ለሰው ልጆች ሥልጣኔና የዘመናዊነት መሻሻል ፈር ቀዳጅ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው ተብለው ከሚታሰቡት ውስጥ በይነ መረብ (ኢንተርኔት) ዋንኛ ተጠቃሽ ነው። ዓለማችንን የሚመራው መረጃ ነው። ይህን ታላቅ ቁልፍ ሳይዛባና ትክክለኛውን እውነታ ሳይለቅ በሁሉም ስፍራ እንዲደርስ ደግሞ ሁነኛ መንገድ ያስፈልጋል። የሰው ልጆች እንደየ አካባቢያቸው ባህልና የአኗኗር ሁኔታ ደግሞ አንዱ ከአንደኛው ጠቃሚ መረጃዎችን ይለዋወጡ ነበር።
ቀስ በቀስ ደግሞ እየዘመነና ቅርጹን እየለዋወጠ ፈጣን፣ የተጣራ እንዲሁም ጉልበትንና ወጪን የሚቀንስ “ዲጅታል” መረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል። የኮምፒውተርና የበይነ መረብ ቴክኖሎጂ በዓለማችን ላይ ከተዋወቀበት ጊዜ አንስቶ መረጃዎች ለፈለጋቸው ሁሉ በቅጽበት እንዲዳረሱና ጥቅም ላይ እንዲውሉ አስችሏል። ይህ ሂደት የበይነ መረብ ቋት ላይ ያለን መረጃ በተገቢው ማስተዳደር፣ ማዳረስ ብሎም ፍትሃዊነትን ማረጋገጥ የሚል ፅንሰ ሃሳብ ይዞ ሊመጣ ችሏል።
የተባበሩት መንግሽሥታት ድርጅት የኢኮኖሚና ማሕበራዊ ጉዳይ ክፍል በዓለም አቀፍ ደረጃ የበይነ መረብ አስተዳደር የምክክር ጉባኤ “the Internet Governance Forum (IGF)” እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2006 ጀምሮ እንዲኖር ደንግጎ ባለድርሻ አካላት በፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ሕግና ደንብ ዙሪያ እንዲወያዩና በየጊዜው ሪፎርሞችን እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።
የበይነ መረብ አስተዳደር ምንነት
የበይነ መረብ (የኢንተርኔት) አስተዳደር በመንግሥታት፣ በግሉ ሴክተር እና በሲቪል ማሕበረሰብ በየራሳቸው ሚና የጋራ መርሆዎችን፣ ደንቦችን፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶችን እና የበይነ መረብ ዝግመተ ለውጥ እና አጠቃቀምን የሚቀርጹ ፕሮግራሞችን ማዳበር እና ተግባራዊ ማድረግ ነው። ይህ ትርጓሜ የሰጠው “የቱኒዝ አጀንዳ ለመረጃ ማሕበረሰብ” እንዲሁም በመረጃ ማሕበረሰብ ላይ አተኩሮ 2005 በተካሄደው የዓለም ጉባኤ ላይ በተደረገ የአገራት ስምምነት ነው።
ከላይ በዝርዝር ለማንሳት እንደሞከርነው የበይነ መረብ (ኢንተርኔት አስተዳደር ፎረም) “IGF” ከኢንተርኔት አስተዳደር ቁልፍ አካላት ጋር በተያያዙ የሕዝብ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የብዙ ባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ነው። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2006 ከተካሄደው ከመጀመሪያው ስብሰባ ጀምሮ (አይ ጂ ኤፍ) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ “በቱኒስ አጀንዳ ለኢንፎርሜሽን ሶሳይቲ” በተቀመጠው ትእዛዝ መሰረት በየዓመቱ ይጠራል። ፎረሙ የውይይት መድረክ እንደመሆኑ መጠን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በእኩል መጠን መረጃ ለመለዋወጥ እና መልካም ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ወደ ጠረጴዛው ያቀርባል። አይ ጂ ኤፍ የበይነ መረብ እድሎችን እንዴት ከፍ ማድረግ እና አደጋዎችን እና ተግዳሮቶችን እንዴት እንደሚፈታ የጋራ ግንዛቤን ያመቻቻል።
ምንም እንኳን የቱኒዝ አጀንዳ በሕጋዊ መንገድ አስገዳጅ ባይሆንም የዓለም አቀፍ ጉባዔ ስለ መረጃ ማሕበር ዓላማዎችን እና የድርጊት መስመሮችን በአገር አቀፍ፣ በክልላዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትግበራን በተመለከተ ተከታታይ ምክሮችን ይዘረዝራል። ከእነዚህም መካከል ብሔራዊ ኢ-ስትራቴጂዎችን እንደ ሰፊው አገራዊ የልማት እቅዶች መገንባት፣ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን የቴክኒክ ድጋፍ ፕሮግራሞችን በመጠቀም፣ የተባበሩት መንግሥታት የክልል ኮሚሽኖችን እና የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎችን በአፈፃፀም ሂደት ውስጥ ማሳተፍ እና የሁሉም ባለድርሻ አካላት በአፈጻጸም እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎን ያካትታሉ። ለምሳሌ በ2015 የዓለም አቀፍ ጉባዔ ስለ መረጃ ማሕበር ውጤቶች አፈጻጸም አጠቃላይ ግምገማም ተጠርቶ ነበር። አጀንዳው በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ከሚያዝያ 2006 ባወጣው ውሳኔ 60/252 ጸድቋል።
እ.ኤ.አ በታህሳስ 2015 የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ከፍተኛ ደረጃ ስብሰባ በኒውዮርክ ተካሂዶ ነበር። በቱኒዝ አጀንዳ በሚፈለገው መሰረት የዓለም አቀፍ ጉባዔ ስለ መረጃ ማሕበር ውጤቶችን አፈጻጸም ለመገምገም ወስኗል። ስብሰባው የተጠናቀቀው በመንግሥታት መካከል የተስማማበት የውጤት ሰነድ በማጽደቅ ከሌሎች ጋር በቱኒዝ አጀንዳ ውስጥ የተቀመጡትን ቃላቶች በማረጋገጥ፣ ባለፉት 10 ዓመታት የተመዘገቡ ለውጦችን በማረጋገጥ፣ የዲጂታል ክፍፍልን በማገናኘት እና በማጠናከር ረገድ የበለጠ ጥረት እንዲደረግ በመወሰንና ምክረ ሃሳብ በመስጠት ነበር። በዓለም አቀፍ ጉባዔ ስለ መረጃ ማሕበር ውጤቶች አፈጻጸም አጠቃላይ ግምገማ ላይ አዲስ ከፍተኛ ደረጃ ስብሰባ ለ2025 ታቅዷል። በዚህ ታላቅ ስብሰባ ላይም የእድገት ሂደቶችን ለመገምገም እና ሁለቱንም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እና ተግዳሮቶችን ለመለየት እንደታሰበ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚያ በፊት ግን ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤን በመጪው ዓመት ህዳር ወር ላይ ታስተናግዳለች።
ብሄራዊ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የፈጠራ ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠቱን የሚያመለክቱ በርከታ ተግባራትን እያስተዋልን እንገኛለን። ከዚህ ውስጥ ወጣቶች ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት ማእከላትን መገንባትና ትላልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን (እንደ ኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የመሰሉ) ይፋ ማድረግ ይገኝበታል። በቅርብ ጊዜ ወስጥ ደግሞ ዓለም አቀፍ ተሳትፎውን በማስፋት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ምህዳር ውስጥ ለመግባት ልዩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የሚያመለክቱ ጉዳዮችን እያስተዋልን ነው። ለዚህ ማሳያው ከኢንተርኔት አስተዳደር የሚመለከተው ይገኝበታል።
በቅርቡም ኢትዮጵያ የመጀመሪያው ብሔራዊ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ በአካል እና በኦንላይን ጥምረት አካሂዳለች። ጉባኤው በመጪው ዓመት ህዳር ወር በአዲስ አበባ የሚካሄደው የ 17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ(ፎረም) አካል እንደሆነ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል። በጉባኤው የበይነ መረብ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ጥቅሞች፣ ተመጣጣኝ እና ትርጉም ያለው የበይነመረብ ተደራሽነት፣ እንደ መሰረታዊ መብት በሚሉት ጉዳዮች ላይ በትኩረት ተመክሮባቸዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ከበይነ መረብ ጋር ተያይዞ የሚመጡ አሉታዊ ጫናዎችን ለመቋቋምና ዜጎች በበይነ መረብ የሚያደርጉት ግኑኝነት አስተማማኝ እንዲሆን የሚያስችሉ ልዩ ልዩ አዋጆች በስራ ላይ እንዲውሉ መደረጉን ይናገራሉ።
ከሶስት ወራት በኋላ የሚካሄደው 17ኛውን ዓለም አቀፉ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ስኬታማ ለማድረግ፣ የሚነሱ ውይይቶች ሁሉን አቀፍ፣ ከዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የተናበቡና የሚነሱ ሃሳቦች በነጻነት የሚንሸራሸሩበት መድረክ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ በይነ መረብ ከጥቅሙ ባሻገር ከመረጃ መረብ ወንጀሎች፣ ከጥላቻ ንግግሮች፣ የሀሰትና የተዛቡ ዜናዎች ስርጭት አኳያ የተለያዩ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አሉታዊ ጎኖች እንዳሉት ያስረዳሉ። በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገውም ሆነ በህዳር ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ጉባኤ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የመፍትሄ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይ በአገር አቀፍ ደረጃ የተሰናዳው ጉባኤው ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምታስተናግደው 17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ ምረብ አስተዳደር ጉባኤ መሰረት የሚጥል ነው ተብሏል። ገጽታ ለመገንባት፣ ኢትዮጵያ በመስኩ እየሰራች ያለውን ስራ ለዓለም ለማሳየት፣ የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ተሰሚነት ለማሳደግ፣ ከተለያዩ ዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። የበይነ መረብ አስተዳደር ፎረም አስገዳጅ የሆኑ ውሳኔዎች የሚወሰኑበት ሳይሆን ውሳኔ አመንጪና ሰጪ የሆኑት የግሉ ዘርፍና መንግሥት በጉዳዮቹ ላይ መክረው የመረጃና የፖሊሲ ሀሳብ መነሻ ሆኖ የሚያገለግል ነው።
ጥቂት እውነታዎች
17ኛው የዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ዝግጅት ሂደትን አስመልክቶ በብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው የኢትዮጵያ መንግሥት አቋቁሞ ስራ ጀምሯል። ይህ ኮሚቴ የተለያዩ ተግባራትን ሲያካሂድ ቆይቷል። በተለይ ዓለም አቀፍ ጉባኤው ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ከመሆኑ አንፃር በስኬት እንዲጠናቀቅና ኢትዮጵያም ከዚህ መሰል ታላቅ ዝግጅት አትራፊ እንድትሆን በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን መንግሥት በየደረጃው ይፋ እያደረገ ነው።
የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አማካይነት ኢ.ኤ.አ በ 2006 ዓ.ም ይፋ ከተደረገ ጀምሮ ሲካሄድ የነበረ ጉባኤ ነው። ኢትዮጵያም 17ኛውን የኢንተርነት አስተዳደር ጉባኤ ኢ.ኤ.አ 2022 እንድታስተናግድ ተመርጣለች። ይህንን ተከትሎ ነው መንግሥት ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን እያደረገ ነው የሚገኘው።
የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር መረጃ እንደሚያመለክተው ጉባኤው ከበይነ መረብ እድገት ጋር የተያያዙ አንገቢጋቢ ጉዳዮችን፤ በይነ መረብ አስተዳደርና ሌሎች በበይነ መረብ በድጂታል ቴክኖሎጂዎች ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ የዓለም ክፍል የሚመጡ የግሉ ዘርፍ፤ መንግሥትና የዘርፉ ፖሊሲ አውጪዎች በተገኙበት የሚካሄድ እና በበይነ መረብ አስተዳደር ላይ የሚነሱ ሃሳቦች የጋራ ግንዛቤ የሚፈጠርበት መድረክ ነው። የዲጂታል ቴክኖሎጂ እና የበይነ መረብ አስተዳደርን በተመለከተ በየዓመቱ በሚካሄደው መሰል ፎረም ላይ ከተለያዩ ሀገር የተውጣጡ ተወካዮች ተገናኝተው የሚወያዩበት፤ መረጃ የሚለዋወጡበት፤ ልምድ የሚቀስሙበት እንደሆነም ይሄው መረጃ ያሳያል።
የኢንተርኔት አስተዳደር ፎረሙ ከኢንቴርኔት ጋር ተያይዞ ያሉ ዕድሎችን እንዲሁም ፈተናዎችና ተግዳሮቶችን በተመለከተ የሚነሱ ሃሳቦች የሚንሸራሸርበትና የጋራ ግንዛቤ የሚወሰድበት ነው።
ኢትዮጵያ የምታሰናዳውን የጉባኤውን ዝግጅት አስመልክቶ መሰናዶውን ስኬታማ የሚያደርጉ ውይይቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። አጠቃላይ ዝግጅቱም ከውጭ ጉዳይ፤ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ፤ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ጉሙሩክ ኮሚሽን፤ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፤ ፌዴራል ፖሊስ፤ ኢትዮ ቴሌኮም፤ ጤና ሚኒስቴር፣ ከቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን፣ ከብሄራዊ ባንክ በቅንጅት የሚሳተፉበት ነው።
እንደ መውጫ
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ቀርፃ እና አጽድቃ ወደ ስራ ገብታለች። ከዚህ የስትራቴጂ ሰነድ እንደምንረዳው ዲጂታል ኢትዮጵያ የዲጂታል እድሎችን በመጠቀም ፈጠራ የታከለበትና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል በኢትዮጵያ መንግሥት የሚመራ ተነሳሽነት መሆኑን ነው። ከአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ እና የአስር ዓመት የልማት ዕቅድን ከመሳሰሉ ቁልፍ አገራዊ ስትራቴጂዎች ጋር እንዲሁም እንደ አፍሪካ ህብረት አህጉራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ካሉ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂዎች ጋር የተሳሰረ መሆኑንም ያስረዳናል።
ይህን ስትራቴጂ ለማሳካት ደግሞ በመጪው ህዳር ወር የሚካሄደው “ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ” አይነት መድረኮች ጠቀሜታቸው የጎላ ነው። በተለይ የበይነ መረብ አጠቃቀም ፍትሃዊነት፣ እድገትና አስተዳደርን በተመለከተ ኢትዮጵያ ከአደጉ አገራት ልምድ ለመለዋወጥ እድሉን በስፋት የምታገኝበት ይሆናል። ከዚያም ባለፈ የአገር ገጽታን ለመገንባት፣ ወጣቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂና መሰል ዘርፎች ላይ በቀጥታ ተሳታፊ እንዲሆኑና ትስስር እንዲፈጥሩ አጋጣሚውን የሚከፍት ዝግጅት እንደሚሆን የጠበቃል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2014