ደመናው በጭጋግ ተሸፍኖ፣ የእርሻ ማሳው በሰብል ተሸፍኖ፣ ምድር አረንጓዴ ለብሳ የአይን መስህብ የምትሆንበት፤ ሰዎች የተዘራ ዘር ለፍሬ በቅቶ የጥጋብ ዘመን እንዲሆን የሚመኙበት የክረምት ወቅት መውጣት በብዙዎች ዘንድ ይናፈቃል። ዛሬ ዘመን ሰልጥኖ መሻገሪያ ድልድይ ተሰርቶና መጓጓዣውም ተመቻችቶ እንጂ በክረምቱ በሚሞላ ወንዝ ምክንያት መሻገሪያ ጠፍቶ ዘመድና ወዳጅ ለወራት መለያየት ግድ እንደነበርና ክረምቱ ሲወጣ በናፍቆት እንደሚገናኙ ታሪክ ያስታውሰናል።
ደመናው ገልጦ ብርሃን ሲሆን፣ ወቅት ሄዶ ወቅት መተካቱ ብቻ ሳይሆን፣ የሰዎች ተስፋም አብሮ ይለመልማል። ባለፈው ያጡትን ለማግኘት፣ ለሕይወት መስመራቸው የሚሆነውንም ለማቀድ፣ የተበላሸ ሕይወት ከነበራቸውም ለማስተካከል ቃል የሚገቡት ዘመን ሲለወጥ ነው። እንዲህ ያለው ተስፋና ቸር ምኞት በኢትዮጵያውያን የተለመደ ነው።
በመገናኛ ብዙሃን ሳይቀር ሰዎች የአዲስ ዓመት እቅዳቸውን፣ ተስፋቸውንና ምኞታቸውን እየተጠየቁ ለሌሎች ትምህርት ሆኖ ማስተላለፉም እንደ አንድ ባህል ተወስዷል። ይህ ሁሉ ተስፋና ምኞት የሚሰምረው ግን ሀገር ሰላም ስትሆን እንደሆነ አሁን ኢትዮጵያ ሀገራችን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ መገንዘብ ይቻላል።
ሰዎች እየተጨነቁና እያሰቡ ያሉት በአዲሱ የዘመን መለወጫ ስላቀዱት ሰለነገ የሕይወት መስመራቸው ወይንም አዲሱን ዓመት በምን ሁኔታ እንደሚቀበሉት ሳይሆን፣ ዛሬን ውለው ስለማደራቸውና በሕይወት ስለመቆየታቸው ነው። በዚህ ወቅት አርግጠኛ ከሚሆነው ሰው ይልቅ ‹‹እስኪ ቆይ›› የሚለው ሰው በዝቷል።
በተለይም የጦርነት ወላፈኑ በደጃቸው እያለፈ ከነገ ዛሬ ምን እሆን ይሆን? እያሉ ለሚጨነቁ በቅርብ ቤተሰባቸውና ወገናቸው ላይ ሞትና ስቃይ ምን እንደሆነና የመደፈር ወንጀልን እያዩ ለሚያሳልፉ፣ የጉዳቱ ሰለባ ጭምር ለሚሆኑ ከመናገርም በላይ ነው ችግሩ። ‹‹ጆሮ ሲመታ አይን ያለቅሳል›› እንዲሉ አንጻራዊ ሰላም ባለበት የሀገሪቱ ክፍል የሚኖረው ዜጋም ቢሆን በሥነልቦና እየተጎዳ ነው።
የጦርነት ወላፈኑ ባይደርስብትም ወገኑ በሞትና በስቃይ ውስጥ ሆኖ እንቅልፍ ሊተኛ አይችልም። የጦርነት ወላፈኑ እንደማይደርስበትም እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለው ስጋት ውስጥ እንዲወድቁ ያደረጋቸው ጉዳይም ግልጽ ነው።
ሰዎች በመኖርና ባለመኖር መካከል ሆነው የእለት ኑሮአቸውን በሰቆቃ እንዲያሳልፉ፣ ቀያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ፣ ኀዘንና ምሬት እንዲያደቃቸው፣ የመሳሪያ ድምጽ በመስማት ሞታቸውን እንዲያስቡ፣ በወገናቸው ስቃይ ቅስማቸው እንዲሰበር፣ ብቻ የሰው ልጅ በቃላት መግለጽ በማይቻል ሁኔታ ውስጥ እንዲሆን ያደረገው በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት የከፈተው አሸባሪው ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ትህነግ) ነው።
ቡድኑ አምና ከፊሉ በሬውን ጠምዶ ለእርሻ ሥራ ዝግጅት እያደረገ፣ ከፊሉም የእርሻ ሥራውን ጀምሮ በነበረበት ወቅት የጦርነት ነጋሪት ጎስሞ ህዝብን ለእልቂት፣ የግለሰብ፣ የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት ለውድመት ዳርጓል። ተምረው ሀገራቸውን ይጠቅማሉ የተባሉ ሕጻናትና ታዳጊዎችን ለጦርነት ማግዷል።
በጦርነቱ የህክምና መስጫዎችን፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት ገቢ በማስገኘት አስተዋጽኦ የነበራቸውን ፋብሪካዎች በማውደም በሀገርና በሕዝብ ላይ ተዘርዝሮ የማያልቅ ጥፋት ፈጽሟል።
በዜጎችም ላይ በተለይም ከኢትዮጵያውያን የማይጠበቅ በአይን ለማየት፣ በጆሮ ለመስማት የሚቀፍና ዘግናኝ የጭካኔ ድርጊቶችን ፈጽሟል፤ ለሕዝብ ቆሜያለሁ የሚል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እየነዛ፣ አስተዳድርሃለው፣ እታገልልሃለው ለሚለው ሕዝብ እንኳን ሳይራራ የትግራይን ሕዝብ የከፋ መከራና ስቃይ ውስጥ ከቷል።
ይህንኑ እኩይ የጥፋት ድርጊቱን የመንግሥትን የሰላም እጆች በመርገጥ ለሶስተኛ ጊዜ በሀገር ላይ ጦርነት በማወጅ ቀጥሎበታል። አብዛኛው የግብርና ሥራ ተጠናቅቆ ዳር ለመድረስ የቀናት እድሜ በሚጠበቅበት፣ ዜጎችም መንግሥት የጀመረው የሰላም መንገድ ሰምሮ ከጦርነት እሳት ውስጥ የሚወጡበትን እየናፈቁ ባለበት ወቅት ለሰላም የተዘረጋውን እጅ ረግጦ የተለመደውን የሰው ፍጅትና ሀብት ንብረት ማውደሙን ተያይዞታል።
ቡድኑ ትግራይ ሕዝብ የሚላከውን ሰብአዊ ድጋፎች በመዝረፍ ለጦርነት እያዋለ ይገኛል። በቅርቡን በአደባባይ ለሰብአዊ ድጋፍ ሊውል የተከማቸ ነዳጅ በመስረቅ በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ አሰፋሪ የተባለውን የወንጀል ድርጊቱ በአደባባይ ፈጽሟል። ይህንንም አይኑን በጨው አጥቦ ለማስተባበል ሞክሯል። ‹‹የሌባ አይነደረቅ መልሶ ልብ ያድርቅ›› እንደሚባለው።
ጥፋቱ ተነግሮ የማያልቀው ይህ ቡድን እንኳንስ የበዓል አዲስ ተስፋን ይቅርና የነገ የሰው ልጅ ህልውናንም ለማጨለም የተነሳ በመሆኑ ዜጎች ቡድኑን የጀመረው ጦርነት በድል ፍጻሜ እንዲያገኝ በሚችሉት ሁሉ ሊንቀሳቀሱ ይገባል። ስለ ነገ ተስፋቸው ቡድኑን አምረው ሊታገሉት ያ ስፈልጋል።
‹‹ወርቅ በእሳት ይፈተናል›› እንደሚባለው ሕዝባችን ስለ ሀገሩና ስለቀጣይ ተስፋዎቹ በአንድነት በመቆም የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በሙሉ በጽናት አሸንፎ የሚሻገርበትን አቅምና ቁርጠኝነት መፍጠር ይኖርበታል። ለዚህም የሚሆን ዝግጁነት በየእለቱ መፍጠር ይጠበቅበታል።
‹‹በጥባጭ ካለ ማንም ጥሩ ውሃ አይጠጣም›› ቢባልም ዘመን ከዘመን መሸጋገራችን አንድ ተስፋ ነውና ዘመኑን በደስታ መቀበሉ በራሱ ተስፋ ይሰጣል። የተስፋ ሌላው ተስፋ ማድረጊያውና ማከሚያ መንገዱ ዛሬ በጦርነቱ ቀያቸውን ለቀው በማይመች ሁኔታ በመጠለያ ውስጥ የሚገኙትን፣ በተለያየ ምክንያት ችግር ውስጥ የወደቁትን በሚቻለው ሁሉ በማገዝ ነው።
በዚህ የጦርነት ጊዜ ውስጥ ሆነን ቸር መመኘታችንን አናቆምም። ለሰው ልጅ የተሰጠው ትልቁ ተስፋ በመሆኑም በጦርነት ለስቃይ የተዳረገው ሕዝብና የደቀቀው ኢኮኖሚ መልሶ እንዲያገግም የጦርነቱ መቆም ትልቁና ዋነኛው ቢሆንም ሰዎች የእለት ተእለት ተግባራቸውን በማስቀጠልና የልማት ተሳትፎቸውንም በማጠናከር ኢትዮጵያን ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።
በጦርነት ውስጥም ሆነን እንደሀገር ያሳካናቸው እና ዓለም አቀፍ እውቅና ያስገኝልን የልማት ስራዎች አሉ። እነዚህን ስኬቶች 2015 ዓ.ም አጠናክረን በማስቀጠል አዲሱ ዓመት የበለጠ የስኬት ዘመን እንዲሆን ልንተጋ ይገባል። አዲስ ዓመት የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ አጠናክረን የምናስቀጥልበት የልማት ጊዜ እንዲሆንልን ብርታቱንና ጉልበቱን እንድንታደል ምኞቴ ለሁላችሁም ይሁን።
መልካም አዲስ ዓመት።
ለምለም ምንግሥቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም