ከወጣትነት ዕድሜ አለፍ ያለ ቢሆንም ገና አፍላ ወጣት ይመስላል። መልከመልካምና ትሁት ነው። ለቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ እንደመሆኑ በልዩ እንክብካቤ አድጓል። በልዩ እንክብካቤ ማደጉ ታድያ ከስኬት ጎዳና አላስቀረውም። በለጋነት ዕድሜው ስለ ሥራ ክቡርነት እና ስለ በጎ ሥራዎች ጭምር ከወታደር አባቱ ብዙ ተምሯል። ወታደር አባቱም በስነምግባር ታንጾ እንዲያድግ ዋጋ ከፍለዋል። በተለይም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ አገሩን በታማኝነት ማገልገል እንዲችል፤ የውትድርና ስነምግባርን ለህዝብ ከመኖር ጋር አጣምረው አስተምረውታል።
ለትምህርት ትልቅ ትኩረት ይሰጡ የነበሩት ወላጅ አባቱ መቶ አለቃ መሰለ ገብረየስ፤ ልጆቻቸው በትምህርት እንዲገፉ ምኞታቸው ነበር። ከትምህርታቸው ጎን ለጎንም የሁሉ ነገር መሰረት የሆነውን ታላቁን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያነቡ አግዘዋቸዋል። በተለይም 11ኛ እና የመጨረሻ ልጃቸው ለሆነው አቶ ዳንኤል ታላቁን መጽሐፍ ቅዱስ ገና በልጅነቱ አበርክተውለታል። ታላቁን መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ ብዙ ማትረፍ እንደሚቻል እየተነገረውና እያነበበ ያደገው ዳንኤልም ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው፤ ለብዙዎች መትረፍ የሚችል፤ ጠንካራ ሰው መሆን ችሏል።
በፍጹም ስነምግባርና በአገር ፍቅር ስሜት ያደገው አቶ ዳንኤል መሰለ የዕለቱ የስኬት እንግዳችን በመሆን የሥራ እንቅስቃሴውን አጫውቶናል። የወታደር ልጅ የግድ ወታደር ባይሆንም በአገር ፍቅር ስሜት ልቡ ተነክቶ ስለማደጉ ግን ጥርጥር የለውም። የሥራ ክቡርነት ከማመን ባለፈ ታታሪና ትጉህ ሠራተኛ ሆኖ እንዲያድግ በመደረጉ ምክንያት ስኬታማ መሆን ችሏል። ‹‹ማንም ሰው ሥራን ሳይንቅ ከዝቅታው ዝቅ ብሎ መሥራት ከቻለ ስኬት ከእርሱ ጋር ናት›› የሚለው አቶ ዳንኤል፤ ከልጅነቱ ጀምሮ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርቷል። በአሁኑ ወቅትም ዳኒ ቢዝነስ ግሩፕ በተሰኘው ድርጅቱ አምስት የሚደርሱ እህት ኩባንያዎችን እያስተዳደረ ይገኛል።
የዳኒ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል መሰለ፤ ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በጆን ኤፍ ኬኔዲ ትምህርት ቤት፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በጥቁር አንበሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። የመጀመሪያ ድግሪውንም በፋይናንሲንግ አድርጓል።
የንግድ ሥራን ከእህል በረንዳ እንደጀመረ የሚናገረው አቶ ዳንኤል፤ አሁን ለደረሰበት ደረጃም በእህል በረንዳ የነበረው የንግድ ሥራ የጎላ አስተዋጽኦ እንደነበረው ያስታውሳል። በእህል በረንዳ ያዳበረው የእህል ንግድ እሴት በመጨመር ወደ ዱቄት ፋብሪካ ለማሳደግ ጊዜ አልፈጀበትም። በኪሳራና በተለያዩ ምክንያቶች የተዘጉ ፋብሪካዎችን ኮንትራት በመውሰድ ዱቄት በማምረት ለገበያ ያቀርብ ነበር። በከተማ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የተዘጉ አምስት የሚደርሱ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ መመለስ ችሏል።
ከእህል ንግድ ቀጥሎ ፋብሪካ ላይ ትኩረት በማድረግ የተዘጉ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ መመለስ የቻለው አቶ ዳንኤል፤ በንግዱ ዘርፍ በቂ ልምድና ዕውቀት ቀስሟል። ከእህል ንግድ ጋር ተያያዥ በሆነው ዱቄት ፋብሪካ መሰማራቱ አዳዲስ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም ምቹ ሆኖለታል። በዳኒ ቢዝነስ ግሩፕ ውስጥ ቀዳሚ የሆነው ያምሮት የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሲሆን ፋይን ውሃ፣ ኢምፖርት ኤክስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማራው ዳይባት ትሬዲንግ፣ ዲኤም ጀነራል ትሬዲንግና ቡና ወደ ውጭ ገበያ መላክም ተከትለዋል።
ያምሮት የምግብ ማቀነባበሪያና ፋይን ውሃ ማምረቻ ቡራዩ ታጠቅ ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ዲኤም ጀነራል ትሬዲንግ የተባለ መቀመጫውን ጅቡቲና ዱባይ ያደረገ ካምፓኒ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የተለያዩ ጥሬ ዕቃዎችን ያቀርባል። ጠቅላላ ንግዱም በዳይባት ትሬዲንግ አማካኝነት ይከናወናል። ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ከሚያስገቧቸው ምርቶች መካከልም፤ ለብስኩት ፋብሪካዎች የሚውል ግሉኮስ፣ ለውሃ ፋብሪካ የሚያገለግሉ ጥሬ ዕቃዎች፣ ለፕላስቲክ ማምረቻ የሚያገለግሉ የተለያዩ ጥሬ እቃዎች፣ ለሳሙና ፋብሪካ ግብዓት የሚሆን ኑድልስ እና ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ኤክስካቫተሮችና ሲኖትራኮች ይጠቀሳሉ።
ወደ አገር ውስጥ ከሚያስገቧቸው ጥሬ ዕቃዎች መካከል በተለይም ለብስኩት ፋብሪካዎች ሾርት ሊንግ የተባለ ቅቤን በከፍተኛ መጠን በማስገባት ለብስኩት ፋብሪካዎች ያቀርባሉ። በዳኒ ቢዝነስ ግሩፕ ውስጥ ከሚገኙት እህት ኩባንያዎች መካከል ቀዳሚ በሆነው ያምሮት የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ፓስታ፣ ማኮረኒና ዱቄት ይመረታል። ለእነዚህ ምርቶችም በአገር ውስጥ የሚመረተው የስንዴ ምርት በዋናነት ግብዓት ሆኖ ያገለግላል።
እነዚህ ምርቶችም አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በብዛት ወደ ክልሎች የሚሰራጭ እንደሆነ ያነሳው አቶ ዳንኤል፤ በተለይም ሀረር፣ ወለጋ፣ ምስራቅ ሀረርጌ፣ ሻሸመኔና ጂንካ ድረስ የያምሮት የምግብ ማቀነባባሪ ምርቶች የሆኑት ፓስታና ማካሮኒና በስፋት ተደራሽ ይሆናሉ። ምርቶቹን በየአካባቢው ተደራሽ ለማድረግም ከ60 የሚልቁ የድርጅቱ መኪኖች የጎላ ድርሻ አላቸው። በአዲስ አበባ ከተማ መርካቶ ገበያ ውስጥም የያምሮት ምግብ ማቀነባበሪያ ምርቶች 30 በመቶ ድርሻ አለው። ፓስታና ማካሮኒ በቀን 1500 ኩንታል፤ ዱቄት 1300 ኩንታል የማምረት አቅም አለው።
በያምሮት የምግብ ማቀነባባሪያ ውስጥ የሚገኘው የማካሮኒ ፋብሪካው ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ እንደሆነ ያጫወተን አቶ ዳንኤል፤ ማሽነሪዎቹ ከጣልያን አገር የመጡና ከፍተኛ አቅም ያላቸው እንደሆኑ ተናግረዋል። ያምሮት የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አጠቃላይ ሰባት ሺ ካሬ ስፋት ባለው ቦታ ላይ የተቋቋመ ግዙፍ ፋብሪካ ነው። ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ የሆነው የማካሮኒ ማሽንም በሰዓት 30 ሺ ኪሎ ግራም ማካሮኒ ማምረት ይችላል። ይህን ማሽን የሸጠው የጣልያን ድርጅትም ከፍተኛ አቅም ያለውን የማካሮኒ ማምረቻ ማሽን በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ መሸጡን እንዳስተዋወቀና መረጃው የካምፓኒው እንደሆነ ነው ያስረዳው።
ማካሮኒ እያመረተ ያለው ይህ ግዙፉ የጣልያን ማሽን 12 ዓመቱን የያዘ ቢሆንም ወደፊት ለበርካታ ዓመታት የሚያገለግል ይሆናል። ማምረቻ ማሽኑ አዲስና የተሻለ ቴክኖሎጂ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ትውልድን የሚያበቃና አገር የሚጠቅም ዘመናዊ ማሽን ነው። ማሽኑ ከእጅ ንክኪ ውጭ በሆነ መንገድ ኮምፒዩተራይዝድ በሆነ መንገድ በቀላሉ የሚሠራ እጅግ ዘመናዊ ማሽን እንደሆነም አቶ ዳንኤል ተናግሯል።
ሌላኛው ፋይን ውሃ ማምረቻም በቡራዩ ታጠቅ ኢንዱስትሪ መንደር ከያምሮት ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ጀርባ ይገኛል። ዳይባት ትሬዲንግ የተባለው ድርጅት ደግሞ ቢሮው ልደታ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፤ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችንና ወደ ውጭ ገበያ የሚላከውን የቡና ንግድ በወጪና ገቢ ንግድ ያሳልጣል። ዳይባት ትሬዲንግ ወደ ውጭ ከሚልከው ቡና ይበልጥ በርካታ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ይታወቃል።
‹‹ከተሰማራሁባቸው የሥራ ዘርፎች ሁሉ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ በእጅጉ አዳላ ነበር አሁን ግን ሁሉንም እንደልጆቼ አያቸዋለሁ›› የሚለው አቶ ዳንኤል፤ ፕሮጀክቶች እጅግ በጣም ያስደስተውና ይስበው እንደነበር በማስታወስ፤ በተለይም ማሽኖች ሲተከሉ የነበረውን ጉጉትና ትጋት 12 ዓመታትን ወደኋላ ሄዶ ያስታውሳል። ታድያ አንደኛው የሥራ ዘርፍ ላይ በብዙ ማተኮር በሌሎቹ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ በመኖሩ አሁን ላይ ሁሉንም እኩል ይከታተላል። ለዚህም አሁን ያለበት ሁኔታ ምቹ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሁሉንም የሥራ ዘርፎች በተቻለ አቅም እንደሚከታተልና ውጤታማ እንደሆነም አጫውቶናል።
በእህል በረንዳ ከእህል ንግድ ጀምሮ የተዘጉ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ በመመለስ ንግድን የተቀላቀለው አቶ ዳንኤል፤ የመጀመሪያ የሆነውን ያምሮት የምግብ ማቀነባበሪያ በ10 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል እንዳቋቋመ ያስታውሳል። የዛሬ 12 ዓመት ገደማ የተቋቋመው ያምሮት የምግብ ማቀነባበሪያ አምስት እህት ኩባንያዎችን መፍጠር የቻለ ሲሆን በአሁን ወቅትም በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ አንድ ሺ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።
‹‹የእግዚአብሔር ቃል የሰው ልጆችን ሕይወት ያርቃል›› የሚለው አቶ ዳንኤል፤ ገና በልጅነቱ ከወላጅ አባቱ በተበረከተለት ቅዱስ መጽሐፍ ሕይወቱ እንደተቃኘ ይናገራል። ዛሬ ለደረሰበት ስኬትም ቀዳሚው የእግዚአብሔር እርዳታ ቢሆንም ታላቁን መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበ ማደጉ ደግሞ የሕይወቱን ቀጥተኛ መንገድ እንዲያገኝና መልካም ነገሮችን ለማድረግ አነሳስቶታል። ታላቁን ቅዱስ መጽሐፍ በመጥቀስ ‹‹የሚሰጡ እጆች የተባረኩ ናቸው›› በማለት መስጠት መታደል እንደሆነም ያነሳል። ሰዎች በጎ ነገርን ማድረግ የሚችሉት ሲፈቀድላቸው መሆኑን በመግለጽ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ያለውን ተሳትፎም አጫውቶናል።
የዳኒ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል መስጠት የማይቋረጥ ልግስና እንደሆነ ያምናል። በተለያዩ አጋጣሚዎች የተለያዩ እገዛዎችን ለሰዎች ያደርጋል። ጊዜ ከመስጠት ጀምሮ አቅም በፈቀደ መጠን ለብዙዎች መትረፍ የሚያስደስተው እንደሆነም ይናገራል። እስካሁን ሰርቻለሁ ከሚለው በጎ ሥራዎች መካከልም በቡራዩ ታጠቅ አሸዋ ሜዳ ዳያስፖራ ሰፈር የአስፓልት መንገድ ሥራ እጅግ የሚያስደስተው ሥራ ነው። መንገዱ የአካባቢው ነዋሪ በብዙ የተቸገረበት መንገድ እንደመሆኑ የህዝቡን ችግር ለማቅለል ትልቁን ድርሻ ወስዶ መንገዱ እንዲሰራ ምክንያት ሆኗል።
አካባቢው የታመሙ ሰዎችን በአምቡላንስ ይዞ ለመውጣት እጅግ አስቸጋሪና ብዙ መኪኖች እየተሠበሩ የሚገቡበት እንደነበር የሚያስታውሰው አቶ ዳንኤል፤ መንገዱ እንዲሰራ ተነሳሽነቱን በመውሰድ የጎላ አበርክቶ አድርጓል። መንገዱ ሶስት ኪሎ ሜትር የሚደርስ ሲሆን በአካባቢው ማህበረሰብ እና በመዘጋጃ ቤቱ ትብብር መንገዱ መጠናቀቅ ችሏል። አጠቃላይ ሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ ለጠየቀው መንገድ የአካባቢው ማህበረሰብ ሶስት ሚሊዮን ብር ሲያዋጣ አቶ ዳንኤል ደግሞ አራት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል። መንገዱም ዳኒ ዳያስፖራ መንገድ በመባል ተሰይሟል።
ከመንገድ ሥራው በተጨማሪም ቀደም ሲል ከሱማሌ ተፈናቅለው መደወላቡ ላይ ለሰፈሩ ዜጎች በአይነት የአምስት መቶ ሺ ብር ድጋፍ አድርጓል። ቡራዩ አካባቢም በአንድ ወቅት በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ 60 አባወራዎች ቤት ሰርቶ አስረክቧል። በትምህርት ቤቶችና ሌሎች አገራዊ ጉዳዮችንም ይመለከተኛል በማለት ድጋፉን ሳይሰሰት የሚሰጠው ዳንኤል፤ ለአገርና ለህዝብ መድረስ ከልግስና ባለፈ ግዴታም ጭምር እንደሆነ ይናገራል።
ማንም ሰው በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ በቅንነት፣ በታማኝነትና በፍጹም መታተር መሥራት ከቻለ ስኬት ይከተለዋል ብሎ የሚያምነው አቶ ዳንኤል፤ በቀጣይም ኢንዱስትሪ ዞን የመገንባት ዕቅድ እንዳለው ገልጿል። ለዚህም ሆለታ ላይ አንድ መቶ ሺ ካሬ መሬት ቦታ አዘጋጅቷል። በዚሁ ቦታ ላይ የኢንዱስትሪ መንደር በመገንባት የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት የተዘጋጀ ሲሆን በአሁን ወቅትም በኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ መሥራት ለታሰበው የተለያዩ ሥራዎች አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። የቅድመ ዝግጅት ሥራው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ በሚገባበት ወቅትም አምስት ሺ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል።
በኢንዱስትሪ መንደሩ 19 የሚደርሱ ሼዶች የሚገነቡ ሲሆን በእያንዳንዱ ሼድ ውስጥ የተለያዩ ምርቶች የሚመረት ስለመሆኑ ያመላከተው አቶ ዳንኤል፤ ይህ ከፍተኛ አቅም ያለውና የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት የተዘጋጀው የኢንዱስትሪ ዞን በአብዛኛው የፕላስቲክ ማሸጊያ የሆኑ መሳሪያዎችን ማምረት የሚያስችሉ ማሽኖችን በመትከል ወደ ሥራ የሚገባ ይሆናል ብሏል።
በመጨረሻም ብዙ ሰዎች ቦታቸውን በመተው በማይመለከታቸው ጉዳይ ሲጠመዱ ያስተዋለው አቶ ዳንኤል፤ ሰዎች በራሳችን ጉዳይ እንጠመድ፤ በተለይም ወጣቶች በራሳቸሁ ጉዳይ ተጠምዳችሁ ከትንሽ ጀምሮ ሥራ ፈጣሪ መሆን፣ እራሳችሁንና አገራችሁን የምትጠቅሙ ሁኑ በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል። በመጪው ዘመንም ኢትዮጵያ ፍጹም ሰላም እንድትሆን በመመኘት ሃሳቡን ቋጭቷል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 /2014