ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም ወዲህ የዓለምን ሕዝብ ሰላም ከሚፈታተኑ በርካታ ችግሮች መካከል አንዱ የሽብር ሥራ እንደሆነ ማንም ይረደዋል። ሽብር ቤትን ያፈርሳል፤ ጎረቤትን ይበትናል፤ መንግስትን ያስነሳል፤ አገርንም ያጠፋል። እንደውም በአባባሉ ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› አይደል የሚባለው።
ከሽብር አንጻር በተለይ የውጭ ዓለሙን ትተን በአገራችን ብቻ ያለውን ብንመለከተው በሬ ወለደ አይነት ወሬዎች ብዙ ነገሮቻችንን በእጅጉ እየደበላለቁት መሆኑን መናገር ለቀባሪው አረዱት ነው። አንድ ነገር ብቻ ላንሳ፤ በአሁኑም ሆነ ከዚህ በፊት በነበሩት ጦርነቶች ሳቢያ የሆነውን።
የመጀመሪያው ሽብርን መተዳዳሪያቸው ያደረጉ ኢ-መደበኛ የሚዲያ አካላት ሲሆኑ፤ አሸባሪው ሕወሓት ቀደም ባለው ጊዜ ሆነ አሁን የለኮሰው ጦርነት ከለላ በማድረግ ሽብርና የሽብር ድርጊት ዋነኛ መተዳደሪያቸው አድርገው ሲንቀሳቀሱ ተስተውለዋል፤ ሁለተኛው ደግሞ እራሱ ሕወሓት እና እሱም መሰል አገር ጠል ኃይሎች የሚፈጥሩት ሽብርና የሽብር ተግባሮች ናቸው።
እነዚህ በሕዝብ ስም ሕዝብን የሚሸጡና ኪሳቸውን የሚያደልቡ ኢ-መደበኛ የሚዲያ አካላት የሙያ ስነምግባር ሆነ ሰብአዊ የሞራል እሴት የሌላቸው የመሆናቸው እውነታ የጥፋታቸው አድማስ ከፍ ያለ እንዲሆን አድርጎታል። አገርና ህዝብንም፣ ያስከፈሉትና እያስከፈሉት ያለውም ዋጋ ከፍ ያለ ነው።
ስልጣኑን በህዝባዊ እንቢተኝነት ያጣውና ይህንንም ማመን ያቃተው አሸባሪው ሕወሓትም ቢሆን ስልጣኑን በሽብር መልሶ ለመያዝ በሚያደርገው የአልሞት ባይ ተጋዳይነት መወራጨት በትግራይ ህዝብ ደም እየቆመረ ይገኛል ።
የእነዚህ ታሪካዊ ጠላቶችና የሌላ አካል ተልዕኮ ያነገቡ ኃይሎች እኩይ ተግባር እንደ አገር በተደጋጋሚ ጦርነትና መፈናቀል አምጥቷል። ሕዝባችን የተረጋጋ ሕይወትን እንዳይኖር አድርገውታል። ከእለት ወደ ዕለት እረፍት አልባ ሕይወትን እንዲያሳልፍም ገፋፍተውታል። ሕዝቡን እንዳያመርት አድርገው ተደጓሚና የሰውን ድጋፍ ጠባቂም አድርገውታል። በተለይም አሁን ይህ ባህሪያቸው ተፈጥሯዊ መለያቸው እና ግብራቸው ጭምር መሆኑን አፈትልኮ የወጣው ሰነዳቸው መረዳት ተችሏል።
በሁሉም አካባቢዎች ላይ የእርስ በእርስ ግጭት መፍጠር ከቻሉ በሕዝብ ደም የመቆመሩትን እድል እንደሚፈጥርላቸው፤ ቢዝነሳቸውን በቀላሉ ማሯሯጥም እንደሚያስችላቸው በሰነዳቸው በድፍረት አስቀምጠዋል። ለእነዚህ ኃይሎች ሰላም ገዳያቸው እንጂ አልሚያቸው በፍጹም ሊሆን አይችልም። የእንጀራ ገመዳቸውን ይበጥሰዋል። ለዚህም ነው በቻሉት ልክ ሰላም ማጥፋት ላይ ተሰማርተው የሚንቀሳቀሱት።
እርቅ ከወረደ የለመዱት ጥቅም ይቀርባቸዋል። ከዛም ባለፈ በቀደሙት ጦርነቶች ምን አተረፋችሁልን የሚል ጥያቄ መምጣቱ አይቀርም። ይህንን እውነት ላለመጋፈጥ ሁልጊዜ ጸባ ጫሪነታቸውን ይዘው ይቀጥላሉ፤ እየቀጠሉም ነው። በዚህም ደግሞ ከዓመት በላይ በሆነው ጦርነት ውስጥ እልፍ አላፍ የሆኑ ወገኖቻችን ለእልቂት ተዳርገዋል፤ ጦርነቱን ሽሽት እናቶችና ሕጻናት በየጎዳናው ላይ ወድቀዋል። የሚበሉት አጥተው ተኮራምተዋልም። የሚልሱት የሚቀምሱት በማጣታቸው የተነሳም የሞት አፋፍ ላይ የቆሙት እንዲሁ።
በአፋር በጋሊኮማ፣ በጎንደር በጭና፣ በሰሜን ወሎ አጋምሳ፣ በሰሜን ጎንደር ማይካድራ የተካህዱ ጭፍጨፋዎች ለዚህ ማሳያ ናቸው። ይህ የታሪክ ጠባሳ የመጣው ከቀደመው ታሪክ መማር ባለመቻላችን እንደሆነ አሁንም ወያኔ እና መሰል የጥፋት ፈረሶች ሊያዩት አይፈልጉም። ከቀደሙ ታሪኮቻችን ከመመርመር ይልቅ የቀደሙ የታሪክ ስህተቶችን ማጉላት ይቀናቸዋል።
ከቀደሙ የታሪክ ስህተቶቻችን ለመማር የሚያስችል እድል እንዳናገኝም አበክረው ይሰራሉ። አንተ የእንትና ዘር፤ አንቺ የእንትና ዘር እየተባባልን በመካከላችን መቃቃር ይፈጥራሉ። ለዚህ ደግሞ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ረብጣ ዶላሮችን ይቀበላሉ። እርሱን እየተጠቀሙ እኩይ አላማቸውን ያስፈጽማሉ።
አሸባሪው ሕወሓትን እና መሰል የጥፋት ፈረሶችን የሚጋልቡት የውጭ ኃይሎች በእርዳታ እና መሰል ማጭበርበሪያ ስራዎቻቸው ዛሬም ብዙ ተግባርን ይከውናሉ። ዋነኛ ተግባራቸው አድርገውም ይህንን የማጭበርበር ሥራ ይዘውት እየተጓዙ ነው። ይህ በእርዳታ እና መሰል ትርኪ ምርኪ ሥራ የሸፈኑት ተልእኮ ዋነኛ ግቡ አገርን ማፍረስ ነው። ይህንን የታሪካዊ ጠላቶች አገር የማፍረስ አላማ ማክሸፍ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተቀዳሚ ተግባር ነው።
አገርን ለማዳን ደግሞ ዘር እየቆጠሩ ከመነታረክ መውጣት ያስፈልጋል፤ መተባበር መንፈስን ወደ ውስጥ ማስገባትም ይገባል። በአንድ ላይ እጅ ለጅ ተያይዘን መቆምን መሰረታዊ ግብ ማድረግም የዛሬው ተቀዳሚ ተግባር መሆን ይገባዋል። ይህ ካልሆነ ግን እነኝህ ታሪካዊ የአገራችን ጠላቶች የሚያስነሱት እሳት ሁላችንንም ላንመለስ ለብልቦ እና አቃጥሎ መብላቱ አይቀርም። በተቻለን ሁሉ ከቀደሙ የታሪክ ስህተቶቻችን መማር የአሁን ተግባራችን መሆን አለበት። ምክንያቱም ታሪክ መኖሪያም መማሪያም ነው፤ ታሪክ መሻገሪያም መከበሪያም ነው።
ትርጉሙን ላልተረዳው ታሪክ መጥፎና የማይጠፋ ጠባሳ ነው። ታሪክ ትውልድን እስከነነብሱ መቅበሪያም ነው። አሁን እየሆነ ያለውም ይህ ነው። ስለዚህ ትውልዱን የሚያድን መካሪ አባቶች፣ ምሁራን፣ የፖለቲካ ኃይሎች ያስፈልጉናል። ዘካሪ እና መካሪ እናትና መምህርም ሊኖሩን ይገባል። አንድነት ላይ የሚሰራና ስለአንድነት የሚሰብክ ሕዝብም፣ የፖለቲካ ተዋናዮች መፍጠር ያስፈልጋል።
ጠላት በዋናነት አገርን እያፈረሰ ያለው በሚፈበርካቸው የውሸት ፕሮፓጋንዳዎች ነው። ይህንን ባለፈው ጦርነት ከፍ ያለ ዋጋ ከፍለንበት በአግባቡ መረዳት ችለናል። አሁንም ከትናንቱ ስህተታችን ስለመማራችን በቂ ማስተማመኛ የለም። ዛሬም በጠላቶቻችን ተራ ፕሮፓጋንዳ የሚታለሉ ጥቂቶች አይደለም። ይህ ደግሞ ዳግም የደም ዋጋ እንዳያስከፍለን መስራት ይገባናል።
በጦርነት ቀጠና ያለው ሕዝባችን በወገን ኃይሎች (በመከላከያ ልዩ ኃይል ፋኖና ሚሊሺያ) ሊታመንና ከጎኑ ሊቆም ያስፈልጋል። ጆሮውን ለበሬ ወለደ ትርክት ሰጥቶ ከሀብት ንብረቱ ሊፈናቀል አይገባውም። ጠላቴን እኔ ራሴ ተፋልሜ አቆመዋለሁ ! በሚል ቁርጠኝነት ተነሳስቶ ለጠላቱ ሬት ሊሆን ይገባል።
ሁሉም ለአገሩ ሉአላዊነት መከበር አርበኛ መሆንን ከአሁኑ ጀምሮ ማሳየት አለበት። ጦርነቱ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ስለሆነ እኔን አይነካኝም፤ አይመለከተኝም በሚል መቀመጥ የዋህነት ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከየአለበት ተሞ በመሄድ ለወገኖቹ መከታ መሆን ይገባዋል። በቻለው ሁሉ ጠላትን ድል ለማድረግ መረባረብ አለበት። አንድ ሆኖ ስለአገር ብሎ መንቀሳቀስም ይገባዋል። ወሬን ሰምተው የተባሉትን ከፍለው የኖሩበትን ቀዬ መልቀቅን ምርጫ ማድረግን ማቆም ያስፈልጋል።
በአምባገነኖች መገዛትና አለመገዛት የሕዝብን ውሳኔ የሚጠይቅ ነው። ይህ እንዳይሆን በነቂስ ወጥቶ መፋለም ምርጫ ሳይሆን ግዴታ እንደሆነ ልናምንበት ያስፈልጋል። እድላችንን በራሳችን ለመወሰን ተግባሩ መፋለም ብቻ መሆንም አለበት። ‹‹ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ›› እንደሚባለው የችግሩን ግዝፈትና ክብደት ከእኛ በቀር ሊያውቀው የሚችል ስለሌለ ሁላችንም ለድሉ ጠጠር መወርወር ላይ መረባረብ አለብን።
ጦርነቱን በአንድነት አለመመከት ቤተሰብን ማጣት፤ ራስን ለአደጋ ማጋለጥና ሕይወትን ጭምር መገበርን ሊያስከትልብን ይችላል። ሁሉም ባለበት ሆኖ የቻለ በጉልበት፤ ያልቻለ ደግሞ በጸሎት ማገዝ ላይ መታተር አለብን። የዚህን ጊዜ አሸናፊነታችንን እናረጋግጣለን። ሰላም ሆነንም ወደልማቱ ጎዳና እንገባለን።
ስናለማና ስንሰራ ደግሞ ጠባችን ይደርቃል፤ መቃቃራችንም ይቀንሳል። ደም በላ ነጋዴዎችም ይከስሙና እድገት ቦታውን ይረከባል። የተረጋጋ ትውልድና አገርም ይኖረናል። ስለሆነም ለአንድነታችን ዘብ እንቁም፤ ለጦራችን ተገንና ብርታት እንሁን በማለት ጽሁፌን ላሳርግ። ሰላም !!
ክብረ ነገስት
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2014