አዲስ አበባ፡- መንግሥት በቀጣይ ዓመት በሰላም፣ በህግ የበላይነት፣ በዴሞክራሲ ግንባታ፣ በቱሪዝምና ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጎልበት ረገድ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ አመለከቱ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ «ከመጋቢት እስከ መጋቢት» በሚል ርዕስ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የዶክተር ዓቢይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡበትን 1ኛ ዓመት በሚሊኒየም አዳራሽ ሲከበር እንደገለጹት፤ ዓምና በዚህ ወቅት የአገሪቱ ቀጣይነት ልጡ የራሰ ጉድጓዱ የተማሰ ይመስል ነበር። በኢትዮጵያውያን ብርቱ ክንድና በፈጣሪ ዕርዳታ እዚህ መድረስ ተችሏል።
«ኢትዮጵያውያን ሰይፍ ያስፈልገናል» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እሱም ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅር መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያንን እንደ ጥንቱ ታላቅ የማድረግ ፕሮጀክት ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ መሆኑንም ገልጸዋል። በአማራና በትግራይ፤ በጊዴዮና በጉጂ፣ በሶማሊያና በአፋር ህዝቦች መካከል ሰላም፣ ይቅርባይነትና ፍቅር እንዲወርድ ይሰራል ብለዋል።
በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ረገድም በተለይ በቀጣይ ዓመት የሚካሄደውን ምርጫ ፍጹም ነጻና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ዳግም ለአፍሪካ ምሳሌ ለመሆን እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
የህግ የበላይነት በማስከበር በኩልም፤ ህግ የሚያስከብሩና የሚተረጉሙ አካላት እያንዳንዱን ዜጋ ከጥቃት የሚከላከሉ ሆነው እንደሚዋቀሩ ገልጸው፣ የተፈናቀሉ ዜጎች
ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ብቻ ሳይሆን ባሉበትም እንዲቋቋሙ የሚሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ባለፉት ሰባት ወራት በኢንቨስትመንት፣ በብድር፣ በድጋፍ፣ ኢትዮጵያውያ ለዘመዶቻቸው ከሚልኩት ገንዘብ 13 ቢሊዮን ዶላር ማምጣት መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ ተናግረዋል። ከ13 ቢሊዮን ዶላሩም ስምንት ቢሊዮን ዶላር ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። ቀሪው ገንዘብም በጅምር ያሉ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ መዋሉንና በተለይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከአጋጠመው ችግር ተላቅቆ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቅ የሚያስችል ቁርጠኛ አመራር መስጠታቸውን ተናግረዋል ።
ቱሪዝምን በሚመለከትም በመጪው መስከረም ወር ብሄራዊ ቤተ መንግስት በሙዚየምነት ከአዳዲስ ሥራዎች ጋር ለህዝብ ክፍት ይደረጋል። በቀጣይ ዓመትም አዲስ አበባን የማስዋብ ፕሮጀክትም ቢያንስ አንድ አራተኛው ይጠናቀቃል ሲሉ ተናግረዋል።
የማዕድን ዘርፍ ማጎልበትና የውጭ ምንዛሪን የማስገኘት ሥራ እንደሚሰራ የተናገሩት ዶክተር ዓብይ፤ በተለይ ደግሞ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠርን ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል።
«እኔ ያለ እናንተ ምንምና የማልረባ ነኝ» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ «የጎደለና ያልተሟላ ነገር ካለ በከፍተኛ ትህትና ኢትዮጵያውያንን ቆሜ ሳይሆን ዝቅ ብዬ ይቅርታ እጠይቃለሁ» ሲሉ ተናገረው «ቁጣና ተግሳጻችሁ ለእኔ ሽልማቴ ነው፤ ተስፋ ጥላችሁብኝ በዳተኝነት ሳይሆን ከዕውቀት ማነስ የተነሳ ያልሰራሁት ከሌለ በስተቀር ሙሉ ጊዜዬን ሰጥቼ እንዳገለገልኩ እረዳለሁ ብለዋል።
«ዓላማዬ በነጻነት የሚኖሩባትን ኢትዮጵያን መፍጠርና ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ነው እንጂ፤ ምንም የሸፍጥ ሀሳብ የለኝም» ሲሉ አረጋግጠዋል። «ኢትዮጵያ ምትክ የሌላት ብቸኛ አገራችን ናት» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያን ከሚያቆረቁዝና ከአፍራሽ ድርጊት መታቀብ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
«ለውጡ ብዙዎች የሞቱለት፤ የተገረፉለት፤ የታሰሩለት፣ የተሰደዱበት፣ ያለቀሱበት፡ የጸለዩበት የሁላችን ድምር እንጂ፤ የጥቂት ግለሰቦች አልነበረም፤» ያሉት ዶክተር ዓብይ፤ «በብዙዎች የመጣን ለውጥ በተባበረ ክንድና በመደመር ሃሳብ መጠበቅና ማስቀጠል ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚጠበቅ አደራ ነው» ብለዋል። አሁንም ኢትዮጵያ ታሪኳን አድሳ ለአፍሪካና ለዓለም አርአያ ሆና እንደምትቀጥልም ተናግረዋል።
የአንዱን ዓመት የለውጥ ጉዞ ለመዘከር በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመውታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2011
በአስቴር ኤልያስ