ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዲሠጥ የሚሉት ይገኙበታል።
በቀድመው የትምህርት ሥርዓት 10ኛ ክፍል ይሰጥ የነበረው አገራዊ የመልቀቂያ ፈተና እንዲቀር የተደረገ ሲሆን፣ አጠቃላይ ፈተና በክልል ደረጃ 6ኛ ክፍል እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ላይ ይሰጣል። ከዚህ ቀደም ሦስት ዓመት የነበረው የተማሪዎች የዩኒቨርስቲ ቆይታ ዝቅተኛው አራት ዓመት እንዲሆን ተደርጓልም። ለሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች በመጀመሪያ ዓመት ከሚሠጡ ትምህርቶች ውስጥ እንደ ጂኦግራፊ፣ አንትሮፖሎጂ፣ ሶሺዮሎጂና ሥነ-ምግባር የመሳሰሉት ተካተዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 2 / 2015 ዓ.ም