የኢትዮጵያ መንግስት በአስር ዓመቱ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መሪ እቅድ ላይ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ማእድንን የኢኮኖሚ እድገቱ ምሰሶ ብሎ ይዟቸዋል። የማዕድን ማኒስቴርም ለማዕድን ዘርፉ የተሰጠውን ይህን ትኩረት ታሳቢ በማድረግ በ2014 በጀት ዓመት የተለያዩ ተግባሮችን አከናውኗል።
አገሪቱ የማዕድን ሀብቷን በማልማት ለኢኮኖሚው እድገት የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ ለማድረግ ከተከናወኑ አበይት ተግባሮች መካከል የተወሰኑትን በዚህ በ2014 ዓ.ም ማጠናቀቂያ እና በ2015 ዓ.ም ዋዜማ ላይ ሆነን በምድር በረከት አምዳችን እንዳስሳለን።
ኢንቨስትመንት በተለይም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ሰላምን በእጀጉ ይፈልጋል፤ ኮሽታንም ቢሆን የሚታገስ አይደለም። ይሁንና አገሪቱ ባለፉት ዓመታት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በአሸባሪው ሕወሓት በተደጋጋሚ በተከፈቱባት ጦርነቶችና በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በብዙ ፈተና ውስጥ ሆናም ኢንቨስተሮችን መሳቧን ቀጥላለች። ኢንቨስተሮችን ከሳበችባቸው ዘርፎች አንዱ ደግሞ የማዕድን ዘርፉ ነው፡፡
ለዚህም በአብነት መጠቀስ ካለባቸው መካከል በማዕድን ዘርፉ ሰገሌ በሚባለው የኢትዮጵያ ክፍል ወርቅ እና አብረው የሚገኙ ማዕድናትን ለማውጣት የሚያስችለውን ፈቃድ አግኝቶ ሥራ መጀመሩን ያስታወቀው የኖርዌዩ አኮቦ ሚኒራልስ ኩባንያ አንዱ ማሳያ ነው። የኩባንያው ኃላፊ ጆርገኝ ኤቭጄን ኢትዮጵያ የተረጋጋችና ሰላም ሆና እንዳገኟት ይገልጻሉ። ሃላፊው ኩባንያው በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንቱ መስክ መዋዕለ ነዋይ ለማፍሰስ ሲወስን እንዴት ግጭት በተቀሰቀሰበት የጦር ቀጠና ትሄዳላችሁ የሚሉ ጥያቄዎች ከሌሎች አቻ ኩባንያዎች ቀርቦለት እንደነበር ይናገራሉ። ከእነዚሁ ኩባንያዎች አዲስ አበባ በአሸባሪው እጅ ወድቃለች የሚል የተጋነነ መረጃም ደርሷቸዋል። መረጃው ፍጹም ሃሰት እንደሆነና እንዲያውም ኢትዮጵያ ከሌሎች የማዕድን ማውጣት ሥራ ከሚካሄድባቸው በርካታ አገራት ይልቅ የተረጋጋች እና ሠላማዊ አገር እንደሆነች ኩባንያቸው በወቅቱ ማረጋገጡን ተጠቁሟል፡፡
ኃላፊው በወቅቱ በኢትዮጵያ ላይ የተቀናጁ የመገናኛ ብዙኃን የሃሰት ዘገባዎች ሲሰሩ እንደነበር አስታውሰው፣ ዘገባውን ተከትሎ በአዲስ አበባ የሚገኘው የኖርዌይ ኤምባሲ የኖርዌይ ዜጎች አዲስ አበባን ለቀው እንዲወጡ ጥሪ ማድረጉንም ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ኤምባሲው ጥሪ ካደረገበት ቀን በፊትም ሆነ በኋላ እርሳቸውም ሆኑ ሠራተኞቻቸው ምንም የሽብርም ሆነ ያለመረጋጋት እንቅስቃሴ በመዲናዋ እንዳላስተዋሉና በስራቸው ላይ እንደሆነም ነው ያስረዱት። ማዕድን የሚያወጡበት ቦታ በአሸባሪው ቡድን ተይዞ ከነበረው አካባቢ 1 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር እንደሚርቅ ነው ጆርገን ኤቭጄን መግለጻቸውን ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ታህሳስ 8 ቀን 2014 ዓ.ም የዘገበውን ከማዕድን ሚኒስቴር ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
እየተጠናናቀ ያለው ዓመት ማዕድን ሚኒስቴር ከሚቀጥለው ዓመት አንስቶ የድንጋይ ከሰል በግዥ ከውጭ እንደማያስገባ ውሳኔ ላይ የደረሰበት ነበር። ይህ የሚሆነውም የውጭ ምንዛሬ በመመደብ በግዥ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ምርት በመተካት ነው። ይህን ታሳቢ በማድረግም ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ስምንት ከሚሆኑ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ከሚያወጡ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ኩባንያዎቹም የድንጋይ ከሰል ማውጫ ማሽኖችን በመግዛት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት እንደሚገቡ በውል ስምምነቱ ወቅት መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ድረገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በወቅቱም የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንደተናገሩት፤ የድንጋይ ከሰል እስካሁን ባለው ተሞክሮ ለሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች ነበር የሚውለው። ነገር ግን የብረታ ብረት አምራች ፋብሪካዎችም 50 በመቶ የሚሆነውን የድንጋይ ከሰል በግብአትነት በመጠቀም ነው የማምረት ስራቸውን የሚያከናውኑት። ወደፊት ሌሎች የብረታብረት ማምረቻ ፋብሪካዎች ሲከፈቱ ግብአቱ ስለሚያስፈልግ የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ማምረት የግድ ነው፡፡
ሚኒስትሩ ኢኒጂነር ታከለ ኡማ ስምንቱንም የመግባቢያ ስምምነቱን ከፈጸሙ ማግስት ጀምሮ ወደ ሥራ በመግባት የሚያስፈልገውን ግብአት በማቅረብ የድርሻቸውን እንዲወጡ በወቅቱ አደራ ብለውም ነበር። ግብአቱ በአገር ውስጥ ተመርቶ ለፋብሪካዎቹ መቅረቡ ለድንጋይ ከሰል ግዥ በዓመት የሚወጣውን ወደ ሶስት መቶ ሚሊየን ብር ወጭ ከመቀነሱ በተጨማሪ የኃይል ግብአት ለሚፈልጉ ማንኛቸውም አምራች ኢንዱስትሪዎች ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ለሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለኃይል ግብአት የሚውለው የድንጋይ ከሰል በበቂ ሁኔታ ማቅረብ ባለመቻሉና በዋጋ መናር ምክንያት ሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተቸግረው እንደነበር ሲገለጽ ቆይቷል፤ የሲሚንቶ ምርት የመሸጫ ዋጋ ከፍተኛ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች አንዱም የዚህ ግብአት በአገር ውስጥ አለመመረት መሆኑን የሚገልጹም አሉ። ችግሩ እየተጠናቀቀ ባለው በጀት አመት የተባባሰ ቢሆንም፣ ሲንከባለል የመጣ መሆኑም ይታወቃል፡፡
በማዕድን ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በአገር የኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለው የወርቅ ማዕድን እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ትልቅ ድርሻ እንዲኖር በማድረግ ረገድ ደግሞ የባህላዊ ወርቅ አምራቾች ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይጠቀሳሉ፡፡
ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በኩባንያዎች ተመርቶ ወደ ብሄራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን በአጠቃላይ ወደ ባንኩ ከሚገባው ወርቅ አምስት ከመቶ እንኳን አይሆንም። ወርቅ ለባንኩ በማቅረብ በኩል የላቀውን ድርሻ የያዙት ባህላዊ ወርቅ አምራቸቾ ናቸው። እነዚህ አምራቾች ወርቁን የሚያመርቱት በሁዋላ ቀር መንገድ ነው፤ ለጤናና ለአካላዊ ጉዳት በሚያጋልጥ እጅግ አድካሚ በሆነ ሁኔታ። በዚህ አይነት መንገድ ካመረቱት ወርቅ የድካማቸውን ያህል ገቢ እንደማያገኙም ተደጋግሞ ይገለጻል።
ማዕድን ሚኒስቴር ይህን ችግር ለመፍታትም ሰርቷል፤ አምራቾቹን ተጠቃሚ ያደርጋል ያለውን ውሳኔ ያሳለፈውም በዚሁ እየተጠናቀቀ ባለው አመት ነው። አምራቾቹ ለሚያመርቱት ወርቅ ከዓለም የወርቅ መሸጫ ዋጋ ከ10 እስከ 29 በመቶ ጭማሪ ያለው ክፍያ እንዲያገኙ ተደርጓል። የጭማሪ ማስተካከያው ለአምራቾች ገቢ ከሚያበረክተው በጎ አስተዋጽኦ በተጨማሪ ወደ ብሄራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን እንዲጨምር አስችሏል። ቀደም ሲል በህገወጥ መንገድ በሚከናወን ግብይት ምክንያት ወርቅ በሚፈለገው መጠን ወደ ባንክ አይገባም ነበር። ለውጡ የተወሰዱ የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎች ውጤት እንደሆነም ከሚኒስቴሩ መረጃ መረዳት ተችሏል። በሌላ በኩልም ዘርፉ ከወቅቱ የዓለም ሁኔታ ጋር እንዲራመድ፣ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲያድግ፣ተወዳዳሪም እንዲሆን ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ለመስራት ተግባራዊ እንቅስቃሴም መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፤ ዘርፉ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኝ ማዕድን ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ከሆኑት የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ አፍሪካ ልማት ባንክ እንዲሁም ከኔዘርላንድ ልማት ባንክና ከፈረንሳይ ልማት ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፤ የጂኦተርማል የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በፋይናንስ ለመደገፍ ከተቋማቱ ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በውይይቱ የገንዘብ ሚኒስትሩን አቶ አህመድ ሽዴን ጨምሮ የዓለም ባንክ፣ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክን ከመሳሰሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና አጋሮች በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ዙሪያ መነጋገራቸውም በወቅቱ ተገጻል። በውይይቱ ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም በተመለከተም ለፋይናንስ ተቋማቱ ተወካዮች ገለጻ እንደተደረገላቸውና የፋይናንስ ተቋማቱ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የማዕድን ፕሮጀክቶችን ለማገዝ እንዲሁም የማዕድን የግል ክፍለ ኢኮኖሚን በፋይናንስ ለመደገፍ ያላቸውን ፍላጎት መግለጻቸውም ነው የሚኒስቴሩ ማህበራዊ ድረገጽ መረጃ ያመለከተው። ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማቱ በዚህ ደረጃ ዘርፉን ከሚመራው ተቋምና ከከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ጋር መነጋገራቸው ለዘርፉ እድገት ተስፋን ያሳድራል፡፡
የማዕድን ዘርፉን የተመለከተ አጠቃላይ መረጃ ለማግኘት ክፍተቶች መኖራቸውም ሌላው በዘርፉ የሚነሳ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። የሥነምድር ትምህርት ክፍል ያላቸው አንዳንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) መጠነኛ የሆነ ሙዝየም ቢኖራቸውም፣ አጠቃላይ አገራዊ ሀብቱን በሚዳስስ መልኩ በተደራጀ ሁኔታ ስፋት ያላቸው ሙዚየሞች አለመኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። የማዕድን ሀብቷ አይነት፣ የሀብቱ መገኛ ሥፍራዎች፣ አጠቃላይ የሆነ መረጃ አገሬውም ሆነ የዓለም ማህበረሰብ የሚያውቅበትና አይቶም አድናቆቱን ሊገልጽ የሚችልበት አልፎም ተርፎም አልምቶ ሊጠቀምበት የሚያስችል ጋለሪ (የማሳያ መዘክር) ሳይኖራት መቆየቷ በአንዳንዶች ይነሳል፡፡
አሁን ግን ማዕድን ሚኒስቴር ኢትዮጵያ የማዕድን ጋለሪ እንዲኖራት መሠረት በመጣል ክፍተቱን በመሙላት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ተግባር ያከናወነው በዚሁ ዓመት ነው። ሚኒስቴሩም ጋለሪውን የጎበኙ የተለያዩ አካላትም የማዕድን ጋለሪውን ለአገር ትልቅ አበርክቶ ያለው ሲሉ አስተያየታቸውን በጽሁፍና በማህበራዊ ድረጋጾች (ፌስቡክ) ጭምር በማስፈር አድንቀውታል፡፡
‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ››እንዲሉ፣ የጋለሪው መደራጀት የማእድን ሀብቱ በተለያየ መንገድ እንዲገለጽና ገቢም እንዲያስገኝ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ተስፋ አሳድሯል። የአገር ውስጥም የውጭ ኢንቨስትመንትም ለመሳብም የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተጠቁሟል። ባለሀብቱ በጋለሪው ውስጥ በሚያገኘው መረጃ መሠረት ማእድን ለማልማትና ተጠቃሚ ለመሆን መሰማራት የሚፈልግበትን አካባቢና የማዕድን አይነት ለመለየት ሂደቱን ቀላል ያደርግለታል።
ጋለሪው የቱሪስት መስህብ ሆኖ ገቢ በማሰገኘት በአገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይም አስተዋጽኦ ያበረክታል። የአገር ገጽታን በመገንባትም ሚናው የጎላ ይሆናል። ለቱሪስቱና ለኢንቨስተሩ በጽሁፍ ማስረጃና በቃላት ከሚነገረው በላይ ማዕድናቱን በአይኑ ማየት እንዲችል መመቻቸቱ የበለጠ ትኩረትን ይስባል።
ለዘርፉ ተመራማሪዎችም መረጃ የማግኘት ድካማቸውን ከመቀነሱ በተጨማሪ የጥናት ሥራቸውን ለመለየትም ቀላል መንገድ ይሆንላቸዋል። በዘርፉ ምሁራንን የሚያፈሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸው በቅርብ ርቀት ላይ በተግባር የተደገፈ ዕውቀት አደንዲያገኙ ያግዛቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከምድር በታች ከሚገኘው የማዕድን ሀብቷ አንዱ የሆነው ነዳጅም ጥቅም ላይ ሳይውል ቆይቷል። ማልማት ተጀመረ ሲባል ሲቋረጥ እዚህ ተደርሷል። ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የተፈጥሮ ጋዝ ልማትም ብዙ ርቀት ሳይጓዝ መቅረቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ግን ሚኒስቴሩ በኦጋዴን አካባቢ ያለውን የነዳጅና የተፈጥሮ ሀብት አቅምና አዋጭነት ጥናት የውል ስምምነት ኤልሲኤአይ(LCAI) ከተባለው የአሜሪካ ኩባንያ ጋር አድርጎ ኩባንያውም በስምምነቱ መሰረት ጥናቱን አጠናቅቆ በማስረከብ የምሥራች አብስሯል። የጥናት ውጤቱን የሚያረጋግጥ ሰርተፍኬት ርክክብ በኩባንያውና በሚኒስቴሩ መካከል ተደርጓል፡፡
በጥናት ግኝቱም በኦጋዴን አካባቢ 7 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ ጥልቀት ያለው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል። የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ የማረጋገጫ ሰርተፍኬቱ ምን ያህል የተፈጥሮ ጋዝ እንዳለን የምናውቅበት ነው ሲሉም ተናግረዋል። ‹‹የሰርተፍኬቱ ሚና ሀገራችን ያላትን የተፈጥሮ ሀብት እውቀት፣ ልምድና ፍላጎት ሳይኖራቸው አንቀው ካቆዩት ኩባንያዎች በማላቀቅ ሊሰሩና ሊያለሙ ከሚችሉ ትላልቅ ኩባንያዎች ጋር ለመሥራት ያስችላል›› ሲሉ በወቅቱ ተናግረዋል፡፡
የዓመቱን አንኳር ክንውኖች ያነሳነውም በ2015 በጀት አመት በእቅድ የተያዙት ለውጤት እንዲበቁና አገር በዘርፉ የምትጠብቀው እንዲሳካ በማሰብ ነው፡፡
ኢንጂነር ታከለ ኡማ የማዕድን ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ የአገሪቱን የማእድን ሀብት ለአገሪቱ ጥቅም ማዋል እንዲሁም ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚሉት ዋና ግቦቻቸው ስለመሆናቸው መናገራቸው ይታወሳል። ‹‹የተፈጥሮ ፀጋ የሆነውን ይህን ሀብት በፍትሐዊነት ካልመራነው ለአገር የሚያበረክተው ትልቅ ሚና ወደሌላ ሊሄድ ስለሚችል የፍትሐዊነት ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ይሰጠዋል ነበር ›› ያሉት። ዘርፉ በአስር አመቱ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሪ እቅድ ያለበትን ሃላፊነት እንዲወጣ፣ ኢንቨስትመንት እንዲስብና ለወጣቶችም የሥራ ዕድል እንዲፈጥር፣ አቋራጭ መንገዶችን በመዝጋት በቀጥታ ለአገር ጥቅም እንዲውል እንደሚሰሩ አስታውቀውም ነበር።
በዘርፉ የተከናወኑ ተግባሮች ይበል የሚያሰኙ ናቸው። ዘርፉ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ሚኒስቴሩም ሃላፊነቱን ይበልጥ ለመወጣት እንዲችል አሁንም ጠንክሮ መስራት ይኖርበታል። የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ለማምረትና ከውጭ የሚገባውን ለማስቀረት ከኩባንያዎች ጋር የተጀመሩ ስራዎች በትኩረት ሊሰራባቸው ይገባል።
የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ማምረት ፋይዳው ብዙ ብዙ ነው፤ የኢንዱስትሪዎችን የኃይል ፍላጎት ማሟላት፣ የውጭ ምንዛሬ ማዳን፣ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻል ትልቅ ነገር ነው። ይህን ሁሉ ታሳቢ በማድረግ እንዲሁም ሚኒስቴሩ በድንጋይ ከሰል ልማቱ የያዘውን እቅድ ለማሳካት አንዳንድ ኩባንያዎች ከሚኒስቴሩ የሚጠብቁት ድጋፍ ፈጥኖ ሊደረግላቸው ይገባል።
ባህላዊ የወርቅ አምራቾች የድካማቸውን ያህል ገቢ እንዲያገኙ የተከናወነው ተግባር አምራቾቹንም መንግስትንም ተጠቃሚ ያደረገ ነው፤ ምርታማነቱ ይበልጥ እንዲጨምር ግን አመራረቱን ከሁዋላቀር መንገድ ማውጣት ይገባል። ለእዚህም የማምረቻ ቁሳቁስ ድጋፍና ስልጠና መመቻቸት ይኖርበታል፤ ዘመናዊ የወርቅ ማጠቢያ ማሸኖች ባለቤት ለመሆን የሚያደርጉት ጥረትም ድጋፍን የሚፈልግ ነው። መልካም አዲስ አመት !
ለምለም ምንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2014