ነፃ አገልግሎት ሰዎች ገንዘብ ወይም ሌላ የተለየ ጥቅም ሳይፈልጉ በራሳቸው ተነሳሽነት ወደውና ፈቅደው የሚከውኑት ተግባር ነው። በነፃ አገልግሎት ሰዎች ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ግዜያቸውን ወይም እጃቸው ላይ ያለውን ሀብት ለሌላቸው ያበረክታሉ። ይህም በበጎ የሚታይና በአርያነት የሚጠቀስ ተግባር ሲሆን በዚሁ ነፃ አገልግሎት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሲሆኑ ይታያል።
የነፃ አገልግሎት ተግባር እንዲቃናና በርካቶችም በዚህ በጎ ተግባር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ወጣቶች ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። በዚህ የክረምት ወቅትም በርካታ ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ውስጥ በመሳተፍ እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ግዚያቸውንና ገንዘባቸውን አገልግለቱን ለሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በነፃ እየሰጡ ነው። በዚሁ ተግባር አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ወጣቶችን መጥቀስም ይቻላል።
ወጣት ብርሃኑ ጋሻው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ነዋሪ ነው። በክፍለ ከተማው የወጣቶች ማህበር ሰብሳቢም ነው። የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ገና በልጅነቱ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ እንደጀመረ ይናገራል። አሁንም በዚሁ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ ሙሉ ግዜውን በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ይገልፃል።
እርሱና ሌሎች ወጣት ጓ ደኞቹ በዚህ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች በጎነት በሆስፒታል፣ በአይሲቲና የመአድ ማጋራት መርሃ ግብሮች ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ያስረዳል።
በተለይ በጎነት በሆስፒታል በሚለው መርሃ ግብር ከክፍለ አገር ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ታካሚዎችን መረጃ በመስጠት፣ ቋንቋ በማስተርጎምና በከተማዋ ሲንቀሳቀሱ የሚፈልጓቸውን ቦታዎች በማሳየት የነፃ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ይጠቁማል። ታካሚዎችን የማስታመምና የማገዝ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱንም ይናገራል።
በአነስተኛና ጥቃቅን ስራ ተሰማርቶ እንደሚገኝ የሚናገረው ወጣት ብርሃኑ የነፃ በጎ ፍቃድ አገልግሎቱን ከስራው ጎን ለጎን እንደሚያከናውን ይገልፃል። የነፃ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመስጠቱ ከፍተኛ የአእምሮ እርካታ እንደሚሰማውና ‹‹በጎ ስራ መስራትና የወለደን ማህበረሰብ ማገለግል ግዴታም ውዴታም ነው›› ይላል።
‹‹አገልጋይነት ከወጡበት ማህበረሰብ ዝቅ ብሎ ማገዝ ነው›› የሚለው ወጣት ብርሃኑ በተለይ አቅመ ደካሞችን መርዳት ትልቅ የመንፈስ እርካታ እንደሚሰማው ይገልፃል። በነፃ አገልግሎ ከአባቶችና እናቶች የሚያገኘው ምርቃት ለእርሱ ከገንዘብ በላይ መሆኑንም ያመለክታል።
ሌሎች ወጣቶችም የአገልጋይነት መንፈስ ተላብሰው ወገኖቻቸውን እንዲያገለግሉና የወጡበትን ማህበረሰብ እንዲረዱ ካልባሌ ቦታ ርቀው ወደዚህ የተቀደሰ ተግባር እንዲመጡ ጥሪውን ያቀርባል። ይህም ለቀጣይ ህይታቸው መቃናትና የስራ ልምድና ተነሳሽነት እንዲያገኙ አስተዋፅኦ እንዳለውም ይጠቅሳል።
በጎ ፍቃደኝነት እድሜ፣ ፆታ፣ ሃይማኖትና ብሄር የማይለይ በመሆኑ ሁሉም ወጣቶች የአገልጋይነት ስሜት ተላብሰው በበጎ ፍቃድ ቢሳተፍ አገልግሎቱን ለሚፈልጉ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ መሆን እንደሚቻልም ነው ወጣት ብርሃኑ የሚገልፀው።
ወጣት ዚያዳ ያጅቡ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ነዋሪ ናት። የነፃ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ገና የሰባት ዓመት ልጅ እያለች በትምህርት ቤት እንደጀመረችና በሂደት እያሳደገችው እንደመጣች ትናገራለች። አገልግሎቱን ስትጀምር በአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ውስጥ በመታቀፍ ህፃናቶችን በማስጠናት እንደነበርም ታስታውሳለች።
በዚህ መልኩ የጀመረችው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እያደገ፤ በኮቪድ ወቅትም ጎልብቶ ዛሬ ላይ የትራፊክ ነፃ አገልግሎት እየሰጠች እንደምትገኝ ትገልፃለች። ‹‹ነፃ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ለመግለፅ ቃላቶች ያጥሩኛል›› የምትለው ወጣት ዚያዳ በህይወቴ ከሚያስደስቱኝ ስራዎች መካከል አንዱ ይኸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ነው ትላለች። በህይወት ዘመኗ ደስ ብሏት እየሰራችው ያለችው ስራም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መሆኑን ጥገልፃለች። ከዚሁ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዋ በተጨማሪ ትምህርት እንደምትማርና ማታ ላይ እንደምታስተምርም ነው ወጣት ዚያዳ የምትናገረው።
ሁሉም ወጣቶች የአገልጋይነትን መንፈስ በመላበስ በበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ላይ መሳተፍና ህብረተሰቡን ማገዝ እንደሚችሉ የምትናገረው ወጣት ዚያዳ፤ ሰው ለመርዳት በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በእውቀትና በጉልበት መርዳት ስለሚቻል ሁሉም ወጣት ለማገዝ ፍቃደኛ ከሆነና ውስጡን ለበጎ ስራ ዝግጁ ካደረገ በርካታ ስራዎችን መስራት እንደሚቻል ታብራራለች።
ወጣቱ በህይወት ዘመኑ በጎ ስራ ሰርቶ ማለፍ ስላለበት ከሚሰሩት ስራ ጎን ለጎን እርዳታ የሚሹ ወገኖችን በመጠየቅና በማገዝ በርካታ ስራዎችን መስራት እንደሚችሉም ትጠቁማለች። ይህም ከምንም በላይ የአእምሮ እርካታን እንደሚሰጣቸው ትገልፃለች።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ወጣት ማህበር በአስተባባሪነት እየሰራ የሚገኘው ወጣት አቤል ባደገ ከማስተባበር ስራው በዘለለ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃግብር በቤት እድሳት፣ በሆስፒታል አገልግሎት፣ አረጋውያንና የጎዳና ልጆችን በማንሳትና በመመገብ፣ የበጎ ፍቃድ ትምህርት በመስጠት ስራ በተዘዋዋሪ ሲሳተፍ እንደቆየ ይናገራል።
‹‹የሰው ልጅ የተፈጠረው ለአንድ አላማ ነው ያም ማገልገል ነው›› የሚለው ወጣት አቤል መገልገለው የሚጀምረውም ከሰብአዊነት ነው ይላል። በተለይ ወጣት ከማንም በላይ ጉልበትና ግዜ ያለው በመሆኑ ይህን ጉልበቱንና ግዜውን ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ማበርከት እንደሚገባው ያመለክታል። ከእርሱ በታች ያሉ ታናናሾቹን ደግሞ ስለዚህ አገልግሎት ማስተማር እንደሚገባውም ይጠቅሳል።
በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ስምንት ዓመት እንዳስቆጠረና በነፃ አገልግሎት ሲሰጥ ደስ እንደሚለው፤ ይህን አገልግሎት ክረምት ወይም በጋ ሳይል እንደሚሰጥ ያስረዳል። በዚህ አገልግሎት የአእምሮ እርካታ ለማግኘት ምንም ነገር ከማድረግ የሚያግደው ነገር እንደሌለም ይናገራል። ሙሉ ግዜውን ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሰጠ ቢሆንም አሁንም ብዙ እንዳላገለገለ እንደሚሰማውም ይገልፃል።
ተፈጥሮ የራሷ ህጎች አሏት። ከነዚህ ህጎች ውስጥም አንዱ የመስጠትና የመቀበል ህግ እንደሆነ የሚገልፀው ወጣት አቤል፤ አንድ ሰው ወደዚህ ምድር የመጣው ለመስጠትና ለመቀበል እንደሆነ ያስረዳል። የሰው ልጅ በህይወቱ መልካም ነገርን ማግኘት ከሆነ መልካም ነገርን መስጠት እንዳለበት ይገልፃል።
እርሱም በህይወቱ ስኬትና የተሻለ ነገር ስለሚፈልግ ለሌሎች የተሻለ ነገር በመስጠት ማግኘት እንደሚችል አምኖበት ወደ በጎ ፍቃድ አገልግሎት እንደገባ ያመለክታል። ቋሚ የሚለው ገቢ እንደሌለውና ሙሉ ግዜውንም ለዚሁ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንደሰጠ ይጠቁማል።
በጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ላይ ብቻ አተኩሮ በመስራቱ ከተለያዩ ሱሶች ስለመራቁ፣ ስራ አጥ መሆኑን ስለመርሳቱ፣ ለነገ የተሻሉ ተስፋዎችንና መንገዶችን ለማየት ስለመቻሉም ነው ወጣት አቤል የሚገልፀው።
ወጣቱ በዚህ ግዜ አስተሳሰቡን ቀይሮ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን መስጠት እንዳለበትም ተናግሮ፤ ወደኋላ ከሚጎትቱ ነገሮች በመላቀቅ በነፃ ማገልገልን መማር እንዳለበትም ይመክራል። በዚህም ያተርፋል እንጂ አይከስርም ይላል።
ወጣት ፀሃይ ተሾመ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወጣቶች ማህበር ውስጥ ምክትል ሰብሳቢ ሆና ትሰራለች። በሁሉም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘርፎች ውስጥ ወጣቱ ተሳታፊ ሆኖ እንዲሰራ የማስተባበር ስራዎችን እንደምትሰራም ትናገራለች። እርሷም በዚሁ የበጎ ፍቃድ ስራ ተሳታፊ ሆና እየሰራች እንደምትገኝም ትገልፃለች።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ከአስር ዓመት በፊት እንደጀመረች የምትናገረው ወጣት ፀሃይ፤ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ውስጥ መሳተፍ ከሁሉም በላይ ትልቅ የአእምሮ እርካታ እንደሚሰጣት ትገልፃለች። ለነገ ህይወቷ ትልቅ መሰረት እንደሆናትም ትናገራለች። ‹‹ገንዘብና ሀብት አላቂ ቢሆንም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ግን እርካታን የሚያጎናፅፍ በመሆኑ መቼም የሚያልቅ አይደለም›› ትላለች ወጣት ፀሃይ።
እርሷ በምታስተባብረው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቶች በሁሉም ዘርፎች ስራዎችን ሲሰሩ እንደቆዩ ተናግራ፤ በተለይ በበጎነት በሆስፒታል፣ በቤት እድሳት፣ አቅመ ደካማዎችንና አካል ጉዳተኞችን በመደገፍ፣ ህፃናትን በመደገፍ በማስተማርና በትራፊክ አገልግሎት በርካታ ስራዎች እንደተከናወኑ ታብራራለች።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሚፈለገው ልክ ተደራሽ አልሆነም የምትለው ወጣት ፀሃይ፤ በተለይ ወጣቱ በንቃት እየተሳተፈ ባለመሆኑ አቅመ ደካሞችንና በገቢ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው ትጠቁማለች። ይህ ደግሞ ከዛሬ ሊጀምር ይገባል ትላለች።
ወጣቱ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት መሳተፍ ካልቻለና ለወጣበት ማህበረሰብ ርዳታና ድጋፍ ካላደረገ ጨካኝ፣ የማይተጋገዝ፣ የማይረዳዳና የማይተጋገዝ ማህበረሰብ እንደሚፈጠርም ነው ወጣት ፀሃይ ስጋቷን የምትገልፀው። በወጣቱ በኩልም ከበጎ ፍቃድ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ያለው ግንዛቤም አነስተኛ በመሆኑ በዚህ ረገድ ጠንካራ ስራ ሊሰራ እንደሚገባም ታሳስባለች።
ከበጎ ፍቃድ አገልግሎት ውጪ ቋሚ ስራ እንደሌላት የምትናገረው ወጣት ፀሃይ፤ ሙሉ ግዜዋን በዚሁ የነፃ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ አተኩራ እየሰራች እንደምትገኝ ትገልፃላች። ወጣቱ ማህበረሰብ ባለው ሞያና እውቀት ክፍያ ሳይጠብቅ በአገልጋይነት መንፈስ ህብረተሰቡን በነፃ እንዲያግዝ መልእክቷን ታስተላልፋለች።
ይህን ለማድረግ ታዲያ በቅድሚያ በወጣቱ በኩል የአስተሳሰብ ለውጥ ሊኖር ይገባል ትላለች። በጎነት ክፍያው ለራስ በመሆኑ ሁሉም በበጎነት ስራዎች ውስጥ እስከተሳተፈ ድረስ ሌሎችን ጠቅሞ ወደፊት ራሱንም መጥቀም እንደሚችል አውቆ መስራት እንዳለበትም ትመክራለች።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2014