በደቡብ ክልል ከሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች መካከል በአንዷ ነዋሪ የሆኑ ናቸው የዶሴ አምድ ባለታሪኮቻችን። በልምላሜ ያጌጠ አካባቢ ውስጥ የሚኖሩት ቤተሰቦች በህመምና በችግር የተጎሳቆሉ፤ ኑራቸውን ለመግፋት የሚሰማሩበት የስራ ዘርፍ በሙሉ ብዙም ተስፋ የሚሰጥ ያልሆነላቸው ነበሩ። አባት በእርሻም በንግድም የቤተሰባቸውን ህይወት ለማሻሻል ቢደክሙም ኑሯቸው ግን ከእጅ ወደ አፍ ብቻ እየሆነ ያበሳጫቸዋል። በዚህም ምክንያት በመጠጥ እራሳቸውን አደንዝዘው ወደ ቤት ይገባሉ።
እናት የልጆቻቸው አባት በተስፋ መቁረጥ የተውትን ቤተሰብ ህልውና ለማስጠበቅ ፤ አሰልቺ የሆነባቸውን ኑሮ ለመለወጥ የቻሉትን ሁሉ ጥረት ያደርጋሉ። ሆኖም ግን ብዙ እንዳሰቡት አልተሳካላቸውም። በድህነታቸው ላይ ብዙ ልጆች በመውለድ ያጋጠማቸው ጉዳት ተዳምሮ ሰውነታቸው የቤትም የውጪም የስራ ጫና ሲወድቅበት መቀበል እየተሳነው ድካምና ህመም ያንገዳግዳቸዋል። ህመምና ድካም የሚያንጠራውዘውን የእናቷን መከራ በዝምታ መመልከት ያቃታት የበኩር ልጃቸው ይህን የኑሮ ዳገት ከጎናቸው ሆና ለመግፋት የበኩሏን ጥረት ታደርጋለች።
ተስፈኛዋ ወጣት
ገና በአፍላ እድሜዋ የህይወትን ፈተና እንድትጋፈጥ የተፈረደባት ወጣት ናት። ልጅነቷን በቅጡ ሳታጣጥም አድጋ ነው በለጋ እድሜዋ ወደ ስራ አለም የገባችው። ይች ወጣት ከችግረኛ ቤተሰቦች በመወለዷ የተነሳ የትምህርት ቤት ደጅን ረግጣ አታውቅም ነበር። ፊደል ቆጥራ ባታውቅም የኑሮ ውጣ ውረድ ካለ እድሜዋ ብስል እንደትሆን አድርጓታል። ባላት አቅም የእናቷን ድካም ለመቀነስና ኑሯቸውን ለመደጎም ዘወትር ደፋ ቀና ትላለች።
ምንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ የኑሮን ዳገት መግፋት ያቃታቸው ፤ እሷና እህት ወንድሞቿን ለመሳደግ ደፋ ቀና የሚሉት እናቷ አቅም ማጣትና ህመም ተደጋግፈው ሲደቁሳቸው ማየት እጅጉን ያሰቅቃት ጀመር። ዛሬ ደህና ሆነው ሲንቀሳቀሱ ከዋሉ ለሚቀጥሉት ሶሰት አራት ቀናት አልጋ ላይ የሚያውላቸው ህመም ጉዳይ እጅግ አሳስቧታል። እድሜዋም እየበሰለ ሰውነቷም እየጠነከረ የሄደችው ወጣት የእናቷ ህመም ከእለት ወደ እለት እየባሰ መሄድ እንቅልፍ ስለነሳት “እናቴን እየሰራሁ አሳክማለሁ” የሚል ሀሳብ ታስባለች። ይህንንም እቅዷን ለቤተሰቡ አቅርባ ከህክምና የተረፈውን ገንዘብ ልትልክላቸው ቃል ገብታ ከተወለደችባት የገጠር ቀበሌ ወደ ዳራማሎ ወረዳ እናቷን ይዛ ትወጣለች።
ኑሮ ያሰበችውን ያህል ቀላል ያልሆነላት ይች ወጣት የቀን ስራ እየሰራች እናቷን ማሳከምና ማስተዳደር አንድ ብላ ጀመረች። ገና በለጋ እድሜዋ የወደቀችባት ወጣት ማልዳ በመነሳት ወደ ስራዋ ሮጥ ሮጥ ትላለች። ከስራ ስትመለስ ታማሚ እናቷን የመንከባከብ ሀላፊነቷን ለመወጣት ደፋ ቀና ትላለች። ወጣቷ ጥዋት ማታ ስራ ላይ ብትውልም ድካም ያላጠወለገው ተፈጥሮ የለገሰቻት የወጣትነት ውበት ፍክት ድምቅ ብላ እንድትታይ አድርጓታል።
ሳትለብስ የሚያምርባት፤ ሳትበላ የምትወዛው ይህች ወጣት በምትሰራበት አካባቢም ሆነ በተለያዩ ስፍራዎች የብዙ ወንዶች አይን ይከተላታል። የጡቷ ጉች ጉች ማለት፣ ቁመናና ትህትናዋ በብዙዎች አይን እንድትገባ አድርጓታል። በወጣች በገባች ቁጥር ዋልጌ ወንዶች ለከፋም ያስቸግራታል። እሷ ግን በስራ ራሷንና ቤተሰቦቿን ለመደገፍ ቆርጣ በመነሳቷ ከስራዋ በቀር ምንም የሚታያት ነገር አልነበረም። የማባበያ ቃላትና ትናንሽ ስጦታዎች ከእናቷ ህመም በላይ ልቧን ገዝቶ ወደ ፍቅር እንድታስብ አላደረጋትም።
ጠዋት ማታ እናቷ ተገቢውን ህክምና አግኝተው ወደ ቀድሞ ጤንነታቸው እንዲመለሱ መጣር ብሎም ከእነሱ የተረፈውን ገጠር ላሉ እህት ወንድሞቿ አንዳንድ ነገር መላክ የዘወትር ሀሳቧ ነበር። ያሰበችውን እያደረገች በሌላ በኩል ደግሞ ለእናቷ ጤንነት ትጨነቃለች። ይህች ጠንካራ ልጅ ለቀጣይ አመት ደግሞ ትምህርት ቤት እገባለሁ የሚል እቅድ በልቧ ሰንቃለች። ለዚህም ትንሽ ገንዘብም መቆጠብ ጀምራለች።
ሁሌ ተስፋ ያጠገበውን ፊት ይዛ የምትወጣው ይች ወጣት አብሯት የቀን ስራ በመስራት የሚተዳደረው አቶ ሁሴኖ ጋውቶ የተባለ ሰው አይኑን ጥሎባት ኖሯል። እሷ የተከራየችበት ግቢ ውስጥ ተከራይቶ መኖሩም ጠዋት ማታ ስትወጣና ስትገባ እንዲያስቸግራት ምክንያት ሆኖለታል። ይህ ሰው በጎልማሳ እድሜ ክልል የሚገኝ ቢሆንም የዚህች እንቡጥ ገላ አሳስቶታል።
ክፉ አሳቢው ወንጀለኛ
አቶ ሁሴኖ ጋውቶ ከዳራማሎ ወረዳ በቅርብ ርቀት ተወልዶ በአካባቢው ባህልና ስርአት ያደገ ሰው ነበር። በአካባቢው ወግና ባህል መሰረት እድሜው ለአቅመ አዳም ሲደርስ ሚስት አግብቶ ልጆችም ያሉት ሰው ነበር። ከተወለደበት ቀዬ ዙርያ ያሉ ወረዳዎች በመዘዋወር የተለያዩ የጉልበት ስራዎችን እየሰራ ቤተሰቡን ከመደጎም ባሻገር በእርሻ ስራ የሚተዳደር ነው።
ይህ ሰው ተጨማሪ ገቢ ላግኝ ብሎ በቀን ስራ ከተቀጠረበት ቦታ ላይ ስራዋን በትጋት የምትሰራውን ወጣት እቴነሽ ላንዲቦ ላይ አይኑን ከጣለባት ጊዜ አንስቶ የቤተሰቡን ጉዳይ እርግፍ አድርጎ ትቷል። እደግፈዋለው ያለውን ቤተሰብ ሀሳብ ወደ ጎን በመተው ውሎ አዳሩ እሷን ብቻ መከተል የእሷን መውጫ መግቢያ መቃኘት ሆኖ ነበር። የልጆቹን እናት ባለቤቱን፤ ልጆቹም ጭምር መኖራቸውን እስከሚረሳ ድረስ በክፉ ሀሳብ አቅሉን አጥቷል።
እንደሚታደን እንስሳ ወጥመዱን አጥምዶ በልቡ ያሰበውን ክፉ ሀሳብ ለመፈፀም የሚታትረው ይህ ሰው የጣለው ወጥመድ ውስጥ የምትገባዋን ይህችን ወጣት ይዞ ህልሟን ለማሰናከል ክንፉን ለመስበር ቋምጦ ይጠብቃል።
የአስራ ስምንት ዓመት ወጣት የሆነችውን ወጣት ለማጥመድ የጣለው መረብ ዛሬ ሳይዝለት አይቀርም። ወጣቷና ሰውየው አንድ ጊቢ ውስጥ ተከራይተው በመኖራቸው የተነሳ ያለችበትን ሁኔታ ለመረዳት ምንም አያግደውም ነበር። ሁሉንም ነገር በአይነ ቁራኛ ይከታተላል። ላሰበው እኩይ ተግባር ምቹ የሆኑ ቀናትንም ይጠባበቃል።
በእለቱ ተከራይተው በሚኖሩበት ግቢ የወጣት እቴነሽ እናት በህመም ምክንያት ወደ ሆስፒታል ሄደው እዛው እንዲያድሩ በመደረጉ ምክንያት ታማሚ እናቷን ሆስፒታል አስተኝታ የሚቀመስ ነገር ለማዘጋጀት ወደ ቤት ትመለሳለች። ወጣቷ ከእናቷ ጋር ከቤት ወጥታ ብቻዋን መመለሷን ያየው ይህ ሰው ወዳጅ መስሎ ምን እንደገጠማት ይጠይቃታል። እሷም እናቷ ግሉኮስ እንደሚያስፈልጋቸውና በሆስፒታሉ ሲሰጣቸው እንደሚያድር ተናግራ በአነስተኛ ገንዘብ የተከራየቻት አነስተኛ ቤት ውስጥ ገብታ ስራዋን መስራት ይጀምራለች።
ጠዋት እናቷ ጋር ይዛ የምትሄደውን ቁርስ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና የምትለው ይህች ልጅ የእናቷን በቤት አለመኖራቸውን አጋጣሚ በመጠቀም ወደ ውስጥ ይገባል። ይህ ይደርስብኛል ብላ ያላሰበችው እቴነሽ በድንጋጤ አፏ ይተሳሰራል። ንግግሯንም ሆነ ተማጽኖዋን ያደመጣት አልነበረም። ጎረቤት እንዲደርስላትም ድምጿን ከፍ አድርጋ ጩሀት አሰማች። ከመቅፅበት በሩን ዘግቶ መሬት ላይ ከተነጠፈው መኝታ ላይ ጣላት። በሀሳብ ውጣ ውረድ የደነዘዘው ሰውነቷ ጉልበታሙን ሰው መቋቋም አቃተው ። ይሄን መልካም አጋጣሚ ያገኘው ሰውም በችግርና በሀሳብ ማዕበል የምትዋትተውን ወጣት አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ፈጸመባት።
የአስራ ስምንት ዓመት ወጣት የሆነችውን እቴነሽን በቀን 16/ 11/ 2014 ዓ.ም ከምሽቱ አራት ሰዓት አስገድዶ የመደፈር ጥቃት ይደርስባታል፣ የግል ተበዳዯ እቴነሽ ባሰማችው የድረሱልኝ ጩኽት ህብረተሰቡ በቦታው በመገኘት ሊያስጥላት ቢሞክር በሩ ከውስጥ በመቀርቀሩ የተነሳ ሙከራቸው ሳይሳካ ቀረ።
ሆኖም ግን ድምጿን የሰሙ የአካባቢው ነዋሪዎች ከቦታው አልጠፉም። የተሰበሰቡት ሰዎች በኃይል በሩን ገንጥለው ሲገቡ ይህን ክፉ ድርጊት ፈፅሞ ማምለጫውን ሲያሰላስል አገኙት ። ምንም እንኳን ልጅቷን ከወንጀሉ ማትረፍ ባይችሉም ተከሳሹ ላጠፋው ጥፋት ቅጣቱን ማግኘት እንዲችል ማድረግ እንዳለባቸው ተመካከሩ። በፈጸመው አጸያፊ ድርጊት ህግ ፊት ቀርቦ እንዲቀጣ ሌላውም አካል እንዲማርበት ወደ ህግ ቦታ ወሰዱት።
ፖሊስም የአይን ምስከሮችና የሆስፒታል የምርመራ ወረቀትን በመመልከት ወንጀለኛው ላይ ተጨማሪ ምርምራ ስራ ሲያካሂድ ቆይቶ ያጠናቀረውን የሰነድ ማስረጃ ለወረዳው አቃቤ ህግ በማቅረብ ክስ መስርቶ ጉዳዩን ሲከታተል ቆይቷል።
በልጃቸው ጉዳት ክፉኛ የተሰበሩት እናት
ወትሮም ያለእድሜዋ የቤተሰብ ሀላፊነት መውሰዷ የሚያስጨንቃቸው እናት መች ተሽሎኝ ልጄን አሳሪፊያት በሚል ተስፋ ውስጥ ባሉበት ወቅት ልጃቸው ላይ የተፈፀመው ድርጊት መስማታቸው ልባቸውን አቁስሎታል። ተወዳጇ ልጃቸው በጠዋት ሆስፒታል መጥታ እንደምትወስዳቸው ነግራ ከተለየቻቸው በኋላ ባለቻቸው ሰአት ያለመምጣቷ ነገር ልባቸው እንዲረበሽ አድርጎታል።
“ምን ሆና ይሆን…?” በሚል የሀሳብ መንገድ ሲመላለሱ ባሉበት ወቅት ልጅቷ ለህክምና ምርመራ እሳቸው ወደተኙበት ሆስፒታል ትመጣለች። ምርመራዋን እስክትጨርስ እግረ መንገዳቸውን እናቷ ወደ ተኙበት ክፍል ጎራ ያሉት ጎረቤቶች የሆነውን ሁሉ ሲነግራቸው በአቅም ማጣትና በተስፋ መቁረጥ በተዳከመ ድምፅ ከልባቸው አነቡ። እንባቸውን አፈሰሱ።
ገና ሮጣ ያልጠገበችውን የአይን ማረፊያ ልጃቸውን በክፉ አይኑ ያየባቸውን ሰው ማንነት ሲሰሙ “ ጨዋ መሰሎ አታለለኝ…” በማለት ከልባቸው ቢያዝኑም ልጃቸው እንዳትሰበርባቸው ጠንከራ ሆኖ ለመታየት እየሞከሩ ነው። ልጃቸውንም ጠንክሮ ለማጠንከር በውስጣቸው የያዙትን ይዘው ፈገግ ለማለት ሲሞክሩ ይታያሉ።
ገና በማለዳው ሀላፊነት ተሸክማ እንደ ልጅነቷ ሳትጫወትና ሳትቦርቅ ያደገችው ልጃቸው እጣ ይህ መሆኑ በጣም ቢያሳዝናቸውም በህግ ጥላ ስር ሆኖ ለፍርድ መቅረቡ ደግሞ በጥቂቱም ቢሆን ልባቸው እንዲያርፍ አድርጎታል።
ውሳኔ
አቃቤ ህግ ያቀረበውን ክስ የተመለከተው የወረዳው ፍርድ ቤት የሰውና የሰነድ መረጃዎችን ሲመረምር ቆይቶ በተከሳሾቹ ላይ የመጨረሻውን ፍርድ ለማሳለፍ በቀነ ቀጠሮ ተገኝቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል ተከሳሹ በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ መሆናቸውን አረጋግጦ የክስ መከላከያቸውን እንዲያቀርብ ዕድል ሰጥቷል፡፡ ተከሳሹም ወንጀሉ ፈጽሞ አላስተባበለም። ጥፋተኛ መሆኑንም በአደባባይ ገለጸ።
በቀነ ቀጠሮው የተሰየመው የወረዳው ፍርድ ቤትም የተከሳሹን ማስረጃዎች መርምሮ በቀን 9/12/2014 ዓ.ም በዋለው የወንጀል ችሎት በተከሳሹ ላይ የአምስት አመት ከስድስት ወር የእስራት ቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 /2014