ብዙውን ጊዜ የ”ሰው” ነገር የብዙ ጥናት መስኮችና የበርካታ አጥኚዎች ዐቢይ ርእሰ ጉዳይ ሲሆን ይታያል። ከኃይማኖት ተቋማት ጀምሮ እስከ እለት ተእለት የሰዎች መስተጋብር ድረስ ”ሰው” የሚለው ጽንሰ ሀሳብ እና ይኸው ጽንሰ ሀሳብ የሚገልፀው ግዘፍ የነሳው ፍጡር ሰማይና መሬት ከተላቀቁበት ጊዜ ጀምሮ መልሰው እስኪገጥሙ (ከገጠሙ ማለት ነው) ድረስ (እንደ ደበበ ሰይፉ አገላለፅ) ሲፈጭ፣ ሲሰለቅ፤ ሲወቀጥና ሲደለዝ ነው ከራሞቱ። በተለይ በኪነጥበቡ አለም ይህ አዲስ አይደለም።
በፍልስፍናው አለም ታዋቂው የጥንት ግሪክ ፈላስፋው፣ የ”cynicism” ፍልስፍና መስራች መሆኑ የሚነገርለት (የዚህ ዓለም ሀብት ሁሉ የጠቢባን ነው። እንዴት ቢሉት የዚህ ዓለም ሀብት የአማልክት ከሆነ፣ አማልክት ደግሞ የጠቢባን ወዳጆች ከሆኑ፣ ሀብቱ የጋራቸው መሆኑ አይቀሬ ነው።” የሚል አስተሳሰብን የሚያራምደው) ዲዮጋን ሲኖፕስኪ በፋኖስ ”ሰው” ፈልጎ የማጣቱን ጉዳይ፤ እንዲሁም፣ ”የሰው ነገር በቃኝ …” ካለችው ብዙዬ ጀምሮ ያሉትን ድምፃዊያን እንኳን ትተን፤ ወደ ሥነጽሑፉ፣ በተለይም ወደ ሥነግጥሙ አለም ብንመጣ ”ሰው” የበርካታ ስራዎች ዛቢያ (ኦርቢት) ሆኖ ነው የምናገኘው።
በነገራችን ላይ ዲዮጋን በልመና ነበር የሚተዳደረው። ለምን እንደሆነ ሲጠየቅ ‹‹ሰዎችን ለማስተማር›› በማለት መመለሱ ይነገርለታል፤ የታሪኩ አካልም ሆኖ ተጽፎለታል። ‹‹ምንድን ነው ምታስተምረው?›› ተብሎ ለተጠየቀውም ‹‹ልግስና›› ማለቱም እንደዛው። ይህንን እዚህ ጋር ስንጠቅስለት ከተነሳንበት ርእሰ ጉዳይ ጋር አይጋጭም ብለን በማሰብ ነው።
በሥነጽሑፉ አለም በቀዳሚነት ከነገሱት ቀዳሚያን መካከል አንዱና ተወርዋሪው ኮከብ ዮፍታሄ ንጉሤ “ዓይኔን ሰው ራበው …” ሲል የ”ሰው” እጦት ጠኔ ያንገበገበውን፤ ሎሬቱ በ”የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ” ግጥሙ “ሰው እንዳጣ ምድር በዳ”ን የጀመረበትን ስንኝ፤ ዳኛቸው ወርቁ ከሁሉም በቀደመ ተውኔት ድርሰቱ «ሰው አለ ብዬ» በማለት ራሱን የታዘበበትን፤ አቤ ጉበኛ “መልካሙ ሰው” በማለት ሰው በማግኘቱ ያገኘውን ያወደሰበትን፤ እንዲሁም ከአሁኑ ትውልድ ወጣት ገጣሚያን አንዱ አንተነህ አክሊሉ ”አዲሱ ሰው” በማለት ወደ አብርሆት ዘመን ሊያሻግረን የሞከረበትን …. ስራዎች ሁሉ እያነሳን ስለ ”ሰው” መጨዋወት እንችላለን።
እዚህ ድረስ ከተግባባን በቂ ነውና ወደ ዛሬው ”ሰው”፤ ወደ አምዳችን ልዩ እንግዳ እንመለስና እንጨዋወት። መጽሐፉ ”ለጠቢብ ሰው ትምህርትን ስጠው፤ ጥበብንም ያበዛል።” (ምሳሌ 9፣9) ይላል እኛም ዛሬ ጥበብን ያበዙ፤ አብዝተውም ”ብዙ ተባዙ …” በተባለው መሰረት ለተባዛነው ያዳረሱና እያዳረሱም ያሉ፤ በማዳረሳቸውም ብዙዎቻችንን የታደጉና እየታደጉም ያሉ ጠቢብን ይዘን ቀርበናል። ”የሰው ነገር …” ከሚለው ድባብ ወጥተን ወደ እንግዳችን የሕይወት ልምድ፣ ሙያዊ (ከጤና አኳያ) አበርክቶትና ተያያዥ ጉዳዮች እንሂድ።
ፕሮፌሰር ተስፋዬ ቢፍቱ ይባላሉ። የተወለዱት ጅማ አካባቢ አጋሮ ሲሆን፤ ጊዜውም 1943 ዓ.ም ነው። ዛሬ አለም አቀፍ ሰውና የ71 ዓመት እድሜ ባለፀጋ ናቸው። ዛሬ በሙያቸው አንቱ የተባሉት (በእንግሊዝኛው renowned medicinal scientist, Medicinal chemist, Distinguished Senior Investigator and Director of Discovery Chemistry, key player in the Januvia™ project …. ይሏቸዋል)
ዶክተር ተስፋዬ ትምህርታቸውን በተመለከተ
ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ እዛው ትውልድ ስፍራቸው በሚገኘው ”ራስ ደስታ ዳምጠው ትምህርት ቤት”፤ ከዛ አዲስ አበባ፤ ከዛ ወደ ባህርዳር አምርተው ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በ1968 (እ.አ.አ) ሲመረቁም ባለ ከፍተኛ ውጤት ተመራቂ በመሆናቸው ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ እጅ ልዩ የወርቅ ሜዳሊያ ተቀብለዋል።
የመጀመሪያ ሥራቸውን አሀዱ ያሉት እዚሁ አገራቸው ላይ ሲሆን፤ እሱም ንብረትነቱ የአሜሪካኖች በሆነው ቅመማ ቅመም ፋብሪካ ውስጥ ነው። በእነሱው አማካኝነት ያላቸው ችሎታና አቅም ታይቶ ደግሞ ወደ አሜሪካ እንዲያቀኑ እድሉ ተመቻቸላቸው። ከታች እስከ ላይ ዲግሪዎቻቸውንም እዛው አገኙ።
ዶክተር ተስፋዬ ለበርካታ በሽታዎች መድሀኒት (candidate drugs) የሚሆኑ ግኝቶች ባለቤት፤ ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት ሲሆኑ፤ በአለማችን ግዙፍ በሚባሉ ድርጅቶች ውስጥ ለረጅም ዓመታት የሰሩ ሰው ናቸው። በዚህ ሁሉ የስራ ዘመናቸው ውስጥ በርካታ ትሩፋቶች አሏቸው። ለአስም (Asthma)፤ ለአርትራይተስ (Arthritis የቁርጥማት ህመም)፤ ለኮለስትሮል (Cholesterol)፤ ለስኳር በሽታ (Diabetes) ለውፍረት ‘በሽታ’ (Obesity) እንዲሁም የተለያዩ መድሃኒት ግኝቶችና የባለቤትነት መብቶች (Patents) ያላቸው ናቸው። ወደ 120 ሳይንሳዊ ጽሁፎችን የጻፉ፤ ከዓመታት ወዲህ የካንሰር (Cancer) እና ወባ መድሐኒቶች ግኝት ላይ እየሰሩ ያሉ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስትም ናቸው።
ከመደበኛ ስራቸው (Pharmaceutical Research) በተጓዳኝ በተለያዩ የሙያ ማህበራት፣ ተቋማት በአባልነትና ሃላፊነት ሲሰሩ የነበሩትና እየሰሩ ያሉት ዶክተር ተስፋዬ፤ ለምሳሌ፡- Medicine for Malaria Venture (MMV)) ወደ ኢትዮዽያ በመምጣትም (በአዳማ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች) ድጋፍ ሰጥተዋል፤ እየሰጡም ነው። ከእነዚህ ስራዎቻቸው
በተጨማሪም እ.ኤ.አ ከ2009 እስከ 2013 ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ በተለያዩ እውቅ ዩኒቨርሲቲዎች (ጃፈርሰን ዩኒቨርሲቲ፣ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኒው ዮርክ፣ የኦሀዮ ስቴት ዩነቨርሲቲ …) እና አገራት (ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ስዊድን፣ ፖርቹጋል እና ሌሎችም) ውስጥ Medicinal Chemistry and Therapeutics እና ሌሎች ተዛማጅ ኮርሶችን አስተምረዋል።
የሜዲካል ኬሚስትሪ ተማሪ፣ ምሩቅ፣ የመድሀኒት ቅመማ ባለሙያ፤ ተመራማሪው በሚሰሩበት ሜርክ ኩባንያ (Merck & Co.) ውስጥም ቀዳሚ ሳይንቲስት (Chief Scientist) የሆኑ ናቸው። ከ12 በላይ የተለያዩ የበሽታ አይነቶች መነሻዎችን የለዩ፤ ለስኳር ህመምተኞች እያገለገለ ያለውን ጨምሮ ከ100 በላይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ያላቸው፤ በስራ ትጋታቻው፣ በአመራር ብቃታቸው፣ በተለያዩ አገራት (በተለይም በቻይና፣ አሜሪካ እና ህንድ) የስራ ቡድኖችን በማስተባበር ችሎታቸው፣ ባላቸው የካበተ ልምድ ይለያሉ።
የበለጠ ለመስራት ከመፈለጋቸው፤ በተግባቦት ክሂላቸው እንዲሁም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመሄድ በሚሰጧቸው ኮርሶች ውጤታማነታቸው ወዘተርፈ በሚያውቋቸው ሁሉ የተመሰከረላቸው ዶክተር ተስፋዬ ቢፍቱ፤ እ.ኤ.አ በ2016 ከሚሰሩበት ኩባንያ ጡረታ ቢወጡም (ጡረታ መውጣት ማለት መቀመጥ ማለት ሳይሆን፤ እንደውም ለሌላ ስራ መዘጋጀት ነው) በሚል አቋም እየተንቀሳቀሱ ያሉ መሆናቸውም ከሚያስመሰግናቸው መካከል ነው።
ከላይ ጠቆም እንዳደረግነው፣ ዶክተር ተስፋዬ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች በመስራት ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ አንዱ ወደ’ሚወዷት አገራቸው ኢትዮጵያ በመምጣት ከማስተማር ጀምሮ እስከ ማማከር የዘለቀው ድጋፋቸው ነው።
”ሐኪሞች ሁሌም ጀግናዎቻችን ናቸው። ዛሬ ደግሞ ይበልጥ በሕይወት እና ሞት ጦር ሜዳ ላይ ፊታውራሪዎቻችን ናቸው።” የሚሉ ሰዎች እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህ በጤናና ጤና ላይ የተመሰረተ ጀግንነትም ለዛሬው እንግዳችን፤ ለበርካታ በሽታዎች መድኃኒት ለፈጠሩት ኢትዮጵያዊ የሕክምና ሊቅ ዶክተር ተስፋዬ ቢፍቱ ይገባልና ተኪ ጀግኖችን እንደሚያፈሩም እርግጠኞች ነን። ምክንያቱም ዛሬም ጡረታ ወጥተው አልደከሙም። አሁንም ሌላ መድኃኒት ለመፈልሰፍ በጥናት ላይ ይገኛሉ።
ከላይ በጥቂቱ፣ የገባንን ያህል ብቻ የጠቀስንላቸው ሳይንቲስት ከላይ ከዘረዘርንላቸው በተጨማሪ ሌሎች በርካታ መገለጫዎች አሏቸው። አንዱ ከተለያዩ ተቋማት ጠራርገው የወሰዷቸው ሽልማቶቻቸው (ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ፋርማሲስቶች እና መድሀኒት ቀማሚ ሳይንቲስቶች ማህበር (EPPAD) ያገኙት) እንደማሳያ ይጠቀሳል። ሌሎቹ የዶክተሩ ሙያዊ ማንነት፣ ችሎታና ብቃት እንዲሁም አለማ’ቀፋዊነትም ልዩ መገለጫዎች ናቸው።
ስለ ዶክተር ተስፋዬ ቢፍቱ ሙያዊ ማንነትና አስተዋፅኦዋቸው፣ ሰብእናቸውን ይህን ያህል ካልን ማህበራዊ (ቤተሰብን ጨምሮ) መስተጋብራቸው ምን ይመስላል? በስራ ቆይታቸውስ ምን አከናወኑ? አሁንስ ምን አይነት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው? የሚለውን ከራሳቸው አንደበት እናዳምጥ።
የትዳር ህይወቴን በተመለከተ ጉዳዩ እንዲህ ነው። በአንድ ወቅት አባቴ ”መሳሪያ ደብቀሀል” ተብለው ታሰሩ። ልክ እኔም ”ፒኤች.ዲ”ዬን እንደጨረስኩ እሳቸውን መጠየቅ አለብኝ ብዬ ወደ አገር ቤት ተመለስኩ። በዛን ሰአትም ቁጭ ከምል በሚል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኬሚስትሪ መምህርነት ተቀጥሬ ማስተማር ጀመርኩ። በዛን ሰአት (በፈረንጆቹ በ1979) ነው እንግዲህ በወቅቱ የ2ኛ ደረጃ መምህርት ከነበረችው ባለቤቴ ወይዘሮ ትርሲት ታደሰ ጋር የተዋወቅነው። በቃ፤ ጨረስን። ተያይዘንም ወደ አሜሪካ መጣን። እዚሁም እየኖርን ነው።
ከባለቤቴ ጋር ሁለት ወንዶች ልጆችን ያፈራን ሲሆን፤ አንደኛው በፋርማሲና መድሀኒት ቅመማ የዶክተሬት ዲግሪውን ይዞ እየሰራ ነው። አንዱም ዶክቴሬቱን በሕግ ነው የያዘው። ወደ ስራው አለም ስንመጣ እኔ በአሜሪካን አገር የመጀመሪያ ስራዬን የጀመርኩት በአንድ ግዙፍ መርክ (Merck and Co) በሚባል ድርጅት ውስጥ ነው። በጣም ትልቅ ድርጅት ነው። በዓመት የ60 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ ያለው ድርጅት ነው።
በዚህ ድርጅት ውስጥ ስራዬን የጀመርኩት በሽታዎችን በመለየት አዳዲስ መዳኒቶችን በመፈልሰፍ እና መቀመም (drug discovery) ነው። በብዙ አይነት በሽታዎች ላይ ሰርቻለሁ። ለምሳሌ ድርጅቱ ከ60 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሽያጭ የሚያካሂድበትን የስኳር መድሃኒት ጨምሮ በርካታ በሽታዎች ላይ ሰርቻለሁ። ስንሰራ በቡድን ነው። ለብቻ እንኳን ቢሆን ብዙ ሙያዎችና ሰዎች አብረው መኖራቸው የግድ ነው። ካንሰር ላይም ሰርቻለሁ። የሰውና እንስሳት በሽታዎች ላይም እንዲሁ ሰርቻለሁ። በአጠቃላይ የተለያዩ በሽታዎች (inflammation, cardiovascular diseases, thrombosis, obesity, metabolic disorders, anti-cancer agents and infectious diseases ጨምሮ) ላይ የሰራሁ ሲሆን፤ የተለያዩ መዳኒቶችንም (Marizev™ ጨምሮ) አግኝቻለሁ። ከ100 በላይ የባለቤትነት መብት (international patent rights) አለኝ። (ጉግል ውስጥ ”ተስፋዬ ቢፍቱ ፓተንት” ብለው ቢጠይቁ ያገኙታል)።
የአዳዲስ መድሀኒት ስም ፍልሰፋ ክፍልን መርቻለሁ። አሁን ያለሁበትን ሁኔታ በተመለከተ እርግጥ ነው ከመርክ ኩባንያ በፈረንጆቹ ከ2016 ጀምሮ በጡረታ ወጥቻለሁ። ያ ማለት ግን ስራ አቆማለሁ፤ ወይም፣ ስራ አቁሚያለሁ ማለት አይደለም። በፍፁም እንደሱ ማለት አይደለም። ስራ አላቆምኩም። ኒው ዮርክ፣ ጄኔቭ … ባሉና በአፍሪካ ወባ ላይ የሚሰሩ ተቋማትን አግዛለሁ። ኢትዮጵያም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እየሰራሁ ነው። አስተምራለሁ። በአሁኑ ሰዓት፣ በFood and Nutrition ትምህርት ክፍል ሁለት (ዳንኤል እና ለሜሳ) ተመካሪ የዶክትሬት ተማሪዎች አሉኝ።
እዚህ አሜሪካ ጊዜ ከገንዘብም፣ ከምንም በላይ ተፈላጊ ነገር ነው። ከምንም በላይ ጠቃሚው ጊዜ ነው። በመሆኑም ሁሉም ለጊዜ ልዩ ትርጉምና ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል። እኔ የምጠቀምበትን አሰራር ልንገርህ። ለምሳሌ አሁን ከአንተ ጋር የማወራውን ጨምሮ ዛሬ የምሰራቸው ስራዎች በሙሉ አስቀድመው በጊዜ እና በዝርዝር ተቀምጠዋል። በእነዛ መሰረት ነው እንግዲህ ቀኑን ሙሉ የምሰራው።
አንዳንዴ ጊዜ ለሁሉም ነገር፣ ሁሉንም ለመስራት አይበቃም። በመሆኑም ከተያዙት ውስጥ እየታየ መቀነስ፤ አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ መጨመር ሁሉ ሊኖር ይችላል። ካሌንደር (የቀን መቁጠሪያን) ይሁነኝ ብሎ መጠቀም ይገባል። ይህን ማድረግ ከተቻለ እያንዳንዷን ሰከንድ ስራ ላይ ማዋል፤ እያንዳንዷን ደቂቃ በአግባቡ መጠቀም ይቻላል።
ተማሪም ሲኮንም ያው ነው። አንድ ተማሪ ስንት ትምህርት እንደሚማር ማወቅ አለበት። ለየትኛው ምን ያህል ጊዜ እንደሚያስፈልገውም መለየት አለበት። በዚሁ መሰረትም ጊዜውን መድቦ መስራት፣ ማጥናት አለበት። አለበለዚያ በኋላ እሚያደርገውን ነው የሚያጣው። ጊዜውን የተጠቀመ ይመስለውና ጭራሹንም ምንም ሳይጠቀምበት ያባክነዋል። ይህን ሲያደርግ ነው ማንም ሰው ወደ ፊት መሄድ የሚችለው። እንደ አገር የጊዜ አጠቃቀምን እዚህ ካለው አገር ጋር ካየነው የኛ አገር ደካማ ነው ማለት ይቻላል። እርግጥ ነው መዝናናት አያስፈልግም ማለት አይደለም። ያስፈልጋል። በስራ ላይም ግን መትጋት ያስፈልጋል።
እዚህ አሜሪካን ያለን ኢትዮጵያዊያን በከፍተኛ ደረጃ ለስራ ጉጉ ነን። አብዛኙቹ ብዙ ሰአት ይሰራሉ። እዚህ ስንመጣ ትጋታችን የተለየ ነው። እዛም እንደዚህ ቢሆን ጥሩ ነው። በእርግጥ አሁን መጥቼ እንዳየሁት ከተማው ሁሉ ተለውጧል። ያ ደግሞ ዝም ብሎ የሆነ ሳይሆን ሰው ነው የሰራው። ያ የሚያሳየው ደግሞ በጊዜ አጠቃቀምም ላይ ለውጥ መኖሩን ነው። በመሆኑም ጊዜ ሁሉንም ነገር ነውና እሱ ላይ መዘናጋት አያስፈልግም።
የኢትዮጵያውያን የጊዜ አጠቃቀም ሊያስተካክል ይገባል።እኔ ኢትዮጵያን ከልጅነቴ ጀምሮ ኢትዮጵያን አውቃታለሁ። በነጋ ቁጥር ሁሉም ስራ አለው፣ ሁሉም ስራው ላይ ነው የሚተጋው። አንተ ከየት ነህ፤ አንቺ ከየት ነሽ የሚል ነገር የለም። እኔ አሁን አላውቅም እንጂ እኔ በነበርኩበት ጊዜ አንተ ከጉራጌ፣ አንተ ከኦሮሞ፣ አንቺ ከአማራ … የሚል ነገር የለም።
እዚህ ላይ የራሴን ጉዳይ ምሳሌ አድርጌ መናገር እችላለለሁ። እናትና አባቴ ከተለያዩ ቦታዎች ነው መጥተው አጋሮ ላይ የተገናኙት። አቤቴ ከኢሎባቦር መጥተው ነው እዛ የሰሩት፤ እናቴ ከወሎ ነው የመጡትና እዛ የተገናኙት። እኔ አባቴን አንተ ከኢሉባቦር ነህ …. ቦታህ አይደለም ሲባል፤ እናቴን አንቺ የወሎ አማራ ነሽ …. ስትባል ሰምቼ አላውቅም። እንዲህ ያለ ነገር በፍፁም አልነበረም።
አሁንም አንድ ሌላ ምሳሌ ላንሳ። ተስፋዬ አድማሱ የሚባሉ የአንደኛ ደረጃ መምህሬ ነበሩ። በጣም ያግዙኛል። ከሚገባው በላይ ነው እኔ የተሻለ ቦታ እንድደርስ ይጨነቁ የነበረው። ከቤተሰቦቼ በላይ እኔን እዚህ ያደረሱኝ እሳቸው ናቸው። እኔ እኝህ ሰው ምን እንደሆኑ፣ ከየት እንደ መጡ፣ ኦሮሞ ይሁኑ አማራ … ምንም የማውቀው ነገር የለም። ይሄንን ያህል ነበር እኔ የማውቀው እንጂ አሁን እምሰማው ነገር አልነበረም።
ጎረቤቶቻችንን ያየህ እንደሆነ አብዛኛው ሙስሊም ነበር። እኛ ቤት ሚካኤል ይከበራል። አብዛኛዎቹ መጥተው አክብረው የሚሄዱት ሙስሊም ጎረቤቶቻችን ናቸው። ይሄ ነው ያለው እውነት።
እኔ የምሰራበት ተቋም ውስጥ ብዙ አይነት ሰው አለ። በርካታ ቻይናዊያን አሉ፤ ህንዶች አሉ፤ ከስፔን፣ ከጀርመን … የመጡ አሉ፤ በርካታ አፍሪካዊያን አለን። አሜሪካ ልክ እንደኛው አይነት ነች። ብዙ አይነት ሰዎች የሚኖሩባት አገር ነች። ይሁን እንጂ ይህ ብዙነት፤ ይህ የተለያዩ መሆን … ምንም አይነት ችግር ሆኖ አያውቅም።
እኔ የምሰራበት መስሪያ ቤት ውስጥ ከብዙ የተለያዩ ቦታዎች እንምጣ እንጂ በአንድ ላይ ሆነን፤ ተስማምተን፣ ተግባብተን …. እየሰራን ነው። በመሆኑም መስሪያ ቤቱንም እራሳችንንም ተጠቃሚውን የአለም ህዝብንም እየጠቀምነው ነው።
በአገራችን አንተ እንዳልከው ነው፤ ችግሮች ይታያሉ። በፊት የሌሉ፣ አሁን የሚስተዋሉ ነገሮች አሉ። ምንም እንኳን እዛ ሆኜ ሁሉንም ነገር ባላይም እሰማለሁ። ያልነበረ ሁኔታ ነው አሁን ያለው። መከፋፈሉ ምንም አይጠቅምም። ምን ይሰራል መለያየት። ምንም ሆነ ምን አንድነቱ ነው የሚበጀው። አገሪቷ በቂ ሪሶርስ አላት። ሀብት አላት። በጋራ ሰርቶ መጠቀሙ ነው የሚሻለው እንጂ ይህ አሁን የሚሰማው ነገር የትም አያደርስም።
አንድ ነገር ልንገርህ። የዛሬ ሁለት ዓመት አዳማ ዩኒቨርሲቲ አስተምር ነበር። ከዩኒቨርሲቲ ወደ አዲስ አበባ ስንመጣ ሾፌሩ ያለኝ አንድ የገረመኝ ነገር አለ። ”እዚሁ ሊቀሩ ነው?” አለኝና ጨዋታ ጀመርን። ”እርሶ መጥተው እንደገና ከአንደኛ ክፍል ደረጃ ጀምረው ቢያስተምሩን ጥሩ ነበር” ነው ያለኝ። ይሄ ትልቅ ትምህርት ነው። አንድ ሆነን አገሪቷ ያላትን ሪሶርስ ሰርተን መጠቀም ሲገባን እንዲህ አይነት ነገር መሆኑ ተገቢ አይደለም።
ወጣቱን በተመለከተ ማለት የሚቻለው ወጣትነት ዋና አሻራ የሚተውበት ጊዜ መሆኑን ማስታወስ ነው። ወጣትነት ቀልድ አይደለም። በወጣትነት የተደረገው ነው የኋላው ስራ የሚሆነው። በመሆኑም ወጣቱ መገንዘብ ያለበት ከማይመለከተው ጋር ሁሉ የማይመለከተውን ማድረግ ሳይሆን የሚመለከተውን፤ ለነገ እሱነቱ የሚበጀውን ነው መስራት ያለበት። ዛሬ ያላቆየውን ነገ ከየትም አያመጣውም። እርግጥ ነው ወጣቱን ተገቢውን መስመር እንዲይዝ ከማድረግ አኳያ ሃላፊነት ያለባቸው አካላት፣ ተቋማት … አሉ። ቤተሰብ አንዱና ዋናው ነው። ትምህርት ቤት ትልቅ ሃላገፊነት አለበት። አጠቃላይ ህብረተሰቡም እንደዛው።
አንድ ዛፍ ገና በልጅነቱ በአግባቡ ካልተያዘና ተጣሞ ካደገ በኋላ ላስተካክልህ ቢሉት የማይሆን ነገር ነው። ቤተሰብ ለልጆቹ የሚለውን፣ የሚናገረውን፣ የሚያደርገውን … ሁሉ በአግባቡ አስቦበት መሆን አለበት። ቤተሰብ የሚለውን ልጆች እንደ ትክክለኛ ነገር አድርገው እንደሚወስዱትም ማወቅ ያስፈልጋል። በመሆኑም ልጆችን በሚመለከት የሚደረገው ሁሉ ከፍተኛ ጥንቃቄን ይፈልጋል።
ዲሞክራሲ ላልከው ጉዳይ ወደ ዲሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብ ስንመጣ መብትን ብቻ ሳይሆን ግዴታንም የያዘ ጉዳይ ነው። መብት ያለ ግዴታ ሊሆን አይችልም። ለምሳሌ፡- አንድ ሁኔታን ወስደን ማየት እንችላለን። እኔ የአቢሲኒያ ባንክ ሼር አለኝ። ገና ለገና ሼር አለኝ ብዬ በፈለኩ ሰአት እየሄድኩ የባንኩን በር ክፈቱ እያልኩ አልጨቀጭቃቸውም። ባለ አክሲዮን ስለሆንኩ ብቻ አስተዳደሩን እንዲህ ሁን፣ እንዲህ አድርግ … እያልኩ አላሰራ አልለውም። ከመረጥኩት ወዲያ ጊዜ እሰጠውና እሚሰራውን አያለሁ። ጊዜው ሲደርስ እመርጠዋለሁ ወይም አልመርጠውም። ሌላውም እንደዚሁ ነው። ዲሞክራሲ ማለት መደማመጥ ነው፤ ዲሞክራሲ ማለት መብትን መጠየቅ ብቻም ሳይሆን ግዴታንም መወጣት ማለት ነው። ሁሉም በሙያው ስራውን አክብሮ መስራት ማለት ነው።
”ለአገርዎት ምን አስበዋል?” ለሚለው፤ ትልቁ ምኞቴ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ የመድኃኒት ጥናትና ምርምር ማእከል መገንባት ነበር። በአንዳንድ ችግር ምክንያትና የተቋሙ ዝግጅት ማነስ ለጊዜው አልተሳካም። በዚህም ምክንያት ተመልሼ ልመጣ ችያለሁ። ይሁን እንጂ ችግሮች ተፈትተው የታሰበው ይሳካል የሚል ተስፋ አለኝ። እዛ በነበርኩበት ጊዜ ተነጋግረናል። በጨረሱ ጊዜ፤ በማንኛውም ጊዜ እንዲጠሩኝ ነግሬያቸዋለሁ። ለመምጣትና ለመስራት በጣም ደስተኛና ፈቃደኛ ነኝ። ይጠሩኛል ብዬም ተስፋ አድርጌያለሁ።
ሌላው ከቅርብ ጓደኞቼ፣ ከእነ ብርሀነ መዋ ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የመድሀኒት ፋብሪካ የመክፈት እቅድ ይዘን እየተንቀሳቀስን ነው። ጥናቱን ጨርሰን ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅት ላይ ነን።
”ኢትዮጵያ ምን አይነት አገር ሆና ማየት ይፈልጋሉ?” ለሚለው አገራችን ለምለም ነች። ሁሉ ነገር አላት። በቂ ሪሶርስ ያላት አገር ናት። በመሆኑም ሁሉም በጋራ ሰርቶ የሚጠቀምባት፤ ሁሉም በሰላም የሚኖርባት፤ ሁሉም የሚደሰትባት አገር እንድትሆን ነው የምመኘው። በተጨማሪም እኔ ለአገሬ የምመኘው በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ …. ዘርፎች ሌሎች አገሮች የደረሱበት እንድትደርስ ነው የምመኘው። ህዝቡም ልዩነት ደስ የሚልና ጠቃሚ መሆኑን እንዲረዳና እንደውም ሁሉም የየራሱን ባህል አውጥቶ አገር የምትጠቀምበትን መንገድ እንዲያመቻች ነው።
እኔ ለአገሬ የምመኘው መንግስትና ህዝብ የሚደማመጡባት አገር፤ ህዝብ የወደደውን መንግስት የሚመርጥባት፤ የመረጠውን መንግስት ጊዜ ሰጥቶ እሚሰራውን በማየት ጊዜው ሲደርስ በሰራው ልክ የሚወስን (በመምረጥና አለመምረጥ)፤ በየቀኑ ሰላማዊ ሰልፍ፣ በየቀኑ ብጥብጥ …. የማይታይባት አገር እንድትሆን ነው። ሁሉም በሙያው እንዲሰማራ፤ ኢኮኖሚስቱም በኢኮኖሚው እንዲበረታ ሌላውም እንዲሁ እንዲሆን። ሁሉም ፖለቲከኛ የማይሆንባት አገር እንድትሆን እመኛለሁ። አመሰግናለሁ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 29/2014