ባለፈው ዓመት በሀገራችን በሰሜኑ ክልል በተደረገው ጦርነት የውጭም ይሁን የሀገር ውስጥ ጣላቶቻችን ስንገዳገድ የወደቅን መስሏቸው ደስታቸው ከአቅም በላይ ሆኖ ነበር። ይሁን እንጂ ያሰቡት እንዳላሰቡት፤ የገመቱት ፣ እንዳልገመቱት ፤ የጠበቁት እንዳልጠበቁት ሆኗል። በዚህም የተፈጠረባቸው ግራ መጋባት የወቅቱ ትልቁ አጀንዳ እንደነበር ለማስታወስ ሩቅ አይደለም።
ይህ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ መንግሥት ለሰላም እድል ለመስጠት በሚል እጆቹን ለሰላም በማንሳት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ፤ ሀገርን ከጥይት ድምጽ ፤ትውልድን ከእልቂት ፤ የሀገር በረከቶችን ከጥፋት ለመታደግ ሰፊ መንገድ ተጉዟል። በዚህ ለጊዜውም ቢሆን ሀገራዊ እፎይታ ተፈጥሯል።
ይህ የመንግሥት የሰላም መንገድ ገና ከጅምሩ ያልጠዋጠለት አሸባሪው ሕወሓት ፤የተለያዩ አደናቃፊ ሃሳቦችን በመኮልኮል ለሰላም ምንም አይነት እድል መስጠት እንደማይፈልግ በተጨባጭ አሳይቷል። ከዚህም አልፎ እንደለመደው ግጭቶችን በመፍጠር ሀገርና ሕዝብን ወደ አላስፈላጊ ጦርነት ጎትቶ አስገብቷል።
አሁን ጦርነት ለሶስተኛ ጊዜ በአዲስ መልክ ተጀምሯል፤ ዛሬም ድረስ ስለሰላም የሚጮሁ ብዙ ድምጾች ቢኖሩም ፤ በቡድኑ በኩል አድማጭ አላገኙም። ከዛ ይልቅ ዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ ግራ በማጋባት ከጦርነት የማትረፍ የውልደት ባህሪውን በአደባባይ ሲገልጽ እየታየ ነው።
ቀደም ባለው ጦርነት ሕጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ ራሳቸውን ከዓለም አግልለው ለፈጣሪ ለመገዛት የመነኮሱት ጭምር ተጠቂ ሆነዋል። ሕጻናት ያለአሳዳጊ ቀርተዋል፤ አረጋውያኑም ያለጠዋሪ ቀርተው የሞቀው ጎጇቸው እንዲቀዘቅዝ ምክንያት ሆኗል። ክቡር የሆነው የሠው ልጅ ሕይወት እንዳልሆነ ሆኖ አልፏል።
ከሰው አልፎ ተርፎና ለሠው ልጆች ምግብነት የሚውሉ እንስሳት በቁማቸው በጥይት ተደብድበው እንዲሞቱ ሆኗል። በጦርነቱ ምን ያልተፈጠረ ነገር አለ? ብዙዎች ካደጉበት፤ ንብረት ካፈሩበት ወግ ማረጋቸውን ካዩበት (አይበታለው ብለው ተስፋ ካደረጉበት ) ቀያቸው ተፈናቅለው የሠው እጅ ጠባቂ ሆነዋል።
የነገ ትውልድ ማፍሪያ ይሆናሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ትምህርት ቤቶችም ግማሾቹ ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ ሌሎቹ ደግሞ በከፊል ውድመት ደርሶባቸዋል። ተማሪዎችም ቢሆን ከትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳይገኙ ከማድረግ በሻገርም ለሥነ ልቦና ጉዳት ተዳርገዋል። ሰዎች ሲታመሙ፣ ነፍሰጡሮች ምጥ ሲገጥማቸው በፍጥነት የሚያቀኑባቸው ሆስፒታሎች እንዳልሆኑ ሆነው እነርሱም ዳግም መታከምን እና መታደስን ፈልገዋል። ከጦርነቱ ባልተናነሰ መንገድ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴ ምርት በመደበቅ፤ ዋጋ በማናር ማሕበራዊ ምስቅልቅል እንዲፈጠር ረጅም መንገድ ተጉዘዋል። በዚህም በደሃው ሕዝብ ላይ ምሬትን በመፍጠር በመንግሥት ላይ ጫናዎችን ለማበራከት ሰርተዋል። በለውጡ ተስፈኛ የነበረውን ሕዝብ ከተስፋው ለመነጠል የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል።
ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማትም ይሁን መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት ብዙ ዓመታትን ሊፈጅ እንደሚችል ይታመናል ፤ ይህም ሀገሪቱም ማደግ ያለባትን ወይም መድረስ ያለባት የእድገት ደረጃ ላይ እንዳትደርስ ሳንካ መሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም ።
ጦርነት ሊያደርስ ከሚችለው ቁሳዊ፣ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራዎችን አንጻር ዛሬም ሰለሰላም የተሰጠውን እድል መጠቀም ተገቢ ነው ። በተለይም አሸባሪው ሕወሓት ከለመደው የጥፋት፤ የግርግርና የማጭበርበር መንገድ ወጥቶ ለሰላም እድል ሊሰጥ ይገባል።
የሀሰተኛ መረጃዎችም ጉዳይ ከሰላም ጥረቱ ጋር ታሳቢ ሊደረግ የሚገባ ነው። ባለፈው የጦርነት ወቅት ሀገራዊ ፈተና ከነበሩት መካከል ሀሰተኛ የመረጃ ስርጭት እንደነበር የሚታወስ ነው ፤ ይህም ለጦርነቱ አቅም ሆኖ የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን ለማሰብ የሚከብድ አይሆንም።
የሀሰተኛ መረጃዎች ምክንያት ብዙዎች ተረብሸው፤ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንኳን ግራ ተጋብተው አስተውለናል። ዛሬም ቢሆን ሀገሪቱን ለማተራመስ በማሰብ የሽብር ወሬ የሚነዙ በርካታ መሆናቸውን በማሰብ ችግሩን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። መንግሥትም መረጃዎች ማጥራት እና በፍጥነት ለሕብረተሰቡ ማድረስ ይጠበቅበታል።
ባለፈው ጦርነት የውጭ ጣልቃ ገብነት እስከምን እንደነበር የሚረሳ አይደለም። አንዳንድ ሀገራት ጦርነቱን በተዘዋዋሪ መንገድ ለመምራት እና ኢትዮጵያን በእጅ አዙር በባርነት ለመቀራመት ፍላጎት ማሳየታቸውንም በወቅቱ የታዘብነው ነው። ይህንን እውነታም በጥንቃቄ ማየቱ ተገቢ ነው።
ሌላው መጠቀስ ያለበት ጉዳይ እኛ ኢትዮጵያውያን ዛሬም ለመደጋገፍ እና ለመረዳዳት ወደ ኋላ የማንል ሕዝቦች መሆናችን ካሳዩ ክስተቶች አንዱ ያለፈው ጦርነት ነበር። ጦርነቱ በሌለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያውያም በጦርነቱ ቀጠና ያሉ ንጹሐን ዜጎችን ለመደገፍ የሄዱበትን መንገድና ቁርጠኝነት ዛሬ ላይ ልንደግመው ይገባል።
በጦርነት ቀጠና ለሚገኙ ወገኖቻችን ዛሬም ለእለት ጉርስ የሚሆናቸውን ምግቦች ፣ አልባሳት፣ ለሴት እህቶቻችን የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን እና መሰል ድጋፎችን በአይነትም ይሁን በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅብናል። የወደሙ ተቋማትን ለመጠገን እና ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲገነቡ ለማድረግ ግለሰቦች፣ማሕበራት፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ያሳዩትን ድጋፍና ርብርቦሽ ሊደግሙት ያስፈልጋል።
የሃይማኖት ተቋማት ተሰሚነታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ሲቪክ ማሕበራት፣ አክቲቪስቶች ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች በሁሉም መንገድ ሕዝባችን ከትናንቱ ጦርነት ተምሮ፤ ስለ ሰላምና ለሰላም ልቡን እንዲሰጥ ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
ጦርነትን በጦር ሜዳ ማሸነፍ በራሱ አልፋና ኦሜጋ አይደለም ፤አልፋና ኦሜጋ የሚሆነው በሰላም ማሸነፍ ሲቻል ነው። ተስማምቶ ፣ ተፋቅሮ፣ ጥላቻን እና ቂምን ትቶ፣ ይቅር ተባብሎ ሁለንዊ ለሠላም መዘርጋት ሲቻል ብቻ መሆኑን መገንዘብ ያሻል።
በምስጋና ፍቅሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 2 / 2015 ዓ.ም