በዚህ ፍጥረተ ዓለም ውስጥ ከተረጋገጡት እውነቶች መካከል አንዱ ሞት ነው። ማን ነበር ”ከመሞት አልድንም …. አትጠራጠሪ …” ያለው ድምፃዊ? አዎ፣ እውነት ነው። ልዩነቱ ይህ የተረጋገጠ እውነት ድምፃዊው ጋ ሲደርስ በዜማ መገለፁ ብቻ ነው። ”ማን ነበረ ቆንጆ፣ ማን ነበረ አይናማ፣ ታዲያ ምን ያደርጋል መሞት አይቀርማ …” ያለውም እንደዛው።
የሰው ልጅ ጥንካሬ ከሚለካባቸው ጉዳዮች መካከልም አንዱ ይኸው ሞት መኖሩን አውቆ ልክ እንደሌለ አድርጎ በመቁጠር መኖሩ፤ እየኖረም መስራቱ፤ በተለይ ሌሎችን አስቦ ለሌሎች መኖሩ ነውና የያኔ ”ስም ከመቃብር በላይ ነው” የሚለው አባባል ተገቢ ቦታውን አገኘ ማለት ነው።
ዛሬ እዚህ የተገኘነው ስለሞት ለማውራት ሳይሆን ብዙም ሳንጠግባቸው፤ ብዙም ሰርተው ሳይደክሙ፤ ”ገና … መች ተነካና …” እያሉ ባሉበት ሰዓት ድንገት ሽው ስላሉት ባለውለታዎቻችን ሰዎች፤ ከእነዛም መካከል አንዳንድ ነገሮችን ለማለት ሲሆን፤ ከተሳካልንም ማስታወስ፣ መዘከር … ነው።
በእስከዛሬ የአምዳችን ጉዞ የተለያዩ ሰዎችን ከየ ማእዘኑ እያፈላለግን ስለ ህይወትና ስራዎቻቸው፤ አበርክቶና ባለውለታነታቸውን አምዳችን በፈቀደ የቻልነው ያህል ብለናል። ዛሬ ደግሞ፣ ቀኑ ጵጉሜ 2፤ እለቱም (በመንግስት የተሰየመው) ”የአምራችነት ቀን” በመሆኑ እኛም ፊታችንን ወደ ግብርናው ዘርፍ፤ በተለይም ወደ ግብርና ሚኒስቴርና ተመራማሪዎቹ ፊታችንን በማዞር ባለውለታዎችን መዘከር ላይ አድርገናል።
በፍለጋ ሂደታችን ወቅት ፈጥነን ያገኘናቸው የግብርናው ዘርፍ ተመራማሪና ለዘርፉ ምርትና ምርታማነት ከፍ ማለት የበኩላቸውን ያልተገደበ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ የነበሩትን፤ ነገር ግን ገና ብዙ ይሰራሉ ተብለው ሲጠበቁ ቶሎ የተለዩንን ዶ/ር አበበ አጥላውን ሲሆን፤ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ተከትሎ በየኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አማካኝነት (ሀምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም) ለንባብ የበቃው የህይወት ታሪካቸውን እንዳለ ወስደን እንመልከት።
ዶ/ር አበበ አጥላው በቀድሞው ሸዋ ክፍለ ሀገር ተጉለትና ቡልጋ አውራጃ፣ ሞንጃ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ ሰላ ድንጋይ በሚባል ቦታ ግንቦት 13 ቀን 1956 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ዶ/ር አበበ በ1975 ዓ.ም በቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የደብረ ዘይት እርሻ ኮሌጅ በሰብል ልማትና ጥበቃ ቴክኖሎጂ ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡ በ1984 ዓ.ም በኡዝቤኪስታን ታሽኬንት የግብርና ዩኒቨርሲቲ በዕጽዋት ጥበቃ የሁለተኛ ዲግሪ ያገኙ ሲሆን፤ በ1988 ዓ.ም በኡዝቤኪስታን አካዳሚ ታሽኬንት የጄኔቲክስ ኢንስቲትዩት በዕጽዋት ማዳቀልና ጄኔቲክስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡፡
ዶ/ር አበበ አጥላው ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በተለያዩ የምርምር ማዕከላት ያገለገሉ ሲሆን በፓዌ የግብርና ምርምር ማዕከል የማዕከሉ ዳይሬክተር እና የአገር አቀፍ የሩዝ ምርምር አስተባባሪ በመሆን፤ በደ/ዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል የአግሮ ኢኮኖሚ እና የሰብል ማሻሻያ ምርምር አስተባባሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከ2002 እስከ 2010 ዓ.ም በኢንስቲትዩቱ የሀገር አቀፍ የዘር ሥርዓት አስተባባሪ እና የቴክኖሎጂ ብዜት እና ዘር ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
ዶ/ር አበበ አጥላው የተለያዩ አገር አቀፍ ፕሮጀክቶችን በማስተባበር፣ በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ዘር ሥርዓት እና በሌሎች ሥራዎች የኮሚቴ አባል በመሆን በቅንነት እና በታታሪነት ያገለገሉ ሲሆን፤ በዘር ምርምር እና በሌሎች የግብርና ሳይንስ መስኮች ላይ የተለያዩ ጽሁፎችን አሳትመዋል፡፡ ዶ/ር አበበ ባደረባቸው ድንገተኛ ህመም ምክንያት ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን፤ ሀምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡
እንግዲህ ዶ/ር አበበ አጥላው ባጭሩ እኝህ ነበሩ። ይሁን እንጂ ወደ ስራዎቻቸው ስንዘልቅ ዶክተሩን እንዲህ እንደ ዋዛ በአንድ አንቀፅ የምንገልፃቸው አይደሉም። ብዙ ሰርተዋልና ስንገልፃቸውም በዛው ልክ ነው።
እንደተገለፀው ዶ/ር አበበ አጥላው ተመራማሪ ናቸው። በምርምር ስራዎቻቸውም አማካኝነት በርካታ ለአገርና ወገን ተርፈዋል። ይህም በየመድረኩ የሚሰማ ሲሆን፤ አሁን አሁን (የሁሉም) የምርምርና ግኝት ስራዎቻቸው ውጤት እያሳዩ ነው የሚሉ ወገኖች እየበዙ መጥተዋል። ”መረጃ” ሲባሉ ደግሞ ስንዴን በዋቢነት መጥቀስ ጀምረዋልና ደስ ይላል።
ከስንዴ ጋር በተያያዘ በአንድ ወቅት ባህር ዳር ላይ በተካሄደና ምርትና ምርታማነት ላይ ባተኮረ ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ዋና መስሪያ ቤት የቴክኖሎጂ ማስፋፋት ዳይሬክተር ዶ/ር አበበ በአማራ ክልል ለምርምር፤ እንዲሁም ለምርትን ምርታማነት እንቅፋት የሆነውን አሰራር የገለፁ ሲሆን፤ ዘርን አባዝቶ ለማሰራጨት ዋናው ቁልፍ ተግዳሮት የዘር ማባዣ መሬት አለመኖር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይህንንም ለመፍታት ባለድርሻ አካላት በጋራ በመወያየት ለምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች በቂ የሆነ የዘር ማባዣ መሬት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በአጽንኦት አስገንዝበዋል፡፡
”ይህ ምሁራዊ አስተያየታቸው ምን ፋይዳ አስገኘ?” የሚለውን እንመልከት፡፡ የምሁሩን አስተያየት ከግምት ውስጥ በማስገባት የክልሉ የግብርና ቢሮ ከ25,000 ሄክታር በላይ ለምርምር ማዕከላት እንዲገባ ቃል ገብተዋል፡፡
ከትልቁ ትልቅ፤ ከትንሹ ትንሽ … በመሆን አዋዋልን አሳምረው የሚችሉበት መሆናቸው የሚነገርላቸው ዶክተር አበበ፤ በሄዱበት ሁሉ የለውጥ፣ ምርትና ምርታማነት አርአያ መሆናቸው ይመሰከርላቸዋል፡፡ ስራዎቻቸው ከዚህ በመለስ ተብለው ብቻ የሚገለፁ ሳይሆኑ በአገሪቱ አራቱም ማዕዘን አሻራቸውን አሳርፈዋል።
ወትሮም ቢሆን ”ዶክተር”፣ ”ፕሮፌሰር”፣ ”ተመራማሪ”… ሲባል የብዙዎቻችን ልብም ሆነ እግር የሚኮበልለው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ ከዛም ወደ ፍልስፍና ወይም ሌላ ዲፓርትመንት ሆነና፤ አርሶ ከሚያበላን ጋር በመሆን የመኖራችን ዋልታና ማገር የሆኑትን፤ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩትን ሊቃውንት ልብ አንላቸው ሆኖ እንጂ ዶ/ር አበበ አጥላውም ሆኑ ሌሎች የዘርፉ ተመራማሪዎች ያገራችን ምሰሶ ስለመሆናቸው ስራቸው ብቻ ሳይሆን ህልውናችን ራሱ ምስክር ነው።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ “የግብርናና አካባቢ አስተዳደር ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ቃል ሲያካሂድ በነበረው ስምንተኛው ሀገራዊ አውደ ጥናት ላይ በርካታ የግብርና ምሁራን 23 ጥናታዊ ጽሑፎችን ያቀረቡ ሲሆን፤ አንዱም አገሪቱ በምትከተለው በምግብ እራስን የመቻል ስትራቴጂ ውስጥ ቁልፍ ተዋናይ የነበሩት ዶ/ር አበበ አጥላው ነበሩ።
ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር የተገኙት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በ1960ዎቹ በሀገር አቀፍ ደረጃ የስንዴ ምርታማነት በሄክታር ስድስት ኩንታል ነበር፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት በተከናወኑት ተግባራት ምርታማነቱን በሄክታር ወደ 25 ኩንታል ማሳደግ ተችሏል፡፡ አሁን የወጡት ምርጥ ዝርያዎች ይህን ከእጥፍ በላይ ያሳድጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለዚህ እውን መሆን ደግሞ የዶክተር አበበ እና ሌሎች የዘርፉ ምሁራን አስተዋፅኦ የማይተካ ነው።
የስንዴ ዝርያን በተለያዩ አካባቢዎች የሚያስፋፋው ፕሮጀክት አስተባባሪ የነበሩት ዶክተር አበበ አጥላው፤ በተለያዩ ጊዜያት የሚለቀቁ ዝርያዎች ከአየር ንብረት መለወጥ ጋር ተያይዞ በአዳዲስ በሽታዎች እየተጠቁ መሆናቸውን በማስተዋል በርካታ ስራዎችን ሲሰሩ እንደ ቆዩ ይነገርላቸዋል። ይህ ችግር ከተወገደ ግን በአካባቢው የተሰራጩት የስንዴ ዝርያዎች የተሻለ በሽታ የመቋቋም እና ከፍተኛ ምርት መስጠት እንደሚችሉ ማረጋገጣቸውም እንደዛው።
ይህንኑ በልባችን ይዘን የዶ/ር አበበን ስራዎች ስንፈትሽ ከላይ የጠቀስንላቸውን ብቻ አይደለም የምናገኘው። ከስንዴው በዘለለም ወደ ጤፉ ጎራም ተሰማርተው፤ የደረሱበትን ውጤት ይዘው ”እነሆ” ማለታቸውን እንረዳለን።
ዶ/ር አበበ ጤፍን በተመለከተ ሰፋ ያለና ለሚዲያ ፍጆታ ሁሉ የዋለ ጥናት አላቸው። በዚህ ጥናትም ስለ ጤፍ ብዙ ያሉ ሲሆን፤ ”ኢትዮጵያውያን ከማንኛውም አዝርዕት በበለጠ (በቆሎን ሳይጨምር) ጤፍ ይዘራሉ፤ ያመርታሉ፤ እንዲሁም ይመገባሉ፡፡ ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን አባወራዎች ወደ ሶስት ሚልዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ ጤፍ ይዘራሉ፡፡ የጤፍ ሳይንሳዊ ስሙ ኤራግሮስቲስ ጤፍ ሲሆን የተገኘውም ከኢትዮጵያ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በኢትዮጵያ ወደ 15 በመቶ የሚጠጋው ካሎሪ ከጤፍ የሚገኝ ነው፡፡”
ይህ ብቻም አይደለም፣ ጤፍን በተመለከተ ሌላ የሚሉት ያላቸው ሲሆን፤ እሱም ”ጤፍ ከስንዴና በቆሎ ያነሰ ምርት ነው የሚሰጠው፡፡ አማካይ አገራዊ ምርቱ 1.5 ቶን በሄክታር ነው፡፡ ነገር ግን በአመቺ ማብቀያ ቦታዎች ሊገኝ የሚችለው ምርት ወደ 3 ቶን በሄክታር ነው፡፡” የሚለው ነው። ”ለተለያዩ የግብርና ከባቢዎች (የአየር ንብረት ዞኖች) የሚስማሙ የተለያዩ ዘሮች አለመኖራቸው፡፡” ዋናው ችግር ነው የሚለውና ሌሎች በርካቶችም የሳቸው የጥናት ውጤትና መፍትሄ አፈላላጊ ሀሳቦቻቸው እንደ ነበሩ በጽሑፍ ሰፍሮላቸዋል።
”ጤፍ በኢትዮጵያ ሁለተኛው ታዋቂ አዝርዕት ቢሆንም ከሌሎች ለቋሚ ምግብነት ከሚውሉ ሰብሎች አንፃር በታሪክም የተዘነጋ ነው፡፡ በጤፍ ውስጥ ያሉት ንጥረ-ነገሮች ደረጃ ከሌሎች አዝርዕቶች ጋር ተመሳሳይ ሲሆን በአይረን፣ ካልሺየም፣ እና ኮፐር ይዘቱ ከሌሎች አዝርዕቶች ይበልጣል፡፡ ነገር ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጤፍ አነስተኛ ንጥረ-ነገሮችን የያዘ ነው የሚል የተሳሳተ አረዳድ ነበር፡፡” የሚለው ግኝታቸውንም ስለ ሁላችንም አረዳድና ግንዛቤ ሲባል እዚህ ላይ ማንሳቱ ፋይዳው ብዙ ነውና ዶ/ር አበበ በሙያቸው አንድ ወደ ፊት ናቸው ብንል ያስኬደናል።
ዶ/ር አበበ ጤፍን በተመለከተ ከላይ የጠቀስንላቸው አስተያየት ብቻ አይደለም ያላቸው፤ ”የኢትዮጵያ ገበሬዎች የጤፍ ዘርን በመበተን ይዘራሉ፡፡ ይህ የሆነውም በጣም አነስተኛ የሆነ የዘር መጠን በመስመር ለመዝራት በቂ ስለማይሆን ነው፡፡ ዘርን በመበተን ከመዝራት ይልቅ በመስመር መዝራት የተለያዩ ጥቆሞች አሉት፤ እንደየ አፈሩ አይነት አረም ማረምን ያቀላል፤ እንዲሁም የዘር መጠን ከ10-15 ኪሎ ግራም በሄክታር ዝቅ እንዲል ያደርጋል፡፡ እስከ 15 ኪሎ ግራም በሄክታር የሚደርስ የዘር መጠንን በቀላል አፈሮች ላይ መዝራት እና ብዙ የዘር መጠን በከባድ መረሬያማ አፈሮች ላይ መዝራት ማዳበሪያን በአግባቡ ለመጠቀምና ግሽበትን ለመከላከል ይረዳል፡፡” የሚል ምልከታና ምክርም አላቸው።
በፓርትነርሺፕ ፎር ኢንክሉሲቭ አግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሸን ኢን አፍሪካ (PIATA) አጋርነት ከአልያንስ ፎር ግሪን ሪቮሉሽን ኢን አፍሪካ (AGRA) በተገኘ ድጋፍ በተዘጋጀና በጁላይ 2019 በተከለሰ ጥናታቸው ”ኢትዮጵያ ባለው የጤፍ ምርት ዋናው ተግዳሮት አነስተኛ የአፈር ለምነት ነው፡፡” የሚሉት ዶ/ር አበበ ” ችግሩንም ለመቅረፍ ባህላዊ የአፈር ለምነትን መጠበቂያ ዘዴዎችን፤ የሰብል ተረፈ ምርት፣ ፍግ፣ እና አፈራርቆ ወይም ቀላቅሎ መዝራትን ይጨምራሉ ሲሉ ይመክራሉ፡፡ በገበያ የሚቀርቡ ማዳበሪያዎች ኤንፒኤስ፣ ኤንፒኤስቢ፣ ኤንፒኤስዜድ፣ ኤንፒኤስቢዜድ እና ዩሪያ ናቸው፡፡” ሲሉም ችግሮችንና መፍትሄዎችን ያስቀምጣሉ። ዝርዝሩ ብዙ ነው።
ዶ/ር አበበ ልክ እንደ ስንዴው ሁሉ፣ ጤፍን አስመልክተው በርካታ ተጨባጭ ነገሮችን ያነሱ ሲሆን አንዱም ”አርሶአደሮች ጤፍን በባህላዊ መንገድ በእበት በተለቀለቀ አውድማ ላይ ይወቃሉ፡፡ የተሰበሰበው ጤፍ አውድማው ላይ ይበተን እና ምርቱን ከግርዱ ለመለየት ከብቶች ወይም ሌሎች የጋማ ከብቶች እንዲያበራዩት ይደረጋል፡፡ ይህም ምርቱ ከአፈር ጋር እንዲቀላቀልና ከከብቶች እበት ጋር እንዲነካካ በማድረግ የምርት ጥራትን ይቀንሳል፡፡ ጤፍን በንፋስ አማካኝነት ምርቱን እና ግርዱን ለመለየት መበተን የጤፍ ፍሬዎች እንዲባክኑ በማድረግ የጤፍን የገበያ ዋጋ ይቀንሳል፡፡” በማለት ለዘመናት የመጣንበትን አሰራር የሚፈትሽ። እንደሳቸው አተያይ ይህም መሻሻልና ወደ ዘመናዊነት መምጣት አለበት።
ባጠቃላይ፣ ዶ/ር አበበ አጥላው በግብርናው ዘርፍ የበቁ ሰው ናቸው። በበርካታ ጥናትና ምርምር ስራዎቻቸው ዘርፉን ወደ ፊት ፈቀቅ ካደረጉት ምሁራን ባልደረቦቻቸውም አንዱ ናቸው። የተፈረደብን ከሚመስለው የድህነት አዙሪት እንድንወጣ እያደረግን ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ ሁነኛውን ስፍራ ይዘው እየተጫወቱ የነበሩ ሰው ናቸው። ምናልባት ለሌሎቻችን የሰለቸ የሚመስለው ”ምርትና ምርታማነት” ከወሬ አልፎ በተግባር እንዲታይ ለማድረግ እየተጉ ካሉት ሰዎች መካከልም አንዱ ነበሩ። በመሆኑም፣ እዚህ ስናስታውሳቸው፤ በዛሬው ”የአምራችነት ቀን”ም ስንዘክራቸው በአምራችነታቸው ምክንያት ነው ማለት ነውና፤ በድጋሚ ”ነፍሳቸውን በገነት ያኑረው!!!” እንላለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2/2014